Print this page
Tuesday, 26 October 2021 00:00

«መዳኛ ስዕል»

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(1 Vote)

   ፩
ዓለም ጆሮዋ ደንቁሯል -  ውስጤ የሚላትን፣ ህልሜ የሚያወጋት አትሰማምና። ይህቺ ምድር ዓይኗ ታውሯል፤  የልቤን ከተማ አታይምና። የእውነት ምስል ጠፍቷት ዱላ ይዛ ትደናበራለች። ልቤ ላይ የምሽጠው መጠበቅ እንዳለ ይሄም በመኖሬ ያገኘሁት ጥቁር ትሩፋት እንደሆነ አታውቅም። ይህቺ ምድር የልቤን ከተማ አታይም።  ስትንቀሳቀስ እያዘገመች፣ ስትሄድ በረጠበ እግሯ ልክ እንደ ድኩማን ሽማግሌ...እዚያ ማዶ እንደተረሳች አሮጊት...ጧሪ ቀባሪ ማጣት ይሉት...ቅዠትን እንደ እውነት፣ እውነትን ደግሞ ልክ እንደ ቅዠት የሚከትቡ የዘመኔ ፀሃፊያን የነብሴን ጓዳ አንዴ ቢቃኙ...የእንባዬን ጅረት ቢዳስሱ የዓለም ሲሶ ህዝብ ላይ የሚያገኙት ታሪክ ልቤ ላይ ተከትቧል። ሁሉም ነገር እያደር ያልቃል። ሙቀቱ የበዛ ፍቅር በረዶ በሆነ ሃዘን ይጠናቀቃል። ያቺ ጠይም ኮረዳ የወዛ ቆዳዋ ተሸብሽቦ ፣ ስትስስቅ ድዷ እየታየ፣ እነዚያ አማላይ ዓይኖቿ ሞጭሙጨው እንዲሁ በነበር አቁፋዳ ውስጥ ገብታ አፈር ትለብሳለች። እዚህ ምድር ላይ የማያልቅ ነገር ቢኖር  ቶሎ ቶሎ ማለቅ ነው። እንዲሁ የሚዘበዝበው ልቤ፣ እንዲሁ ቀን አላሰተኛ ያለኝ አዕምሮዬ ነገዬን አጥብቆ ይናፍቃል። ነገ...አንተ የመለኮት ታናሽ ...አንተ የመናፈቅ ማይ ፣ የተስፋዎች ጌታ አንተ...ነገ...አንተ አንተ አንተ ልቤ ደጋግሞ ያወድስሃል...ልቀኝልህ፤ ቁጭ እልና ቅኔ ተራ ይሆንብኛል። ነገ አንተ የልቤ ከተማ... ልዘምርልህ እከጅልና ቃል ሳላወጣ ሁሉም ነገር ከዝምታ የማይሻሉ ይመስለኛል...ነገ ነገ እያልኩ፣ ነገን እያወደስኩ...ስለ ነገ ልዘምር እያሰብኩ ሶስት ጥንድ አመታት አለፉ። በዚያ በር የወጣው እግሩ በዚያ በር እንደሚመለስ አውቃለሁ። ያ አለንጋ ጣቱ ፊቴን እንደዳሰሰ ...ከንፈሩ ከንፈሬ ላይ እንዳረፈ ደግሞ ሊያየኝ ይመጣል።  ዓይኑ እንደ ጨረቃ የደመቀ ነው። ከዋክብት ለእሱ የሚያሸበሽቡ ይመስላሉ። ህይወትን አንዴ አይቻታለሁ። ያቺ የተያየንበት ቀን መለያያችን ነበር። ህይወት መወለድ ከሆነ እኔ የተወለድኩት ሊለየኝ ሲል ነው።  መወለድ መኖር ከሆነ እኔ የምኖረው ይመጣል በሚሉት ትልቅ ተስፋ ነው። የት ይሆን ያለው ብዬ አላስብም...የትም ቢሆን ግድ የለኝም።  ብቻ ይመጣል...ፍቅሬን ብሎ...ትዝታ አማሎት...ናፍቆቴ አጓግቶት ይመጣል... እስከዛው ትዝታ ልዩ መድሃኒት ነው።  ይመጣል። አሁን በነዚያ ሙቅ ከንፈሩ ከንፈሬን ይስመኛል። እቅፉ ውስጥ ከቶኝ እንደሚወደኝ ሊነግረኝ ይመጣል። አንድ ቀን ይመጣል። ያለ እኔ ዓለሙ ጎዶሎ ነው። ያለ እኔ ህይወቱ መራራ ነው።  ይመጣል....
