Sunday, 17 October 2021 18:22

"ሰው ተማረ የሚባለው መቼ ነው?"

Written by  በአስናቀው አሰፋ
Rate this item
(3 votes)


            አንድ የቦረና ገበሬ ማታ ማታ ልጃቸው ምን ሲማር እንደዋለ ይጠይቁታል፡፡ አንድ ቀን ልጁ ለአባቱ ስለ እንቁራሪት የህይወት ኡደት (life cycle) እንደተማሩ ይነግራቸዋል፡፡ አባቱም በግርምት አይ ልጄ፤ ስለምታስቸግረን የወባ ትንኝ ትተው ስለ እንቁራሪት አስተማሩ
          
              የሰሞኑ የካቢኔ ሹመት ላይ አንድ የምክር ቤት አባል ያነሱት ጥያቄ፣ ብዙ ጊዜ ከኔ ጋር የኖረውን ነገር በጽሁፍ እንዳቀርበው ወተወተኝ፡፡  ስለ ትምህርት ሲነሳ በዋናነት የሚነሱ አራት ጉዳዮች አሉ፡፡ (1) ተደራሽነት (Access)፤ (2) ጥራት (quality)፣ (3) ፍትሃዊነት (equity) እና (4) ችግር ፈችነት (relevancy) ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እነዚህን አራት ጉዳዮች ቅደም ተከተል ሰጥተን፣ አንድ በአንድ መፍትሄ መስጠት አለብን ሲሉን፤ ሌሎች የለም በሁለንተናዊ መልኩ መታየት አለበት ይላሉ፡፡ የእኔ ሃሳብ ከሁለተኛው ቢሆንም፣ ይህ ጽሁፍ በአራተኛው ነጥብና በአጠቃላይ "መማር ማለት ምን ማለት ነው" በሚለው ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
ነገሬን በጥያቄ ልጀምር፡፡  አንድ ሰው ተማረ የምንለው መቼ ነው በአንድ የትምህርት አይነት ለምሳሌ በሂሳብ ጎዳና ዲግሪ ሲበጥስ የስምንተኛ ክፍል ሲያጠናቅቅ ማትሪክ ሲፈተን … ወይስ ክፍሉን በትክክል አላስታውሰውም፤ ግን በእርግጠኝነት ከ7-10 ካሉት ባንዱ ነው፡፡  አንድ ቀን የአማርኛ መምህራችን ስለ ትምህርት አንድ ምንባብ ያነቡልናል፡፡ የሳቸውን ክፍለ ጊዜ ሁሉም ተማሪ ፀጥ ረጭ ብሎ ነው የሚከታተለው። በሌላ ምክንያት ሳይሆን ባላቸው መስህብ።  በተለይ ምንባብ ሲያነቡ ዜማ አለው።  በክፍሉ ውስጥ በተከተበ ግን የማይታይ መስመር ተከትለው ይሄዳሉ ይመጣሉ። ብቻ መላ ሰውነታቸውና ድርጊታቸው ተዋህደው የተማሪውን ቀልብ ይገዛሉ፡፡ ሥለ ትምህርት ባነበቡልን ቀንም የነበረው ሁኔታ ትላንት የሆነ ያህል ይታየኛል፡፡  ሁሉም ተማሪ ልቡ ጉሮሮው ወስጥ እንደተሰነቀረች ዓይኖቹ ፈጠው፣ የመምህሩን እርምጃ እየተከተሉ በጥሞና ያዳምጣል፡፡
መምህራችን ከምንባብ በኋላ በሳቸው ዜማና ሽብሻቦ ተመስጦ አንዳንዴ በአካል እንጂ በመንፈስ ለሚጠፋው መንጋ ተማሪ ጥያቄ መጠየቅ ልማዳቸው ነው፡፡ በዚያ ቀንም አንድ ጥያቄ ጠየቁ፡፡  አንድ ሰው ተማረ የምንለው መቸ ነው ሁላችንም ተቁለጨለጭን፡፡ መለሱ ከየት ይምጣ።  ድንገት አንድ ተማሪ እጁን አወጣ፡፡ መምህሩ ቶሎ እድል አልሰጡትም፤ትወና ላይ ባለ አርቲስት እንቅስቃሴ፣ በቀስስታ ወዲያና ወዲህ እያሉ፣ የሌላ ተማሪን አጅ ይጠባበቃሉ፡፡  ወይ ፍንክች! የዚያ ልጅ እጅ ብቻ ተገትሮ ቀረ፡፡  
