Saturday, 23 October 2021 12:53

የዓለም ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ ቢካሄድስ? እያወዛገበ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ባስተናገደችው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ፊፋ ያስገባው ገቢ ከብሮድካስቲንግ 2.97 ቢሊዮን ዶላር፤ ከማርኬቲንግ 1.6 ቢሊዮን ዶላር፤ ከትኬት ሽያጭ 541 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከመስተንግዶ 148 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ያወጣው ወጭ ደግሞ ለሽልማት ገንዘብ 430 ሚሊዮን ዶላር፤ ለአዘጋጅ አገር የተሰጠ ድጋፍ 383 ሚሊዮን ዶላር፤ ለቲቪ ስርጭት 239 ሚሊዮን ዶላር፤ ለክለቦች የተፈፀመ ክፍያ 182 ሚሊዮን ዶላር፤ ለዓለም ዋንጫው ቅድመ ዝግጅት 44 ሚሊዮን ዶላር፤ ለተሳታፊ አገራት ዝግጅት ተሳትፎ እና ጉዞ እንዲሁም ለሌሎች የኦፕሬሽን ስራዎች 244 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

           ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ)  የዓለም ዋንጫን በየሁለት ዓመቱ ለማካሄድ የያዘው ዕቅድ እያወዛገበ ነው፡፡  የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በእቅዱ ላይ የሁሉንም ወገኖች ሃሳብ የምናጤንበት አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ገብተናል ሲሉ ተናግረዋል። የፊፋ ምክር ቤት በሚቀጥለው ሳምንት በሚያካሂደው ልዩ ስብሰባ በአቅዱ ላይ እንደሚመክር እና በ2021 የመጨረሻ ቀናት ላይ  በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአጀንዳንት በመያዙ ሁኔታ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ ዓለም ዋንጫ በየሁለት ዓመት እንዲካሄድ የቀረበው እቅድን በድምፅ የሚያፀድቁት የማህበሩ 211 አባል አገራት  በሚሳተፉ ጉባዔ እንደሆነም  ታውቋል፡፡
በፊፋ ድንገተኛ እቅድ ላይ በይፋ ተቃውሟቸውን ያሰሙት ከፍተኛ የስፖርት ተቋማት እና ማህበራት ናቸው፡፡ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ IOC፤ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር UEFA፤ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን CONEMBOL፤ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች FIFpro  ማህበር፤ የዓለም ሊጎች ፎረም፤ የአውሮፓ ክለቦች ህብረት እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በአወዛጋቢው የፊፋ እቅድ ዙርያ ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚያስፈልጉ ጥሪ ከማቅረቡም በላይ የዓለም ዋንጫው በየሁለት ዓመቱ  እንዲካሄድ ከተወሰነ በሌሎች ስፖርቶች፤ በሥርዓተ ፆታ እኩልነትና በስፖርተኞች ህልውና ላይ ሥጋት እንደሚያሳድር አስታውቋል። የአይኦሲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ቶማስ ባች በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ መግለጫ የሰጡ ባይሆንም ሰሞኑን በሰጡት አጭር አስተያየት ‹‹በዓለም አቀፍ ውድድሮችን መርሃግብር ላይ መደራረቦችን የሚፈጥርና ከእግር ኳስ ውጭ ያሉ ስፖርቶችን የሚጎዳ አቅጣጫ መሆኑ አሳስቦኛል ብለዋል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር  ፕሬዝዳንት የሆኑት አሌክሳንደር ሲፈሪን በበኩላቸው ‹‹እቅዱ የሚፀድቅ ከሆነ የዓለም ዋንጫን ህልውና አደጋ ውስጥ ይከተዋል›› በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡  የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፊፋ በያዘው አቅጣጫ የሚገፋበት ከሆነ ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች አባል አገሮቻቸውን የሚያገሉበት ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ ገልፀዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር World Athletics ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮው በሰጡት አስተያየት አጠቃላይ እቅዱ እንዳልተመቻቸው በመግለፅ ዓለም ዋንጫን በየሁለት ዓመቱ ለማካሄድ አሳማኝና በቂ ምክንያት አልቀረበም ሲሉ ተችተዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በያዘው አጠቃላይ እቅድ ከ2024 እኤአ ጀምሮ የሚያዘጋጃቸውን ውድድሮች መርሃ ግብሮች በአዲስ ስርዓት እንዲቀጥል ይፈልጋል፡፡ የዓለም ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ መካሄድ የውድድሩን ዝና የሚያሳድግና የሚገኝበትን ገቢም በእጥፍ እንደሚጨምርም አምኖበታል፡፡ የሰሜን አሜሪካ የካረቢያን፤ የኤሽያ እና የኦሺኒያ ኮንፌደሬሽኖች