Sunday, 17 October 2021 00:00

የሊሴ ገ/ማርያም የቀድሞ መምህር በደላቸውን ይናገራሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “ያለሁት በአገሬ ላይ እንጂ ፓሪስ በስደት ላይ አይደለሁም “


               ወይዘሮ ትዕግስት ሃይለጊዮርጊስ ይባላሉ፡፡ በዝነኛው የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት በስፓኒሽ  ቋንቋ  መምህርነት ከ15 ዓመታት በላይ ማገልገላቸውን ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ታዲያ በት/ቤቱ አስተዳደር የተለያዩ በደሎችና የመብት ጥሰቶች እንደደረሱባቸው ይገልጻሉ፡፡ በመጨረሻም ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ መባረራቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ፣ ከወይዘሮ ትዕግስት ሃይለጊዮርጊስ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

               የስፓኒሽ ቋንቋ የትና እንዴት ነው የተማሩት?
በደርግ ጊዜ በኦጋዴን ጦርነት ላይ አባታችን በመሞቱ ምክንያት፣ በ10 ዓመቴ፣ ከታላቅ ወንድሜና ከታናሽ እህቴ ጋር  ኩባ ሄድኩ፡፡ ከመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ በአግሮኖሚስት ማስተርስ እስከቀበል ድረስ ለ11 ዓመት በስፓኒሽ ቋንቋ ነው  የተማርኩት፡፡ በ1983 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ፡፡ ከዚያም በ1986 ዓ.ም ላይ በሰሜን ሸዋ ግብርና ቢሮ ተቀጥሬ ለሰባት አመታት አገለገልኩ፡፡ ከዚያም ሊሴ ገብረማርያም ት/ቤት የስፓኒሽ ቋንቋ አስተማሪ እንደሚፈልግ ሰማሁና፣ አመልክቼ ለመቀጠር ቻልኩ፡፡ ጥሩ የስፓኒሽ ቋንቋ ችሎታ ስለነበረኝ፣ በወቅቱ የት/ቤቱ ዋና የስፓኒሽ ቋንቋ መምህር ለነበረው ረዳት ሆኜ ነው  መስራት የጀመርኩት፡፡ የስፓኒሽ ትምህርት የሚሰጠው ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ነው፡፡ ምንም የስፓኒሽ ቋንቋ የማያውቁ የ9፤ 10 እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎችን ነበር የማስተምረው፡፡
ከስራዎ እንዲሰናበቱ የተደረገው በምን ምክንያት ነው?
እኔም ራሴ ምክንያቱን አላውቀውም፡፡ በመጀመርያ የስፓኒሽ ቋንቋ አስተማሪዎች 3 ነበርን። አንድ ሜክሲኳዊ፣ አንድ ፈረንሳዊና እኔ ማለት ነው፡፡ ከዚያ የተማሪ ቁጥር ቀንሷል በማለት እኔን ከዲፓርትመንቱ አስወጥተው፣ ተገቢ ባልሆነ ቦታ ላይ መደቡኝ፡፡ ይህን ውሳኔ ሲያስተላልፉ ዋና ዳያሬክተሩ፣ የሂሳብ ሹሙና ሌላ  የአስተዳደር ሰው፣ የትምህርት ቤቱ መመርያና ህገ ደንቡ በማይፈቅደው   ሁኔታ ወደ ሌላ የስራ መደብ ማዛወር መብታቸው መሆኑን  ሊያሳምኑኝ ሲሞክሩ፣ "ደሞዝሽን አንነካም" ብለውኝ ነበር።  እኔም የለፋሁበት ደሞዜን ላለማጣትና ስራዬን ለመቀጠል ስል፤ በህግ ማሸነፍ እንደምችል በመገመት፣ ከነበርኩበት መደብ ወርጄ መስራት ጀመርኩ፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን ጠርተው "አንቺን እዚህ ቦታ ላይ እያሰራን የያዝሽውን ደሞዝ ብንከፍልሽ ልክ አይደለም" የሚል ማሳሰቢያ ሰጡኝ፡፡ ለምን እንደዚህ ታደርጋላችሁ ብዬ ብጠይቅም፣ መልስ አጣሁ፡፡ መብቴን ለማስከበር እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ክስ ብመሰረትም፣ መፍትሄ አላገኘሁም፡፡ ከሚከፈለኝ ደሞዝ በጣም ወርጄ እሰራም ጀመር፡፡ ከክሱ በኋላ እኔን መከታተልና ማሳደድ ያዙ፡፡
የሚከፈልዎ ደሞዝ ምን ያህል ነበር?
