Sunday, 31 October 2021 19:47

ወጋገን ባንክ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት እያከበረ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ወጋገን ባንክ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል በተለያዩ ክዋኔዎች ማክበር ጀመረ። ከትናንት በስቲያ ስታዲየም ፊት ለፊት በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ ማክበር የጀመረው የብር ኢዩቤልዩ በዓል በበጎ አድራጎት ሥራ ያለፈ ሲሆን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ለሚገኘውና የልብ ህሙማን ህፃናትን በነፃ ለሚያክመው የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የ1 ሚ. ብር ድጋፍ አድርጓል።
በልገሳ ስነ-ስርዓቱ ላይ የማዕከሉ የበጎ ፈቃድ አምባሳደሯ አርቲስ መሰረት መብራቴና የማዕከሉ አመራሮች ተገኝተው ድጋፉን ተቀብለዋል።
በክብረ በዓል  ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብድሽ ሁሴን ባንኩ ባለፉት 25 ዓመታት የባንክ አገልሎት ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካቶችን የባንክ አልግሎት ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ፣ ለሀገሪቱ የባንክ ዘርፍ እድገት የጎላ አስተዋፅኦ ስለማበርከቱም ተናግረዋል።
ባንኩ እስካሁን ለ5 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት፣ የልማት ጥሪዎችን በመቀበልና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ሀገራዊ ሃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን የተናገሩት አቶ አብድሽ በጠንካራ አመራሮቹና በሚከተለው የዘመነ አሰራ እዚህ ደረጃ መድረሱንም ጨምረው ገልፀዋል።
ወጋገን ባንክ ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም በ16 ባለሃቶች በተፈረመ 60 ሚ. ብር መነሻ ካፒታልና በተከፈለ 30 ሚሊዮን ብር ተመስርቶ በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ ባለ አክስዮኖች ያሉት ሲሆን እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2021 ዓ.ም የተከፈለ ካፒታሉ 3.2 ቢሊዮን መድረሱና አጠቃላይ ካፒታሉም  ወደ 5.5 ቢ. ማደጉም ተገልጿል። በአሁኑ ሰዓት የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ 398 ቅርንጫፎች መክፈቱንና በቅርቡም በዘርፉ ተወዳደሪና ስኬታማ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችለውን  የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ ነድፎ ስራ ላይ ያዋለ ሲሆን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ አዲስ መዋቅር አዘጋጅቶ ለደንበኞቹ አርኪና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። ባንኩ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት ለቀጣዮቹ  8 ወራት በተለያዩ ተግባራት ማክበሩን እንደሚቀጥል የባንኩ አመራሮች ገልጸዋል።

Read 1941 times