ስነሳ አንድም ነገር አልያዝኩም። ወደ ውጪ ወጥቼ የስፈሬ አስፋልት ላይ መጓዝ ጀመርኩ። ሁሉም ሰዎች ደስ የሚሉ ይመስላሉ። ሰፈረ ሰላም -  ሰላም የራቃት፣ እግዜር የተረሱ ነፍሶችን አስቀምጦ በቁጣ የመሸጋባት መንደር ትመስላለች። ኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ፊት ለፊት ይታያል። አንዳንድ የሚመላለሱ የሰፈሬ ሰዎች አሉ። ልጆች ጠባቧ ቅያስ ውስጥ ይጫወታሉ። እኔም መንገዴን ይዤ እራመዳለሁ። ከእግዜር ስር ያስደፋኝ ተስፋ ነው። ዓይኔ የሚያየው በተስፋ ብርሃን ነው። ሁሉም ነገር ከንቱ ነው የሚሉ የከንቱ አፈ ቀላጤዎች አሉ። ሁሉም ነገር ከንቱ አይደለም። ተስፋ የሚባል ውብ ብርሃን አለ። ፍቅር ይሉት የእግዜር ስጦታ አለ። አዎ! ፍቅር ይዞኛል። ግን ጉዳዩ ፍቅር ብቻ አይደለም።  ሶስት ጥንድ አመታት ተጉዞ እጁን ያልሰጠ ፍቅር ወደ መጠበቅ ተቀይሯል።
ይናፍቀኝ ነበር። እዚያ ሰው መሃል ተያይዘን ስንጠፋ፣ ልንቦዬን እየነካካ ደግሞ ወደ እዚያ የማላውቀው አለም ሲወስደኝ። ይሄ  ይሄ ይናፍቀኛል። እዚያ ሰፈር የማውቀው ተኮላ ሳላየው  ፊት ለፊቴ ተገትሯል። ሰላም አለኝ። እንደነገሩ ሰላም አልኩት። ቀይ መልኩ ላይ ትልልቅ ዓይኖች አሉ። ጎራዳ አፍንጫ አፅናፍ ዓለሙን ለማነፍነፍ የሚያንስ አይመስልም።
“እንዴት ነሽ?” አለኝ።
“ደህና ነኝ”
“ወዴት እየሄድሽ ነው”
“ዝም ብዬ ነው የወጣሁት ። ወክ ነው መሰለኝ” ሳቅ አልኩ።
“ዛሬ አብሬሽ ብውል ብትፈቅጂልኝ” አለኝ...
ደነገጥኩ...ከእኔ ምን ይፈልጋል? እንደ ባህታዊ የልቤን በር ዘግቼ ከምኖርበት ዓለም ሊያወጣኝ ነው? ወይስ ያ ሶስት ጥንድ አመታት ያቀፍኩትን ተስፋ ሊያጨልም ነው? አልገባኝም! ብቻ እሺ አልኩት።
መጓዝ ጀመርን። መሳለሚያ ስንደርስ ቆም አለና...”እዚህ ትንሽ ነገር እንቀማምስ” አለኝ። “እሺ” አልኩት። ተያይዘን ገባን...የማን እንደሆነ የማላውቀው የባዕድ ሃገር ሙዚቃ ተከፍቷል። ሴቶች እዚህም እዚያም አሉ። አንዳንዶች በዝምታ ይጠጣሉ። ሌሎች ደግሞ ተነስተው ይደንሳሉ። ደስ የማይል ቤት ነው። አንድ ቦታ መርጠን ተቀመጥን።ሴቶቹ በዓይናቸው  እሳት ይገርፉኝ ጀመር። ሴት ልጅ እርስ በእርስ አይዋደዱም የሚል ነገር እሰማለሁ። ብዙ የሴት ጓደኛ ስለሌለኝ አስቤበት አላውቅም ነበር። አሁን ግን እውነት መሰለኝ። ምናልባት ገበያቸውን የነጠኳቸው ስለመስላቸው ነው። ጥብስ አዘዘ። እና ወይን። እስከዛ ደስ የማይል ነገር ማውራት ጀመረ።
“ሁሉም ነገር ደስ አይልም” አለኝ...