በስፓኒሽ ቋንቋ አስተማሪነቴ የሚከፈለኝ ደሞዝ በወር 52ሺ ብር ደርሶ ነበር፡፡ በትምህርት ደረጃዬና በአገልግሎት ዘመኔ ነው እዚያ ላይ የደረስኩት፡፡ ማስተርስ አለኝ። በደሞዜ የደረስኩበት ደረጃ፣ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳሰበው መጣ፡፡ በትምህርት አሰጣጥ ጥራት ላይ ጥያቄ አልነበረም፡፡ ለ15 ዓመታት ስሰራ የቃል ማስጠንቀቂያ እንኳን ደርሶኝ አያውቅም፡፡ ሃላፊነቴን በአግባቡ ነበር የምወጣው፡፡ ከወላጅ፤ ከተማሪ፤ ከዳይሬክተሩም ሆነ ከሌላው የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ቅሬታ ቀርቦብኝ አያውቅም። ከዚህ ቀደም በነበሩት ሃላፊዎች አማካኝነት፣ በ2008 እ.ኤ.አ ፈረንሳይ ፓሪስ፣  ለልምድ ልውውጥ  ተመርጬ ሄጃለሁ፡፡ የትምህርት ደረጃን መሰረት አድርጎ የደሞዝ ማስተካከያ ሲመጣ ችግር ተፈጠረ፡፡ እዛ ደረጃ ላይ ያልደረሱ የውጭ ዜጋ አስተማሪዎች፣ ኢትዮጵያውያንን መግፋት ጀመሩ፡፡
“ከስፓኒሽ ቋንቋ ዲፓርትመንት አንቺን ቀንሰንሻል” ብሎ ዲያሬክተሩ ሲያሳውቀኝ፣ "ወደ ቤተ መፃህፍት ክፍል እናዛውርሻለን” ነበር ያለኝ፡፡ ሂሳብ ሹሙ ግን ይህን ውሳኔ በፍፁም አይሆንም ብሎ ተቃወመ፡፡ ከዚያም ደሞዜ በአስር እጥፍ ተቀንሶ ተማሪዎችን የመጠበቅ ስራ ላይ ተመደብኩ፡፡ ሃላፊነቴም ተማሪዎችን ከበር ላይ ከወላጆቻቸው መቀበል፣ በተለያየ ምክንያት ሲቀሩ  መቆጣጠር፣ አስተማሪዎች ሲቀሩ ተክቶ ማስተማር፣ በግቢ ውስጥ የተማሪዎችን ጨዋታና እንቅስቃሴ መቆጣጠርና መከታተል፤ በመዋዕለ ህፃናት ደረጃ ያሉትን ህፃናት ተማሪዎች ማጫወት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይህንንም ለሁለት ዓመት ያህል አንገቴን ደፍቼ ሰርቻለሁ። ከዚህ በፊት የስፓኒሽ ቋንቋ በክፍል ውስጥ ከ15 እስከ 25 ተማሪዎችን ነበር የማስተምረው፤ ጀማሪዎችንና የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑትን፡፡
ከስራዎ በተባረሩ ጊዜ ምን አሉ?
