Sunday, 24 October 2021 00:00

ለኢትዮጵያ ሙዚቃ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከመንዙማ፣ ከአሚናዎች፣ ከጉባኤ ቃና የተፈለቀቁ ሙዚቃዎች
(በጣም የምወዳት ባለቅኔ ድምጻዊት/
ሸማ ነጠላውን ለብሰው
አይበርዳቸው አይሞቃቸው
ሐገሩ ወይናደጋ ነው
አቤት ደም ግባት – ቁንጅና
አፈጣጠር ውብ እናት
ሐገሬ እምዬ ኢትዮጵያ
ቀጭን ፈታይ እመቤት
እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ትልቅ ደረጃ ላይ ካደረሱት ድምፃዊያን መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ ታዋቂው የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲ ኤን ኤን፤ በተደጋጋሚ ጂጂን እና የሙዚቃ ስራዎቿን አቅርቧል፡፡ ሌሎች የሚዲያ ተቋማትም በአዘፋፈን ስልቷ፤ በድምጿ፤ በሙዚቃ ቅንብሯና በአጠቃላይ ታሪኳን በተመለከተ ሰፊ ሽፋን ሲሰጧት ቆይተዋል፡፡ ይህች ስመ ገናናዋ ድምፃዊት ጂጂ ከ14 ዓመታት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሐገሯ መጥታ በህዝቧ ፊት የሙዚቃ ስራዎቿን አቅርባለች፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው ባለፉት 20 ዓመታት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም የሙዚቃ፤ የሥነ ግጥም እና የሥነ ፅሁፍ ሃያሲያን ስራዎቿን ተንትነውላታል። በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ጉባኤ ላይ በቀረበ ጥናት፤ ጂጂ ከኢትዮጵያ ድምፃዊያን የሚለያት ሙዚቃዎቿ እጅግ የጠለቀ የኢትዮጵያዊነት መንፈስን  በውስጣቸው አምቀው የያዙ በመሆናቸው እንደሆነ የተገለፀበትም አጋጣሚ አለ፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው ሐገሯን በሙዚቃዎቿ ውስጥ የምትገልፅባቸው መንገዶችም እየተነሱ ተተንትነዋል፡፡ ለጂጂ ሀገር ማለት ቤተሰቧ፣ ኑሮዋ፣ ትዝታዋ፣ መልክዐ ምድሯ፣ ወንዞችዋ፣ ተራሮችዋ፣ ህዝቧ… ሲሆኑ የአቀራረብ ዘይቤዋ ጆሮ ግቡና እጅግ ማራኪ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ደግሞ አባይ ወንዝ ላይ የተፃፉ አያሌ የኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ተሰብስበው ሚዛን ላይ ተቀምጠው ነበር። በርካታ ገጣሚያንና ድምጻዊያንን አባይን በየራሳቸው እይታ ሲገልፁት፤ ሲያንቆለጳጵሱት፤ ሲሞግቱት፤ ሲወቅሱት፤ ሲቆጩበት… እንደነበር በጥናት ተዳሷል። በመጨረሻም በግጥም፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኃህን፤ በሙዚቃ  ጂጂን የሚያክል የጥበብ ሥራ ግን አልተገኘም ተብሏል፡፡ ፀጋዬ የስነ ግጥም ጣሪያ ሲሆን፤ ጂጂ ደግሞ የሙዚቃው ቁንጮ ተብላለች፡፡ ከፀጋዬ የሚከተለው ቀርቦ ነበር፡-
ዓባይ የጥቁር ዘር ብስራት፣
የኢትዮጵያ የደም ኩሽ እናት፤
የዓለም ስልጣኔ ምስማክ፣
ከጣና በር እስከ ካርናክ፤
ዓባይ የአቴንስ የጡቶች ግት፣
የዓለም የስልጣኔ እምብርት፤
ጥቁር ዓባይ የጥቁር ዘር ምንጭ፣
የካም ስልጣኔ ምንጭ፤
ዓባይ-ዓባይ ዓባይ-ጊዮን፣
ከምንጯ የጥበብ ሳሎን፣
ግሪክ ፋርስና ባቢሎን፣
ጭረው በቀዱት ሰሞን፡፡
ዓባይ የአማልእክት አንቀልባ፣
የቤተ-ጥበባት አምባ፤
ከእሳት ወይ አበባ
ይህ የሎሬት ፀጋዬ ግጥም በኢትዮጵያ ሥነ ግጥም ውስጥ ደረጃው አንደኛ ነው ተብሏል፡፡ ፀጋዬ ራሱ በባለቅኔነቱ ግዙፍ ሰብዕና ቢሰጠውም፣ ይህ አባይ የሚለው ግጥሙ ደግሞ በተለያዩ የሥነ ግጥም መለኪያዎች  ልዕለ ጥበብ (Masterpiece) ነው ተብሏል፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባው የጂጂ ዓባይ በሙዚቃው ዘርፍ ከፀጋዬ ገ/መድህን ዓባይ ጋር በእኩል ደረጃ ተደንቋል፡፡
የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና፡፡
ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት፡፡
ግርማ ሞገስ
የአገር ፀጋ የአገር ልብስ
ግርማ ሞገስ፡፡
ዓባይ…
የበሐረው ሲሳይ
