Print this page
Saturday, 23 October 2021 12:59

የአዲሱ መንግሥት ቀጣይ የቤት ሥራ?

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም የተመሠረተው አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሀገራችን ከተደቀነባት ውስጣዊና ውጫዊ  ተግዳሮቶች አንጻር ከፊት ለፊቱ ከባድ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።  
ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የተተከሉት መዋቅሮች፣ ዋጋግራቸው ገና መነቀል አልጀመረም፡፡ በእነዚህ መዋቅሮች ላይ ከቅብ ለውጥ ባለፈ ሥርነቀላዊ እርምጃ ካልተወሰደ፣ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እየተባባሰ እንደሚሄድ ብዙዎች ሥጋት አላቸው፡፡  
በአዲሱ መንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎች
አዲሱ መንግሥት ባልተለመደ መልኩ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ባሉ ካቢኔዎች ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ማካተቱ ትኩረት የሚስብ የፖለቲካ ኹነት ሆኖ አልፏል፡፡ ለመሆኑ ፓርቲዎቹ ከገዢው ፓርቲ የቀረበላቸውን የአብረን እነጥሪ የተቀበሉበት አግባብ ውስጠ ደንባቸውን ተከትለው ነው ወይስ ከመርህ ባፈነገጠ መልኩ ነው? የሚለው  በብዙዎች ዘንድ የሚመላለስ ጥያቄ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ይኽንን በተመለከተ በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከብልፅግና ፓርቲ በቀረበለት አብሮ የመሥራት ጥሪ ላይ ውይይት በማድረግ፣ አብሮ መሥራት በ536 ድጋፍ፣ በ79 ተቃውሞና በ25 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ መጽደቁን፣ ኢዜማ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስታውቋል። የእናት ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ወርቁ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ከመንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት ከውሳኔ ላይ የደረሰው፣ ሥራ አስፈጻሚው፣ በጠቅላላ ጉባኤ በተሰጠው ሥልጣን አማካኝነት ነው፤ብለዋል፡፡
ተቃዋሚዎችን በካቢኔ ወይም በሥራ አስፈጻሚ ውስጥ የሥልጣን ተጋሪ ማድረግ፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት መንግሥታት ያልተለመደ ነው። ይኽንን እርምጃ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች በተለያየ አጽናፍ ይተረጉሙታል፡፡ ገሚሶቹ የፖለቲካ ብዝኃነትን ከማሳደግ አኳያ እንደ ትልቅ እርምጃ ይወሰዳል፤ ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሥልጣን ከማጋራት ባለፈ፣ ተጠያቂነት ያለው ሥርዓትን ለመቀለስ የመንግሥት ዋንኛ ትኩረቱ፣ በተቋማት ግንባታ ላይ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡
በርግጥ የሀገራችን የፖለቲካ ጨዋታ በዜሮ ድምር ስልት የተቀየደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን ጽንፍ የረገጠ የፖለቲካ ዘይቤ ወደ መሀል እንዲመጣ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር የመሥራት ውሳኔን በተመለከተ አንዳንድ ወገኖች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መራጩ ሕዝብ እንዲመርጣቸው የተከራከሩባቸው ፖሊሲዎች ዕጣፈንታ ምንድን ነው?  የፖለቲካ ልሂቃን ይህን በተለያየ ማእቀፍ ነው የሚተነትኑት። ገሚሶቹ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ከማጎልበት አኳያ ፋይዳው የላቀ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ያብራራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ፣ ከገዢው ፓርቲ ጥሪ ሲቀርብላቸው የተቀበሉበትን አግባብ ይሞግታሉ፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመንግሥት የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው የሚተገብሩት ፖሊሲ የማን ነው? ገዢው ፓርቲ ግንኙነት የፈጠረው ከሹመኞቹ ጋር በግል ነው ወይስ ከወከላቸው የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ነው? ሲሉም ሞጋች ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ለመሆኑ በውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች የተከበበው አዲሱ መንግሥት ቀዳሚ ሥራዎቹ ምንድን ናቸው?       