በመጨረሻም ለዚሁ ልጅ እድሉን ሰጡት፡፡ ተማሪውም በኩራት ከመቀመጫው ብድግ ብሎ፤ አንድ ሰው ተማረ የምንለው የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ ማምጣት ሲችል ነው አለና ተቀመጠ፡፡ በመልሱ እርግጠኛ ባንሆንም፣ ልጁ በትክክል እንደመለሰ ያልገመተ ተማሪ ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እኛና መምህራችንን የሚያግባባን አንዳች ነገር ነበር፡፡  ለተማሪ አያስጨበጭቡም ግን ተማሪ በትክክል ሲመልስ ከፊታቸውና ከትወናቸው የምንረዳው፣ መግለጽ የምታስቸግር አዳች ነገር አለች፡፡ እሷን ካሳዩ በቃ፣ የአንድ ክፍል ተማሪ ሳይሆን ሰልፍ ላይ ስማችን ተጠርቶ እንደተጨበጨበልን ነበር የምንቆጥረው፡፡  ያችን ምልክት ለተማሪው አሻሩት፡፡  እግረ መንገዳቸውንም ሌሎቻችሁ ክፍል ውስጥ አልነበራችሁም ማለት ነው ብለው የቀረውን ተማሪ በነገር ሸንቆጥ አደረጉት፡፡
አንድ ሰው ተማረ ለመባል የግድ ዲግሪ መበጠስ እንደሌለበት ከዚያን ቀን ምንባብ ተረድቻለሁ፡፡ የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ ሲባልም፣ በቀና መልኩ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡  ትምህር ሂደት ነው፡፡ ልቦናችንን ክፍት ካደረግነው በየቀኑ እንማራለን፤ ፊደል ካልቆጠረውም ጭምር፡፡  በአዲስ አበባ መንገዶች የሚያሽከረክር ሹፌር የተጠቀመበትን ሶፍት ወይንም ባዶ የውሃ ኮዳ በመስኮት ሲጥል ሳይ ግርም ይለኛል። ምክንያቱም በህጉ መሰረት ማንኛውም ሹፌር ቢያንስ 4ኛ ክፍል ማጠናቀቅ አለበት።  እነዚህ ሾፌሮች ግን እስከ 4ኛ ክፍል ፊደል ቆጠሩ እንጂ ስለ አካባቢ ንጽህና ግንዛቤው የላቸውም (አልተማሩም) ማለት ነው፡፡  እንደዚህ አይነት ምሳሌዎችን ብዙ ማንሳት ቻላል፡፡
አንድ ዘመዴ ለትምህርት ጀርመን አገር ሄዶ የሆነውን ሲያጫውተኝ፣ በዚያው አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ሆኖ ወደ ሱፐር ማርኬት ይሂዳሉ፡፡ እነዚህ ጥንዶች በግምት 4 ዓመት ከሆነው ልጃቸው ጋር ነበሩ፡፡ ገበያቸውን ገብይተው ከሱፐር ማርኬቱ ሊወጡ ሲሉ ልጁ ከወላጆቹ እግር ላይ ተጠምጥሞ በጀርመንኛ እየተኮላተፈ አላስወጣም ይላል፡፡ እንግዳው ሰውዬ ለህጻኑ ያልተገዛለት ነገር ቢኖር ነው በሚል ግምት፡ ምን ፈልጎ ነው ብሎ ወላጆቹን ይጠይቃል። ጉዳዬ ሌላ ነበር፡፡ ድርጅቶች አዲስ ምርት ሲያስተዋውቁ ለቅምሻ በየሱፐር ማርኬቱ ምርታቸውን በነጻ ያድላሉ፡፡ ታዲያ ይህ ልጅ ወላጆቹ ሳይከፍሉ የቅምሻ እቃውን ይዘው ሊወጡ ሲሉ ስርቆት ስለመሰለው ሚስ ያልከፈላችሁበትን እቃ ከሱፐር ማርኬት እንዳትወስዱ ብላናለች በማለት ወላጆቹን ሌባ ሌባ! ብሎ ለማስያዝ ነበር የሞከረው። መምህሯ ምን ያህል ልጁን እንደቀየሩት አያችሁ ምንም እንኳን ውጤታማነቱ ብዙ የሚተች ቢሆንም፤ የኛ አገር ትምህርት ፊደል ማስቆጠሩ ላይ ስለሚያተኩር፡ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ፡ ሁለተኛ ዲግሪ ወይንም ሶስተኛ ዲግሪ ያለው ሰው በሙስና ተጨማልቆ ልናገኘው እንችላለን፡፡ ይህ ሰው የወንጀለኛ መቅጫ አንቀጾችን አበጥሮ ያውቃል፡፡ ህጻኑ ግን አንቀጾችን ሳይሆን እንደ አምላኩ የሚያምናትን መምህሩን ጠቅሶ "አትነኳትም" አለ፡፡ ታዲያ ማን ነው የተማረው - ልጁ ወይንስ ባለዲግሪው
