Monday, 10 September 2012 14:48

“ያልተኖረ ልጅነት” የአንዲት እንቦቅቅላ ንፁሕ ነፍስ የተከፈለበት መፅሐፍ!

Written by  አለባቸው ሞ.
Rate this item
(30 votes)

ባለታሪኳን ደግሞ በሕይወት ባያገኛትም፣ ድህነትና በሽታ ተጋግዘው ሳር ባሳከሏቸው በቀጫጭን ለጋ ጣቶቿ ተሰፍረው የተሰደሩት ቃላት፣ ህፃኗ እንስት የታላቅ ነፍስ ባለቤትነቷን ለመግለፅ አልተሳናቸውም፤ እናም ደራሲው፣ ስቃዩዋን ሁሉ ችላ፣ ጥርሷን ነክሳ በመከራ በከተበቻቸው ደብዳቤዎች መነሻነት፣ የዚችን ታላቅ ባለ ርዕይ ህፃን መራራና ፈታኝ የሕይወት ታሪክ፣ ኢዮብ ከተስፋዋና ከጥንካሬዋ በተዋሰው የእይታ መነፅር እየተገራ ወደ መፅሐፍ ሊቀይረው ወሰነ፤ የሚያውቋትን ሰዎች ቃለመጠይቅ ሲያደርግ የሰማው የሕይወት እውነትም፣ ሰዎች ሁሉ ሊያውቁት የሚገባ ታሪክ ያላት እንቦቅቅላ መሆኗን አስረገጠለት፤ አስረግጦም፣ የሕይወት ታሪኳን መፅሐፍ አደረገው፡፡

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ፣ “ይህን መፅሐፍ አንብበኸዋል?” በማለት በእጁ የያዘውን መፅሐፍ አቀበለኝ፡፡ መፅሐፉ አዲስ እንዳልሆነብኝ ተናግሬ ተቀበልኩት፡፡ “እንደ እና ፍራንክ እስትንፋሷ እስከተቋረጠችበት የመጨረሻ ሰዓት ድረስ፣ በተስፋና ለሌሎች ሰዎች በመኖር ታላቅ ፍቅር ያተረፈች የአንድ ኢትዮጵያዊ እንቦቅቅላ፣ የኑሮ ገድል የዘከረ መፅሐፍ ነው!” አለኝና የንባብ ፍላጐቴን ቆሰቆሰው፡፡

አመለዘውድ የተባለች የአሥራዎቹ እድሜ ባለፀጋ ህፃን ያለፈችበት የህይወት እውነት፣ ከሀገራችን የሻገተ የኑሮ ጣጣ ጋር አዋዶ፣ እውነተኛ ታሪኳን በተዋበ ቋንቋ የተረከ መፅሐፍ መሆኑን ተመለከትኩ፡፡ እናም፣ ይህን መፅሐፍ በወፍ በረር እቃኘዋለሁ - አካዳሚያዊ ሂስ ግን አይደለም፡፡

“ያልተኖረ ልጅነት” ስር በሰደደ ድህነትና በኤች.አይ.ቪ በሽታ ከምድረ ገፅ ሊጠፋ በተቃረበ በዋናው ባለታሪክ በነአመለዘውድ ቤተሰብ መሪር ህይወት ላይ የሚያጠነጥን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2001 ዓ.ም ለህትመት የበቃና እስከ አራተኛ እትም የደረሰ 232 ገፆች ያሉት ተራኪ ኢ-ልቦለድ መፅሐፍ ነው፡፡ ደራሲው ኢዮብ ጌታሁን፣ “ከሞናሊዛ ጀርባ” የሚል የአጭር ልቦለድ መፅሐፍ ያለው ሲሆን፣ ይህን በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው “ያልተኖረ ልጅነት” ሁለተኛ መፅሐፉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

