Tuesday, 19 October 2021 00:00

አንድ ጥሬ የት ትደርሳለች? ከእጅ ካመለጠች፤ ሁሉንም ታዳርሳለች

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 ድሮ ነው አሉ፡፡ ወደ ህንድ ያቀና አንድ ጥበበኛ ተጓዥ፣ ጥሩ እድል ገጠመው። እጅግ ወደ ተዋበው ቤተመንግስት፣ እጅግ ከተከበረው ንጉስ ዘንድ እንዲገባ ተፈቀደለት።
ንጉሱ፤ ወደር የለሽ ምርጥ የቼዝ አዋቂ ነው ይላሉ - የአገሬው ሰዎች፡፡
ጥበበኛው ተጓዥ፣ የንጉሱን ዝና ሰምቶ ኖሯል፡፡ አክብሮቱን ለመግለፅና ንጉሱን ለማስደሰትም ስጦታ አዘጋጅቷል፡፡
ከጥሩ እንጨት የተሰራ፣በዝሆን ጥርስ ያጌጠ፣ ማራኪ የቼዝ መጫወቻ ነው ስጦታው፡፡
አልተሳሳተም፡፡ ሥጦታውን ሲያቀርብ፤ ንጉሡ በጣም ተደሰተ፡፡ ለጌጠኛው የቼዝ መጫወቻም፣ ወዲያውኑ ማዕረግ ተሰጠው።
“ንጉሳዊ የቼዝ መጫወቻ” ተብሎ ተሰየመ፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ፣ እንደ ምረቃና እንደ ክብረ በዓል ነውና፤ ንጉሱ ተጓዡን እንግዳ ለጨዋታ ጋበዘው፡፡
ጥበበኛው ተጓዥ ግን፣ ይቅርብኝ አለ። ንጉሱን ለመግጠም ችሎታ እንደሌለው ለማሳየት፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና ተናገረ፡፡ ንጉሱ ግን፣ ግድ የለም አለ፡፡ ሞክር፤ ካሸነፍክ፣ ከረታኸኝ ያሻህን ነገር እሸልምሃሁ አለ ንጉሡ፡፡
ጥበኛው ተጓዥ አልተግደረደረም፡፡ እሺ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ፍልሚያው ተጀመረ፡፡ ጨዋታው ጊዜ የሚፈጅ ቢሆንም፤ ያለ ብዙ ፈተና፣ጥበበኛው ተጓዥ፣ በቀላሉ አሸናፊ ሆነ፡፡
ለካ፣ ያ ሁሉ ትህትና፤ ያ ሁሉ መግደርደር የውሸት ኖሯል፡፡ ሽልማት ፈልጎ ነውና፡፡ ንጉሡ በውርርድ ቃል እንዲገባለት ፈልጎ ነውና፡፡ ብልጣ ብልጥ መሆኑ ነውና።
ንጉሡ ተናዷል። ግን  ምን ይደረግ? ወደፊት መጠንቀቅ እንጂ፤ የፈሰሰ አይታፈስ ነገር። አታለለኝ የሚል ስሜት ቢፈጥርበትም፣ ቢናደድም፣ ንጉሡ ቃሉን አላጠፈም፡፡
ምን እንድሸልምህ ትሻለህ ብሎ ተጓዡን ጠየቀው፡፡
ሩዝ አለ ተጓዡ፡፡ ሩዝ ይሸልሙኝ፡፡
ሩዝ? ይሄ የስንዴ ዘመድ? እህል?  ይሁና። “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ነው”  ብሎ አልተሳለቀም። ምንቸገረው። ወርቅ፣ አልማዝ፣ እንቁ… እንዲህ አይነት ሽልማት ነበር ንጉሡ የጠበቀው። ሩዝ? እንግዲህ፣ ምን ያህል ይሁንልህ? ስንት ጆንያ፣ ስንት ኩንታል?
ተጓዡ እንግዳ፣ አሁንም በትህትና ተናገረ።
የቼዝ መጫወቻው ባለ 64 ንጣፍ ሰንጠረዥ አይደል?
