Sunday, 31 October 2021 19:34

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የጥፋቱ ሀይል፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ
ተቦርን በየነ

  ይህ የሆነው ከ33 ዓመታት በፊት ነው!
“እንዴት አላማጣን የመሰለ ቦታ ይለቀቃል? እንዴት እንደ ግራካሶ የመሳሰሉ ቦታዎች ይተዋሉ? በሚል ብዙ ተከራከርኩ። እንግዲህ እምቢ ካልክ ያንተ ፋንታ ነው አሉኝ። ከዛ የሶቪየት አማካሪዎችን ሎቢ አደረጉብኝ። በዚህ አይነት ትግራይ እንዲለቀቅ ሆነ።”
(የሌ/ኮ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ትዝታዎች፤ ገፅ 272-273)
ኢህአዴግ ከላይ ከተጠቀሰው የትግራይ መለቀቅ በኋላ በሶስት አቅጣጫ ትኩረት በማድረግ፣ ኢህአዴግ ፋና በሚል ስያሜ ወደ መሀል ሀገር የሚያደርገውን ዘመቻ ጀመረ።
አቅጣጫ 1-
ከስታይሽ ተነስቶ በዋጃና ቆቦ መሀል ላሊበላን ወደ ቀኝ ትቶ፣ የወረታ-ወልዲያን መንገድ ቆርጦ ኮን በመግባት፣ ጊጣ የሚባል በረሀ አቋርጦ ወገልጤና ይገባል። ከዚያም ወደ መቅደላ፣ አጅባር፣ተንታ፣ኩታበር ድረስ በመዝለቅ ደሴን ይከባል። የዚሁ አካል የሆነው ሌላው ሀይል ለጋምቦ፣ አቅስታ፣ ገነቴ፣ መካነሰላም፣ ሳይንት፣ ጓሜዳ፣ ጫቀታ፣ ሶማ እያለ ጎጃም ድረስ ይዘልቃል። ሌላኛውም ሀይል ወደ ወረኢሉ በመገስገስ ካቤ፣ ጀማ፣ መራኛ፣ መሀልሜዳ፣ አለም ከተማ እያለ ወደ ደብረ ብርሀን ይገባል።
አቅጣጫ 2-
ወልዲያ፣ጋሸና፣ገረገራ፣ደብረዘቢጥ፣ጋይንት፣ጉና፣ክምርድንጋይ፣ጋሳኝ፣እያለ ወደ መሀል ይዘልቃል።
አቅጣጫ 3-
ቆቦ፣ መርሳ፣ ኡርጌሳ፣ ሀይቅ፣ እያለ ደሴ ድረስ ይዘልቃል።
ይህ ወታደራዊ እቅድና ስልት ኢህአዴግ ከ33 አመታት በፊት ለስልጣንና ለድል በቃሁበት ያለው ነው። ይህንንም አስመልክቶ ሜ/ጄ ታደሰ ወረደ በአንድ ወቅት የሰጡት ምስክርነት በቪዲዮ ውስጥ ተካትቷል። በተመሳሳይ አሁን ጦርነቱ እየተካሄደባቸው ያሉ የደቡብ ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ያላቸውን ወታደራዊ ጠቀሜታ በተመለከተ ሌ/ጄ አበባው ታደሰ የሰጡት ቃለምልልስም አብሮ ተካትቷል።
የጥፋቱ ሀይል ዛሬም እንደ ትናንቱ ተመሳሳይ በሆነ ስልት ወረራውን እያከናወነ መሆኑን ልብ ይሏል!

