Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 15 September 2012 11:50

“አጥንቱ ካርድ ተሞልቶበታል…”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

በዓል በሰላም አለፈ? ዓመቱን ሙሉ ሰላም ያድርገውማ፡፡ የምንበሳጭበትን፣ የምናዝንበትን፣ ተስፋ የምንቆርጥበትን ቀንሶልን ‘ዋሻው ጫፍ ላይ ያለውን ብርሀን እንድናይ’ ያድርገንማ!የበዓል ሰሞን አይደል…ይቺን ስሙኝማ፡፡ የሮሚዮና ጁሊየት ትያትር መድረክ ላይ እየታየ አዳራሹ ጢም ብሏል፡

ጁሊየት፡- “ሳመኝ ሮሚዮ፡፡ ሳመኝና እቤቴ ልሂድ፡፡”

ሮሚዮ፡- “ልስምሽ አልችልም፡፡”

ጁሊየት፡- “እባክህ ሳመኝና እቤቴ ልሂድ የእኔ ሮሚዮ!”

ሮሚዮ፡- “አይሆንም፡፡ ልስምሽ አልችልም፡፡”

ጁሊየት፡- “እባክህ፣ እባክህ ሮሚዮ፣ ሳመኝና እቤቴ ልሂድ!”

ይሄኔ ተመልካች ውስጥ የነበረ ሰው ስልችት ብሎ ምን አለ መሰላችሁ፡፡ “አቦ፣ ሳማትና ሁላችንም ቤታችን እንሂድበት፡፡”

“አቦ፣ ሳማትና ሁላችንም ቤታችን እንሂድበት፣” የሚያሰኙ ፊልሞች በርከት እያሉ ስለሆነ…አለ አይደል…‘ሆምወርክ’ ትንሽ ቢሠራ አሪፍ ነው፡፡ ይሄ ሲኒማ ቤቶችን በሰልፍ የሚያጥለቀልቀው ተመልካች የሄደ እንደሆነ መመለሱ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡

ስሙኝማ…ዛሬ ከትወና ሳንወጣ አልተላቀቅንም…ተዋናዩ ከመድረክ ሲወርድ አዳራሹ በጭብጨበ ተናጋ፡፡ ከትርኢቱ በኋላ ለጓደኛው ምን ይለዋል… “ከመድረክ ስወርድ ሰዉ አዳራሹን በጭብጨባ ሲያናጋው ሰማህ አይደል!” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም “ለምን እንዳጨበጨቡ ግን ታውቃለህ?” ሲል ይጠይቀዋል እሱም “ስለሚያደንቁኝ ነዋ!” ይላል፡፡ ይሄኔ ጓደኝየው ምን አለው መሰላችሁ… “ያጨበጨቡት ስላደነቁህ ሳይሆን ከዛ ትዕይንት በኋላ ተመልሰሀ ወደ መድረክ እንደማትወጣ ስላወቁ ነው፡፡”

እናማ ሲጨበጨብ ሁልጊዜ አድናቆት እንዳልሆነ ማወቅ ደግ ነው፡፡ በየፊልም ቤቱ እዚህ ግባ ለማይባል ፊልም የጭብጨባ መሪ ሆነው የሚሠሩ እንዳሉ የዚች ጽሁፍ ጸሀፊ ሁለት ሦስቴ ያየው ነው፡፡ ይሄኔ ነው እንግዲህ የ‘አጥንትና የካርድ’ ነገር የምትመጣው፡፡ አዎ፣ በአጥንቱ ካርድ የተሞላላቸው ‘ቺር ሊደርስ’… አለ አይደል… ‘ሮትን ቶሜቶ’ ሊወረወርበት ለሚገባው ፊልም ሲያጨበጭቡ…የሆነ ነገር ተበላሽቷል፡፡

የአጥንቷንና የካርዱን ጨዋታ ስሙኝማ!