በመጀመሪያው ንጣፍ ላይ እንዲት ፍሬ ሩዝ፡፡
በሁለተኛው ምንጣፍ ላይ እጥፍ….ሁለት ፍሬ፡፡
በሦስተኛው ንጣፍ ላይ እጥፍ …. አራት ፍሬ፡፡
 በአራተኛው ንጣፍ ላይ እጥፍ…ስምንት ፍሬ፡፡
እንዲህ እንዲህ፣ ሁሉንም ንጣፎች የሚሞላ ሽልማት ይሥጡኝ አለ-ጥበበኛው ተጓዥ፡፡
ጭራሽ የሩዝ ፍሬ? የሩዝ ጥሬ? በጣም ጥሩ። እንደሻህ ይሆንልሃል፡፡ የጠየቅኸንን ሽልማት እንሰጥልሃለን አለ ንጉሡ፡፡ የግምጃ ቤት አማካሪውን ጠርቶ፤ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ሽልማቱን ስጡት አለ፡፡
የግምጃ ቤት አማካሪው ግን፣ ብዙም ሳይቆይ፣ ወደ ንጉሡ ተጠግቶ ይቅርታ ጠየቀ፡፡ የንጉሡን ትዕዛዝ መፈጸም አልቻለም፡፡ “የማይሞከር ነው ጌታዬ” በማለት የአማካሪነቱን ተናገረ።
ምን? ለምን?
ለሽልማቱ የሚበቃ ሩዝ የለም፡፡ ንጉሡ ድሃ ስለሆነ አይደለም፡፡ ሃብታም ነው። ሞልቶ የተረፈው ከበርቴ ነው። ግን በቂ ሩዝ የለውም። በየትኛውም አገር ቢሆን የዚህን ያህል ሩዝ ወይም ስንዴ ያለው ንጉሥ የለም፡፡ የዘመኑ ነገስታት ሁሉ ጎተራቸውን አራግፈው ቢያዋጡና ቢደመር፤ ኢምንት ጠብታ አይሆንም። ሽልማቱ የውቅያኖስ ያህል ብዙ ነው። የሁሉም አገር የሩዝ አዝመራ ቢጠራቀም እንኳ፣ አሁንም በጣም ይጎድላል፡፡
ሽልማቱ፣ ገና ከመነሻው፣ አጀማመሩ፣ አንድ ጥሬ፣ ሁለት ፍሬ፣ አራት፣ ስምንት እያለ ሲቀጥል፣ ቀላል ይመስላል፡፡ ግን፣ ከከባድም በላይ ነው- ለማሰብ የሚያስቸግር፡፡
እንኳን ድሮ ይቅርና፣ ዛሬ እንኳ፣ በእጥፍ እየተባዛ፣ የቼዝ ንጣፎችን የሚሞላ የሩዝም የስንዴም ምርት የለም። አዎ የሩዝና የስንዴ ምርት ባለፉት 60 ዓመታት ወደ ሶስት እጥፍ አድጓል።
2 ቢሊዮን ኩንታል ነበር የሩዝ ምርት (በ1950)። ዛሬ ከ5 ቢሊዮን ኩንታል በላይ ሆኗል- ዓመታዊው የአለም ምርት።
እንግዲህ አስቡት። በኩንታልና በቢሊዮን ነው ጨዋታው። ከመቶ ዓመት በፊት፣ የመላው አለም የሩዝ ምርት ከ1 ቢሊዮን ኩንታል ወደ ሁለት ለማድረግ ብዙ ዓመት ፈጅቶበታል።
አንድ ኩንታል ሩዝ ውስጥ፣ ስንት የሩዝ ፍሬ  (ጥሬ) እንደሚኖር ይታያችሁ። በጥንት የሚዛን ስሌት፣ አንድ ኪሎ ሩዝ፣ 50 ሺ ጥሬ ሩዝ ገደማ ነው ይባል ነበር።
አንድ ኩንታል፤ 5 ሚሊዮን ጥሬ መሆኑ ነው። በ2 ቢሊዮን ኩንታል አባዙት።
በቁጥር አንጻፈው ቢባል፤ 10 እንበልና 15 ዜሮዎችን እናስከትላለን። ይሄ የአንድ ዓመት ጠቅላላ የዓለም ምርት ነው - የሩዝ ፍሬ በቁጥር።
ለቼዝ ንጣፎች የተፈለገው የሽልማት ግን፣ ከሺ እጥፍ በላይ፣ ከሺ ዓመታት ምርት በላይ ነው።
ንጉሡ፣ ከባድ እዳ ውስጥ ገባ።  የማይቻል  የማይሞከር እዳ ነው፤ በራሱ ላይ  የተጫነው። አገሩ ሁሉ ተሸጦም አይሞላለትም። እና ምን ተሻለ?
