Sunday, 31 October 2021 19:44

በ7.7 ቢ.ብር የተቋቋመው አቤት ታክሲ በቅርቡ መኪኖቹን ወደ ስራ ያስገባል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በቀጣዮቹ  አምስት ዓመታት 25 ሺህ መኪኖችን ስራ ላይ ያሰማራል
ከሶስት ዓመታት በፊት በ7.7 ቢ ብር በጀት የተቋቋመውና የ2021 የአውሮፓ  ስሪት የሆኑ ባለ አምስት ባለ 7 እና ባለ 26 መቀመጫ የትራንስፖርት መኪኖችን በሀገራችን በመገጣጠም ስራ ላይ የተሰማራው አቤት ታክሲ፣ የመጀመሪያዎቹን መኪኖች በቅርቡ ስራ ላይ እንደሚያሰማራ አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ባለፉት ሶስት ዓመታት መገጣጠሚያ ፋብሪካ  በመገንባት፣ አንዳንድ ህጋዊ ሂደቶችን የመጨረስና አስፈላጊ የህግ  ሂደቶችን በመከወን ስራ ላይ መቆየቱን የገለፁት ሀላፊዎቹ በተለይ አንዱና ዋናው የመኪኖቹ መገጣጠሚያ ኮምቦልቻ ከተማ እንደመሆኑና አሁን ያለው የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ችግር እስካልፈጠረ ድረስ የመጀመሪያዎቹ መኪኖች ተገጣጥመው ስራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ጀርመን ጣሊያንና ራሽያ ሰራሽ የቮልስ ዋገንና የላዳ ኩባንያ የ2021  ባለ 5፣ባለ 7 እና ባለ 26 መቀመጫ ሚዲባስና ሜትር ታክሲዎች ሲሆኑ በኤሌክትሪክና በቤንዚን የሚሰሩ እንዲሁም ከአየር ንብረት ጋርም የተዋደዱ ናቸው ተብሏል፡፡
አቤት ታክሲ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ዘመናዊ የሜትር ታክሲዎችንና መለስተኛ አውቶቡሶችን በማሰማራት ችግሩን ለማቃለል የተፈጠረ ድርጅት መሆኑን የአቤት ታክሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ደሜ ገልጸው ድርጅቱ በቀጣዩ አምስት ዓመታት ውስጥ 60 ሺህ ሰዎችን የመቅጠር፣ ብዙ ጋራዦችን የመስራት፣ በርካታ የጥሪ ማዕከሎችን የመክፈትና 15 ሺህ ባለ 5 እና ባለ 7 እንዲሁም መቀመጫ እንዲሁም 10 ሺህ ባለ 26 መቀመጫ ሚዲ ባሶችን ስራ ላይ የማሰማራት እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በርካታ ድርጅቶች መኪና እናስመጣለን እያሉ ገንዘብ በመሰብሰብ ቃላቸውን ሳይጠብቁ ስለ መቅረታቸውና ድርጅታቸው ከዚህ አንጻር እምነት ይጣልበት እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ “እኛ ወደ ስራው ስንገባ ትልቅ ተግዳሮት የሆነብን ይሔው የእምነት ጉዳይ” ነው ያሉት ዶ/ር ሙሉ ለወረፋ መጠበቂ ብቻ 30 ሺህ፣50 ሺህ እና 60 ሺህ ብር ከማስከፈል ውጪ ሌላ ገንዘብ እንደማይቀበሉና የመኪናውን 25 ወይም 30 በመቶ የሚያስከፍሉት መኪናውን ሲያስረክቡ ብቻ እንደሆነ ገልጸው በእምነት በኩል ችግር እደማይገጥማቸውና እስካሁንም ከ200 በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
የውጪ ምንዛሬ እጥረትን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄም ስራው የተጀመረው ከውጪ አገራት በተገኘ ብድርና ብድሩም በውጪ ምንዛሬ ተገኘ በመሆኑ በምንዛሬ እጥረት የሚስተጓጎልበት ምክንያት የለም ብለዋል፡፡
አቤት ታክሲ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአሁኑ ወቅት ጋራዞችን በግዢና በኪራይ  ቦታዎች እያስተከለ እንደሆነ የገለጹት ሀላፊዎቹ፣ታክሲዎች ስራ ሲጀምሩ የእጅ በእጅ ክፍያና በኤሌክትሮኒክስ ክፍያም አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ የክፍያ ታሪፍን በተመለከተ አሁን ገበያ ላይ ካለው ታሪፍ የሚቀንስ ይሆናል ተብሏል። አቤት ታክሲ በዋናነት የትራንስፖርት ችግሩን ለመቅረፍ በአዲስ አበባና በአጎራባች አካባቢዎች የሚሰራ ይሁን እንጂ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር በኩል በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው በጎ ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ሀላፊዎቹ ገልጸዋል። አቤት ታክሲ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር በቀን 50 መኪኖችን የመገጣጠም አቅም  የሚኖረው ሲሆን፣የራሽያው ስሪት ለዳ በባህር ዳር የጀርመኑ ቮልስዋገን በኮምቦልቻ እንደሚገጣጠሙ ታውቋል፡፡

Read 1789 times