እጅግ በጣም ነው የተሰማኝ፤ ሞራሌን ጎድተውታል፡፡ ልጄን የነፃ ትምህርት እድል እንድትጠቀም በማድረጌ ከደረጃዬ ወርጄ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ በአንድ በኩል በትምህርት ቤቱ ከነበረው ዘመናዊ ባርነት እንደተላቀቀ ሰውም ነፃነት ተሰምቶኛል፡፡ ከትምህርት ቤቱ ካባረሩኝ በኋላ ለልጄ ተሰጥቶ የነበረው የነፃ ትምህርት እድል ከዲሴምበር በኋላ እንደሚቋረጥና ከዚያ በኋላ ከፍዬ ማስተማር እንዳለብኝ ነው ያሳሰቡኝ፡፡ ልጄ ከኬጂ ወደ ኬጂ ስሪ ስታልፍ ሙሉ ኤ ነበር ያመጣችው።
ዘመናዊ ባርነት ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የትምህርት ቤቱ ሃላፊዎች አምባገነኖች ናቸው፡፡ የሚናገሩትን ሁሉ የእግዚአብሄር ቃል ያደርጉታል፡፡ ሰራተኞች የሚደርስባቸውን በደሎች በግልፅ መናገር አይችሉም፡፡ የሰራተኞች ማህበር ለስሙ ነው የተቋቋመው፡፡ በእኔ ላይ ለደረሰው በደል ምንም ያደረገው ነገር የለም፡፡ የማህበሩ አባልና መዋጮውንም ስከፍል የነበረ ቢሆንም፣ ምንም ነገር አላደረገልኝም። ከማህበሩ ሰዎች የሚከራከረው አቶ ሐሺም የሚባል የማህበሩ ሊቀ መንበር  ብቻ ነበር። እሱንም ከአስተማሪነት አንስተው ተማሪ ጥበቃ ላይ መድበውታል፡፡ ሰራተኞች የሚደርስባቸውን በደሎች የሚቃወሙበት እድል የለም፡፡ ማህበሩ ለሰራተኛው ከመቆምና መብትን ከማስከበር ይልቅ ከበላይ ሃላፊዎች ትዕዛዝ እየተቀበለ ጥፋቶችን አጋንኖ ይመሰክራል። በእኔ ላይ ራሱ የመሰከረብኝ የማህበሩ ፀሃፊ ነው፡፡ "ከአስተማሪነት ወደ ተማሪ ጥበቃ ስትወርድ አምናና ፈቅዳ ነው” ብሎ መስክሮብኛል። መጀመርያ ስለደረሰብኝ በደል ግን ለመመስከር አልፈለገም፡፡
ትምህርት ቤቱ ከስራ ካበረርዎ በኋላ  ምን እርምጃ ወሰዱ?
ወደ ፍርድ ቤት ሄጄ አመለከትኩ። ሁለት ጠበቃ አቁመውብኝ ሲከራከሩ ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ ለእነርሱ ተፈረደ። ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብልም አልሆነም፡፡ ከዚያም ወደ ሰበር ሰሚ ይግባኝ ጠይቄ አልሆነም፡፡ አሁን በሊሴ ገብረማርያም ላሉት ኢትዮጵያዊ ሰራተኞች ነፃነት ነው የምጮኸው፡፡ በትምህርት ቤቱ ብዙዎች በግዞት ላይ ናቸው፡፡ የሚገርመው አብሮን ስፓኒሽ ሲያስተምር የነበረው ሜክሲኳዊ ሲሞት ቦታው ክፍት ነበር፤ የውስጥ ማስታወቂያ ሲወጣ ጠይቄያአቸው “አንቺን አንፈልግም” አሉኝ። የትምህርት ቤቱን ብልሹ አሰራር በተመለከተ የዛሬ ዓመት በህዳር ወር በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጣውን ዘገባ ማስታወስ ይቻላል። በገዛ አገራችን ላይ አዲሶቹ ፈረንሳውያን የት/ቤቱ ሃላፊዎች እያዋረዱን ነው። የወረደ ተግባራቸውን በአንድ ምሳሌ ልገልፀው እችላለሁ፡፡ በትምህርት ቤቱ በየጊዜው በሚደረግ ግብዣ ላይ ሁሉም አብሮ መብላትና መደሰት ቢኖርበትም፣ "ያዘጋጀነው ድግስ ለአስተማሪዎች እንጂ ለአስተዳደር ሰራተኞች አይደለም" በሚል የሚመልሱበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አንድ ግቢ ምግብ ቀርቦ የአስተዳደር ሰራተኛ አይበላም፤ ምግቡ የተዘጋጀው ከፍ ከፍ ላለ አስተማሪና የውጭ ዜጎች ነው ብሎ ከሰልፍ ላይ መመለስን ምን ይሉታል፡፡
እርስዎ በመጨረሻ ምን ይላሉ?
