Print this page
Monday, 01 November 2021 05:26

ፍካሬ ቴዎድሮስ

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

ለረጅም አመታት ነዋሪነቱን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ዕውቁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ አጋጠመው በተባለው ችግር ምክንያት ባለፉት ሳምንታት የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። አንዳንድ ማህበራዊ ትስስር መድረኮች ድምፃዊውንና የቅርብ ወዳጆቹን ስሜት በሚጎዳ መልኩ መረጃዎች አሰራጭተዋል በሚል የቤተሰብ አባላት ትክክለኛውን ሁኔታ ለማስረዳት ሞክረዋል።
የሙዚቃ ባለሙያው ችግር ቢደርስበትም በማንኛውም ሰው ላይ ሊያጋጥም ከሚችል የሕይወት ውጣ ውረድ የተለየ አይደለም። “የሕይወት መስመር መዛነፍ” ስለመሆኑ እርግጠኛ ባንሆንም ቴዎድሮስ ከነዳገትና ቁልቁለቱ እጣው በሆነው የራሱ የሕይወት መንገድ እየተጓዘ ነው። አሁን እዚህ ላይ ደርሷል። ጉዞው ይቀጥላል። መልካሙን ሁሉ!
ግን ጭለማውን ከማማረር ኩራዝ መለኮስ!
ቴዎድሮስ ታደሰ የመጀመሪያ የሙዚቃ ስብስቦቹን ለአድማጮች ካቀረበበት ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ በርካታ ሥራዎችን አቅርቧል። በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስድስት ሥራዎችን እንዳሳተመ ብንሰማም ብዙ አድማጮች ዘንድ ያልደረሰ ወይም በደንብ ያልተደመጠው የመጨረሻ ሥራው “ትላንትና ዛሬ”ን ከጨመርን ምናልባት ቁጥሩ ሰባት ሳይደርስ አይቀርም። “ሳዱላዬ ነይ”፥  “አጉል ተቆራኝቶኝ” ፥ “ደግሞ ባይኔ”፥ “በመላ በሰበብ”፥ “በጉዴ እወጣና” የመሳሰሉት ሙዚቃዎች ከተወዳጅነታቸው በተጨማሪ ወደበዃላ የመጡ ድምፃውያን መንገዳቸውን እስኪያገኙ መተዋወቂያ ሆነዋቸዋል። እሱም የነሙሉቀን መለሰና መልካሙ ተበጀን እዘፍን ነበር እንዳለው።
በእውነቱ ግን የቴዎድሮስን እምቅ ችሎታ ያሳየው በአንጋፋው የሙዚቃ ሰው ሙላቱ አስታጥቄ አቀናባሪነት የተሰራው “ዘለሰኛ’ የብቃት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን ደረጃ ማውጫም ነው። በሀገራችን በተለይም በኦርቶዶክስ ክርስትና ቅዳሴ ውስጥ የሚታወቀውን ጥንታዊውን ያሬዳዊ ዜማ ከሃይማኖታዊ አውዱ አውጥቶ ከከበሮ እስከ ትንፋሽ መሳሪያዎች፤ ከጊታር እስከ ዛይለፎን በሀገርኛ ጃዝ የተሰራ የጊዜን ፈተና ያለፈ ዜማ ነው።
የቴዎድሮስ ድምፅ ከሰምና ወርቅ ግጥሞቹ ጋር ለመንፈሳዊነት ያቀርበናል። እንደዛ አይነት ቅንብር የቡድን ሥራ ቢሆንም ከበቁ ሙዚቀኞች ጋር መጫወት ግን የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም።
ከዛ በዃላ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የቆየ አይመስልም። ባህር ማዶ ተሻግሮ ዓመታት ካስቆጠረ በዃላ 1989 ዓ.ም ላይ ከአድማስ ባንድ ጋር “ዝምታ”ን ይዞ ብቅ አለ። የስብስቡ መጠሪያ  “ዝምታ” ይሁን እንጂ ቴዎድሮስ እዛ ላይ ያላለው ነገር የለም። ሙዚቃው ላይ የተሳተፉት ዛሬም ድረስ አገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ባለሙያዎች እንዲሁም የውጭ ሃገር ሰዎች ናቸው።  ይህም “ዘለሰኛ” ላይ እንዳነሳነው መናበብ የመቻልና በሱ ችሎታ የመተማመን ጉዳይ ነው።
ዝምታ አስር ዘፈኖችን ያካተተ ስብስብ ነው። አንዳንዱ ዘፈን ሁለትና ሶስት  ዜማ በውስጡ ይዟል። “እኔም ላይመቸኝ” በወቅቱ ከተማው ውስጥ ተወዳጅ የነበረውን አሜሪካዊ የጃዝ ሙዚቀኛ ኬኒ ጂን ያስታውሳል። ሙዚቃው ሲጀምር ያለው የትንፋሽ መሣሪያ ድምፅ ለረጅም ጊዜ አዕምሮ ውስጥ የመቅረት ሃይል አለው። ምናልባትም ሳናውቀው ኬኒ ጂ ሳይመርዘን አልቀረም። ሌሎቹም ዘፈኖች በሚገርም የሙዚቃ አጨዋወት አንዳንዴም “የዘመን ኩርንችት”ን አይነት ያልተለመደ አነጋገር ከያዙት ግጥሞች ጋር የተለያየ ስሜት ውስጥ ያስገባሉ።
አማዞን ድረገፅ ላይ ስለዝምታ ስብስብ አስተያየቱን የሰጠ ለቋንቋው ባዳ የሆነ የሙዚቃ አዋቂ ስብስቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አጨዋወቶችን ያሳያል ይላል። “ባይኔ መጣሽ ወይ” የሚለው ምርጫው ሲሆን ስለ ሌሎቹ ሲፅፍ ከዛ ጋር እያነፃፀረ ነው።
ከዓመታት በፊት ያወጣው “ትላንትና ዛሬ” ብዙ አልተባለለትም። በቅጡ ተዋውቋል ለማለትም ያስቸግራል። ቴዎድሮስ በጣም በራሱ ከመተማመኑ የተነሳ ይሁን ሌሎች የማናውቃቸው ችግሮች ብዙም ግልፅ አይደለም። ስለ ድፍረቱ የተለያየ ሙዚቃ መሞከር የሚፈልግ ስለመሆኑ ግን የሕንድ ሙዚቃ መሣሪያዎች የተካተቱበትን ዘፈኖቹን በማዳመጥ ማየት ይቻላል።
ለጊዜው ግን መድረኩን ዃላ መቀመጫ ላይ አድርገን የጤንነቱን ጉዳይ ጋቢና እናስገባለን። ትከሻውን ቸብ። አይዞኝ!Read 1016 times