“እንጃ እኔ ጋር ሁሉም ነገር ጥሩ ነው። ልቤ ላይ ትልቅ ተስፋ አለ። እሱን ይዤ ነው የምኖረው...”
“ባለቤትሽ እንደወጣ ቀረ ማለት ነው? በየሆስፒታሉ ጠይቀሻል...ፖሊስ ጣቢያስ?”
“የቀረኝ ቦታ የለም፤ ሁሉንም አዳርሻለሁ። ግን እደሚመጣ አውቃለሁ። በህይወትም እንዳለ አውቃለሁ። ነፍሴ ትነግረኛለች። እሱ ይመጣል። አንድ ቀን ይመጣል። ዘለዓለምም ቢሆን እጠብቀዋለሁ። ብቻዬን እጠብቀዋለሁ።” ድንገት ስሜታዊ ሆንኩ።
“አይ ከዚህ በዃላማ የራስሽን ህይወት መቀጠል አለብሽ”
“በፍፁም አይሆንም። መጥቶ ከሚያጣኝ ብጠብቀው ይሻላል። ሰው ፈልጎኝ እንዲያጣኝ አልፈልግም። ሰው ሊየየኝ መጥቶ ጀርባዬን ብሰጠው ቅር ይለኛል። ፍቅርን የፈለገ ሰው ፊት መንሳት ያስከፋኛል። እኔ ከእሱ ውጪ ሌላ ቦታ መሄድ አልችልም። በእሱ የፍቅር እግር ብረት የታሰርኩ ነኝ። የትም አልሄድም....እስር ላይ ነኝ እኮ...የፍቅር እስር የመውደድ እስር...ማንም አይረዳኝም። እንደምታየኝ ጓደኛም ብዙ የለኝም። ውጪ የምትኖር አንድ የልብ ወዳጅ ብቻ ነው ያለችኝ።  እውነተኘ ወዳጅ አንድ ይበቃል። የልብ ወዳጅ አንድ ይበቃል። እንደዚያ ነው። አንተን እራሱ ለምን ተከትዬህ እንደመጣሁ አላውቅም። ምናልባት ሳላውቀው ልቤ ብቸኛ ሆኗል። ምናልባት ሳይገባኝ አጠገቤ ሰው እፈልግ ይሆናል። ምናልባት...”
“እኔ እንኳን ብዙ ጊዜ ላናግርሽ እፈልግና ዝምታሽ እያስፈራኝ ተመልሻለሁ። ልቀርብሽ እሞክርና አንዳንድ ሁኔታሽ ያስፈራኛል” በዚህ መሃል ጥብሱ መጣ....ወይኑ ተቀዳ...እየበላን መጎንጨት ጀመርን።
“ብዪ እስኪ...”
“እሺ”
“አታስዋሺኝ እና ጓደኛሽ ልሆን እፈልጋለሁ። የቅርብሽ ሰው እንድታደርጊኝ እፈልጋለሁ።”
ዝም አልኩ
አጎረሰኝ...
“ምነው ዝም አልሽ...”
“እየበሉ ማውራት ጥሩ አይደለም ብዬ ነው”
“ይህቺማ ማምለጫ ናት”
“አይ እንደው ግርም ይለኛል። ዘመኑ ፈጣን ነው በእርግጥ። ሁሉም ነገር እንደዚህ ጥብስ አሁን በስሎ ካልደረሰ ይላል። ሁሉም ነገር ሂደት አለው። ጓደኝነትም ሂደት አለው። ፍቅርም እንደዛው። አሁን የምትለኝ ነገር አስቸጋሪ ነው ታውቃለህ? በሂደት የሚታይ ነገር ነው። የቅርብ ወዳጅ እንዲሁ ከመንገድ የሚገኝ ቢሆን ሁሉም ዛሬ ባለቅርብ ወዳጅ ነው። (ጎረስኩ) እናልህ ሂደቱን እንጠብቀው እስኪ። እኔም ተስፋዬን ልይ...”