መፅሐፉ፣ የልቦለድንም የኢልቦለድንም ያፃፃፍ ስልት የዘናነቀ ሲሆን፣ በይዘቱ የኢ-ልቦለድን፣ በቅርፅ የፈጠረ ልቦለድን ወረሷል፡፡ እውነተኛ ታሪኮች፣ የአንባቢን ቀልብ ገዝተው እንዲነበቡ ለማድረግ በሚያስችል፣ በቋንቋ ውበትና ለትረካ ቴክኒክ አብዝቶ በሚጨነቅ በፈጠራዊ ኢ-ልቦለድ አፃፃፍ የተከተበ ልብ አንጠልጣይ መፅሐፍ ነው፡፡

ደራሲው በመግቢያው ላይ በፈጠራዊ ኢ-ልቦለድ አፃፃፍ ዘዴ የሚቀርብ እውነተኛ ታሪክ እንዲነገር ሳይሆን እንዲታይ ተደርጐ ነው የሚተረከው” ባለው መሰረት፣ የአመለዘውድን ቅንጣት የህይወት ገጠመኝና በህፃን አዕምሮዋ የተዋቀረ የኑሮ ፍልስፍናዋን አጉልቶ ለማሳየት ብዙ ደክሟል፡፡

መፅሐፉ በሦስት አብይ ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን፣ “የመጀመሪያዎቹን ሁለት ክፍሎች የፃፍኳቸው በይበልጥ ከቃለ መጠየቅ ባገኘሁት መረጃ ተመርኩዤ ነው፡፡ በሦስተኛው ክፍል ግን ከቃለ መጠይቁ መረጃ በተጨማሪ የአመለዘውድን ደብዳቤዎች አካትቻለሁ” በማለት ደራሲው፣ 41 ሰዎችን በአካል፣ በሥልክና በኢ-ሜይል እንዳናገረ ጠቁሟል፡፡ መፅሐፉ 59 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን፣ እያንዳንዱ ምዕራፍ የሚጀምረው የተጠያቂ ሰዎችን አስተያየት በመጥቅስ መልክ በቀጥታ በማስፈር ነው፡፡

ደራሲ ኢዮብ፣ ከዋናዋ ባለታሪክ ከየአመለዘውድ ጋር በአካል የተያየው አንድ ቀን ሲሆን፣ በ”የአፍሪካ በኤች.አይ.ቪ ወላጆቻቸውን ያጡ የህፃናት የእንክብካቤ ጣቢያ” ውስጥ ሲገናኙ፣ የነበረውን ድባብ በውብ ቋንቋ እንደሚከተለው ገልፆታል፤

“…ዞር ብዬ በፈገግታ እጄን ለመጨረሻ ስንብት ወዘወዝኩላት፡፡ ቀጭን እጇን እሷም ወዘወዘችልኝ፡፡ ከመቅፅበት ፊቷን ፍፁም ልዩ በሆነ፣ ብሩህነቱ በጨፍጋጋ ቀን ጥቅጥቅ ደመና በርቅሶ ከሚወጣ የፀሐይ ጮራ በሚልቅ አስደሳች ፈገግታ ሞላችው፡፡

እውነተኛና ንፁህ ፈገግታ ነበር፡፡ በዚያ ልዩ ፈገግታ ውስጥ የልጅነት ዓይን አፋርነት፣ የዋህነትና ፍቅር ይንፀባረቅ ነበር፡፡ ከታመመችና አቅም ከሌላት ደቃቃ ሕፃን ላይ እንደዚያ አይነት ኃይለኛ ጉልበት ያለው ፈገግታ ማየቱ እጅግ አስደነቀኝ፡፡ እስከ ሕይወቴ መጨረሻ ሊረሳኝ የማይችል፣ ትዝታው ልብን በደስታ እያሞቀ፣ ከስር፣ ከጥልቁ ደግሞ ከባድ ሀዘን የሚጭር እፁብ ድንቅ ፈገግታ ነበር…” (ገፅ 7)፡፡