የፊፋን እቅድ በፀጋ እንደሚቀበሉ አመልክተዋል። ባለፈው ሰሞን በጉዳዩ ላይ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ከ80 በላይ የቀድሞ እውቅ ተጨዋቾችም ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ከእነሱም መካከል ሮናልዶ ሊውስ ናዛርዮ፤ ጀርገን ክሊንስማን፤ ሮበርቶ ካርሎስ፤ ዲድዬር ድሮግባ፤ ፒተር ሽማይክልና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በፊፋ የእግር ኳስ እድገት በሚመለከቱ እቅዶች ላይ በሃላፊነት የተሾሙት የቀድሞ እውቅ አሰልጣኝ ቬንገርም የአባል አገራቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሰልጣኞች በአጀንዳው ላይ ለሚሰጡት አስተያየት ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ በማቅረብ ድጋፋቸውን የገለፁ ሲሆን «አንድ ላይ የምንሰባሰብበት አጋጣሚ በጣም ጥቂት ነዉ። ይሁንና እነዚህን አጋጣሚዎች መቀበል አለብን። እንዲህ ያለ ዉይይት ሁላችንም እግር ኳስ በዓለም ላይ ያለዉን ልዩ ቦታ ለመጠበቅና ዓለም አቀፍ እንድናረገው ይረዳናል።» ብለዋል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር የዓለም ዋንጫው በየሁለቱ ዓመቱ መካሄድ ለአባል አገራት የተሳትፎ እድልን ከፍ የሚያደርግ፣ ማጣርያዎች በቂ የዕረፍት ጊዜ ኖራቸው እንዲካሄዱ የሚያስችልና ተጨዋቾች ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው የሚያደርጉትን ጉዞ የሚቀንስ እቅድ መሆኑን አመልክቷል። የፊፋ እቅድ በአባል አገራቱ የሚፀድቅ ከሆነ፤ በ2026 እኤአ ላይ አሜሪካ፤ ካናዳና ሜክሲኮ በጣምራ ከሚያዘጋጁት 23ኛው የዓለም ዋንጫ በኋላ 24ኛውን የዓለም ዋንጫ በ2028 ለመቀጠል ነው የታሰበው፡፡
ፊፋ ከአንድ ዓለም ዋንጫ የሚያገኘው ገቢ ከ6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን የሚገመት ሲሆን ውድድሩን በየሁለት ዓመቱ በማካሄድ የሚገኘውን ገቢ ለመጨመር እንደሚቻል አረጋግጧል፡፡ በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 5.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፤ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተቀንሶ ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ትርፍ ተገኝቶበታል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ብራዚል ያስተናገደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ 2.6 ቢሊዮን ዶላር እንዳተረፈም ይታወቃል፡፡  
በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ባስተናገደችው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ፊፋ ያስገባው ገቢ ከብሮድካስቲንግ 2.97 ቢሊዮን ዶላር፤ ከማርኬቲንግ 1.6 ቢሊዮን ዶላር፤ ከትኬት ሽያጭ 541 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከመስተንግዶ 148 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ያወጣው ወጭ ደግሞ ለሽልማት ገንዘብ 430 ሚሊዮን ዶላር፤ ለአዘጋጅ አገር የተሰጠ ድጋፍ 383 ሚሊዮን ዶላር፤ ለቲቪ ስርጭት 239 ሚሊዮን ዶላር፤ ለክለቦች የተፈፀመ ክፍያ 182 ሚሊዮን ዶላር፤ ለዓለም ዋንጫው ቅድመ ዝግጅት 44 ሚሊዮን ዶላር፤ ለተሳታፊ አገራት ዝግጅት ተሳትፎ እና ጉዞ እንዲሁም ለሌሎች የኦፕሬሽን ስራዎች 244 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
በ2022 እኤአ ላይ ኳታር ለምታዘጋጀው 22ኛው የዓለም ዋንጫ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ስር በሚገኙ 6 ኮንፌደሬሽኖች ማጣርያዎች  ከወራት በኋላ ሲጠናቀቅ 32ቱ  ተሳታፊ አገራት ይታወቃሉ፡፡ በዓለም ዙርያ የሚካሄዱት ማጣርያዎች ሳይጠናቀቁ በአዘጋጅነት በቀጥታ ኳታር፤ ከአውሮፓ ደግሞ ጀርመንና ዴንማርክ ተሳትፏቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣርያዎች በ4 ዙር ከተካሄዱ በኋላ 17 አገራት ኳታር ከምታዘጋጀው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ውጭ ሆነዋል፡፡ እነሱም ኢትዮጵያ፤ ኮንጎ፤ ጅቡቲ፤ ጊኒ፤ ጊኒ ቢሳዎ፤ ላይቤርያ፤ ኬንያ፤ ማላዊ፤ ሞሪታኒያ፤ ሞዛምቢክ፤ ናሚቢያ፤ ኒጀር፤ ሩዋንዳ፤ ሱዳንና ዚምባቡዌ ናቸው፡፡ የምድብ ማጣርያው የሁለት ዙር ጨዋታዎች እየቀሩት ወደ የመጨረሻው ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሁለት አገራት ሴኔጋልና ሞሮኮ ብቻ ናቸው። አይቬሪኮስትና ካሜሮን በምድብ 4 ውስጥ በመሪነት ለመጨረስ እስከመጨረሻው የሚፋጠጡ ሲሆን ከምድብ 7 ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ዙር በቀሪዎቹ የምድብ ማጣርያዎች ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያደርጉትን ጉዞ ይወስናሉ፡፡

Read 12177 times