“ያንቺ ተስፋ ካልታየ የእኛ ወዳጅነት ሊቀር ነው?”
“እንደዚያ እንኳን አይሆንም። ማን ነህ አንተ ስለ እኔ ተስፋ መቅረት የምትናገረው?"
ዝም አለኝ። ምግቡ ተበልቶ አልቆ ወይኑን መጠጣት ጀመርን። ሞቅ እያለኝ መጣ።
“እና እየተዝናናሽ ነው እንዴ” አለኝ...
“ውስጤ ሁሌ እንደተዝናና ነው። መዝናናት ማለት እንዴት ያለ ነው? መዝናናት የውስጥ ሰላም ይመስለኛል። ሰላም ባይኖረኝም ለሰላም እየቀረብኩ ነው። ያ ደግሞ አንዱ የመዝናናት ክፍል ነው።”
“ሃሃሃ ነገር ታወሳስቢያለሽ ልበል”
“እንደፈለክ በለው ፣ ብቻ እውነቱን ነው የምናገረው።”
ሞቅ እንዳለኝ ተነሳሁ። እሱም አብሮኝ ተነሳ። ስወጣ የውጪው ቀዝቃዛ አየር ተቀበለኝ። ሰማይ ላይ ጨረቃ ደምቃለች። ተያይዘን ወደ እዚያች እግዜር የመሸገባት ሰፈረ ሰላም አዘገምን። ነገሮች የተቀያየሩብኝ መሰለኝ። ይሄ ሰው የጫረው እሳት አሁን ድረስ እየተቀጣጠለ ነው። ተስፋዬን ፣ ህልሜን ተጠራጥሮታል። እኔ ግን በዛ አላምንም። እና ተስፋዬ፣ የሚመጣውን ብርሃን አያለሁ። ተስፋ የሌለው ሰው ሞቶ እንደተቀበረ በድን ነው። ነገን ለማየት የማይናፍቅ ማን ነው? የባሌን ዳና እየፈለኩ፣ የዓለም በብርሃን ላይ  (ብርሃን አንዳንዴም ይጨልማል) እንዲሁ እብሰለሰላለሁ። የመለያየት ግድ አይደለም። ጉዳዩ ፍቅር ብቻ አይደለም።  ጉዳዩ መጠበቅ ነው። የሄደ እስኪመለስ...ልቤ ጨረቃ አናት ላይ የተንጠለጠለች ትመስላለች። አዎ! ዓለም ጅሮዋ ደንቁሯል።  ማን ነው የሚረዳኝ? ማን ነው ህልሜ የሚታየው...ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው ያለ ማን ነው? ማንም ይሁን ብቻ አንድ ድብቅ ነገር የተገለጠለት ሰው ነው። ለሁሉም ጊዜ አለው። የሚሄድም የሚመጣበት ጊዜ አለው። የተኖረ የሚረሳበት፣ ተስፋ የሚጨልምበት፣ ዓለም የምትነቃበት፣ የደነቆረ ጆሯዋ የሚሰማበት፣ ዓይኗ በክርስቶስ ተዓምር የሚያይበት ጊዜ አለ። አንድ ቀን፣ ያቺ የደስታ ቀን ስትመጣ፣ ያቺ የፌሽታ ጊዜ ስትደርስ ሁሉም ነገር ይሆናል። ሁሉም ነገር ይስተካከላል። በዚህ ሃሳብ ተወጥሬ ቤቴ እንደደረስኩ ልብ አላልኩም ነበር። ቻው ተባብለን ወደ ቤት ገባሁ። ቤቴ ባለ ሁለት ክፍል ናት። በሩ እኔ እንደተቀበለኝ  ነገ እሱን  ይዞ ይመለሳል። በወጣበት በር ይገባል። ሁሉም ነገር ይቀየራል። የመጠበቅ እንባዬም ይታበሳል። ስድስት ዓመት እንደ ቀልድ ሄደ። እነዚያ አስለቺ ክረምቶች ፀደይን እየጎተቱ መጡ። ዘመን ተቀየረ። ሁሉም ነገር ልክ አይደለም። የሚሄደው ጊዜ ተመልሶ ይመጣል። እና እንዲያ ነው።
