Monday, 18 October 2021 00:00

አዲስ ምዕራፍ፤ አዲስ መንገድ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያ  ምድረ ቀደምት አገር ናት እንላለን፡፡ ለዚህ መልሳችንና ማስረጃችን በአፋር አካባቢ በአርኮየሎጂስት ቁፋሮ የተገኑት ከሶስት ሚሊዮን ዓመታት በላይ እድሜ ያላቸው የሰው ቅሬታ አካሎች ናቸው፡፡qa
በዓለም ታሪክ ውስጥ ጥንታዊ የስልጣኔ ታሪክ ካላቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት ስንል ማስረጃችን  የአክሱም ሀውልቶች፣ ጥንታዊ ቤተ መንግስቶች፣ እምነት ምኩራቦችና ሌሎችም ታሪካዊ ቅርሶች ናቸው፡፡ ትናነትና ከሮምና ከግሪክ እኩል የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ እነሱም በሚገኙበት ደረጃ መገኘት አለመቻሏ ደግሞ ግልፅ ነው፡፡
በትግራዩ ራስ ሚካኤል ስሁል ጀማሪነት ጎንደር ላይ የተጀመረው ዘመነ መሳፍንት በየአካባቢው ከእኔ ሌላ የሚሉ አምባገነን መሪዎችን ፈጥሮ ማዕከላዊ መንገስታቱን ይበልጥ ደካማ አድርጎ፤  ነገስታቱ በመሳፍንቱ ፈቃድ የሚወጡና የሚወርዱ  ሆነው ወደ መቶ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ አለፈ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በ1841 ዓ.ም አካባቢ ተነስተው ዘመነ መሳፍንት ዘግተው የተበታተነቸውን ኢትዮጵያ ወደ አንድ ማሰባሰብ ጀመሩ፡፡ ከእሳቸው  ቀጥሎ ሥልጣን የያዙት አፄ ተከለ ጊዮጊስና አፄ ዩሐንስ  በጅምሩ ላይ ሳይጨፈምሩበት፤ አፄ  ዩሐንስ የነበረውን ግዛት ለማስጠበቅ ሲታገሉ ዘመናቸውም ሕይወታቸውም አለፈ፡፡ ከእሳቸው ቀጥለው የተነሱት አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያ አሁን ያላትን መልካ ምድራዊ ስፋት ያዛ እንድትቆም አደረጓት፡፡
መጀመሪያ አፄ ቴዎድሮስ በኋላም አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን መልሰው ያቋቋሙበት መንገድ፣ የዛሬዋ ኢጣሊያ የጥንቱ ሮም መንግስት ተመልሶ የቆመበት መንገድ ቢሆንም፣ ይህ መንገድ በአገራችን “የነፍጠኛ  ሥርዓት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እንዳይከበርና እንዳይወደድ ተደርጓል፡፡
አፄ ምኒልክ በዘር ግንዳቸው አማራ ቢሆኑም አገዛዛቸው ሌላውን ያገለለ አልነበረም፤ሆኖም ነፍጠኝነት ለአማራው የተለየ ቅጥያ በመደረጉ በአለፉት ሰላሳ ዓመታት በየደረሰበት በየምክንያቱ አማራው የሚከሰስበት የሚወቀስበት፣ ለጥቃት የሚጋለጥበት  ሆኖ ቆይቷል፡፡
ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ደግሞ ነፍጠኝነት  በፌደራል መንግስት ሆነ በክልል ደረጃ  እንደ አንድ የፕሮፓጋንዳ  ግባት ተደርጎ ሲቀሰቀስበት፣ ፕሮፖጋንዳ ሲሰራበት የቆየ መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ በየቦታው የሚንገላታው፣ የሚደበደበው፣የሚታሰረሰው፣ሃብት ንብረቱን የሚቀማው ጥና ሲል ደግሞ የሚገደለው አማራው መሆኑን፣ አገር ከዳር እስከ ዳር ያውቀው እውነት ነው፡፡ ደብድበውና ዘርፈው እንዴት እንዲህ አደረጋችሁ ሲባሉ፣ “እሱማ አማራ ነው” የሚል መልስ የሚሰጡ ተሿሚዎች መኖራቸውንም ደጋግመን የሰማነው ደረቅ እውነት ነው፡፡ ለእነሱ አማራ ቢገሉት የማያስጠይቅ እንስሳ እንጂ እንደነሱ የሰው ፍጡር አይደለም፡፡
ለአማራው ዘረኛ የሆነ “ነፍጠኛ” የሚል የማጥቂያ ስም እንዲሰጠው አንድ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው የአጼ ምኒልክ መንግስት፣ አማራ ከሌላው የኢትዮጵያ ብሔረሰብ እራሱን ነጥሎ፣ በሌላው ላይ ራሱን የበላይ አድርጎ የገዛበት ወይም ያስተዳደረበት መንግስታዊ ሥርዓት ግን አልነበረም፡፡ የንጉስ ነገስቱ የአፄ ምኒልክ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና አስተዳዳሪዎች ከኦሮሞና ከሌላው ብሔረሰብ መካከል የተገኙ መሆናቸውም ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ስለዚህም ኢትዮጵያ አሁን የምትጀምረው አዲስ መንገድ.፣ አዲስ ምዕራፍ፣ አማራውን “ነፍጠኛ” ከተባለ የጥፋት ስም ማላቀቅ መቻል አለበት፡፡ ሐሰተኛ ትርክቶች መታረም ይኖርባቸዋል፡፡ እስከ አሁን የተነዛው እና  በተሳሳተ መረጃ የተተከለው የጥላቻ ግንድ በአንድ ጊዜ ባይሆንም፣ እየተነቀነቀ ተነቅሎ እንዲወድቅ መደረግ አለበት፡፡
አዲሱ ምዕራፍ ለአማራው ሕዝብ አዲስ፣ ከጥላቻ የፀዳ መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከተለጠፉበትና ኢላማ ካደረገው የዘረኝነት ስም የሚላቀቅበት  መሆንም ይገባዋል፡፡

Read 2123 times