Monday, 01 November 2021 00:00

በ50 አመት እስር የተቀጡት የቀድሞው የላይቤሪያ መሪ በጡረታ ጉዳይ መንግስትን ከሰሱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በሴራሊዮን በፈጸሟቸው የጦር ወንጀሎች በአለማቀፉ ፍርድ ቤት የ50 አመታት እስር ተፈርዶባቸው ከ2012 አንስቶ በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ቻርለስ ቴለር፣ #የጡረታ መብቴን አላከበረልኝም፤ ጥቅማጥቅሜን ከለከለኝ; በሚል በአገሪቱ መንግስት ላይ ክስ መመስረታቸው ተዘግቧል፡፡
ከአስርት አመታት በፊት በሴራሊዮን በተቀሰቀሰውና ብዙዎችን ለሞት በዳረገው የከፋ የእርስ በእርስ ግጭት አሰቃቂ የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል በቀረቡባቸው 11 ክሶች ጥፋተኛ ሆነው የተገኙትና በ2012 ዘ ሄግ በሚገኘው ፍርድ ቤት የ50 አመታት እስር ተፈርዶባቸው በአንድ የእንግሊዝ ወህኒ ቤት ታስረው የሚገኙት ቻርለስ ቴለር፤ #ላለፉት ሃያ አመታት ገደማ ሊከፍለኝ የሚገባውን የጡረታ ገንዘብና ጥቅማ ጥቅም ከልክሎኛል; በሚል የላይቤሪያን መንግስት በኢኮአስ ፍርድ ቤት መክሰሳቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1989 በላይቤሪያ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አብዮት በመምራት አገሪቱን ለ13 አመታት ለዘለቀ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደዳረጉ የሚነገርላቸውና ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶኢን ከስልጣን በማውረድ ከ1997 እስከ 2003 አገሪቱን ያስተዳደሩት ቻርለስ ቴለር፣ ለእስር የተዳረጉት ላይቤሪያ ውስጥ በፈጸሙት ወንጀል ባለመሆኑ መብታቸው መጣስና ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም ማጣት የለባቸውም ሲሉ የአገሪቱ የመብት ተሟጋቾች ድጋፍ እንደሰጧቸውም ተነግሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቻርለስ ቴለር በወቅቱ የላይቤሪያ መንግስት ላይ ያቀረቡትን ክስ ለመስማት የሚሰየምበትን ቀን አለማስታወቁንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


Read 2657 times