==========================================


ከድህረ-ጋዳፊ ሊቢያ ምን እንማር?
ጌታሁን ሔራሞ


  ሊቢያን ለ42 ዓመታት ያህል በውዴታም ይሁን በግዴታ ሲመራት የነበረው ኮሎኔል መሐመድ ጋዳፊ እ.ኤ.አ. በ2011 ዓ.ም. በሀገሪቱ ውስጥ (ቤንጋዚ) የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመፅን ተከትሎ በተከሰተው በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ከሥልጣኑ ተወግዶ እስከ ወዲያኛው ማሸለቡ ይታወሳል። ከጋዳፊ መወገድ በኋላ ላለፉት አስርት ዓመታት ሊቢያ ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
የመሐመድ ጋዳፊን መወገድ ተከትሎ ሊቢያ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ አለመረጋጋትና ምስቅልቅል ውስጥ ነች። በእርግጥ ለምስቅልቅሉ ብዙዎቻችን በዋናነት የምንጠቅሰው የምዕራባውያኑን ጣልቃ ገብነት ነው። ይህ እውነት ቢሆንም ጣልቃ ገብነቱ የጋዳፊን ቀደምት የአመራር ስህተቶቹን በተወሰነ ደረጃ ሸፍኖለታል ማለት ይቻላል። ኮሌኔል መሐመድ ጋዳፊ የሊቢያ መሪ ብቻ ሳይሆን ተቋሟም ነበር ብንል ማጋነን አይሆንብንም። ሀገር በጠንካራ ተቋማት ላይ ሳይሆን በግለሰብ ሰብዕና ላይ ስትቀነበብ መጨረሻዋ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማስተዋል ሊቢያ ጥሩ ምሣሌ ነች። ከአንድ አቶም ውስጥ “nucleus” ሲወገድ ኤሌክትሮኖቹ እንደ ወትሮው ሥርዓታቸውን ጠብቀው በምህዋራቸው መዞር ስለሚያቅታቸው ውጥንቅጥ ይፈጠራል። ጋዳፊ ሲወገድ ሊቢያ የሆነችው እንደዚያ ነው። የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ለሀገር ሕልውና ቀጣይነት ዋስትና እንደሆነ የሚነገረውም ከዚሁ የተነሳ ነው።
በድህረ-ጋዳፊ በሊቢያ ውስጥ የተከሰቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተዋንያን ብዛት ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው።
እስቲ ለየብቻ በየምድባቸው እንቃኛቸው፦
1. የሀገር ውስጥ ተዋንያን (Domestic Actors)
የሊቢያ ዓመታዊ የነዳጅ ገቢዋ ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ይጠጋል፤ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢዋ ደግሞ ከ150-200 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል። የተፈጥሮ ሀብት ባለጠጋነት በረከትም ቢሆን በአግባቡ ካልተያዘ የራሱ የሆነ መርገምትም አለው። በተለይም የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ ካልሆነ ለማያባራ ግጭትና ቀውስ መንስኤ ይሆናል። ለምሣሌ በአሁኑ ወቅት ናይጄሪያ ውስጥ በሀብት ክፍፍል ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች ከብሔር ግጭቶች ቢበልጡ እንጂ አያንሱም። ከጋዳፊ በኋላም ሊቢያን የገጠማት ፈተና ይኸው ነበር። ቀደም ሲል ጋዳፊ እንዳሻው ሲጠቀምበትና ሲያከፋፍለው የነበረው የነዳጅ ሀብት፣ የእሱን ሞት ተከትሎ በምን አግባብ መሰራጨት እንደነበረበት መወሰን በቀላሉ ለስምምነት የሚያበቃ አልነበረም። በዚህና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች የሀገር ውስጥ ተዋንያን ስብጥር የሚከተለውን ይመስላል፦
1.1. የፖለቲካ ቡድኖች፦ በዚህ ምድብ ሥር ወደ 5 ንዑሳን ቡድኖች አሉ። እነርሱም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የጋዳፊ ዘመን የፖለቲካ ልሂቃን፣ በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ልሂቃን፣ በክልል ደረጃ ያሉ የጎሳ አለቆች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና በትምህርታቸው ላቅ ባለ ደረጃ ያሉ ምሁራንና ከጣሊያን አቻዎቻቸው ጋር ቀረቤታ ያላቸው ምሁር ሊቢያዊያን ሴቶች ናቸው።
1.2. የፀጥታ ኃይሎች ቡድን፦ በዚህኛው ምድብ ደግሞ ወደ 6 ንዑሳን ቡድኖች ይገኛሉ። ዝርዝራቸውን እንደሚከተለው በእንግሊዝኛ ላስቀምጥ፦
Remnants of the Libyan Army under Gaddafi.
Heads of Militias
Local Salafist Islamist Extermists and Terrorists
International Terrorist Groups with Libyan components, including al-qaeda in the islamic Maghreb and later, ISIS.
Petroleum Guards with Tribal ties
Criminal Ganfs, including kidnappers and smugglers.
2. ጣልቃ ገብ የውጭ ኃይሎች፦
እነዚህን ጣልቃ ገብ የውጭ ኃይሎችን በሶስት ጎራ መክፈል ይቻላል፤እነርሱም፦
ከጋዳፊ መወገድ በፊት ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱ በኋላ ከጋዳፊ መወገድ በኋላ በስመ-ፀጥታና ኢኮኖሚ ዕርዳታ ጣልቃ ገብነቱን ቀጥለውት ነበር።
ግብፅ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ጆርዳንና የአረብ ኢሚሬትስ በአንድ በኩል በመሆን እገዛቸውን ቶቡሪክ ከተማን ማዕከል ላደረጉ ኃይሎች አደረጉ። ቆይቶ ራሺያ ይህን ምድብ ተቀላቅላለች።
እገዛቸውን ሚስራታና ትሪፖሊ ላሉ የሊቢያ ኃይሎች ካደረጉ ሀገራት ውስጥ ደግሞ ኳታር ፣ ቱርክና ሱዳን ይገኙበታል።
እንግዲህ ሊቢያ ከፈራረሰች በኋላ በሀገር ውስጥ 11 ቡድኖች፣ ከሀገር ውጭ ያሉ ደግሞ ወደ 10 ሀገራት እያመሷት ይገኛሉ። በሊቢያ ዘመቻ ወቅት ጦርነቱን በቀጥታ የመራው 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ከሥልጣኑ ከወረደ በኋላ፣ በውሳኔው እንደተፀፀተ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። እንደዚያም ሆኖ ከባራክ ኦባማ ውሳኔ በስተጀርባ የነበሩ ሶስቱ ሴቶች (ሂላሪ ክሊንተን፣ ሱዛን ራይስና ሳማንታ ፓዋር) ለሊቢያ ቀውስ ተጠያቂ ስለመሆናቸው ብዙዎች የሚስማሙበት ሃቅ ነው።
እንግዲህ እኛም ሕወሓት በየጊዜው “ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች” የሚለውን ነጠላ ዜማውን በሚያሰማን ወቅት ሊቢያ ትዝ ትለን ዘንድ ግድ ነው። ሟቹ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን፣ ጦርነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተካሄደ ቀጠናዊና ብዙዎችን የሚያሳትፍ ስለመሆኑ በግልፅ ተናግሮ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጦርነት በአንዳንዶች “The New War” ወይም “The Postmodern War” እየተባለ ይጠራል።፤ ሌሎች ደግሞ The Hybrid War ይሉታል። ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ እንደ ሊቢያ ሆና ማየት የሕወሓት የጦር አበጋዞች የሰርክ ሕልማቸውና ትልማቸው ነው...አይሳካላቸውም እንጂ!
ምንጭ ፦( Origins of the Libyan Conflict and Options for its Resolution
By Jonathn M. Winer, 2019 (Free pdf download available online)

