Saturday, 16 October 2021 00:00

አዳም ረታ፤ ጎምቱ ብዕረኛ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(5 votes)

 "--ልብወለድ ጸሐፊ በሚጽፍበት ወቅት የግድ በሳይንሳዊ መንገድ በተጠና እውነታ ላይ ብቻ ተመስርቶ እንዲጽፍ አይገደድም፣ ምክንያቱም ሥነ-ጽሑፍ፣ ደራሲዎች ግላዊ ርዕዮተ-ዓለማቸውን በነፃነት ለመግለፅ የሚጠቀሙበት መንገድ (subjective intellectual activity) ነዉና፡፡--"
                      
                ባለፈው ሳምንት በቀዳሚዉ ክፍል ጽሑፌ፣ በያዝነዉ ዓመት መስከረም 22 በወጣዉ የዚሁ ጋዜጣ እትም ላይ ሐሙስ ቅዱስ ወይስ እርኩስ? በሚል ርእስ አቶ ያዕቆብ በተባሉ ጸሐፊ የቀረበውን ሥነ-ጽሑፋዊ ምልከታ በመሞገት፣ ግላዊ ምልከታዬን አቅርቤ ነበር፡፡ ይኸ ጽሑፍ ቀጣዩ ክፍል ነዉ፡፡ የዛሬው ጽሑፌም የተዛቡ ሆነው ያገኘኋቸዉን የአቶ ያዕቆብ አቋሞች አፅንኦት ሰጥቶ የሚሞግት ነዉ፡፡
በአቶ ያዕቆብ ጽሑፍ በግልፅ ካስተዋልኳቸዉ የተዛቡ አረዳዶች ዉስጥ አንዱ፣ ጸሐፊዉ በተፈጥሮ ሳይንሳዊ እዉነታ (empirical scientific reality) እና በሥነ-ጽሑፋዊ የፈጠራ ሥራ (literary work) መካከል ያለዉን ሰፊ ሚና በቅጡ ያለመረዳት እክል ነዉ፡፡ ልብወለድ ጸሐፊ በሚጽፍበት ወቅት የግድ በሳይንሳዊ መንገድ በተጠና እውዉነታ ላይ ብቻ ተመስርቶ እንዲጽፍ አይገደድም፣ ምክንያቱም ሥነ-ጽሑፍ፣ ደራሲዎች ግላዊ ርዕዮተ-ዓለማቸዉን በነፃነት ለመግለፅ የሚጠቀሙበት መንገድ (subjective intellectual activity) ነዉና።
ጸሃፊው ከላይ በጠቀስኩት ዳሰሳቸው የአዳምን አፍ አስመልክተዉ እንዲህ የሚል የተዛባ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡-
ይሄን መጽሐፍ እስካጋምሰዉ ድረስ ንባቡ አሰልቺ ሆኖብኝ ደጋግሜ ለማቋረጥ አመንትቼ ነበር፡፡ በበርካታ ዓመታት ንባቤ እንደዚህ መጽሐፍ ተራኪዉ፣ ደራሲዉና ገጸ ባሕርያቱ  በአተራረክ ሂደት ቅጥ በሌለዉ ሁኔታ የተዘበራረቁበት ሌላ ልብወለድ አጋጥሞኝ አይዉቅም፡፡ ብዙ ገጾች ላይ በግርጌ ማስታወሻ መልክ የተሰነቀሩ ተቀጥላ ታሪኮች ከዋናዉ ታሪክ በምን ተለይተዉ የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንደሰፈሩ እንኳን ግልፅ አይደለም፡፡
    አቶ ያዕቆብ አዛብተዉ ያቀረቡትን ያህል አፍ ንባብን እንዳይቀጥሉ የሚፈታተን አሰልቺ ልብወለድ አይደለም፣ እንደውም በአዲስ መንገድ የቀረበው የአተራረክ ሂደት መጽሐፉን ተወዳጅ አደረገው እንጂ፡፡ ጸሐፊው ከአፍ የላቀ ምን አይነት ግሩም የልብወለድ ሥራ እንዳነበቡ ቢጠቁሙን መልካም ነበር፡፡
