Monday, 01 November 2021 05:27

ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ካህን ወንጉሥ

Written by  ዶ/ር መንግሥቱ ጎበዜ
Rate this item
(0 votes)

በየዓመቱ ጥቅምት 19 ቀን የታላቁ ኢትዮጵያዊ ካህን ወንጉሥ የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ የዕረፍት መታሰቢያው በስሙ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ይከበራል። ይህ በዘመነ ላስታ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያና በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መካከል ለዓርባ ዓመታት የኢትዮጵያ መሪ የነበረው ዝነኛው ንጉሥ በብዙ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶቹ የምናስታውሰው ታላቅ የሀገር ባለውለታ ነው። ይህ ጽሑፍም ይህን ምክንያት በማድረግ ለአንባብያን ይደርስ ዘንድ የተቀናበረ ነው። ከሦስት ክፍለ ዘመናት በላይ ኢትዮጵያን የመራት የድኅረ አክሱሙ የላስታ መንግሥት በካህናት ነገሥታት መኖርና  በድንቅና ዘመን ተሻጋሪ የውቅር ዓለት አብያተ ክርስቲያናቱ በሚገባ ይታወቃል።  በዘመነ ላስታ አሥራ አንድ ነገሥታት እንደነበሩ ሲታመን ከነዚህ መካከል አራቱ ማዕረገ ክህነት ያላቸውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ የተሰጣቸው ናቸው። እነዚህም ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ሀርቤ፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኩቶለአብ ይባላሉ። በእነዚህ ነገሥታት ካህናት ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት፣ ፍፁም ሰላምና የምጣኔ ሀብት እድገት መኖሩን ከታሪካዊ ማስረጃዎች እንገነዘባለን። በዚህ ዘመን መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ከመቸውም ጊዜ በላይ ተጣምረው ለመንፈሳዊ ልዕልናና ለሀገራዊ ብልጽግና ልዩ አስተዋጽኦ ነበራቸው።
ይምርሐነ ክርስቶስ ክህነትን ከንግሥና ጋር አስተባብሮ በመያዝ በታሪክ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ መሆኑ ይታመናል። የይምርሐነ ክርስቶስ አባቱ ዛንስዩም ሲባል  እናቱ ግን ስሟ በጽሑፍ መዛግብት አልተገለጸም። ይሁንና ለቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ የሕይወት ጉዞ መሠረት ከአባቱ ይልቅ እናቱ እንደነበረች በመጽሓፈ ገድሉ በስፋት ተገልጿል። ይምርሐነ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የነበረው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ አጤ ጠንጠውድም ይባል የነበረ ሲሆን መናገሻ ከተማውም ከቅዱስ ላሊበላ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ (6 ኪሎ ሜትር ገደማ) በስተሰሜን አቅጣጫ የምትገኘው አደፋ እንደነበረች ይገመታል። ንጉሥ ጠንጠውደም አማካሪዎቹን ሰምቶ ይምርሐነ ክርስቶስ ሲያድግ ከልጆቹ ይልቅ እርሱ ሥልጣኔን ይወርስብኛል በማለት እስከ ሞት ድረስ ያሳድደው እንደንበርና በእናቱ ምክንያት ከሞት ተርፎ መጨረሻም ለስደት እንደተዳረገ ተመዝግቧል። እናቱም ልጇ ይምርሐነ ክርስቶስ እንዳይሞትባት በመሥጋት ራቅ ወዳለ ቦታ ይሄድ ዘንድ ክርስቶስ ይምራሕ ብላ መርቃ እንደሰደደችውና ስሙም በዚህ ምክንያት ይምርሐነ ክርስቶስ እንደተባለ ይነገራል።