ሰላም እና ደህንነትን ማስጠበቅ
“ከሚወደድ ልፍስፍስ አስተዳደር ይልቅ ጠንካራና የሚፈራ መንግሥት ይመረጣል ”ይላል፤ የማካቬሊ መርህ። እርግጥ ነው አንድ መንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣን (soverign power) አለው የሚባለው በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና ባገኘበት የግዛት ማዕቀፍ ውስጥ ሕግን የማስፈጸም፣ ሕግን የማውጣትና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ አቅሙ ጥያቄ ውስጥ በማይገባ ጊዜ ነው። በዚህ ረገድ አዲሱ መንግሥት ብዙ ፈተናዎች ከፊቱ ተደቅነዋል። ሕወሓት አፈር ልሶ ተነስቷል፡፡ የጥፋት ቡድኑ በሚፈጽመው መጠነ ሰፊ ጥቃት፣ ብዙዎች ለሞትና መፈናቀል እየተዳረጉ ነው። ሥልጣን የያዘው መንግሥት፣ ይኽንን አውዳሚ ኃይል፣ በአጠረ ጊዜ በወታደራዊ ቋንቋ ልክ ማስገባት ካልቻለ፣ በሀገሪቱ ላይ የዳመነውን የመከራ ዝናብ ቀና ብሎ ለማየት ያስፈራል፡፡
ምናልባትም መንግሥት ጨከን ያለ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር የምእራባውያን ጫጫታ ከወትሮው በተለየ መልኩ ሊበራከት ይችላል፡፡  ለዚህም እንደ መፍትሄ የሚወሰደው አጋር ሀገራትን ማበራከት ነው፡፡ የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያ ላይ እያራመደ ያለው አቋም የሶሪያ ግልባጭ መሆኑን የፖለቲካ ልሂቃን ይገልጻሉ።  አሜሪካ በሰብአዊ ቀውስ ጭምብል ኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ማሰቧ አይቀርም፡፡ እዚህ ጋ አሌክሳንደር ኮባይርኮ የተባለ የፖለቲካ ተንታኝ፣ በራሺያ ካውንስል ድረገጽ ላይ ያሰፈረውን ጽሑፍ ዋቢ ማድረግ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
“አሜሪካ በሰብኣዊ ቀውስ ሽፋን እየተከተለች ያለው ጣልቃ ገብነት፣ በሶሪያ ጦርነት ወቅት ያራመደችው ፖሊሲ ግልባጭ ቅጂ ነው፡፡ ሀገሪቱ በሶሪያ ላይ በተከተለችው ግልጽ ጣልቃ ገብነት የተነሳ አያሌ የአገሪቱ ዜጎች ለሞትና ስደት ቢዳረጉም፣ የደማስቆስ መንግሥትን ግን ማስወገድ አልተቻለም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በብዙ ረገድ የተሻለ የጂኦ ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍን የመወሰን አቅምን ተላብሳለች፡፡ ከአሜሪካ በደረሰባት መገፋት ሳቢያ ሌሎች ኃያላን  ሀገራት ከጎኗ መሰለፍ ጀምረዋል፡” ይላል፤ አሌክሳንደር ኮባይርኮ። ስለዚህ መንግሥት ከወታደራዊው ዘመቻ ባልተናነሰ ምእራባውያን የሚፈጥሩትን ጫና ለመመከት ከራሺያ፣ ቻይና እና ቱርክ ጋር ያላትን ቁርኝት አጠናክራ መቀጠል አለባት ሲልም ያሳስባል፡፡
በአግድሞሽ የሥልጣን ክፍፍል የዋጀ ጠንካራ መንግሥት
ሰላምና ደህንነትን ከማስጠበቁ ጎን ለጎን መጤን ያለበት ጉዳይ ተጠያቂነት የሰፈነበት ፍትሐዊ አስተዳደርን ማንበር ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት፣ የዜጎች መብትን የሚረግጥ ሥርዓት የተዘረጋው በፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት እንደነበረ ከማንም የተሰወረ ሐቅ አይደለም፡፡  በመንግሥትና በፖለቲካ ፓርቲ ሥልጣን መካከል ያለው ቀጭን መስመር በወጉ ካልተሰመረ የሥልጣን መደበላለቅ ይፈጠራል፡፡ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ውስጥ አስፈጻሚው በቅጡ ልጓም ካልተበጀለት፣ ሌሎች ቅርንጫፎችን የእርሱ አላማ ተገዢ ያደርጋቸዋል፤ የሚል ሥጋት አለ፡፡
