Saturday, 23 October 2021 12:45

በኢትዮጵያ ብቸኛው የዶሮና የእንስሳት ሀብት ዓውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   አስረኛው የኢትዮጵያ ፓልተሪ ኤክስፖና 6ኛው የአፍሪካ እንስሳት አውደርዕይና ጉባኤ ከጥቅምት 18-20 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲሁም ከጥቅምት 22 እሰከ ህዳር 22 ቀን 2014 በበይነ መረብ እንደሚካሄድ ተገለፀ።
በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የንግድ ትርኢቶች አዘጋጅ በሆነው ፕራና ኢቨንትስና መቀመጫውን ሱዳን አገር ባደረገው አጋሩ “ኤክስፖ ቲም” ትብብር ቀዳሚና ሁሉን አቀፍ የዶሮና እንስሳት ሀብት ቴክኖሎጂ ግብአትና መፍትሄዎች ዓለምአቀፍ የንግድ ትርኢት በሁሉም የእንስሳት ሀብት ገበያ ሰንሰለቶች ላይ ያሉ አካላት ይሳተፉበታል ተብሏል።
ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት አውደ ርዕይና ጉባኤዎች ለዶሮ፣ ለእንስሳት መኖ፣ ወተት፣ ለስጋና ለእንስሳት ጤና ዘርፍ እድገትና ልማት ከፍተኛ እድገት ያበረከቱ መሆናቸው በውጤት ተረጋግጧል ያሉት የፕራና ኢቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ፣ የ2014ቱ ይህ ሁነትም ተቀዛቅዞ የቆየውን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱን ጨምረው ገልጸዋል።
ለሶስት ቀናት በሚካሄደው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ አጠቃላይ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩና መሰረታቸውን በኢትዮጵያ፣ በጀርመን፣ በሀንጋሪ፣ በዮርዳሮስ፣ በኔዘርላንድስ፣ በስኮት ላንድ እና ሱዳን ያደረጉ ዓለም አቀፍ የዘርፉ መሪዎችና ጠንካራ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የንግድ ትርኢት ስለመሆኑም አዘጋጁ ፕራና ኢቨንትስ ሀሙስ ረፋድ ላይ በስካይላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህ የንግድ ትርኢት ከኢትዮጵያና ከጎረቤት ሀገራት ከሚመጡ ከ3 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ጋር የሚፈጥሩትን የቴክኖሎጂ ሽግግርን መሰረት ያደረገ የንግድ ትስስር ላቅ ያለ ስኬት እንደሚመዘገብበት ይጠበቃል ተብሏል።
የንግድ ትርኢቱ በመንግስት በኩል በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና በእንስሳት መድሃኒትና የእንስሳት መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባስልጣን የሚደገፍ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ለኪዎች ማህበር፣ ከኢትጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀነባባሪዎች ማህበር እንዲሁም ከኢትዮጵያ የእንስሳት አርቢዎች ማህበር ጋር በትብብብር እንደሚሰራ ተገልጾ፣ የፓን አፍሪካን ቻምበር ኦፍ  ኮሜርስና ኢንዱስትሪ የሁነቱ አጋር እንደሆነም ታውቋል።
በኢትዮ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም የሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦት ግን በሚፈለገው መጠንና ጥራት ፍላጎቱን ማዳረስ እንዳልቻለ በመግለጫው የተብራራ ሲሆን እንደዓለም አቀፍ የግብርና ድርጅት መረጃ ኢትዮጵያ እ.ኤአ በ2030 456 ሺህ ቶን የከብት ስጋ፣ 14 ሺህ 231 ቶን ወተት፣ 96 ሺህ ቶን ዶሮ፣ 54,000 ቶን እንቁላል እንዲሁም 265 ሺህ ቶን የበግና የፍየል ስጋ እንደምትጠቀም ግምቱን ያስቀመጠ ሲሆን ይህንን ፍላጎት በአግባቡ ለማሟላት እንዲህ አይነት ኤክስፖዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አቶ ነብዩ ለማ ጨምረው ገልጸዋል።
መንግስት በ2022 ዓ.ም የወተት ምርቱን 11.8 ቢሊዮን ሊትር፣ የስጋ ምርትን 1.7 ቢሊዮን፣ የእንቁላል ምርቱን 5.5 ቢሊዮን የዶሮ ስጋ ምርትን 106 ሺህ ቶን የአሳ ምርትን 247 ሺህ ቶን እንዲሁም የማር ምርትን 152 ሺህ ቶን ለማድረስ በአስር ዓመት የልማት እቅዱ ውስጥ አካትቶ እየተንቀሳቀሰ ስለ መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የግብርና ሚኒስትር ዲኤታውን ወክለው የተገኙት ሃላፊ ገልፀዋል።

Read 1328 times