ይምርሐነ ክርስቶስ የስደት ኑሮውን ከአገር ወደ አገር፣ ከገዳም ወደ ገዳም በመዘዋወር የቤተክርስቲያን ትምህርት እየተማረና መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠ አሳልፏል። በዚህ ወቅትም የግብጽ ገዳማትንና ቅድስት ምድር ኢየሩሳሌምን መጎብኘቱ ይታመናል። በስደት እያለ  ከአሮን ወገን የሆነችውን ቅድስት ሕዝባን አግብቶ ለታላቁ የቅስና ማዕረግ በቅቷል። በመንፈሳዊ ሕይወቱ ምስጉን የነበረው ይምርሐነ ክርስቶስ በክህነት ሥልጣኑ ብዙ ገቢረ ተአምራትን እንዳደረገ በገድሉ ላይ ተገልጿል። ንጉሥ ጠንጠውደም መሞቱ ከተሰማ በኋላ ይምርሐነ ክርስቶስ ወደ አገሩ ተመልሶ አደፋ በተባለችው ቦታ በታላቅ ሕዝባዊ ክብር ታጅቦ የመንግሥት ዙፋኑን ተረክቧል።  ይምርሐነ ክርስቶስ የንግሥና ስሙ ዳዊት ይባል ነበር። በዘመኑ በግብጽ ይኖር የነበረው አርመናዊ የገዳማትና የአብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ጸሓፊ የኢትዮጵያ ካህናት ነገሥታት በዳዊት ዙፋን ተቀምጠው ፍርድ ይሰጣሉ ብሎ የዘገበው በዚሁ በይምርሐነ ክርስቶስ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
ይምርሐነ ክርስቶስ ከነገሠ በኋላ አንዳንድ ሥር ነቀል አዋጆችንና ለውጦችን ማድረጉ ተገልጿል። ጥንቆላ፣ ሟርት፣ መተት፣ አስማት የመሳሰሉ ኋላ ቀር ተግባራት እንዲቀሩ አድርጓል።  ከሱ በፊት ተስፋፍቶ የነበረውን ብዙ ሚስቶች የማግባትን ልማድ አስቀርቶ አንድ ወንድ በአንድ ሴት አንዲት ሴት ደግሞ በአንድ ወንድ እንዲጸኑ ከበድ ያለ መልእክት አስተላልፏል። ድሃና ሀብታም በሆኑ ሁለት ወንድማማቾች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍል እንዲኖር የተወደደ ዳኝነት አድርጓል። በዚሁም መሠረት ከአንድ እናትና አባት የተወለዱ ሁለት ወይም ሶስት ወንድማማቾች ከአንድ ማሕጸን ተገኝተዋልና ባለጸጋው ለችግረኛው ያካፍል ዘንድ ሥርዓት ሠርቷል።
ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተመንግሥቱን ከአደፋ ዛዚያ ወደምትባል ቦታ በማዛወር ለሃያ ሁለት ዐመታት ድንኳን ዘርግቶ ቤተመንግሥታዊና ቤተክህነታዊ አገልግሎቱን ይፈጽም ነበር። የቦታው ስያሜ ‘ዛዚያ’ የተሰኘው በግእዝ ‘ዝዬ ሰመርኩ’ ትርጉሙም ‘ይህችን ቦታ ወድጃታለሁ’ ብሎ ንጉሡ በመናገሩ ከዚያ የተወሰደ ነው። ዛዚያ ከቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ የዋሻ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን በስተምዕራብ አቅጣጫ በስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሁለት ሸለቆዎች መካከል የምትገኝና በልማልሜ የተዋበች ደልዳላ ቦታ ነች።  ከሃያ ሁለት ዐመታት የዛዚያ ቆይታ በኋላ ይምርሐነ ክርስቶስ ወግረ ስኂን ተብሎ በሚጠራው ጥቅጥቅ ባለ ደን በተሸፈነ እና ታቹ ባሕር በሆነ ትልቅ ዋሻ ውስጥ የሚደነቅ ቤተ ክርስቲያንና ቤተ መንግሥት አንጿል። ንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን በወርቅና በብር ለማስጌጥ መሰል የከበሩ ማዕድናትን ፍለጋ ሠራዊቱን አስከትሎ ወደ ዐረብ ሀገር ተጉዟል። ይሁንና በዚያው በዐረብ ምድር እያለ በድንገት ታመመና በዘጠና ሰባት ዓመቱ ጥቅምት 19 ቀን በማረፉ ምክንያት ሠራዊቱ የቅዱሱን አስከሬን ተሸክመው ወደ ሀገሩና ወደ ቦታው ተመልሰዋል። ሥርዐተ ቀብሩም በሊቀ ጳጳሱ አትናቴዎስ መሪነት ከቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ በስተደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ በዋሻው ውስጥ ተፈጽሟል። በዚህም ምክንያት የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ዐመታዊ በዐል በዕረፍት ቀኑ ጥቅምት 19 በርካታ ምእመናን በሚገኙበት በድምቀት ይከበራል።
ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ ገናና በዐለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑት የሀገራችን መሪዎች ተርታ የሚመደብ ነው። የመካከለኛው ዘመን ቁልፍ ዓለም አቀፍ ክስተት የነበረው የመስቀል ጦርነት የታወጀው በቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ዘመነ መንግሥት ነው።  የምዕራብ አውሮፖ ክርስቲያኖች በመስቀል ጦርነት ወቅት ያልጠበቁት ሽንፈት በመካከለኛው ምሥራቅ የእስልምና ኀይሎች ሲገጥማቸው አጋዥ ይሆናል ብለው በምናባቸው የሳሉት ነው ተብሎ የሚታወቀው ቄሱ ንጉሥ ዮሐንስ (Prester John) መገኛ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች።  ቄሱ ንጉሥ ዮሐንስ ርእሰ ጉዳይ መሆን የጀመረው በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው ሩብ ዓመታት ገደማ በዘመነ  ንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ እንደመሆኑ  ምንአልባትም ከጊዜው መገጣጠም፣ ከታሪኩ መመሳሰል፣ ንጉሡ እውነተኛ ካህን መሆኑና መሰል ነገሮችን ካስተዋልን በምዕራባዊያን ክርስቲያኖች ለአጋርነት ይፈለግ የነበረው ቄሱ ንጉሥ ዮሐንስ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ሊሆን የመቻሉ ግምት ከፍ ያለ ነው።
ንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ የግብጽ ሙስሊም ሡልጣኖች በአገራቸው የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ስቃይ ሲያበዙባቸውና ሲያሳድዷቸው ክርስቲያኖቹን ለመታደግ ሡልጣኖቹን ለማስደንገጥ የዐባይን ወንዝ ለመገደብ ሙከራ ያደርግ እንደነበር ተመዝግቧል። በአንድ ወቅት የዐባይ ወንዝ በግብጽ እያነሰ በመሄዱና ግብጻውያንም በውሃ ጥም እንዳያልቁ በመፈራቱ የግብጽ መሪዎች ተደናግጠው የዐባይ ውሃ እንዲለቀቅላቸው ለሽምግልና አማላጅ አድርገው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን አቡነ ሚካኤልን ወደ ኢትዮጵያ እንደላኳቸው ይነገራል። ሊቀ ጳጳሱም በዐባይ ውሃ መቆም ጉዳቱ ለእኛ ለክርስቲያን ወንድሞቻችሁ ጭምር እንጅ ለእስላሞቹ ብቻ አይደለምና ተልኬ የመጣሁትም ለዚሁ ነው በማለት ውሃው እንዲለቅላቸው ለንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ተማሕጽኖ አቅርበዋል። የሊቀ ጳጳሱም ጥያቄ በንጉሡና በሕዝቡ ተቀባይነት ስላገኘ ሊቀ ጳጳሱ በደስታ ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይተረካል።