የሥልጣን ክፍፍል የሚለው መርህ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ እንደ ዋልታና ማገር የሚቆጠር የአሠራር መንገድ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ልጓም የሚበጅለት በሦስቱ  አካላት ማለትም፡- በሕግ አውጪው፣ በአስፈጻሚውና በሕግ ተርጓሚው መካከል ተግባራዊ በሚሆነው የአግድም የቁጥጥርና ሚዛን (Checks and Balance)  ሥርዓት ነው፡፡ መርሁ የትኛውም የመንግሥት አካል፣ ጡንቻውን አፈርጥሞ፤ በሌሎች አካላት ላይ የአፈና ሥርዓትን እንዳይዘረጋ ያግደዋል፡፡ ሕግ አውጪው ወይም ፓርላማው ለአስፈጻሚው ታዛዥ አይሆንም፡፡ ከአስፈጻሚው አካል ተረቆ የመጣውን በሙሉ ያለምንም ማንገራገር አያጸድቅም፡፡ ይህ አይነት አሰራር ባለፉት ዐሥርት ዓመታት፣ በኢትዮጵያ የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ላይ የሚንፀባረቅ እንዳልነበረ ታዛቢዎች ይስማማሉ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ራሳቸውን እንደ ሕዝብ ተወካይ ሳይሆን፣ እንደ መንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኛ (ሲቪል ሰርቫንት) ነበር የሚቆጥሩት፡፡ ሕወሓት የሚዘውረው ኢሕአዴግ፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የእዝ ሰንሰለት ተጠፍሮ የተያዘ ስለነበር የምክር ቤቱ አባላት ለማእከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ተገዢ መሆን ነበረባቸው። እዚህ ጋ በውል የምንመለከተው የፓርቲ ሥልጣንን ፈርጣማነትን እንጂ የመንግሥት አቅም አልነበረም፡፡ ሥልጣን የተረከበው መንግሥት፤ “በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን” መሆን የለበትም፡፡ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤቱ ሕይወት ሊኖረው ይገባል፡፡
ለአብነት የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባው ላይ የተስተዋለው የሐሳብ ልዩነት፣ በብዙዎች ዘንድ በበጎ ጎኑ ተወስዷል፡፡ ገዢው ፓርቲ ያቀረባቸውን ካቢኔና ረቂቅ አዋጅን በማጽደቅ ሒደት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ሞጋች ጥያቄ ተሰንዝሮ ነበር፡፡ ይኽ አይነት ልምድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጎለብት የቋሚ ኮሚቴ አባላትን ማጠናከር እንደ አንድ መፍትሄ ሊወሰድ ይችላል፤ የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ በቋሚ ኮሚቴ ውስጥ አቅም ያላቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በማካተት፣ የአስፈጻሚውን ክፍል መገዳደር የሚችል ሞጋች ፓርላማን እውን ማድረግም ይቻላል፡፡   
የሕዝብ እንደራሴዎች ለመረጣቸው ሕዝብና ለኅሊናቸው ታማኝ መሆን እንዳለባቸው በሕገመንግሥቱ ላይ ተደንግጓል።  ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ይኽንን እውነታ ለመታዘብ አልታደልንም። በምክር ቤቱ ውስጥ በሕዝብ የተወከሉት እንደራሴዎች ራሳቸውን እንደ መንግሥት ተቀጣሪ ሰራተኛ ነበር የሚቆጥሩት፡፡ ታማኝነታቸው ለገዢው ፓርቲ ስለነበር፣ አስፈጻሚው ያመጣው ረቂቅ ያለ ምንም ክርክርና ተቃውሞ  በሙሉ ድምጽ ይጸድቅ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የዲሞክራሲ ሥርዓት ዋንኛ መርህ የሆነው የቁጥጥርና ሚዛን ስልት (checks and balances) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ደብዛው አልነበረም፡፡