ሞቅ ብሎኝ ስለነበር አልጋዬ ላይ በጀርባዬ ተንጋለልኩ። ስድስት ዐመት ቆይቶም አልጋው እሱን እሱን ይሸታል። ከዚህ ጊዜ በዃላም ነገሮች አልተቀየሩም። እኔም ቆሜ እየጠበኩት ነው። አንድ ለሊት በህልሜ ከእሱ ጋር አደርኩ። አቀፈኝ። ሳመኝ ደጋግሞ። እናም ማልቀስ ጀመርኩ። ተመልስህ መጣህ አይደል ብዬ አነባሁ። ይሄ ነገር ከመኖር በላይ ነው። ከፍቅር ይልቃል። ከእውነት ጋር አይወዳደርም።  ሰማዩ እና መሬቱ ትዝታ ነው። ነበር ነው ምጥ አለሙ። የተረገዘው ሽል ትላንትን የሚያስብ የነገ ታሳሪ ነው። የዛሬ አንገት ደፊ፣ የነገ ደስተኛ ሽል።
ድንገት ውጪ ያለችው ጓደኛዬ ከሃያ አመት በዃላ ሃገር ቤት እንደምትመጣ ስልክ ደውላ ነገረችኝ። ደስ አለኝ። ምናልባት እሷ ትረ’ዳኝ ይሆናል። ምናልባት እሷም ተስፋዬን ትጠራጠረው ይሆናል። የኔን የፍቅር አጋር መጥፋቱን እንጂ መልኩን ስለማታውቀው ቅር አለኝ። የሚወዱት ወዳጅ የሚያፈቅሩትን ቢያይ እንዴት ደስ ይላል። ባስተዋውቃቸው እወድ ነበር። በፎቶም አታውቀውም። ብርሃኑ ቢጨልምም እንደሚነጋ ታምን ይሆናል። ከዚህ ሁሉ የገረመኝ እጮኛ  እንዳላት መናገሯ ነው። በእውነቱ የሚያስደስት ነገር ነው። እዚህ ሃገር ቤት እንደሰራች አውቃለሁ። እና ለጋብቻው እንደሆነ የምትመጣው ነገረችኝ። ጥሩ ባል እንዳገኘች ነገረችኝ። ደስ አለኝ። ጓደኛው ሲደሰት የማይደሰተው ሳጥናኤል ብቻ ነው። አዳም የሄዋንን ደስታ ሊሞላ ሞት ይዞብን መጣ። አዎ! ወዳጅነት እዚህ ጋር የመድረስ ግድ ነው። ወዳጅነት ያለምንም ጥቅም የስሜት ትስስር... ነው።  

መተኛት የመሰለ ቅዱስ ሞት አይቼ አላውቅም። ጊዚያዊ ሞት፣ ጊዚያዊ መዳን ነው። ህመማቸው የሚጠዘጥዝ ፣ የማይሽሩ የሚመስሉ ቁስሎች በጊዚያዊ ሞት ይረታሉ። እንቅልፍ ውስጥ ስንሆን ለጊዜውም ቢሆን ዓለምን እንረሳለን። ህመም ችላ እንላለን። ደስታም ሳይቀር  የምንምነት በርኖስ ለብሶ ያንቀላፋል። ሃዘን ለሰዓታትም ቢሆን ይሞታል። ተስፋም የለም። ብርሃን በድቅድቅ ጨለማ ይለወጣል። ዓይናችንን እንከድናለን። የት እንደወደቅን እንኳን አናውቅም። በፊት የእንቅልፍ ትውስታ አለኝ። እናቴ ሞታ እየተለቀስ (ያኔ ለብዙ ነገር እንባ አይወጣኝም ነበር) እኔ አብሪያቸው ቁጭ ባልኩበት እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ። ሰዎች ተቀየሙኝ። በእናቴ ሞት ላይ ሆኜ ለእንቅልፍ መረታቴ አስገረማቸው። እኔ ግን ከማንም በላይ የምወደው እናቴን ነበር።