(‘እውነተኛ ታሪክ’ ብላችሁ ያዙልኝ፡፡) የቤት ሠራተኛዋ አሪፍ ሥጋ ወጥ እየሠራች እያለ ምድረ አጥንት ሆዬ እየተገላበጠ ያየ ዘቡሌ ምን ይላል መሰላችሁ… “እስቲ አንድ አጥንት ስጪኝ…” እሷዬዋም ‘ኖ ፍሪ ላንች’ የሚለው ነገር የገባት ኖራ “አጥንት ብሰጥህ ምን ታደርግልኛለህ?” ስትለው  ዘቡሌም “የሞባይል ካርድ እሞላልሻለሁ፣” ይላታል፡፡

ይሄኔ እሷዬዋ “በል አንዱን አውጥተህ ብላ…” ትልና ወጣ ትላለች፡፡ ዘቡሌም የአጥንት ዘር አንድ ሳይቀረው በሙሉ ቅርጭጭ ያደርግላችኋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ቃሉን አጥፎ ካርዱን ሳይሞላላት ይቀርና ትበሽቃለች፡፡ ማታ ባለቤቶቹ እራት ሲበሉ ምንም አጥንት የለም፡፡ እሷዬዋ ትጠራና “አጥንቱ ሁሉ የት ገባ?” ብለው ሲጠይቋት ምን አለች አሉ መሰላቸሁ…“ካርድ ተሞልቶበታል፡፡”

እናላችሁ… ብዙ ነገር ለእኛ ስንለው ለሌላ የሚሄደው ‘አጥንቱ ካርድ እየተሞላበት’ ነው፡፡

የሆነ ሥራ ፈላጊ የሚንከራተት ምስኪን ድንገት ዕድሉን ያገኝና ለሆነ መሥሪያ ቤት የክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ይመዘገባል…ከፈተና በኋላ “ለኢንተርቪው አልፈሀል…” ይባላል፡፡ እሱዬው ኢንተርቪው ላይ… ምን አለፋችሁ…ላሪ ኪንግ ምናምን ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡

ከዛ ቢጠብቅ ምንም የለም፣ ቢጠብቅ ምንም የለም! ይሄኔ…“የዛ የክፍት ሥራ ቦታ ነገር እንዴት ሆነ?”  ሲል ይጠይቃል፡፡ ምን ብለው ይመልሱለታል መሰላችሁ…“ውይ እሱማ ሰው ከተቀጠረበት ወር ሆነው እኮ!” ልክ ነዋ…‘አጥንቱ ካርድ ተሞልቶበታላ!’

እናላችሁ… ብዙ ቦታ ‘አጥንቱ ካርድ እየተሞላበት…’ አለ አይደል… ‘ፌይር’ አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ካርዱ የሚሞላበት አይነት መአት ነው…ግን ነገርየው፣ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡

የሆነ ባለጉዳይ የበዛበት አገልግሎት ቦታ ተሰልፋችሁ ትጠብቃላችሁ፡፡ ምናልባትም ሦስት አራት ሰዓት ቆማችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ (በነገራችን ላይ ብዙ ቦታ ሦስትም አራት ሰዓትም ጠብቆ አገልግሎት ማግኘት ‘ዕድለኝነት’ እየሆነ ነው፡፡) የሆነ ሰው ጣደፍ ብሎ ይመጣና ሰልፉን አልፎ ይሄዳል፡ በሩ ላይ ከጠባቂው ጋር ሰላምታ ተለዋውጠው ይገባል፡፡ …“እኛ ሰልፍ እኮ ነው የያዝነው” ሲል ጠባቂው ምን ይላል መሰላችሁ…“እሳቸው ቀጠሮ አላቸው” ይላችኋል፡ ሁላችሁም እኮ በቀጠሮ ነው የተሰለፋችሁት! እናማ…‘አጥንቱ ካርድ ሲሞላበት’ አገልግሎት ለማግኘት ሰልፍ እንኳን አያስፈልግም፡፡