የመፅሐፉ ደራሲ፣ “አመለዘውድ በሚያሳድጋት ድርጅት ውስጥ ለሚሰሩ ሰዎች፣ ለሌሎች ለምታውቃቸው ሰዎች እንዲሁም ለአሜሪካውያን የብዕር ጓደኞቿ ደብዳቤ መፃፍ እንደምትወድ” ሰምቶ ጥቂት ደብዳቤዎቿን የማንበብ እድል ሲያገኝ አንድ ነገር አስተዋለ፤ “የቃላት አጠቃቀሟ፣ በደብዳቤው የገለፀችው ለሰው ያላት ፍቅር፣ ፈጣሪን አንድም ቀን አለማማረሯ…” እጅግ አስደነቀው፡፡

ባለታሪኳን ደግሞ በሕይወት ባያገኛትም፣ ድህነትና በሽታ ተጋግዘው ሳር ባሳከሏቸው በቀጫጭን ለጋ ጣቶቿ ተሰፍረው የተሰደሩት ቃላት፣ ህፃኗ እንስት የታላቅ ነፍስ ባለቤትነቷን ለመግለፅ አልተሳናቸውም፤ እናም ደራሲው፣ ስቃዩዋን ሁሉ ችላ፣ ጥርሷን ነክሳ በመከራ በከተበቻቸው ደብዳቤዎች መነሻነት፣ የዚችን ታላቅ ባለ ርዕይ ህፃን መራራና ፈታኝ የሕይወት ታሪክ፣ ኢዮብ ከተስፋዋና ከጥንካሬዋ በተዋሰው የእይታ መነፅር እየተገራ ወደ መፅሐፍ ሊቀይረው ወሰነ፤ የሚያውቋትን ሰዎች ቃለመጠይቅ ሲያደርግ የሰማው የሕይወት እውነትም፣ ሰዎች ሁሉ ሊያውቁት የሚገባ ታሪክ ያላት እንቦቅቅላ መሆኗን አስረገጠለት፤ አስረግጦም፣ የሕይወት ታሪኳን መፅሐፍ አደረገው፡፡

የመፅሐፉ አፅመ ታሪክ የሚጀምረው በየአመለዘውድ ወላጆች ነው፡፡ የቀን ሠራተኛ አባቷ አቶ ግርማ ይመር እና የጠጅ ቤት የቀን ሠራተኛ የነበረች እናቷ ድንቄ በአጋጣሚ ይዋደዳሉ፡፡ በአንድ ቤት መኖር ሲጀምሩ የአመለዘውድን ታላቅ ተሾመን ጨምሮ ከእሷ በታች ሁለት ወንድሞችን ወልደው በቀን ሥራ በሚገኝ ገቢ ቤተሰቡ ይተዳደራል፡፡ ድህነት ቤቱን ሰላም አሳጣው፡፡ ባልና ሚስቱ ከድህነታቸው የተደበቁ እየመሰላቸው ጠጅና አረቄ ይጐነጫሉ፡፡ ነጋ መሸ በቤት ውስጥ ሰላም የለም፡፡ በርግጥ አቶ ግርማም ሆኑ ወይዘሮ ድንቄ ለልጆቻቸው ይጨነቃሉ፡፡ ኑሮ ግን የማይገፋ ቋጥኝ ይሆንባቸዋል፡፡ በዚህ መካከል አቶ ግርማ ቀድመው ይሞታሉ፡፡ ወ/ሮ ድንቄ ውሃ እየተሸከሙ ልጆቻቸውን ጦም እንዳያድሩ በማድረግ ተዋደቁ፡፡ እናትም በሽታ ጣላቸው፡፡

የሚጥል በሽታ ያለባቸውን እናቷን ጨምሮ ቤተሰቡን የማስተዳደር ሃላፊነት ከ14 ዓመቷ ህፃን አመለዘውድ ትከሻ ላይ አረፈ፡፡ ትምህርቷን አቋርጣ ከየጐረቤቱ እየለመነች የታናናሽ ወንድሞቿንና የበሽተኛ እናቷን ሕይወት ለማስቀጠል ተጣጣረች፡፡ በዚህ መካከል እናቷም ሞቱ፡፡ ከዚህ በኋላ እጅግ አስከፊ በሆነ ሕይወት ውስጥ ማለፋቸው ግድ ሆነ… እናት አባታቸውን የገደለው ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ለአመለዘውድና ለታናሽ ወንድሟ ሚካኤል አልተመለሰም ነበረ…