አንዳንዴ እናቴ  በህልሜ ትጠራኛለች። ምን እንደምትፈልግ አላውቅም። እነዚያ ከንፈሮቿን ጉንጬ ላይ ስታሳርፍ የሚሰማኝ ስሜት አንዳች ልዩ ነገር ነው። ስራ ባደነደኗት እጆቿ ፊቴ ይዛ ታለቅስ ነበር። በጠባሽው ጡቴ ከልጆች ጋር አትጣዪ ትለኛለች። እኔ ግን የእናት ፍቅር ባለማወቄ፣ ወይ ቂል ...ወይም  ልጅ  አሊያም ሁሉቱንም እንደመሆኔ መልሼ እዛው ነኝ። በጭቃ ላይ እየተራመድኩ፣ ጭቃ እያቦካሁ ግንፍል ሰው ሆኜ ነበር። በዚህም ውስጥ እናቴን እንዳስመረርኳት አላውቅም ነበር።  እናትነት ከባድ ነገር ነው። በጭንቅ ፣ በስቃይ የወለዱት እየሳሙ አሜን የሚሉ፣ በባላቸው እየተገፉ ልጃቸውን ከጥቃት የሚከላከሉ፣ ነፍሳቸውን ለልጃቸው እንደ ጭዳ የሚሰዉ እነሱ እናቶች ናችው። እናት ማለት ድርብ ቅድስና፣ ድርብ አማልክትነት ነው። እናት ማለት ታሞ የመዳን፣ አልቅሶ የመሳቅ፣ ሞቶ ወደ ህይወት የመመለስ ፀጋ ነው። እናትነት የፅናት እና የትግል  ፍሬ ነው። እናትነት ሳቅ ነው። ከዘለዓለም ደጃፍ ፍቅርን የመዛቅ የሁልጊዜ ፌሽታ ነው። ምናልባት እናቴን ካየዃት ዘመን ስለራቀ ፍቅሬም ተረስቶኝ ይሆናል። ግን በዓለም ላይ ከስህተት የፀዳ ነገር ቢኖር እናትነት ነው እላለሁ። ሁሉም ነገር በእሷ ዓለም ውብ ነው። ሁሉም ነገር ሃሴት ነው። እንዲህም ነበር ይባላል። እንዲህም ተደረገ ይባላል። እውነት መልክ ቢኖረው እናቴን  ይመስል ነበር። ፍቅር  አካል ቢኖረው እናቴን ይመስል ነበር። እሷ እንዲያም እንዲያ ናት። ድምቀቷን ለእኔ ብላ ያጣች፣ ቁንጅናዋን ለእኔ ብላ የተወች የዓለም ባይተዋር ነበረች።
አንድ ቀን እንደልማዴ ተጣልቼ ስመጣ አገኘችኝ። ከንፈሬ ደምቷል። ታድያ ልትቀጣኝ ዱላ ይዛ መጥታ “ተይ ስልሽ ለምን አትሰሚኝም” ብላ እየሳመችኝ አለቀሰች። እናትነትን ሳስብ እነዚህ ሁላ ነገሮች ይመጡብኛል። ብቻዋን ስላሳደገችኝ ይሁን ወይ በሌላ ምክንያት አንዳች ምትሃት ነበር ከእሷ ጋር ያስተሳሰረኛል። እሷን ሳስብ ያ የጠፋው እንባዬ ጉንጬ ላይ መፍሰስ ይጀምራል። አሁንም ጉዳዩ ፍቅር አይደለም። ለእኔ ብላ የከፈለችው፣ ለእኔ ብላ የቻለችው እሱ ነው እንባ ሆኖ ጉንጬ ላይ የሚወርደው። እናት ለልጇ ብላ ዓለምን በቃኝ ያለች የፍቅር ባህታዊ ነች። ፍቅር በእሷ አንደበት ሲነገር እንዴት ይጥማል? እሷ ብቻዋን ሆና ዓለም ላይ ብዙ ናት። እሷ የልጇ ሰማይ ላይ የምታበራ ፀሃይ ናት። ሞታ እንኳን ብርሃኗን አይቀንስም። አስክሬኗ ብቻዉን ህይወት ነው። እሷ...አሁን እንኳን ጉንጬ ላይ እንባ እየፈሰሰ ነው። የእሷን ሞት በየትኛ የህይወት ትግል፣ በየትኛው ፍቅር እረሳሁት? እኔ ሞቼ ቢሆን እሷ እንደማትረሳኝ አውቃለሁ። እኔ ግን ተካዃት። በሌላ ፍቅር ቀየርኳት። የተስፋዬን ጮራ በሌላ ተስፋ ሽጥኳት። ካሰብኳት ስንት ዓመት ሆነኝ?