የቅዱስ ይምረሐነ ክርስቶስን ደግነት፣ ክርስቲያናዊ የብቃት ደረጃውንና መንፈሳዊ አስተዳደሩን በዝና ሰምተው ይህንኑ ለማየት ከመካከለኛው ምሥራቅ (ከግብጽ፣ ከግሪክ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከሶሪያና ሌሎችም አካባቢዎች ሊሆን ይችላል) ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ ጳጳሳት፣ ኤጲስቆጶሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና መነኮሳት የተካተቱበት ክርስቲያኖች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ተመዝግቧል። እነዚህም ክርስቲያኖች በጀሯቸው የሰሙትን በዐይናቸው ስላዩትና በንጉሡ ገቢረ ተአምራትና መንፈሳዊ ሕይወት ተመስጠው ወደ አገራቸው ሳይመለሱ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በዚያው እንደቆዩ ይነገራል። እስከ ዛሬ ድረስ ዐጽማቸው ዐጽመ ቅዱሳን ተብሎ ምንም ሳይፈርስ በክብር አንድ ላይ በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ በስተምዕራብ አቅጣጫ በዋሻው ውስጥ ይገኛል።  ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስን ሊጎበኙት ከመጡ ሰዎች መካከልም ሊቀ ጳጳሱ አቡነ አትናቴዎስ በዋናነት ይጠቀሳሉ። በሊቀ ጳጳሱ ጉብኝት ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ እጅግ ተደስቶ በዘመኑ ለነበሩት የእስክንድርያው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ከፍተኛ ምስጋና ማቅረቡና እሳቸውም ኢትዮጵያን  እንዲጎበኙ ግብዣ ማድረጉ በጽሑፍ ተመልክቷል።
ከሁሉም በላይ ይህ ታላቅ ንጉሥ የሚታወሰው ከቅዱስ ላሊበላ ከተማ በስተሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በ42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወግረ ስኂን በሚባል ቦታ በትልቅ የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ ባነጸውና በስሙ በሚጠራው ዕድሜ ጠገብ ቤተ ክርስቲያን ነው። ይህ ቤተ ክርስቲያን በአገራችን በከፍታው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው የአቡነ ዮሴፍ ተራራ (4190 ሜትር ከፍታ ያለው) ግርጌ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድ በምዕራብ አቅጣጫ ቁልቁል ተጉዘው የሚደርሱበት ነው። የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከባቢያዊ ሁኔታ በማራኪ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጡና አገር በቀል የጽድና የወይራ ዛፎች በበዙበት ጥቅጥቅ ደን ምክንያት ልዩ ግርማ ሞገስን የተላበሰ ነው።  ቤተ ክርስቲያኑ የታነጸው ከግዙፉ ዋሻ ውስጥ ከባሕር ላይ በተደለደለ መሬት ነው። የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሁኖ በውጭም ሆነ በውስጥ በረቀቀ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የተሠራ ነው። በውጭ በኩል በቀደመው የአክሱማዊ የኪነ ሕንጻ ጥበብ እንጨትና ድንጋዮች እየተፈራረቁ እንደ ማገርና መቀነት ሁነው ልዩ ውበትን ፈጥረውለታል። ቤተ ክርስቲያኑ በተለያዩ የመስቀል ቅርጾች የተዋቡ፣ ከዕብነ በረድ ወይም ከከበረ እንጨት የተሰሩ፣ ብዙዎቹ ተከፋች ጥቂቶቹ ደግሞ ዝግ የሆኑ በድምሩ ሃያ ስድስት መስኮቶች ያጌጠ ነው።
አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኑ የውስጥ ክፍል በአግባቡ ተጠርበው በተዘጋጁ ውድ እንጨቶች የተገነባ ነው። የቅድስቱ መሀል ክፍል ጣራ የፈረስ ኮርቻ የመሰለ ወይም የተገለበጠ መርከብ ቅርጽ ያለው ሲሆን ሌላው የጣራ ክፍል ደግሞ በሰባቱ ሰማያት በተመሰሉ በሰባት ክፍሎች የተዋቀረ ነው። የቤተክርስቲያኑ ቅድስት የመሀል ክፍል በማዕዘን በማዕዘኑ ላይ አምስት ክፍሎች ያሉት ፎቅ ይገኝበታል።  በዚሁ በቅድስቱ ላይ የውጩን የቤተክርስቲያን ክፍል አሠራር ንድፍ ተከትለው በጥንቃቄ በተጠረቡ፣ለስላሳ፣ጠንካራ፣ሰፋፊና ከባድ በድንጋይ ላይ የታነጹ ስድስት ምሰሶዎች አሉ። ጣራውን ደግፈው የያዙት የምሰሶዎቹ የላይኛው ክፍል ልዩ የሆነ የአሠራር ጥበብን በተከተሉና በልዩ ልዩ ንድፍና ጌጥ በተዋቡ  ከእንጨት በተሰሩ ቅስቶች (ዐርኮች) የተዋቀረ ነው። የቤተክርስቲያኑ በሮች በውስጥ በኩል ከእንጨት በተዘጋጀ መወርወሪያ ነገር በልዩ ዘዴ የሚከፈቱና የሚዘጉ ደህንነታቸውም አስተማኝ ነው። ቤተ መቅደሱ ሦስት ክፍሎች ሲኖሩት የመሀከለኛው የመቅደስ ክፍል ጣራው ክብ ጉልላት ያለው (የዘውድ ቅርጽ የመሰለ) እና በሥዕሎችና ንድፎች ያጌጠ ነው።  ሁሉም የጣራው ክፍሎች በእንጨት ሰሌዳነት በልዩ ልዩ ንድፎች፣ የመስቀል ቅርጾች፣ ምሥሎችና ሥዕሎች ያሸበረቀ ነው። ከጣራውና ከቅስቶቹ ለየት ባለ መልኩ በሰሜን አቅጣጫ ባለው የቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ የሐዲስ ኪዳንን ታሪክ የሚያስታውሱ በርካታ ሥዕሎች ይገኛሉ። የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን አብዛኛው የውስጥ ክፍሉን ለመሥራት ዐርዘ ሊባኖስ ተብሎ የሚታወቀውን የከበረ እንጨት ተጠቅመውበታል።
በወግረ ስኂን ከቤተ ክርስቲያኑ ሌላ ቤተ መንግሥት ተብሎ የሚታወቅ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሌላ ትልቅ ሕንጻ ዋሻው ውስጥ ይገኛል። ይህ ሕንጻ በብዙ መልኩ ከቤተክርስቲያኑ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም በአሠራሩ ቀለል ያለና ውስብስብ ያልሆነ እንዲሁም የተለዩ ንድፎችና ጌጦች የማይታዩበት ነው። በዚሁ በዋሻው ውስጥ ከቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ በስተደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ መቃብር ዙሪያውን የድንጋይ አጥር ተሠራቶለት በድንኳን መልክ ታነጾ ይገኛል። ቤተ ክርስቲያኑን ለመሳለም የሚሄዱ ሰዎች መቃብሩን ሦስት ጊዜ እየዞሩ ካህኑን ንጉሥ “ፍታኝ ይምርሐነ ክርስቶስ” ማለት የተለመደ ነው። በዚህ ጥንታዊና ዘመን ተሻጋሪ የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሌሎች በርካታ ውድና ድንቅ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችም ይገኛሉ። ይህ ቤተክርስቲያን በግራኝ ጦርነት ጊዜ የብዙ አብያተክርስቲያናትን ንዋያተ ቅድሳትና ቅርሶችን በአደራ ጠብቆ የያዘ ነበር። የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንና ቤተመንግሥት ከታነጹ ጀምሮ ምንም ዓይነት ጥገና ወይም እድሳት ሳይደረግላቸው ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በላይ የተጓዙ ድንቅ ቅርሶች ናቸው።  ይሁንና እነዚህ ታላቅና ዘመን ተሻጋሪ የአገር ሀብቶች በዕድሜና በአገልግሎት ብዛት ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው አፋጣኝ መፍትሔ ካልፈለጉለት የሚደርሰው ጉዳይ አስከፊ ሊሆን ይችላል።


Read 1552 times