አመለዘውድ፣ ህዳር 21 ቀን 1998 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየችባት ቀን ድረስ፣ ጥርሷን ነክሳ ወደ ትምህርት ቤት ትሄድ ነበር፡፡ እስከዚች ቀን ድረስ አመለዘውድ በ16 አመት እድሜዋ ስንቱን መከራ እንዳሳለፈች፣ ፈጣሪዋ ይወቅ! ደራሲው ኢዮብ ከደብዳቤዎቿና ከቃለ ምልልስ የሰበሰበውን መረጃ በሥርአት አዋቅሮ፣ በተዋበ ቋንቋ በወጉ ባይተርከው የእንቦቀቅላዋ ታላቅ ነፍስ ከፊል ጩኸት እንኳ እንዴት ይሰማ ነበር!?

መፅሐፉ ብዙ የሕይወት እጣ ፈንታዎችን አውስቷል፡፡ የአመለዘውድ ታናሽ ወንድም የፀረ-ኤድስ መድሐኒት እየወሰደ ነው፤ የመጨረሻው ወንድሟም በህፃናት ማሳደጊያው ጣቢያ በእንክብካቤ እያደገ ነው፡፡ የብዙ ኢትዮጵያዊያን የፈረሰ ቤተሰብ ማሳያ ተምሳሌት የሆነው የነአመለዘውድ ቤተሰብ ታሪክ የአንባቢያን ልብ ይሰብራል፤ ደግነቱ፣ ይህን የሚጐመዝዝ መሪር እውነት የሚያስቃኝ የትረካ ፍሰት፣ አልፎ አልፎ በደብዳቤዎቹ ከሚከሰተው መደናቀፍ በቀር በወጉ ስለሚንቆረቆር፣ የመፅሐፉን ተነባቢነት አያጐልበትም፡፡ የአቶ ግርማ የትውልድ ቀዬ የሆነው የደቡብ ወሎ ዞን ውጫሌ ወረዳ፣ የሰሜን ወሎ ክፍል እንደሆነ ተደርጐ የተገለፀበት አይነት (ገፅ 18) አጋጣሚ ቢከሰትም፣ የመፅሐፉን ማዕከላዊ ጉዳይ እንደማያጐል መጠቆም መልካም ነው፡፡

በመጨረሻም፣ የአመለዘውድን የአደራ ወንድሞች አይነት ወላጅ ያጡና በደማቸው የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ የሚገኝባቸውን ህፃናት ተንከባክቦ በማሳደግ ባለውለታቸው የሆነው፣ “የአፍሪካ በኤች.አይ.ቪ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት እንክብካቤ ፕሮጀክት” (ኢ-ሜይል! This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ፣ ፖ.ሣ.ቁ 647 ኮድ 1033 አዲስ አበባ) እየተወጣው ያለው ሰብአዊ ኃላፊነት ይደነቃል፤ ይበል ያስብላል፡፡

በመፅሐፉ የመጨረሻ ገፅ ላይ እንዲህ ይላል፤ “ለድርጅቱ የወደፊት የህፃናት መንደር ግንባታ ገንዘብ መለገስ ከፈለጉ አዋሽ ባንክ፣ አፍሪካ አንድነት ቅርንጫፍ፣ በባንክ ማጠራቀሚያ ሂሳብ ቁጥር 0130428279900 በማስገባት የዜግነት ግዴታዎን ይወጡ! ኤች.አይ.ቪ ፖዘቲቭ የሆኑ ህፃናትን ተስፋ ያለምልሙ! በህይወትዎ ትርጉም ያለው መልካም ሥራ ይስሩ!”

 

 

Read 8511 times Last modified on Monday, 10 September 2012 14:58