እያለች ከትውስታ በማይጠፋ የሙዚቃ ስልት የምታንቆረቁር ድምፃዊት እንደሆነች ተነግሮላታል፡፡ እነዚሁ ሁለት የኪነ-ጥበብ ሰዎች ዓባይ ላይ ባቀረቧቸው ስራዎቻቸው የዓባይን መልክ፤ ቁመና፤ ታሪክና ማንነት ገልፀዋል፡፡ ዓባይ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፊው ከመገለፁም በላይ በተለይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተያይዞ መጥቶ ጣና ሐይቅ ውስጥ ገብቶ ግዙፍነቱ ይጨምራል። ጣና ላይ ደግሞ 37 ያህል ደሴቶች አሉ፡፡ በነዚህ ደሴቶች ከ21 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገዳማት አሉ፡፡ እጅግ አስገራሚ የኢትዮጵያ ቅርሶችም በነዚህ ገዳማት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ዓባይ ላይ ይፀለያል፤ ይቀደሳል፤ ይዘመራል፤ በብህትውና ይኖራል፤ ይታመንበታል፡፡  አባይ የኢትዮጵዊያን መንፈስ ነው፡፡ እምነት ነው፡፡ ሀብት ነው፡፡ ይህን አንደምታ ይዘው ነው እነ ጂጂ ዓባይ ላይ ፍፁም ተወዳጅ የሆኑ ስራዎችን ያቀረቡት፡፡
በተመሳሳይ ፀጋዬ ዓድዋ ላይ የፃፈው ሥነ-ግጥሙ ሌላው ተጠቃሽ ስራው ነው፡፡ እጅጋየሁ ሽባባውም ዓድዋ ላይ ያቀነቀነችው ዘፈን እንደ ፀጋዬ ዓይነት እጅግ ጥልቅ ስሜትን የሚያስተጋባ ሥራ እንደሆነ ተመስክሮላታል፡፡ ፀጋዬ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ጋር ፍቅር ጋር የወደቀ ገጣሚ ነው በሚል፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን-ግጥሞቹ ተዘርዝረዋል፡፡ እጅጋየሁ ሽባባውም እንዲሁ ኢትዮጵያዊነትን በስፋት”  የምታስተጋባ ድምፃዊት እንደሆነች በልዩ ልዩ መድረኮችና ጥናቶች ተገልጿል፡፡ በቅርቡም   ከጋዜጠኞች ጋር ባደረገችው ቃለ-ምልልስ፤ የሥነ-ግጥም አድናቂ መሆኗንና ጠቁማ እነ ፀጋዬ ገ/መድህንን በስራዎቻቸው እጅግ እንደምትወዳቸው ተናግራለች፡፡  በተለይ በወለዬዎች መንዙማ እና በአሚናዎች የድምፅ ቅላፄ ላይ ተመስርታ ወደ ዘመናዊ ሙዚቃ አምጥታቸዋለች ይባላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጂጂ ራሷም ትስማማለች፡፡ ገና ከህፃንነቷ ጀምሮ የአሚናዎች የአገጣጠምና የዜማ ስልት እጅግ እጅግ እንደሚገርማትና እንደምትወደው አውስታለች፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት እነ ጂጂ ቤት ለመጣች አሚና ልብሶቿን አውጥታ እንደሰጠቻት የልጅነት ታሪኳን ታወሳለች ጂጂ፡፡  ከመንዙማ እና ከአሚናዎች የሙዚቃ ስልት ተፈልቅቀው የወጡት ስራዎቿ ለህዝብ ጆሮ ቅርብ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በዚህ ስልት ከተጫወተቻቸው ዘፈኖች መካከል ደግሞ “ናፈቀኝ የኛ ቤት ጨዋታ” እያለች የምትዘፍነው ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ- ፅሁፍ መምህር የሆኑት አቶ ወንደሰን አዳነ በጂጂ ሥራዎች ላይ ባቀረቡት ጥናት፤ ለዚህ ሙዚቃ ውበትና የሥነ-ግጥም ብቃቱ እጅግ የተዋጣለት መሆኑን ገልጸዋል። በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ እጅጋየሁ ሽባባው የመጀመሪያዋን አልበም ለቀቀችው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ፅሁፍና የፎክሎር መምህር የሆኑት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በአጋጣሚ የጂጂን ካሴት ማታ ሰምተውት ነበር፡፡ ጠዋት ሊያስተምሩ ወደ ተማሪዎቻቸው ዘንድ መጡ፡፡ እንዲህም አሉ፡- “ዛሬ እንቅልፍ ሳይወስደኝ ነው ያደርኩት” አሉ። ተማሪዎቻቸውም “ምነው? ምን ሆንክ?” አሏቸው፡፡ እርሳቸውም “ፍቅር እየራበኝ” እያለች የምትዘፍን ልጅ እጅግ እየደነቀችኝ ደጋግሜ ስሰማት ነው ያደርኩት” አሉ። ልጅቷን ግን ያወቃት የለም፡፡ እሳቸውም ስሟ እጅጋየሁ ነው፤ከናንተ ውስጥ ሲሉ ጠየቁ፡፡ የሚያውቃት  ግን ጠፋ፡፡ እርሳቸውም ሲናገሩ “በኢትዮጵያ ውስጥ ከ26 ዓመት በኋላ በሙዚቃ ስልቷ ነፍሴን የገዛችው ይህች ድምፃዊት ናት፡፡ በእኔ ግምት የኢትዮጵያን ሙዚቃ ትልቅ ደረጃ ታደርሰዋለች ብዬ የምተማመነው በዚህች ልጅ ነው፡፡Read 1013 times