የአዲሱ የህዝብ ተወካዮች አባል በቁጭት ስለ ትምህርት ሲናገሩ፣ ያ ጠማማ ፎቅ ያፈራቸው ቀና የትምህርት ባለሙያዎችን አስታወሰኝ፡፡ ከነዚህ መሃል ጋሽ መንግስቱ በሥራ ምክንያት ካወቅኋቸው ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ ሰለ ትምህርት ከተነሳ ተናግረው አይጠግቡም፡፡ መንግስቱ አንድ ሁልጊዜ የሚያነሱት ምሳሌ ነበራቸው፡፡ … አንድ የቦረና ገበሬ ማታ ማታ ልጃቸው ምን ሲማር እንደዋለ ይጠይቁታል፡፡ አንድ ቀን ልጁ ለአባቱ ስለ እንቁራሪት የህይወት ኡደት (life cycle) እንደተማሩ ይነግራቸዋል፡፡ አባቱም በግርምት አይ ልጄ፤ ስለምታስቸገረን የወባ ትንኝ ትተው ስለ እንቁራሪት ማስተማሩ ምን ይፈይድልናል ብለው ልጃቸውን ጠየቁት፤ ይሉናል ጋሽ መንግስቱ፡፡  
ከምሳሌው ምን እንማራለን በመጀመሪያ አባትየው ትምህርት ችግር ፈች እንዲሆን ይጠብቃሉ፡፡ ልጃቸው አንድ ደረጃ ደርሶ ሳይሆን ቀን በቀን ሲለወጥ ማየት ይሻሉ። በመቀጠልም በተግባር ላይ የተመሰረተ ትምህርት ይስባቸዋል፡፡ ይህም ማለት መምህራኖቹ ተማሪዎቹ በአካባቢያቸው ሊያዋቸው በሚችሉ ነገሮች ላይ በምሳሌነት ቢያስተምሯቸው ይመርጣሉ፡፡ ሌላኛውና ዋና ተብሎ የሚወሰደው ልጁ በየቀኑ የተማረውን ለአባቱ ማስተማሩ ነው፡፡ የልጁ ትምህርት መፍትሄ ሰጭ በሆነ ቁጥር አባትየው የበለጠ ያስባሉ፤ ካልሆነ ግን ክትትሉ አይኖርም፡፡ ከዚያም አልፎ ልጁ ትምህርቱን እንዲያቋርጥ ሊያስገድዱት ይችላሉ፡፡
ሌላ ምሳሌ ላንሳ፤ ከጥቂት አመታት በፊት አንድ የገጠር አርሶ አደር አግኝቼ ስለ extension package ዝርዝሮች አንድም ሳይስቱ ነገሩኝና በመገረም ማን ነገረዎት ብዬ ጠየኳቸው፡፡ እርሳቸውም ኤክስቴንሽን ሰራተኛ እነደሆነ ነገሩኝ፡፡ ውይይታችን ቀጥሎ ሶስት ልጆች እንደሚያስተምሩ፡ ታላቁ ልጅ 5ኛ ክፍል እንደሆነና ሌሎቹ ከሱ በታች እንደሆኑ አጫወቱኝ፡፡ በእርሳቸው እይታ ትምህርቱን የጨረሰ ልጅ ስለሌላቸው በዕረፍት ጊዜያቸው አባታቸውን ከማገዝ ውጭ ሶስቱም ልጆች ምንም እንደማያደርጉ ገለጹልኝ፡፡ አስቡት፤ አንድ ሰው ኤክስቴንሽን ሰራተኛ ለመሆን ቢያንስ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቅቃል ከዚያም በኤክስቴንሽን ስራ ይሰለጥናል፡፡  ከዚህ ሁሉ ነገር ኤክስቴንሽን ስራ በአንዱ የትምህርት ደረጃ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ቢካተት (1) በሁሉም ቤተሰብ ውስጥ ማለት በሚቻል መልኩ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ወይም የሚማሩ ልጆች ስለሚኖሩ፤ የኤክስቴንሽን ስራ ተደራሽነቱን ያሰፋዋል። (2) ወላጆች የትምህርትን ጥቅም ማየት ሲጀምሩ፣ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ይበረታታሉ፡፡ (3) አብዛኞቹ ወላጆች፣ ልጆቻቸው የሚሏቸውን የበለጠ ስለሚያምኑ፣ የተፈለገው ለውጥ በአጠረ ጊዜ እንዲመጣ ያግዛል፡፡ (4) የመንግስት ወጪን ይቀንሳል፡፡ እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት ቤተሰብን ማስተማርና ተዛማጅ የቤት ሥራዎችን መስጠት የስርዓተ ትምህርቱ አካል አድርጎ መቅረጽ ነው፡፡
