Print this page
Tuesday, 02 November 2021 00:00

የአስፈሪ አደጋዎች ተመሳሳይነት - በ100 ዓመት ልዩነት

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

ካሁን በፊት ያልታየ  አይነት “ሥርዓት”፣ ወይም ታይቶ የማይታወቅ “ሥርዓት አልበኝነት”፣ በመላው ዓለም እየተንሰራፋ የመጣበት ዘመን ላይ ነን። (ፍልስፍና ወይም ርዕዮተ ዓለም፣ ክፉውም ደጉም፣ ትክክለኛውም የተሳሳተውም ሁሉ፣ የላሸቀበት ዘመን ነው - ዛሬ። የሳሙኤል ሃቲንግተን የፖለቲካ ትንታኔ፣ በዚህ እውነታ ላይ የተመሰረተ ነው።
ርዕዮተ ዓለም፣ ጥሩም መጥፎም  ሁሉ ሲሟሽሽ፣ ኋላቀር የፖለቲካ ቅሪቶች፣ እንደ አዲስ፣ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ነፍስ ዘርተው ይነሳሉ፤ በየአይነቱ ይፈለፈላሉ። የሃይማኖት ፖለቲካ፣ የጉልበተኞች የቅርምት ፖለቲካ፣ እንዲሁም የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ በየቦታው እየገነኑ፣ ብዙ አገራት ክፉኛ ይናጋሉ፤ ይተራመሳሉ። ይሄ፣ የሃቲንግተን ትንታኔና ትንበያ ነው - የዛሬ 30 ዓመት ግድም የተተነበየ።
አሳዛኙ ነገር ምንድነው? በሃቲንግተን የተተነበየው ትርምስ፣ ከዓመት ዓመት፣ ብዙ አገራትን በእውን ሲያዳርስ እያየን ነው።
አስፈሪው ነገር ምንድነው? “ኋላቀር የጭፍንነት ፖለቲካ” እና “ዘመናዊ ቴክኖሎጂ” ሲገጣጠሙ፣… መዘዙ የበዛ፣ ጥፋቱ የከፋ ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ አሁን ያለንበት ዘመን፣ በጣም አስፈሪ ዘመን ነው - የዘመናዊ ቴክኖሎጂና የኋላቀር ፖለቲካ ቅይጥ።
በእርግጥ፣”የአስተሳሰብና ኋላ ቀርነት የቴክኖሎጂ ኋላቀርነት” የተዳበሉበት የጥንቱ ጥፋትም፣ ጥሩ አይደለም። በዱላ በድንጋይ፣ አልያም በጦር በጎራዴ መጠፋፋት፣ ምኑ ይወደዳል? መጥፎ ነው። “ኋላቀር አስተሳሰብ” እና “ዘመናዊ ቴክኖሎጂ” ሲቀላቀሉ ግን፣ “አያድርስ” ያስብላል። ቴክኖሎጂ፣ ለክፉም ለደጉም፣ “አምፕሊፋየር” ነው! ማባዣም ማሳለጫም ነው። ከስልጡን አስተሳሰብ ጋር ቴክኖሎጂ ሲጣመር፣ ሰላምን ያሰፋልናል፣ ብልፅግናን ያሳልጥልናል። ሕይወትን ያለመልምልናል።
ከአጥፊ ወይም ከኋላቀር አስተሳሰብ ጋር፣ ቴክኖሎጂ ሲዋሃድ ደግሞ፣ የጥፋት ማባዣ ይሆናል። በጦር በጎራዴ የመጠፋፋት ኋላቀር ታሪክ፣ በአዲስ መልክ ይጦዛል። በክላሽ እሩምታና በታንክ ወደ መጠፋፋት ይሸጋገራል። ከዚህም የከፋ ይሆናል እንጂ።
በሌላ አነጋገር፣ አይዲዮሎጂ (ርዕዮተ ዓለም) የሾቀበት ዘመን፣ በሃቲንግተን አይን ካየነው፣ አደገኛና አስፈሪ ዘመን ነው - 21ኛው ክፍለ ዘመን።
አዎ፤ የዛሬ 90 ዓመት፣ የዛሬ 100 ዓመትም፣ በጣም አስፈሪና አደገኛ ዘመን ነበር። የአደጋው መንስኤ ግን፣ የርዕዮተ ዓለም እጦት አልነበረም። ያኔማ፣ በራሺያ የነገሠው የሶሻሊዝም አስተሳሰብ፣ ወደ መላው ዓለም እየተስፋፋ የነበረበት ዘመን ነው። ኢትዮጵያ የዚህ ጥፋት ሰለባ ሆናለች በደርግ ዘመን፡፡ ከዚያ በፊትም፣የፋሺዝም ተጠቂ ሆና ነበር፡፡ ለምን? የዛሬ 99 ዓመት፣ በጣሊያንም፣ የፋሺዝም ፖለቲካ ሰፍኗል። የሁለቱ ቅይጥ የሆነው “ብሔራዊ ሶሻሊዝም” ተብሎ የተሰየመው ፖለቲካም፣ በሂትለር መሪነት፣ በጀርመን ምድር የገነበበት ዘመን ነው - የዛሬ 90 ዓመት።