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ እድገትና ስልጣኔ ውስጥ ነው የምትገኘው። በእኔ በኩል ብዙ እድሎች ይኖሩኛል፡፡ ከፍ ባሉ ትምህርት ቤቶች የማስተምርበትን ልምድ ነው የያዝኩት፡፡ በትርፍ ሰዓት ቋንቋውን በማስተማርና በማስጠናትም ለመስራት እችላለሁ፡፡ የሚያሳዝነው በትምህርት ቤቱ በሰፈነው ብልሹ አስተዳደር  ሳቢያ ወላጆችና ተማሪዎች፣ እኔን የመሰለ አስተዋይ  ጨዋ  መምህር ማጣታቸው ነው፡፡ መልካም ሥነምግባር ያለኝና በኢትዮጵያዊነቴ የምኮራ ነኝ፡፡ በእኔ ላይ ከደረሰው በመማር በግቢው ያሉ ሰራተኞች በሙሉ መንቃት ይገባቸዋል፡፡ በት/ቤቱ የሰፈነውን ብልሹ አስተዳደር ለመዋጋት መነሳት  አለባቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ት/ቤቱ  የአገልግሎቴን፤ የስራ መፈለጊያዬንና የካሳ ክፍያዬን እንዲከፍለኝ በዚህ አጋጣሚ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡
ከሁሉም በላይ ክብርት ፕሬዚዳንቷ ሳህለወርቅ ዘውዴ የተማሩበት ትምህርት ቤት እንደዚህ መሆኑ ያሳዝነኛል፡፡ ፍትህን ፍለጋ መሄድ ወዳለብኝ ሁሉ እሄዳለሁ። የሚገርመው የእኔ ቤተሰብ በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት የቆየ ታሪክ ያለው ነው፡፡
እናቴ አሁን በህይወት ባትኖርም፣ ለ35 ዓመታት፤ አሁን በአሜሪካ የሚገኘው ወንድሜ ለ10 ዓመታት፣ እኔ ደግሞ ከ15 ዓመታት በላይ፤ በአጠቃላይ ከ60 ዓመታት በላይ ትምህርት ቤቱን አገልግለናል፡፡ ግን በመጨረሻ አሁን ያለው የትምህርት ቤቱ አስተዳደር፣ በብጣሽ ወረቀት፣ "የሶስት ወር ደሞዝሽን እስከ ህዳር ያለውን ተቀብለሽ ውጭ" ብሎ  አባሮኛል፡፡ በጉዳዩ ላይ ባለቤቴ ከሃላፊዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ሞክሮ ያገኘው ምላሽም አሳዛኝ ነው፡፡ “አታከብረንም፤ መጥፎ ንግግር ተናግራናለች” ነው ያሉት። በአገሬ ላይ እንጂ ፈረንሳይ አገር በስደት ላይ አይደለሁም በማለቴ ነው፡፡
"አሁን መልሰን ብናስገባት በሌሎች ሰራተኞችም ላይ ችግር ይፈጠራል” ሲሉም ነግረውታል። ባለቤቴም፤ “አንድ ከፍተኛ ባለሙያ (መምህር) ወደ ጥበቃ ሲመደብ ይህን መናገሩ ቅር ሊያሰኝ አይችልም” ብሎ መልሶላቸዋል። የሚገርመው እኔን ረቡዕ እለት አባርረው አርብ ላይ የሚፈልጉትን ሰው አስገብተዋል። ይህን ጉድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ  እንዲያውቀውና የሚመለከተው አካል ፍትህ እንዲሰጠኝ እጠይቃለሁ፡፡
ለሁሉም ሚዲያ ደግሞ ጉዳዬን አሳውቃለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ፓሪስ  በስደት ላይ አይደለሁም፤ ሀገሬ ላይ ነኝ፡፡ ለመብቴ እታገላለሁ፡፡

Read 4513 times