Tuesday, 26 October 2021 00:00

በእንዲህ የተገኘ ወዳጅ እንዴት ውብ ነው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ተስፋ መስጠቱን እንጂ እምነት መዋረድን እንደሚጨምር ብዙ ሰው አይገነዘብም። ውርደትን ቀምሶ ማሳለፍ ግን
ውሎ ሲያድር የትዝታ ጠባሳ ትቶ ያልፋል።
እምነት ስንል ሁለት መልክ አለው። በሰው የሚታመን አለ፤ በፈጣሪው የሚታመን አለ። ሁለቱም ይፈተናሉ።
አንደኛው ይወድቃል፣ ሌላኛው ይፀናል። ይኸኛው ራሱን ለማስወደድ ወድቆ ይነሳል፤ ያልሆነውን ለመሆን
ይጣጣራል። ጥረቱ ሁሌ ያዘልቃል ማለት ግን አይደለም። ለምሳሌ፣ ታፍሶ እስር ቤት ቢታጎር ምን ማድረግ
ይችላል? የሚበላበት፣ የሚፀዳዳበት፣ የሚያወራበትና የሚጋደምበት ሰዓት ሲገደብለት። ከማማ ላይ ቁልቁል  እንደ ወፍ ሊለቅመው ሲያነጣጥርበት። በ “ደምክን ካፈር እንዳልደባልቅ” ዐይን ሲጎመዠው። ቀን ቀን እንደ እህል
ከተሰጣበት ሜዳ ላይ ተንጋልሎ ቅማል ሲቀምል። ነፋስ የበተነውን ኤሎሄ! ኤሎሄውን መላእክት ለቅመው
ሲመዘግቡለት። ሌት እንደ አጣና ደርድሮ ሲያጋድመው፤ እግር አናቱ ላይ ሲተሻሽበት። በአንድ ጀምበር ሽበት
ሲወርረው። ወንድ ልጅ ባንጀቱ ደም ሲያረግዝ። ልቦና ከሰጠው ያኔ፣ ችላ ያላቸውን ጒዳዮች ከልብ ጉያ እያወጣ
ይበረብራቸዋል። ያከበዳቸው ቀልለው፣ ያቀለላቸው ከብደው ያገኛቸዋል።
በተወሰነ ሥፍራና በጠበበች ሰዓት ውስጥ መገናኘት ያለ ውዴታ ማቀራረቡ አይቀርም። መቀራረብ መተያየትና
መጠናናትን፣ መጠናናትም እያደር መተዋወቅና መገላለጥን ይወልዳል። (ስንቴ አብረው በልተዋል፤ ስንቴ ጎን ለጎን
ተቀምጠው አንሾካሹከዋል። የወዳጁ ግራ ጆሮ ላይ ማርያም እንደ ሳመችው የታየው ግን ገና ዛሬ ነው!)
መገላለጥ የድብብቆሽ ኑሮ ጠር ነው። አብሮነትና ወዳጅነት ለስጋት ፍቱን መድኃኒት ነው። ሰው ሆድና ጀርባውን
ከተገላለጠ እርቃኑን ቀረ፣ ራሱን ለነቀፌታ አመቻቸ። ሌላው ሊያጠፋው ወይ ሊያለማው የሚችልበት ሁኔታ
ተፈጠረ። የማይበጅ ኢትዮጵያዊነት ተሸረሸረ ማለት ነው!
አብሮ መኖር ትልቅ አደራ፣ ትልቅ አደጋ የሆነው ለዚህ ነው። … ወይ ተማምኖ እየተጋገዙ መኖር ነው፤ አለዚያ ያለእረፍት መገዛገዝ፣ ያለእፍረት መነዛነዝ ነው። እምነት የሚመዘነውና የግል የሚሆነው፣ በእሳት ተፈትኖ ካለፈ ነው። የምቹ ዘመን እምነት እንዳልተገራ ወይፈን ለቁም ነገር አይውልም። ዘመን ያመጣውን፤ ዘመን ይሸኘዋል እንዲል በነፍስ ለመገናኘትና በቋንቋ ለመግባባት አንድ ሰሞን አይበቃውም። አስቀድሞ የዲሪቶው ሽፍንፍን መገፈፍ አለበት። ይኸ እውነት ሕዝብና ግለሰብን አይለይም። መተማመን እርቃን መቅረት ነው። መከራም የሚላከው ይህን የማስመሰል ካብ ለመናድ ነው። ካብ ለካብ ሳይተያይ፣ ገሃዱን ሳይሸፋፍን የተገኘ ወዳጅ እንግዲህ እንዴት ውድ ነው? ፍቅሩ እንዴት ድንቅ ነው? ትዝታው እንዴት የማያረጅ ነው?