አንዳንዶች እንደሚያወሩት ከሆነ፣  የታሪኩ መጨረሻ ጥሩ አይደለም። ንጉሡ፣ በተጓዡ እንግዳ ተቆጥቶ በብልጣብልጥነቱ ተበሳጭቶ፣ ሞት ፈረደበት። አጭበርባሪ ነጋዴ፣ ያየር ባየር ቀሻቢ ብሎ ሰቀለው። እንግዲህ፣ “ይባላል” ነው ነገሩ።  የታሪኩ መቋጫ እንዲህ ከሆነ፣ ያሳዝናል። ትራጀዲ ነው።
ሌሎች ግን፣ ንጉሡ አልተበሳጨም ባይ ናቸው። ቢበሳጭም ለአፍታ ያህል ብቻ ነው። ንጉሡ ወዲያውኑ ተረጋግቶ ሲያስበው፤ የእንግዳው ተጓዥ ብልጣ ብልጥነት፣ ለበጎ ነገር ሊያገለግል ይችላል። ብልጠት፣ እንደአያያዛችን ነው አለ። ለማምታታትም ለማምረትም ሊጠቅም  ይችላል። ይህንም በማሰብ፣ ንጉሡ ወሰነ። ተጓዡን እንግዳ ጠርቶ፣ ዋና አማካሪው እንዲሆን ሹመት ሰጠው። Happy ending ልትሉት ትችላላችሁ።
የተዋጣለት አጨራረስ ነው ለማለት ግን ያስቸግራል። በእርግጥም፣ታሪኩ ሌላ ነው ብለው የሚተርኩ አሉ።  እንዴት በሉ።
ታሪኩ፣ ለእልባ አስቸጋሪ ነው።  ለሽልማት የሚበቃ ሩዝም ሆነ ስንዴ የለም። ሊኖርም አይችልም። ብልጣብልጡ ተጓዥ ግን፣ ችግር የለም ብሎ አማራጭ ሃሳብ አምጥቷል።
ባይበቃም፤ የተገኘውን ያህል ስጡኝ አለ። የሰጣችሁኝን ያህል በእምነት ተቀብዬ እሄዳለሁ በማለትም ለማጣደፍ ሞክሯል። ይዞ ጭኖ ለመሄድ ቸኩሏል።
ንጉሡ ግን እሺ አላለም። “ቃል ቃል ነው። ያሻህን ያህል እሸልምሃለሁ ብያለሁ። ምርጫህን በቁጥር ተናግረሃል። ሽልማትህን ቆጥረህ ትረከባለህ” አለ ንጉሱ። የአንድ ኩንታል የሩዝ ፍሬ አንድ ሁለት እያለ  ቆጥሮ ለመጨረስ፣ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ቀን ይፈጅበታል። ቀን ከሌት እንዲህ በቆጠራ ከቀጠለ፤ ብዙም በጤናና በህይወት አይቆይም። ቢቆይም፤ የአንድ መንደር የአመት ምርት፣ 50 ሺ ኩንታል ሩዝ ዘርግፎ እየለቀመ ለመቁጠር መቶ አመት አይበቃውም።
ብልሁ ንጉስና ጥበበኛው ተጓዥ ተዋውቀዋል።
ሽልማቴን በቁጥር ስጠኝ ብሎ ጀመረ- አንግዳው ተጓጓዥ።
ሽልማትህን ቆጥረህ ተረከበኝ ብሎ ታሪኩን ወደ እልባት አደረሰው - ንጉሡ።
ይሄን አጨራረስ ተመራጭ ነው ይላሉ- በአርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ ዙሪያ ሙያዊ መጽሃፍ ያሳተሙ የመረጃ ባለሙያ። አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ ለሃሳብ ለግምት የሚያስቸግር ገጽታ አለው። ግን ደግሞ በቁጥር የሚገለጽ ነው ይላሉ ባለሙያው።  ትረካው ይህን እውነታ አጉልቶ ያሳያል በማለት መርጠውታል።
ነገር ግን፣  ይሄኛው ትረካ፣ ጥበበኛ አጨራረስ ነው ማለትም ይቻላል። ባተጠበቀ አቅጣጫ የሚታጠፍ ነው- አጨራረሱ። ግን ደግሞ፣ የማይመስል፣ የማያሳምን አይደለም። “እውነትም” የሚያሰኝ ለትረካውም  የሚመጥን አጨራረስ ነው።
አንዳንድ ነገሮች፣ ከአጀማመራቸው፣ ጊዜያዊና አላፊ፣ ቀልድና ጨዋታ ይመስላሉ። እየተባዙ እየተዛመቱ፣ ከአፍታ በኋላ ከእጅ ያመልጣሉ። በብልጣ ብልጥነት የተዘሩ ጥቂት ጥሬዎች፣ ባልታሰበ አቅጣጫ እየተሰራጩና እየተዋለዱ፣ እየተተረጎሙና እየተመነዘሩ፣ ከአቅም በላይ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናሉ። ጭፍንነትን፣ ግጭትንና ዘረኝነትን የሚያራግቡ የአስተሳሰብ ቅኝቶች፤ እንዲህ ናቸው። የእለት ተእለት ጉዳታቸው ብዙ አይመስለንም። ከጊዜ በኋላ ግን መጣፊያቸው ያጥረናል።

Read 7520 times