እናም ዓለም በጭንቅ የተሞላ የዋይታዎች ዋሻ ነው። ዋኔ የሚሉ እናቶች በዝተዋል። ደረታቸውን የሚደቁ፣ አመድ ነስንሰው እዝን የሚቀመጡ እናቶች ሞልተዋል። የልጃቸውን ሳቅ ሳያዩ፣ ቡረቃውን ሳይመለከቱ ከህይወት ወደ ሞት የተሻገረ ልጃቸውን የሚያስቡ እልፍ እናቶች አሉ። ድሮ በጭቃ የሚጫወቱ፣ በደግነት የተለከፉ ልጆች አሁን የዘመን ደዌ፣ የዘመን ክፋት ቀፍድዷቸዋል። አሁን አሁን ልጆች አይስቁም። ዘመኑ የመከራ ነው። የዚህ መከራ ተካፋዮች እናቶች ናቸው። ልቤ በዚህም ውስጥ ሆኖ ሊስቅ ይፈልጋል። ቡዙ ነገር ያልረታው ልቤ አሁን ግን እጁን ሊሰጥ ያኮበኮበ፣ ጦርነት ላይ ሆኖ ጥይቱን እንደ ጨረሰ ወታደር  የጨበጣ ውግያ ሊጀምር ይዳዳዋል።
አፄ  ቴዎድሮስ  የህይወትም መምህሬ ነው። በቀቢፅ ተስፋ እጅ ከመውደቅ እራስን ማጥፋት ልዩ ክብር ይመስለኛል። በእርግጥ አንዳንድ የታሪክ ፀሃፊያን ቴዎድሮስ እጁን ያልሰጠው ከዘሮቹ የተላለፈ አንድ ባህል ስለነበር ነው ይላሉ። ይህም ባህል በጠላት እጅ መያዝ ትልቅ እፍረት እንደሆነ አስተምሮታል። ብዙዎች እንደዛ ያደርጉ ነበር። በጠላት እጅ ከመውደቅ እራሳቸውን ይጠፋሉ። እኔም እንደዚህ አስባለሁ። ተስፋ ማጣት ሞቴ ነው። ተስፋ ይሉት ተደጋጋሚ ቃሌ ቢያሰለቻችሁም ቻሉት። እኔ ልብ ውስጥ ያልገባ እንዴት ልቤን ያውቃል?  
ጓደኛዬ ነገ እንደምትገባ ነገረችኝ። ስጦታም እንደያዘችልኝ ተናገረች። ዛሬ መሽቶ እስኪነጋ ጨነቀኝ። ወዳጅን የማይናፍቅ ልብ የተረገመ ይመስለኛል። እና ቀኔ በመቅለብለብ አለቀ። ዓይኗን ማየት አጓጓኝ... ደግሞ የሆነ ነገር ጭንቅ ያዘኝ። እሷ መዓተኛ ልጅ ነች፤ ምን ይዛ እንደምትመጣ አይታወቅም።
ሳያት ተገርሚያለሁ። በጣም ተለውጣለች።  ሰውነቷ መንምኖ በጣሙን ከስታለች። ቅጥነት ውበት ነው እንደሚሉ የፈረንጅ ሃገር ሴቶች መሰለችኝ። አቅፌ ሳምኳት። የሰዓሊ ነፍስ አይታመንም፤  ቅብዝብዝ ነው። እና በራሷ እጅ የሳለችውን ስዕል ሰጠችኝ። ስዕሉ በወረቀት ተሸፍኗል። በፍሬም ውስጥ ገብቷል።  ምን እንደሆነ ስጠይቃት እዚያ ሃገር ሳያቸው ደስ ያሉኝ ፍቅረኞች ስያቸው ነው አለችኝ። ሀበሾች ናችወ ስላት...ሴቷ ፈረንጅ ፣ ወንዱ ደግሞ ሃበሻ እንደሆነ ነገረችኝ።  ፍቅር በዚህም ጊዜ  መጣ...በዚህም ሰዓት ተገኘ። ፍቅረኞችን ማየት ነፍስ እንደሚያድስ ታውቃለች። የሰዓሊ ነፍስ ሁሌም ለፍቅር ቅርብ ነው።  ሰዓሊ የአንድ ዘመን መገለጥ ነው። በብሩሾቹ ሃሳብ የሚዘራ፣  ተዓምርን የሚሰራ የኪነት ጀግና ጥሪ ቢሉኝ ሰዓሊን እጠራለሁ። ስዕል እረቂቅ ነገር ነው። ኪነትን አቅፎ የያዘ እሱ ስዕል ነው። አንዳንዴ የሰዓሊ ነፍስ ቢኖረኝ እላለሁ።