ቢያንስ ለአንድ ሌላ ሰው የልቡን አሳብ መግለጥ ያላወቀ፣ መከራ ያልሞከረውን ምሥኪን በሉት። ከሚመሳስሉት
ክልል ወጣ ብሎ ማየት ያልተቻለውን ዕውር በሉት። መከራ ያልመከረውን ጅል በሉት፤ ወደ ትፋቱ ዳግም፤ ታጥቦ ጭቃ በሉት። ሁሉን እንደ ተጠራጠረ፣ የራሱ እስረኛ ሆኖ ይኖራል። ኑሮው የተሟላ ይመስላል፤ ሕይወትን ግን አያጣጥማትም። ነፍሱን አላካፈለምና፤ የበዛ ሕይወት አይቀበልም። ተዘግቶ እንደ ኖረ ደጅ፣ ብርሃን
እንደማይገባው፣ ለጨለማ ትርፎች መከማቻ እንጂ ለምንም አይበጅ! ይኸ ለግለሰብም ለሕዝብም እውነት ነው።
የእህል ዘር ተቋጥሮ ቢቀመጥ ተቋጥሮ ይቀራል። ተቋጥሮ ይረሣል። ሊያበዛው የሚችለውን የሕይወት ኃይል
በውስጡ ነክሶ ይዞታልና ብቻውን ይሞታል … የተዘጋው ደጅ ሲከፈት ብቻ ጨለማው ሥፍራ ይለቃል።
የተቋጠረው ሲበተን መትረፍረፍ ይጀምራል። ይህን ደጅ የሚከፍትና የተቆለፈውን መዳፍ የሚዘረጋጋ ቅድም
እንዳልነው በአብዛኛው መከራ ነው።
መከራ ባቆራኛቸው ዘንድ ከቀን ቀን የሚከሰተውን ማስተዋል ይጠቅማል። የመጀመሪያው ቀን ላይ ከልማድ
መታገድ፣ የራሴ የሚባል መታጣት ያስቆጣል እንበል። አለዚያም ምግቡ ረሃቡና ጥሙ፣ የሰው ጠረኑ …
መተፋፈጉ ሙቀቱ፣ ማንኮራፋቱ … የመኝታ አለመመቸቱ፣ ኲርፊያው፣ ሌት የጀርባ አጥንት ሲላቀቅ
ድምፃድምፁ፣ ዐመል ያሳጣል እንበል። ውሎ ሲያድር ግን ይህም ይለመዳል። ይባስ ይዋሃዳል። ጊዜ ሲርቅ፣
ሁኔታዎች ሲለዋወጡ፣ በናፍቆት ይታሰባል። ይህ እርቃን የመውጫ አቦሉ ነው።
አሁን ግን መሽቷል፤ ይነጋ ይሆናል … ተስፋ የተደረገበቱ ይዘገያል፤ በልብ ውዝዋዜ “እስከ መቸ ይሆን?”
ይላል። መላ መምታት፣ በጭፍን በሠቀቀን መኖር፣ መፍረክረክ ይጀምራል። ከመሠረቱ ፈርሶ እንደገና አምሮ
ሊገነባ … ይኸኔ የሰው ዋጋ ይታወቃል፤ ቀልሎ መገኘት ወይም ለቁም ነገር መብቃት። መደጋገፍ … ተስፋ
መሠጣጣት፣ በመከራ እየቀለዱ ቀን መግፋት። ይህ የመደማመጥ፣ የመግባባትና የመተሣሠር ሁለተኛ ነው።
ሦስተኛም አለው፦ “ትዝ ይልሃል? … የማያልፍ የለም አለፈ እኮ!” ይላል …
በእንዲህ የተገኘ ወዳጅ እንዴት ውብ ነው? እንዴት የማይረሣ፣ እንዴት የሚመረጥ ነው?
(በምትኩ አዲሱ፤ መስቀል ተ ሠላጢን፣ መለስተኛ ንዛዜ፣ መስቀልኛ ነገር።  ገጽ 131—134)

Read 884 times