 ==========================================

ትኩረታችን  ሁሉ በህወሓት ላይ መሆን አለበት

ሃይለሚካኤል አደራ

የሽብር ቡድኑ አንደበት የሆነው ጌታቸው ረዳ፤ በአብን አመራሮች ላይ የሰነዘረው ዘለፋ ህወሓት ማእከላዊውን መንግስት ለማዳከም ትሄድበት የነበረውን ርቀት ጠቋሚ ነው። በምእራብ ኦሮሚያ፣ በመተከል እንዲሁም  በአዲስ አበባ በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ መንግስትን የፖለቲካ ውጣሬ ውስጥ ለመክተት ያልተሞከረ ነገር አልነበረም - እንዳሰቡት ብዙም ባይሳካም። ከነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጥ በተለይ አብን (የአማራ ፖለቲካ አክቲቪስቶች) በማዕከላዊው መንግስት ላይ እምነት እንዲያጡና እንዲያምፁ ያልተረጨ ፕሮፓንዳ አልነበረም። ግና የተሸረበውን ሴራ ሁሉ አንድም በመንግስት የውስጥ አላማ አንድነት፤ አንድም ለሀገር ተቆርቋሪ የተፎካካሪ ፖለቲካ ኃይሎች ብስለት እየከሸፈ፣ ህወሓቶችን ጭራ ሲያስበቅላቸው እየታዘብን ነው።
አሁንም ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ተቆርቋሪ የፖለቲካ ኃይሎች ትኩረት ሁሉ ህወሓት ላይ መሆን አለበት። ለብዙ ችግሮቻችን ስርአታዊና መዋቅራዊ ምንጭ የሆነው ህወሓት ከስሩ ካልተነቀለ፣ በየቦታው የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት አዳጋች ነው።