ተሰነባብተን ወደ እቤት ገባሁ። ቤተሰቦቿ ከበዋት ስለነበር ብዙ ጊዜ አላገኘሁም ላወጋት። ስላመጣችልኝ ስዕል ብቻ  ትንሽ ነገር ነገረችኝ። ሌላ ነገር ያወራን አይመስለኝም። የስዕሉን ወረቀት ማንሳት ጀመርኩ።  እንደ ጨረስኩ ግን ዓይኔን ማመን አልቻልኩ። እጁን ትከሻዋ ላይ አድርጓል፣ ወገቡን ይዛለች። እንባዬ መጣ። ደግሞ ልስቅም ፈለኩ። መጮህ አማረኝ። ዝም ማለትም ፈለኩ። የተስፋዬን ብርሃን በስዕል የማየው አልመሰለኝም ነበር። በአንዲት የባዕድ ሃገር ልጅ እንደተለወጥኩ አላወኩም ነበር። ፍቅሬ ብዬ የያዝኩት የስድስት አመት ውጥኔ በስዕል ተገለጠ። አዎ እሱ ነው፤  ምናልባት ጥቂት ወፍሯል።  የቀየረኝ እሱ ነው። መጠበቄ የተቋጨው ዛሬ አይደለም? ታድያ ከዚህ በዃላ ምን እሰራለሁ? ሌላ ፍለጋ እንደሄደ ባውቅ ምን ነበረበት? ቻው ቢለኝ ይጎዳል? ሄድኩ ማለት ማንን ገደለ? እንባዬ እየፈሰሰ ነበር።
የመሰበርም አይነት እንዳለው ገባኝ። መጠበቅም መቋጫ እንዳለው ተረዳሁ። አሁን ነፃ ሴት ነኝ። አሁን ከመጠበቅም፣ ከመጠ’በቅም ድኛለሁ። በጓደኛዬ በኩል የመጣው መድሃኒት መሰለኝ። ደህና መሆኑ   ጥሩ መድሃኒት ነው። እኔን ትቶ ሌላ ጋር መሄዱ ደግሞ ቅስም ሰባሪ... ሁለቱም ተመሳሳይ ናቸው። ሁለቱም መልካም መዳኛዎቼ ናቸው።
 ከእንግዲህ ነገን አልናፍቅም። ከእንግዲህ ነገ ከዛሬ አይለይም። ከእንግዲህ ነገ የሚባል ነገር የለም። ከእንዲህ ሁሉም ነገሮች ዛሬ ናቸው። ከእንግዲህ ፍቅሬን በይመጣል አልናፍቅም። ከእንግዲህ ሰው አላምንም። ከእንግዲህ ህይወት ጣዕም የላትም። ከእንግዲህ የተስፋዬ ሻማ ጠፍቶ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነኝ።  ከእንግዲህ በትላንት እና በዛሬ መሃል ድንበር አስምሪያለሁ። ከእንግዲህ እኔም እኔ አይደለሁም። ከእንግዲህ ህይወቴ ተለውጣለች። ከእንግዲህ ከመጠበቅ ህመም ድንኛለሁ። ከእንግዲህ ሁሉም ነገር የክብ ዓለም ሩጫ ነው። ከእንግዲህ...እኔም የማልክለትን ደብዳቤ መፃፍ ጀመርሁ። ከእንግዲህ....
ስዕሉን  ግርግዳዬ ላይ ሰቀልኩት። እንዴት ውብ ናቸው? እንዴት ያምራሉ?

Read 1048 times