የኛ ስርዓተ ትምህርት ባብዛኛው ከውጭ የተቀዳ በመሆኑ፤ አንዳንድ ጊዜ ከአካባቢያችን አውጥቶ ጨረቃ ላይ አውሉ ያሳድረናል፡፡ ለገጠሬው እምብዛም ቢሆንም፤ ለከተሜ ወላጆች የሚያኮራቸው ልጆቻቸው ፊደል ቆጥረው፣ በውጭ ቋንቋ መናገራቸው ነው፡፡ የሚበልጠው ግን ከዚህ በተጨማሪ የአስተሳሰብና ያአሰራር ለውጥ ቢያመጡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ባዶ የውሃ ኮዳ በመኪና መስኮት ስንወረውር አይተው ዝም የማይሉ፤ አልቅሰውና መኪና አስቁመውን፣ ለትራፊክ ፖሊስ የሚከሱን ቢሆን ነበር፡፡  
ለማጠቃለል ያህል፡ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር፣ በየቆንጽላ ጽህፈት ቤቱ መቀጠር የሚችሉ ሰዎችን ማፍራት ላይ አተኩሮ ነበር፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ትኩረቱን ፊደል ቆጠራ ላይ ያደረገው፡፡ ጽህፈት ቤቶቹ በቂ የሰው ሀይል ሲያገኙ፤ በንጉሱ ጊዜ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ (education transformation) ማድረግ ተሞክሮ ነበር። የለውጡ ዋና አላማ ትምህርትን ችግር ፈቺ ለማደረግ ነበር፡፡ አሁንም ትምህርትን ችግር ፈቺ ለማድረግ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለጊዜ ዋጋ አለመስጠት፡ ጉቦኝነት፡ ስንፍና፡ … ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ትምህርት እነዚህንና የመሳሰሉትን ማህበራዊ ችግሮች በሚፈታ መልኩ ካልተደራጀ፣ ከትውልድ ትውልድ እንደተንከባለሉ ይኖራሉ፡፡ ከዚህ ላይ ግን በደካማ ውጤቱ የሚተቸው ፊደል ቆጠራ ትኩረት ሳይነፈገው ነው፡፡
ለብዙ ወላጆችና ልጆች የትምህርት ግብ ዲግሪ ወይንም ዲፕሎማ ይዞ ስራ ማግኘት ነው፡፡ ይሄም ማለት አንድ ልጅ ስራ ለመያዝ ቢያንስ 14 ዓመት በትምህርት ላይ መቆየት አለበት፡፡ ከዚህም አልፎ ዩኒቨርስቲ መግባት ያልቻለ ዋጋ እንደሌለው ተደርጎ በህብረተሰቡ ይታሰባል፡፡
ይህ ሁሉ እንዳይሆን ለእያንዳንዱ ክፍልና ደረጃ ግብ ተቀምጦ ያን ግብ በሚያሳካ መልኩ የትምህርት ሰርዓቱ መዘርጋት አለበት፡፡ አምስተኛ ክፍል ያጠናቀቀ ተማሪ፤ አራተኛ ክፍል ካጠናቀቀው በፊደል ቆጠራው፡ በአስተሳሰቡና እድሜውን ለሚመጥን የስራ መስኮች ተመራጭ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡
ካልሆነ ግን በአንድ ወቅት የከተማ ልማት ሚኒሰቴር ሚኒስትር  እንደነበሩት ሹመኛ በማይሆን ውጤት መኩራራት እንጀምራለን።
ሚኒሰትሩ ድግሪ ይዘው ኮብልሰቶን ስራ ላይ የተሰማሩትን ወጣቶች በቁጥር እየጠቀሱ፣ እንደ ትልቅ የሚኒሰቴር መሥሪያ ቤታቸው ስኬት አድርገው በሚዲያ ሲናገሩ እታዘባቸው ነበር፡፡


Read 10719 times