Tuesday, 02 November 2021 00:00

ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትርፍና ኪሳራ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሰማሩ የአለማችን ታላላቅ ኩባንያዎች አጠቃላይ ገቢ፣ ትርፍና ኪሳራዎችን የተመለከቱ ዘገባዎች ከያቅጣጫው እየወጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ቴስላ ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ካፈሩት ጥቂት ኩባንያዎች ተርታ መሰለፉ ይጠቀሳል፡፡
የአሜሪካው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ ቴስላ አጠቃላይ የገበያ ዋጋ ባለፈው ሰኞ ከ1 ትሪሊዮን ዶላር ማለፉንና በዚህም ኩባንያው ከ1 ትሪሊዮን በላይ ሃብት ያፈራ አምስተኛው የአለማችን ኩባንያ ለመሆን መብቃቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሃብት በማፍራት በታሪክ መዝገብ ላይ መስፈር የቻሉት አራት ብቸኛ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች አፕል፣ ማይክሮሶፍት፣ አማዞንና አልፋቤት መሆናቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ወደ ሌላ ዜና ስንሻገር ደግሞ፣ ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ አፈትልከው በወጡ የደንበኞቹ ሚስጥራዊ መረጃዎች ሳቢያ ክፉኛ ሲብጠለጠል በሰነበተበት በዚህ ሳምንት፣ እስከ ነሐሴ በነበሩት 3 ወራት 9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማግኘቱ መልካም ዜና በስፋት ተነግሮለታል፡፡ ፌስቡክ በሩብ አመቱ ያገኘው ገቢ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ7.8 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው መነገሩን ነው ዘ ኢንዲፔንደንት የዘገበው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የማይክሮሶፍት ኩባንያ የሩብ አመት ትርፍ ባለፈው አመት ከነበረው በ48 በመቶ በማደግ 20.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ለዚህ ስኬት ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው በክላውድ ቴክኖሎጂ የጀመራቸው አገልግሎቶች ትርፋማነት መሆኑንም ኒውዮርክ ታይምስ ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡ ኩባንያው እስከ መስከረም በነበሩት ሶስት ወራት 45.3 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ገቢው ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በ22 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ሮይተርስ ባለፈው ረቡዕ ያወጣው ሌላ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው ኩባንያ ጎግል ባለፈው ሩብ አመት፣ ክብረ ወሰን ያስመዘገበበትን የ53.1 ቢሊዮን ዶላር የማስታወቂያ ገቢ ማስመዝገቡንና ይህም ገቢ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በ41 በመቶ ያህል ማደጉን ያሳያል፡፡ ጎግል በሶስተኛው ሩብ አመት ያገኘው ትርፍ 18.936 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት ክብረ ወሰን ያስመዘገበባቸውን ከፍተኛ ትርፎች እያገኘ መዝለቁንም አክሎ ገልጧል፡፡ በተመሳሳይ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ሰሞንኛ ወሬ የሆነው ሌላኛው የማህበራዊ ድረገጽ ኩባንያ ትዊተር በአንጻሩ፣ ባለፈው ሩብ አመት የ537 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠመው ተነግሯል፡፡

Read 9916 times