Print this page
Saturday, 23 October 2021 12:58

አሜሪካና አውሮፓ ህብረት የአየር ደብደባውን ተቃወሙ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

 • የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጦርነቱ እንዲቆም ዳግም ጥሪ አቅርቧል
 • የህውሃት ታጣቂ ቡድን በሰሞኑ የአየር ድብደባ ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል
 • ትናንት አየር ሃይል ለ4ኛ ጊዜ የህውሃት ወታደራዊ ማሰልጠኛን ደብድቧል
        አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ሰሞኑን በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ውስጥ በሚገኙና የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ይጠቀምባቸው በነበሩ የተመረጡ ኢላማዎች ላይ የፈጸመውን የአየር ድብደባ ተቃወሙ። የአየር ድብደባው ግጭትን የሚያባብስ እርምጃ ነውም ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት  በቲውተር ገጻቸው እንደገለፁት፤ “የኢትዮጵያ አየር ሃይል በመቀሌ ከተማና አካባቢው የፈጸማቸውን የአየር ጥቃቶች የተመለከቱ መረጃዎችን ተዓማኒነት ካላቸው ዘገባዎች ተመልክተናል። ጥቃቶቹ ግጭቱን የሚያባብሱ ሲሆን ሰላማዊ ሰዎችን ለጉዳት የሚዳርግም ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል። “በዚህም የተነሳ የአየር ድብደባውን አሜሪካ አጥብቃ ትቃወመዋለች፤ ሁለቱም ሃይሎች ማለትም የኢትዮጵያ መንግስትና ህወኃት ውጊያውን አቁመው ውይይት መጀመር አለባቸው ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ግጭቱን አቁመው፣ ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ ዳግም ጥሪ አቅርቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት ምክትል ቃል አቀባይ ፈሪሃን ሃቅ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ፤  “የፌደራሉ ሃይል በመቀሌ ከተማ የአየር ድብደባ መፈጸሙ ግጭቱ እንዲባባስና እንዲስፋፋ ያደርገዋል” ብለዋል። የግጭቱ መስፋፋት ደግሞ በአማራና አፋር አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እንዲጨምር እያደረገው ነው ብለዋል። በትግራይ አማራና አፋር ክልሎች ላይ የሚደርሱ ተጨማሪ ጉዳቶችንና በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስቀረት የግጭቱ ተሳታፊ ሃይሎች   ከውጊያው እንዲቆጠቡ ዳግም ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ሰሞኑን በመቀሌ ከተማ በተመረጡ ሂላማዎች ላይ በፈፀመው የአየር ድብደባ  አሸባሪው ቡድን ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል ተብሏል፡፡ ቡድኑ ይጠቀምባቸው የነበሩትን ልዩ ልዩ ወታደራዊ ማዕከላት ሂላማ ባደረገው በዚህ የአየር ጥቃት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ይዞታ የነበረውና በአሁኑ ጊዜ የህወሓት ኃይሎች የወታደር ማሰልጠኛ በማድረግ የሚጠቀሙበት ስፍራ፤ የመሳሪያ ማከማቻ መጋዘኖች፣ የመሣሪያ ጥገና የሚደረግባቸው ቦታዎች፣ የወታደሮች ማሰልጠኛ ካምፖች፣ የወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎች፤ ስንቅና ትጥቅ የሚያመላልሱና ሃብት የሚያሸሹ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ከባድ መሳሪያዎቻ መውደማቸው ተገልጿል።
በትናንትናው እለት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ለ4ኛ ጊዜ በፈጸመው የአየር ድብደባ የህውሃት ወታደራዊ ማሰልጠኛን ማውደሙን የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ አጣሪ ማዕከል በቲዊተር ገጹ ላይ አመልክቷል።
አየር ሃይሉ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ከትናንት በስቲያ  ሐሙስ 9 ሰዓት ላይ  በፈጸመው የአየር ድብደባ፣  የፈደራል መንግሥቱ ንብረት የነበሩና ህወሓት ለሽብር ተግባር ሲጠቀምባቸው የቆዩ  የመገናኛ ብዙኃንና የግንኙነት ማማዎች እንዲሁም መሳሪያዎች ሠመታታቸውና ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ መደረጋቸው ተገልጿል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፈው ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት  ረፋድ ላይ የአየር ሃይሉ በመቀሌ ድብደባ በፈጸመው ድብደባ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ የተባለው ተቋም መውደሙ ታውቋል።
መከላከያ ሠራዊት ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ፤ ላይ እንዳመለከተው  በመቀሌ ከተማ  የተፈጸመው የአየር ድብደባዎች ዒላማ ያደረጉት የጦር መሣሪያ ማምረቻና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎችን ብቻ  ነው ብሏል። የሰሞኑ የአየር ሃይል የመቀሌ ጥቃት የሽብር ሃይሉ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን እንዲሁም ሌሎች ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለማከማቸትና ለመሸሸግ የሚጠቀምባቸውን እና ወደ ወታደራዊ መገልገያነት የቀየራቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ገልጿል።

Read 13292 times