እነዚሁ የጥፋት አስተሳሰቦች፣ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ተገጣጥመው፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ እልቂትንና ውድመትን አስከትለዋል። የስንት ሚሊዮኖች ሕይወት ረገፈ? ስንት ሚሊዮኖች በረሃብ ተሰቃዩ? ስንቱ ከተማ ወደመ? ለምን ታይተው የማይታወቁ፣ የቴክኖሎጂ አይነቶች የተስፋፉበት አስደናቂ ዘመን ነበር - ዘመኑ።
በነዳጅ ዘይትና በኤሌክትሪክ ኃይል፣ የሰው ልጅ፣ ተዓምረኛ አቅም ያገኘበት ዘመን ነው። “አሰምብሊ ላይን” በተሰኘው ዘዴ፣ ቀንና ማታ፣ በገፍ ማምረት የሚችሉ ፋብሪካዎች የተፈጠሩበት የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ስልክና ሬድዮ፣ መኪናና አውሮፕላን፣… ምናለፋችሁ! በሰው ልጅ ታሪክ፣ በጭራሽ ያልታዩ የቴክኖሎጂ አይነቶች የተፈጠሩበት ብቻ ሳይሆን፣ በብዛት ወደ ምርት የተሸጋገሩበት ዘመን ነው። በተዓምረኛ ፍጥነት፣ የሰውን ኑሮ የሚቀይር፣ አስገራሚ ዘመን! ያኔ የዛሬ 100 ዓመት፡፡
ታዲያ፣ለበጎ ብቻ አይደለም፡፡ ለጥፋትም ነው። ፋብሪካውና ቴክኖሎጂው፣ ከጥፋት አስተሳሰቦች ጋር ሲቀላቀል፣… ለጥቃት የሚዘምቱ ታንኮችንና አውሮፕላኖችን ይወልዳል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አማካኝነት የደረሰውን አሰቃቂና ዘግናኝ እልቂትን እስከትሏል።
የጥፋት አስተሳሰብ ክፋቱ፣ ቴክኖሎጂን የጥፋት ማባዣና ማሳለጫ እንዲሆንለት ማድረግ ይችላል።
አስገራሚው ነገር፣ የጥፋት አስተሳሰብ ቢዳከም እንኳ፣ ለጊዜው ትንሽ ፋታ ይገኝ እንደሆነ እንጂ፣ እዚያው በዚያው፣ አስተማማኝ መፍትሄ አይሆንም።
 የተሳሰተ አስተሳሰብ፣ በትክክለኛ አስተሳሰብ (መጥፎው ፍልስፍና በጥሩ ፍልስፍና) ከተተካ ነው፤ መፍትሄ የሚገኘው።
ዛሬ ግን፣ ሁሉም የፍልስፍና አይነት ነው የተዳከመው። ፍልስፍና ሲጠፋ፤ ለረዥም ጊዜ ተዳፍነው የቆዩ ጥንታዊና ኋላቀር የጭፍንነት ቅሪቶች ብቅ ብቅ ይላሉ - የብሔር ብሔረሰብ፣ የጉልበትና የሃይማኖት ፖለቲካዎች ይስፋፋሉ። አጥፊ ናቸው። ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ሲቀላቀሉ ደግሞ፣ ጥፋታቸው ይጦዛል።
ይሄ ነው፤ የዛሬ አደጋ፤ የዓለም አገራትን የሚያተራምስ አደጋ፡፡
አዎ፤ የሶሻሊዝም አስተሳሰብ፣ በተግባር ከስሯል - ባይጠፋም ተፍረክርኳል። በቦታው ትክክለኛ አስተሳሰብ አልተተካም፡፡ ከ200 ዓመት በፊት፣ ከ100 ዓመት በፊት፣ እጅግ ሃያል የነበረው የካፒታሊዝም አስተሳሰብም፣ ሙሉ ለሙሉ ባይሞትም፣ ቀስ በቀስ ተመናምኗል። ትክክለኛ የስልጣኔና የብልፅግና ሃሳቦችን ያቀፈ ቢሆንም፣ የካፒታሊዝም ቅኝት፣ እንደቀድሞው አይደለም። ዛሬ፣ ሰፊ ተቀባይነት የለውም።
ሶሻሊዝምም፣ ካፒታሊዝምም፣ መጥፎውም ጥሩዉም ሁሉ ተፍረክርኮ ሲያበቃ፣ የአስተሳሰብ የፍልስፍና ኦና ተፈጥሯል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ያንሰራሩ ኋላቀር ሃሳቦች፣ ለአለማችን ጤና የሚሰጡ አይደሉም። ጥፋትን ያስከትላሉና። ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር መገጠጠማቸው ደግሞ፣ አጥፊነታቸውንም አብዝቶታል፤ አባዝቶታል።

Read 9664 times