አዳም፣ አፍን ጨምሮ በብዙ ሥራዎቹ ግርጌ ላይ ከዋናዉ ታሪክ ጋር የተሰናሰሉ ተቀፅላ ታሪኮችን የመጻፍ ልምድ ያለዉ ደራሲ ነዉ፡፡ ይኸንም የሚደርገዉ ዋናዉ ታሪክ ሁሉንም ነገር የሚዘበዝብ ችኮ እንዳይሆን፣ ዋናዉ ታሪክ ባተኮረበት ጉዳይ ላይ አስፈላጊ የሆኑ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ለመስጠት፣ የጻፈው ታሪክ ሊፀንስበት የበቃበትን እውናዊ ግላዊ አጋጣሚና አውድ ለመጠቆም (ይህ የአዳም ግላዊ ምርጫ ነዉ)፣ አንባቢ በልብወለድ መልክ ከቀረበለት ታሪክ በመንደርደር በእዛ ጉዳይ ዙሪያ የተፃፉ የገሀዱ ዓለም ሀቲቶችን አፅንኦት ሰጥቶ እንዲመረምር፣ እንዲመዝን፣ እንዲጠይቅ … ወዘተ በመሻት ነዉ፡፡    
ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ፣ ጸሃፊው፣ ከላይ በጠቀስኩት ርእስ በጻፉት ዳሰሳቸው የአዳምን የአተራረክ ስልት በተመለከተ (ጸሐፊዉ ይህን ያሉት በሌሎች የደራሲው ሥራዎች ዉስጥ የሚስተዋለዉን የአተራረክ ስልት አክለዉ እንደሆነ እገምታለሁ) እንዲህ ጽፈዋል፦
… አዳም እንደ ተራኪ ያገኘዉን ቅራቅንቦ ሁሉ እያግበሰበሰ የሚነጉድ ለጋ እብድ ይመስላል፡፡ ምንም ብጣሽ ታሪክ አይንቅም፡፡ ለመጽሐፉ ትርክት ፋይዳ ያለዉንም፣ የሌለዉንም ሽርፍራፊ ትርክት ሁሉ እየለቃቀመ ይደርታል፡፡ ድርሰት ግን ዘገባ አይደለም (writing is not all about narrating the whole story) … የሚያጫዉተዉ የሚያስቆዝመዉ ጠነን ያለዉ፣ የተተወዉ (void) የሆነው፣ ነገር እኮ ነዉ፡፡
እዚህ ላይ ጸሐፊዉ እንዳተቱት፣ አዳም፣ በብዙ ሥራዎቹ ላይ እንደታዘብኩት፣ ከሚጽፈዉ ቁምነገር ጋር ምንም አይነት ቁርኝት የሌለውን አንዳችም ታሪክ ፈፅሞ ሲደርት አይስተዋልም፤ እንደዉም የሚዳስሰዉን ርእሰ-ጉዳይ አስመልክቶ ነገርዬዉ ሽታ ካለው ጠረኑን፣ ቀለም ካለዉ አይነቱን፣ ቅርፅ ካለዉ ግዝፈቱን … ወዘተ በዝርዝር (detail) በማተት ርእሰ-ጉዳዩን በጥልቀትና በቅርበት መገንዘብ እንድንችል እድልን የሚፈጥር ሆኖ አገኘሁት እንጂ፡፡ አንዱ የአዳም አስደናቂ ሥነ-ጽሑፋዊ ክህሎት ይህ የረቀቀና የጠለቀ ምልከታዉ ነዉ፡፡ በሌላ በኩል፣ አዳም አንድን ዐቢይ ማጠንጠኛ ሐሳብ ሙጥኝ ብሎ በዛ ሥራ አማካኝነት ግላዊ ፍልስፍናዉን የሚያትት፣ የሚጽፈዉን ነገር በወጉ የሚያዉቅ ፕሮፌሽናል ደራሲ እንጂ አቶ ያዕቆብ እንዳሉት፣ ከሚጽፈዉ ጉዳይ ጋር ቁርኝት የሌለዉን ግሳንግሱን ሁሉ በዘገባ መልክ የሚያቀርብ ደራሲ አይደለም። የአዳም ዋናዉ አስደናቂ ክህሎቱ እንደዉም በሥራዉ ላይ ያነሳዉን ዐቢይ ጭብጥ ተንተርሶ በዝርዝርና በጥልቀት ርእሰ-ጉዳዩን የሚተነትንበት (analysis) መንገድና ምልከታ (perspective) ነዉ። ከእዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይህ ጽሑፍ ለጋዜጣ የተሰናዳ ሆነ እንጂ ሥራዎቹን እየጠቀስኩ አያሌ ማስረጃዎችን ባቀረብኩ ነበር፡፡      
አቶ ያዕቆብ በጽሑፋቸዉ ሌላ ቦታ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ አስፍረዋል፣ “… አዳም እንደ ደራሲ ከማሳየት ይልቅ መንገር የሚቀናዉ ተራኪ ይመስላል፡፡” የአዳምን ሥራዎች በቅጡ ያጠና ሰው ያለ ጥርጥር በግንባር ቀደምነት ከሚመሰክረዉ ክህሎቱ አንዱ፣ ግላዊ አቋሙን ሙጥኝ ብሎ ሳይዝ፣ ጉዳዩን ከተለያየ አንግል ብቻ እንድመዝነዉ የማድረግ ክህሎቱ ነዉ፡፡ ለምሳሌ አዳም፣ የኮሚኒዝምን ርዕዮተ-ዓለም ለመንቀስ ሲፈልግ የኮሚኒስት አቀንቃኞች የሳቱትን ቁምነገር፣ ርዕዮተ-ዓለሙ ያስከተለውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ … ወዘተ ከማሳየት በቀር የኮሚኒዝም ርዕዮተ-ዓለም ጥላቻዉን በግልፅ በመደስኮር ፕሮፓጋንዳውን የሚነዛ ደራሲ አይደለም፡፡ ይህን ሐሳብ በተጨባጭ ከሚያስረግጡልኝ የደራሲዉ ሥራዎች መካከል አለንጋና ምስር በተሰኘው የአጫጭር ልብወለዶች መድበሉ ውስጥ እግርና ዜጋ የተሰኘዉ የአጭር ልብወለድ ታሪክ እና መረቅ የተሰኘው ረዥም ልብወለዱ ነዉ፡፡ በግልፅ ለመመስከር ያህል፣ አዳም የሚጽፈዉን ርእሰ ጉዳይ ጠንቅቆ የሚያዉቅ፣ ነገር አዋቂ ደራሲ ነዉ፡፡ እኔ እንኳ በ1997 ዓ.ም ታትሞ የወጣዉ ግራጫ ቃጭሎች የተሰኘዉ ሥራዉ ቀስ በቀስ  በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ያስከተለዉን አብዮት፣ በጉልህ መታዘብ የቻልኩ አንዱ የአሁኑ ትዉልድ ጸሐፊ ነኝ፡፡ ያለጥርጥር፣ አሁን የተወሰነ ቡድን የሚያንቆለጳጵሳቸዉ ጸሐፍት፣ የአዳምን ለጋሲ ሊክዱ የማይችሉ ናቸዉ። እንደዉም የአዳም መግነን የስብሀትን ዝና አኮስሶታል፡፡ በእርግጥ ለአዳም አበርክቶት ተገቢውን እዉቅና የለገሱ ሀቀኛ የዘመናችን ጸሐፍትም (አንዱ ሌሊሳ ግርማ ነው) አሉ። ለምሳሌ ኮሌጅ በነበርኩበት ወቅት (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) እኔን በሚያስተምሩኝ ምሁራን አጋፋሪነት ይዘጋጅ የነበረዉ ሃልዮት የተሰኘ የፍልስፋና መጽሔት የፊት ገጹ ላይ አዳም፤ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ንጉሠ ነገሥት የሚል ዐቢይ ርእስ ይዞ በመውጣት ደራሲው ሊለገሰው የሚገባዉን እዉቅና እና ስፍራ በወጉ ለግሶታል፡፡ ይህ ተግባር እጅግ የሚደነቀም ነዉ፡፡ ታላቅ ሥራ ለሠሩ ሰዎቻችን ተገቢውንና ሀቀኛ እዉቅናን መስጠት ይኖርብናል፡፡ ምዕራቡ ዓለም አጋኖ ያንቆለጳጰሳቸዉን የፈረንጅ ደራሲያን ሥራ ጥቂትም ቢሆን አጥንቻለሁ። አዳም፣ ሥራዎቹ በገናናዎቹ ምዕራባውያን አገራት ቋንቋ ሥላልተጻፉና ተተርጉመዉ ስላልቀረቡ ነዉ እንጂ ያለጥርጥር ለሥራዉ ታላቁ የምድራችን ሽልማት የሆነዉን የኖቤል የሥነ-ጽሑፍ ሽልማት እስካሁን በተሰጠው ነበር፡፡ ሥራዎቹ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ቢተረጎሙ የእኔም ብርቱ ምኞት ነው፡፡
አቶ ያዕቆብ፣ ሌላ ቦታ ላይ ደግም ቀጥሎ የቀረበዉን አተያይ ጽፈዋል፣ “… የአዳም ረታን ልብወለዶች አስቀድሞዉኑ ታኝከዉ በተተፉት የኤግዚስቴንሻሊዝምና የአብዘርዲዝም መነፅሮች ለመተንተን የተሽቀዳደሙት ትንታጎች፣ ስለ ስርዓተ ነጥብ ሲነሳባቸዉ ግን ሕጉ ምን ይሰራል? ይሉናል፡፡” በእዉነቱ ግን፣ ፍልስፍናዊ እሳቤዎች (በተለይ ኤግዚስቴንሻሊስት ፈላስፎቹ ፍሬድሪክ ኒቼ፣ ሶረን ኪርክጋርድ እና ዣን-ፖል ሳርተር እና አብዘርዲስቱ ፈላስፋ አልበርት ካሙ ያነሷቸዉ ዘላለማዊ የሆኑት የሰዉ ልጅ ዘወትራዊ ጥያቄዎች) ጸሐፊዉ አዛብተዉ እንደገለፁት ፈፅሞ ታኝከዉ የተተፉ፣ የሚያረጁና የሚያፈጁ ሐሳቦች አይደሉም፤ በተቃራኒዉ ዛሬም ድረስ በገሀድ የሚስተዋሉትን የሰዉ ልጅ የእለት ተእለት ሀልዮአዊ ሁኔታዎች (existential condtions) ቁልጭ አድርገዉ የሚያስቃኙ እንጂ፡፡ ፍልስፋናዊ ሐሳቦች በዘመን ብዛት እዉነታነታቸዉ እንደሚሻር ሳይንሳዊ ዶግማዎች አይደሉም፣ በአመክንዮአዊ ሀቲቶች የተገነቡ ዘላለማዊ ሆነዉ የሚዘልቁ እሳቤዎች እንጂ፡፡ የሕይወት ትርጉም፣ በእዚህ ፈጣሪ አልባ ግኡዝ ፅንፈ-ዓለም (universe) ዉስጥ ብቻዉን ስለሚኖረዉ የሰዉ ልጅ የነፃነት ወሰንን (freedom)፣  ኃላፊነት (commitment)፣ ራስን ማጥፋት (suicide)፣ ሽንገላ (bad faith)፣ ወለፈንዲነት (absurdity)፣ ሐቀኝነት (authenticity)፣ ጭንቀት (anguish)፣ ግብረገብ (morality)፣ ቀቢፀ-ተስፋ (despair) … የመሳሰሉት የኤግዚስቴንሻሊዝም እና አብዘርዲዝም ፍልስፍና ዐቢይ ጭብጦች ፈፅሞ ታኝከዉ የተተፉ አይደሉም፣ ወደፊትም የሰዉን ልጅ ህልዉናዊ ተግዳሮቶች ለመዳሰስ የሚያገለግሉ ሆነዉ የሚዘልቁ ዘላለማዊ እሳቤዎች ናቸዉ እንጂ፡፡