ይቺን ነገር ስሙኝማ… እሷዬዋ ምርጥ የዘፋኝ ድምፅ አለኝ የምትል ነች፡፡ እና እቤት ውስጥ ሁል ጊዜ ስትዘፍን ባሏ ራሱን በመስኮት ብቅ ያደርጋል፡፡ ታዲያ አንድ ቀን እኔ በዘፈንኩ ቁጥር ራስህን በመስኮት የምታወጣው ለምንድነው ብላ ትጠይቀዋለች፡ እሱዬው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “ጎረቤቶቻችን የምዘፍነው እኔ አለመሆኔን እንዲያውቁ…” ብሏት እርፍ፡፡

አልበም ስታወጣ የአጥንትና የካርዱን ጨዋታ በደንብ ከተጫወተች “በናፍቆት ስትጠበቅ የቆየችው፣ የሪሀናን አርማ ያነሳችው…” ምናምን የሚል የእንትን ሲኒማ ቤትን ሸራ የመሰለ ፖስተር ይሠራላታል፡፡ አገሪቷ ይቺዋ የእኛዋ ናታ!

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ተዋናዩ በትያትሩ የመጀመሪያ ትዕይንት ላይ በሽጉጥ ተመትቶ የሚሞትበት ክፍል አለ፡፡ እና ተዋናዩ ስለ ራሱ ያለው አመለካከት ከፍተኛ ነው፡፡ ጓደኛውን ምን ይለዋል…“በመጀመሪያው ትዕይንት ተመትቼ ብሞትም አተዋወኔ ግሩም አልነበር!” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝየው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “መጋረጃው ከመከፈቱ በፊት ብትሞት ይሻልህ ነበር፡፡” የምር…እኛ እንዲህ አስበነው አናውቅም ነበር! ቂ…ቂ…ቂ…

እኔ የምለው…አዲስ ዓመት የመሳሰሉ በዓላት እንግዲህ ስጦታ ምናምን ነገር መቀባበያም ይሆኑ የለ…እሱዬው ለእንትናዬው ስጦታ መስጠት ይፈልጋል፡፡ እናላችሁ… ጓደኛውን ምን አይነት ስጦታ ቢሰጣት ጥሩ እንደሆነ ምክር ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝዬውም “ለመሆኑ አንተን ትወድሀለች?” ሲል ቢጠይቀው “እንዴታ!” ብሎ ይመልሳል፡፡ ይሄኔ ጓደኝየውም “በቃ ማንኛውንም ነገር ገዝተህ ስጣት…” ይለዋል፡፡ እሱዬው ግራ ይገባውና “እንዴት?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ መካሪ ጓደኛ ሆዬ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“አንተን አይነት ሰው ከወደደች ምንም ነገር ትወዳለች ማለት ነው…” ብሎት አረፈ እላችኋለሁ፡፡

ስሙኝማ…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ምነው “መጠጥ አቆማለሁ…” “ሲጋራ አቆማለሁ…” ምናምን የሚል ሰው ቁጥሩ ቀነሰሳ! ለጭለጣው እንደሁ ድፍን አገር እያንደቀደቀው ይመስላል፡፡ ቢራ ፋብሪካው ሁሉ ወደ እኛ እየፈለሰ ነው ያለው እኮ! ወይስ…ዘንድሮ “የመጠጥ ፍጆታዬን በሳምንት አምስት ሊትር የነበረውን ወደ ስምንት ሊትር አሳድጋለሁ…” እየተባለ ነው!

የምር ግን…የመጠጥና የሲጋራ ማቆምና መቀነስ ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገር ‘እንዲህ አደርጋለሁ፣ እንደዛ እሠራለሁ’ እያሉ ማቀድ የቀነሰ ነው የሚመስለው፡፡ ብቻ ደግመን ደጋግመን የምንለው…አንድዬ አዲሱን ዓመት ካለፉት ዓመታት በተለይም ካለቀው ዓመት የተሻለ  ያድርግልንማ!

በ‘አጥንት ካርድ የማስሞላት ባህልን’…አለ አይደል… “ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ጥርግ አድርጎ…” ይውስድልንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 3474 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 12:12

Latest from