=================================

እውነተኛ ባለጠግነት፣ እውነተኛ ስልጣን፣ ራስን መሆን ነው
ኦሾ/Osho

አባቱ ጫማ ሰፊ የሆነው አብረሃም ሊንከን፣ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት በሆነ ጊዜ ሀብታም ከሆኑት ሰዎች ፣የላቀ ደረጃ ካላቸው ሰዎች፣ከተከበረና ዝነኛ ሆኖ ከኖረ ቤተሰብ በመምጣታቸው የበላይነት ስሜት ያላቸውን ሰዎች በሙሉ፣ የጫማ ሰሪ ልጅ ከአናት ሆኖ ሲያዛቸው፣የሃፍረት ስሜት ተሰምቷቸው ነበር። ሊንከን ፕሬዚዳንት በመሆኑ ሁሉም መሸማቀቅ፣ ቁጣ፣ብስጭት አጠላባቸው እንጂ ደስተኛ የነበረ ሰውም የለም።
ሊንከን የመጀመሪያውን ንግግሩን ለህግ መወሰኛ በሚያቀርብበት ጊዜ አንዱ ዘላፊ የሆነ ሰው ተነስቶ፤ “ሚ/ር ሊንከን፤ ንግግርዎን ከመጀመርዎ በፊት የጫማ ሰሪ ልጅ መሆንዎን ላስታውስዎት እወዳለሁ” አለው። ያን ጊዜ ሴኔቱ በሙሉ ሳቀ። ሊንከንን ሊያሸማቅቁት ፈልገው ነበረ። ሆኖም ሊያሸንፉት አይችሉም። ነገር ግን እንዲያፍር ሊያደርጉት ይችላሉ። ይሁን እንጂ እንደ ሊንከን ያለውን የህይውት ስንክሳር አይቶ ወደ ስልጣን የመጣን ሰው እንዳያፍር ለማድረግም እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሊንከን ሰውየውን “አሁን በህይወት የሌለውንና ጫማ ሰሪ የነበረውን አባቴን ስላስታወስከኝ እጅግ ከፍ ያለ ደስታ ይሰማኛል። የሰጠኸኝን ምክር ምን ጊዜም አልረሳውም። ጫማ ሰሪው አባቴ ባይሆን ኖሮ እንደዚህ ታላቅ ፕሬዚዳንት መሆን እንደማልችል ጠንቅቄ አውቀዋለሁ” አለ። ፍጹም ፀጥ ረጭ ያለ ሁኔታ ተፈጠረ። ሊንከን ንግግሩን ቀጠለ......
“እስከማውቀው ድረስ ለአንተም ቤተሰቦች ቢሆን አባቴ ጫማቸውን ይሰራላቸው ነበር። ትልቅ ጫማ ሰሪ ባልሆንም ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ከአባቴ ዘንድ ጥበብን ስለተማርኩ፣ ጫማዎችህ ሲያልቁም ሆነ ችግር ሲያጋጥምህ ላስተካክልልህ እችላለሁ። እንደዚሁም አባቴ ጫማ ይሰራ ስለነበረ የሚሰፋና የሚስተካከል ካላችሁም እዚህ ሴኔት ውስጥ ላላችሁት ለማንኛችሁም ለመስራት ዝግጁ ነኝ። ሆኖም ግን አንድ ነገር እርግጠኛ ሁኑ፤ እንደ አባቴ ግን ፍጹም አይደለሁም። የእርሱ ስራ ፍፁም ወርቅ ነው” ሲል ተናገረና፣ አባቱን እያሰበ አይኖቹ በእንባ ታጠቡ።
እናም ምን ለማለት ነው፤ አንተ ከተራ ቤተሰብ የወጣህ ፕሬዚዳንትም ሁን አንደኛ የተባልክ ጫማ ሰሪ፣ ልዩነት አያመጣም። ቁም ነገሩ ያለው የምትሰራውን ስራ በፍላጎት መስራትህና ያለህን ጉልበት ሁሉ እዛ ላይ ማዋልህ ነው። እራስህን እንጂ ማንንም ሰው ለመሆን መፈለግ የለብህም። በዚህም ጊዜ ተፈጥሮ በድራማ ውስጥ የሰጠችህን ክፍል በደንብ ለመጫወት ከተፈጥሮ ጋር ትስማማለህ፤ ያን ጊዜ ንጉስም ሆነ ፕሬዚዳንት ለመሆን ራስህን አትቀይረውም።
እናም በመጨረሻም እንዲህ እላለሁ፤ ‘’እውነተኛ ባለጠግነት፤ እውነተኛ ስልጣን፣ ራስን መሆን ነው’’።


Read 1798 times