በመሆኑም ከአዲሱ መንግሥት የምንጠብቀው ሚዛኑን የጠበቀ፣ አስፈጻሚውን በቅጡ የሚሞግት ሸንጎን ነው፡፡ የፓርላማ አባላቱ በምክር ቤቱ ውስጥ እውነተኛ ድምጽ መሆን እንዲችሉ፣ የመረጣቸውን ሕዝብ ቢያንስ በየስድስት ወሩ እየሰበሰቡ ማወያየት ይኖርባቸዋል፡፡ በመራጩ ሕዝብና በፓርላማው መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ስለሌለ፣ ለጊዜው በቀጥታ የሕዝብን የልብ ትርታ የሚያደምጡበት ማእቀፍ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡  
ሕገመንግሥቱን የሚሻሻልበትን ማእቀፍ ማመቻቸት
ከሕወሓት ጋር ኩታገጠም መርህን የሚያቀነቅኑት የዘውግ ድርጅቶች፣ የሕገመንግሥቱ መርህን ከመሄስ ይልቅ ትግበራው ላይ ጉንጭ አልፋ ክርክርን ያበዛሉ። ሕገመንግሥቱ ለአፈና አገዛዝ የተመቸ ሰነድ ነው፡፡ በውስጡ ያዘላቸውም አንቀጾች ከተጻፉበት ቀለም የበለጠ ዋጋ የላቸውም፤ ብለው የሚከራከሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ብልጽግና እንደ ፓርቲ በሕገመንግሥቱ  ዙሪያ ያለው አቋም አሁንም ግልጽ አይደለም፡፡ የአማራው ክንፍ ብልጽግና በሰነዱ ላይ ያለው አቋም ከሞላ ጎደል ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ይመሳሰላል። በአንጻሩ የኦሮሚያው ብልጽግና፣ በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ የሚያንጸባርቀው አቋም የሕወሓት ግልባጭ ይመስላል፡፡ ትልቁ ፈተና ይሄንን የልዩነት ስንጥቅ መድፈን ነው፡፡  ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ምስቅልቅል ምክንያት የሆነውን ሕገመንግሥት እንዳለ ማስቀጠል፣ ውሎ አድሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን መውለዱ አይቀርም፡፡
ሕገመንግሥቱ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ቁመናን በመወሰን ረገድ ቁልፍ አንደሆነ ይታወቃል፡፡ የፌደራል ሥርዓቱ፣ መንግሥታዊ ቅርጹና የምርጫ ሥርዓቱ ዕጣፈንታ በሙሉ የሚወሰነው በሰነዱ ነው። ስለዚህ  ሥልጣን የተረከበው  መንግሥት በዘርፉ የካበተ ሙያ እና ልምድ ያላቸውን ልኅቃን የተካተቱበትን  የህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን  በፓርላማው ይሁንታ  በማቋቋም፣ የማርቀቁ ሒደት መጀመር ይኖርበታል፡፡ ረቂቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሪፈረንደም በማጽደቅ፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ “የእኔ ነው” የሚለው ሕገመንግሥት  ባለቤት መሆን ይገባቸዋል።
ማሰሪያ
ሀገራችን እንደከዚህ ቀደሙ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ወሳኝ የለውጥ ቅያስ (critical juncture) ላይ ደርሳለች፡፡ ይህን እጅግ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ፣ በጥበብና በአግባቡ ማስተናገድ ካልቻልን፣ ፍጻሜው ተገማች ባልሆነ ተጨማሪ የመከራ ዘመናት ውስጥ መዳከራችን የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን የኅልውና አደጋ ለማስወገድም ሆነ መዋቅራዊ ማሻሻያ ለማድረግ፣ ከመንግሥት የሚጠበቀው ቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የገዘፈ ነው፡፡

Read 1756 times Last modified on Saturday, 23 October 2021 13:10