Saturday, 23 October 2021 12:49

የአሳማ ኩላሊት የተገጠመለት የመጀመሪያው ሰው በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   በአለማችን የህክምና ታሪክ በአይነቱ የመጀመሪያው በሆነው የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የአሳማ ኩላሊት የተገጠመለት ግለሰብ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ፎርብስ መጽሄት አስነብቧል፡፡
የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ባለሙያዎች ኩላሊቶቹ ስራ ላቆሙበት ታማሚ በቱቦ አማካይነት ከደም ስሮቹ ጋር አገናኝተው የገጠሙለት የአሳማ ኩላሊት ለቀናት በጥሩ ሁኔታ እየሰራ እንደሚገኝና ይህም ስኬት በኩላሊት እጥረት ንቅለ ተከላ ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተው በመላው አለም ለሚሰቃዩ ታማሚዎች ትልቅ ተስፋ ነው መባሉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ይህ ተስፋ ሰጪ የህክምናው ዘርፍ ምርምር ውጤት በመጪዎቹ ጥቂት አመታት ውስጥ የበለጠ አድጎና ተስፋፍቶ ኩላሊቶቻቸው ሙሉ ለሙሉ መስራት ለማቆም በተቃረቡ ታማሚዎች ላይ በሙከራ ደረጃ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል የህክምና ቡድኑ ዳይሬክተር ዶ/ር ሮበርት ሞንቶጎሞሪ መናገራቸውንም አብራርቷል፡፡ ምርምሩ የኩላሊት ህመም ለሚያሰቃያቸው የሰው ልጆች ትልቅ ተስፋን የሰነቀ የምስራች ቢሆንም ታዲያ፣ ለአሳማዎች ግን አስደንጋጭ መርዶ ሊሆን እንደሚችል መነገሩንና ለኩላሊቶቻቸው ሲባል እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው አሳማዎች ሊገደሉና ጉዳዩ የእንስሳት መብት ተሟጋቾችን አደባባይ ሊያስወጣ እንደሚችል መነገሩንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡




Read 3222 times