ሌላዉ፣ ሥርአተ ነጥብን በተመለከተ አቶ ያዕቆብ ከላይ ያሰፈሩት ሀተታ ፍፁም ሐሰት ነዉ፡፡ ለምሳሌ፣ የአዳምን ሥራዎች በኤግዚስቴንሻሊዝም እና አብዘርዲዝም ፍልስፍና አንግል ትንተና ካቀረቡ ግለሰቦች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ግን የአዳምን ፈሩን የሳተ የሥርዓተ ነጥብ  ግልጋሎት አጥብቀዉ ከሚኮንኑ ዉስጥ ነኝ፡፡ ይህን አቋሜን በቀዳሚዉ ክፍል ጽሑፌ ገልጫለሁ፡፡
እንደገናም አቶ ያዕቆብ ሌላ ቦታ ላይ ከእዚህ ቀጥሎ የቀረበዉን አስገራሚ አተያይ አስፍረዋል፦            
… ይሄን ይሄን ሁሉ ሳስብ አዳም በፊሽካ እየተጠራራ ከሚያዳንቀዉ ይልቅ፣ ጠጣሩን እዉነት እየጋተ የሚያነቃዉ፣ የሚያተጋዉ፣ ባስ ሲልም የሚያስደነግጠዉ ደፋር ሃያሲ ያስፈልገዉ ነበር ይሆን? እላለሁ፡፡ አዳም በመጽሐፉ የመዉጫ ገጽ ላይ የድርሰቱ ቅርፅ በሚል ርእስ ሥር፣ ስለ መጽሐፉ ያሰፈረዉ ሀተታም በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ እንዴት በአንድ መጽሐፍ ላይ ራስህን ደራሲም፣ ሃያሲም አድርገህ ትሾማለህ? በበኩሌ ይሄን ሌሎች መጻሕፍቱም ላይ ጭምር የሚከዉነዉን ድፍረቱን በአንባቢዎቹ በነጻነት የማሰብ መብት ላይ እንደተሰነዘረ መራር ንቀት እቆጥረዋለሁ፡፡ ሲፈልግ አንባቢዉ ለዘለዓለም ሳይረዳዉ ይቅር እንጂ ደራሲዉ በድርሰቱ የቅርጽና ይዘት ነጥቦች ላይ ምንም የማለት መብት የለዉም። አንባቢዉ እንደ ንባቡ ጥልቀት፣ እንደ ሕይወት ልምዱ መጠን ሐሳቡን በመሰለዉ መልኩ እንዲያንሸራሽር ሊተዉለት ይገባል፡፡
በግሌ፣ አዳም፣ እንደ ፕሮፌሽናል ደራሲነቱ ይህ ነዉ የሚባል ህፀፅ የሚነሳበት ደራሲ አይደለም፤ አቶ ያዕቆብ ከጠቀሱትና እኔም ከምጋራዉ አግባብነት ከጎደለዉ የሥርአተ-ነጥብ አጠቃቀሙ በስተቀር፡፡ በሌላ በኩል፣ ደራሲያን የየራሳቸዉ ሥራ ላይ ተንተርሰዉ የሚጽፉትን ሀተታ በማዉገዝ አቶ ያዕቆብ ያንፀባረቁት አቋም፤ ሌሎች ሰዎችም ሲናገሩት የሚደመጥ ተራ አስተያየት ነዉ። በተጨባጭ ግን፣ አንድ ደራሲ ሥለ ድርሰት ሥራዉ ይዘትና ቅርፅ አልያም ስለ ሥነ-ጽሑፍ ያለዉን አረዳድ አስመልክቶ የፈለገዉን ጉዳይ ለመጻፍ ከልካይ የለዉም። አዳም ጸሐፊ ብቻ አይደለም፤ የሥነ-ጽሑፍ ንድፈ-ሐሳብ ሊቅም (literary theorist) ነዉ፡፡ ደራሲዉ፣ ሥራዎቹን ሢሠራ ምን አይነት የአጻጻፍ ዘዬን ተከትሎ እንደሠራ መጻፉም ሆነ ስለ ራሱ የድርሰት ቅርፅ ማተቱ፣ ደራሲዉ የተገበረዉን የአጻጻፍ ፍልስፍና እንድናደንቅ ቢያደርገን እንጂ የፈጠረዉ ተግዳሮት ያለም፡፡ እንደዉም፣ ደራሲዉ አፍን ሲጽፍ የተገበረዉን የአጻጻፍ መንገድ (ሥግር) የጻፈዉን ዘለግ ያለ ሀተታ (ከአምስት አመት በፊት ይህ ልብወለድ ሲመረቅ መድረክ ላይ ያነበበዉን ማለቴ ነዉ) አብሮ ቢያሳትመዉ ሸጋ ነበር፡፡  
በመጨረሻም፣ አፍ በተሰኘዉ ረዥም ልብወለድ የቀረበዉ የአዳም አጀማመር አማተሪሽ ነዉ የሚለዉን የአቶ ያዕቆብን  አስተያየትም ፈፅሞ አልቀበለዉም፡፡ የአፍ አጀማመር እንዲህ የሚል ነዉ፦
ቡናማ ፀጉሯን የምትቆረጠዉ አሳጥራ ነዉ፡፡ ሁልጊዜም እንደ ረጠበ ጥቁር ብልቃጥ ያብለጨልጫል፡፡ ኩልኩልቷ በመስቀል ጌጥ የፈካ ነዉ፡፡ ደሞ አንገተ ረዥም ናት፡፡ ተረከዝ የሌላቸዉ ጫማዎች ስለምታደርግ ከዕድሜዋ ልጅ ትመስላለች፡፡ ፈርከክ ያሉ እግሮች አሏት፡፡ የሰርክ ጫማዋ ስኒከር፣ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደሞ የምትለብሰዉ ታይት ሱሪና ቀላል የበጋ ትሬንች ኮት ነዉ። ከአንዱ (ከቀሚስ) ወደ አንደኛዉ (ሱሪ) ለምን እንደተዛወረች የሚገባዉ ጥቂት ነዉ። ከዘነጠች ደሞ የምትለዉጠዉ የጫማዋን ስታይል ብቻ ነዉ፡ ጫማዋ ባለ አጭር ተረከዝ ኪትን ሂል ይሆናል፡፡ በወንዶች አጠገብ ስታልፍ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሴት ጠረን አልነበራትም፡፡ ምድር የምትሸተዉ ካፊያ ሲወርድ አይደለም? ጌርሳሞት ላይ ገና ጎረምሳ አልዘነበም፤ አዉሎ ሲነፍስባት አይደለም? ጌርሳሞት ላይ ገና ብላቴና አልነፈሰም፡፡ ቅልብጭ ያለች ‘ምንም አትል’ የሚሏት አይነት ልጅ ናት፡፡
ከሁሉ ልጃገረዶች ጌርሳሞትን የተለየ የሚያደርጋት ቢያንስ በየወሩ አስገራሚ በሆነ መልክ የከንፈሮቿ ማማር ነዉ፡ ልክ እንደ ሃር የለሰለሱ፣ ልክ እንደ ቀለማም ኩሬ የሚንተገተጉ፤ ልክ ሊፈነዱ እንደደረሱ የፅጌ እምቡጦች የሚያባቡ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ዉብ ክስተት ስንቶቹ ተማርከዋል? ቾኩን በቀኝ እጁ ይዞ ፈዞ ከቀረ የሲቪክ አስተማሪ ጀምሮ (ሽፍቱን ጨርሶ ወደ ቤቱ ከመሄዱ በፊት ይህችን ያማረች የእንስት ትዕይንት በዐይኑ ዉሃ ለማስገባት) ክፍሏ በር ላይ በሚጠብቃት ሐይለኛ ተማሪ በኩል አድርጎ፣ ለገነት መግቢያ ያዘጋጀዉ የብፁዕነት ማርኩ ብትቀነስ ግድ እስከሌለዉ ሌላ ክፍል የሚማር የሆነ የአክራሪ ሃይማኖተኛ ድርጅት አባል ድረስ፡፡ እሷን ያየች ‘ከእኔ በላይ ቆንጆ ለአሳር’ የምትል የአየር ጤና ፕሬፓራቶሪ ኮረዳ በተዛባ ውድድር አንደኛ የወጣ ፊቷን በቅናት ጋርዳ፣ ድምጿን ዝቅ አድርጋ ‘ዉይ ይይይይይ ታድላ’ ብላለች፡፡  
(አዳም፣ 2010፡ ገጽ 7-8)  ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- Telegram:@MekonnenDefro77 ግኘት ይቻላል፡፡Read 435 times