Monday, 01 November 2021 05:28

ጨቅላውን ፍለጋ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

ኮበሌው  ትላንት ባንጸባረቀው ተኮናኝ ድርጊት፣ በሀፍረት ስሜት ጭብጦ አክሏል። ከአዛውንቱ ጠቢብ እግር ሥር ሆኖ ይቅርታቸውን እንዲለግሱት በአይኑ ይማጸናቸዋል፡፡
“ምን ሆነሃል ወዳጄ?” አሉ፤ ጠቢቡ ግራ በተጋባ ስሜት፡፡
“አባት፤ ትላንት መስመር ስቼ ነበር። ከአጋፋሪዎችዎ ጋር ሆነው በመንደሯ ሲያቋርጡ፣ ምራቄን የተፋሁብዎት እኔ ነበርኩ፡፡ ይኽው በጸጸት እየተለበለብኩ፣ እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር፣ ስገላበጥ ነው ያደርኩት፡፡ እርስዎን የመሰለ የተከበረ ሰው አዋርጄአለሁ፡፡ እባክዎን ይቅርታዎን አይንፈጉኝ፤”  አለ እየተርበተበተ፡፡
“ልጄ ትላንት ምራቅ የተፋህበት ሰው ሞቷል፡፡ አሁን ከፊት ለፊት ያለው አዲስ ሰው ነው፡፡ ለማን ነው ይቅርታ የምትለው?” ብለው ጠቢቡ ውስጠ ወይራ መልሳቸውን ሰጡት፡፡  
የጠቢቡ አባባል፣ የመዶሻ ያህል እንደሚያምህ አውቃለሁ፡፡ እንኳን የትላንቱን ልትዘነጋ፣በአፍላ እድሜህ የቋጠርከው ቂም፣ ረመጥ ሆኖ ይለበልብል፡፡ በደጃፍህ ሞልቶ የፈሰሰው አዱኛ፤ እላይህ ላይ እንደዛር የተሳፈርብህን ቆፈን ማባረር አልቻለም፡፡ በደመነፍስ ሐዲድ ላይ እየነጎዱክ፤ይኽው ግምሽ ክፍለዘመን ደፈንክ፡፡ የአዛውንቱ ጠቢብ ጉንተላ፣ ለአንተ ቢጤ በቁም ቅዥት ለሚዋጅ ባተሌ፣ ግራ ነው፡፡
ጠቢቡ የትላንት ጓዛቸውን ጥለዋል፡፡ ከትላንት የሚወራረድ ሒሳብ የላቸውም፡፡  በትላንት መቃብር ላይ የዛሬ ኩታራ ናቸው። ኩታራ ደግሞ የነካው ሁሉ የሚባረክ፣ የሰላምና የፍቅር ቤተመቅደስ ነው፡፡ ዓለም እንድትስቅልህ ከፈለግክ ልጅ ሁን፤ ሲባል አልሰማህም? ለነገሩ እንዴት ትሰማለህ ወዳጄ?  አቅልህን ተነጥቀሃል:: የአንተን ፎልቅልቅ ጨቅላ የበላ ጅብ፣ ለምን አልጮኽ አለ?
 ግድየለህም፣ ልብ ብለህ ተከተለኝማ....
በድሮ ዘመን ነው፡፡ እንድ የጥበብ ሰው ወዲያ ወዲያ ሲንከላወስ፣ ከመስክ ላይ የሚቦርቅ እረኛ ኩታራ ድንገት ከዐይኑ ይገባል፡፡ ጠቢቡ፣ ፍልቅልቁን እረኛ በጥበብ መረብ ማጥመድ እንዳለበት ካራማው ሹክ አለው፡፡ ሸራ ወጥሮ፤ ብሩሹን ከቀለም ጋር አወሃዶ፤ የጥበብ አሻራውን አሳረፈ። እንዳሰበውም፣ የጥበብ ሥራው በሀገሬው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘ፡፡ የእረኛው ፍልቅልቅ ገጽታ የታተመበትን ሸራ፣ ከግድግዳ ላይ ማንጠልጠል የሰላም ምልክት ተደርጎ በሀገሬው ዘንድ ተወሰደ፡፡
ከዘመናት በኋላ፣ ጠቢቡ አንድ ሐሳብ ወደ ምናቡ ብቅ አለ፡፡ የእረኛው ስዕል የሰው ልጅን ከፊል እውነታን ነው የሚያሳየው። በመሆኑም ሌላ የመከፋት፣ የእንግልትና የጭንቀት ተምሳሌትን የሚወክል ጥበባዊ ሥራን፣  ለአይነ ሥጋ ማብቃት እንዳለበት ወሰነ፡፡   
በውጥኑ መሠረት፣ ይኼንን ገጽታ ሊወክል የሚችል ሰውን፣ በገሀዱ ዓለም ለማግኘት በብርቱ ዋተተ፡፡ በማሳረጊያው፤ አንድ የሞት ፍርደኛ ቀናው፡፡የፍርደኛው ገጽታ፣ ሰዓሊው በምናቡ ላስቀመጠው የመንፈስ ጉስቁልና፣ ኹነኛ ወኪል ነው፡፡ ፍርደኛው አይኑ የገሀነም እሳትን ይተፋል፡፡ ገጽታው በብርቱ ይከብዳል፡፡ ሰዐሊው ሸራውን ወጥሮ፣ ቀለሙን በከብሩሹ ጋር ለማዋሀድ ሲያኮበኩብ፣ ፍርደኛው ስቅስቅ ብሎ ማንባት ጀመረ፤
“ምን አጠፋሁ ወዳጄ? ለአንተ ማስታወሻ የሚሆን የጥበብ ሥራ ላይ ምናቤን እያፍታታሁ እኮ ነው፤ ” አለ ሰዓሊው ግራ በተጋባ ስሜት፣
“ከዘመናት በፊት፣ ከለምለም መስክ ላይ አግኝትህ ከሸራህ ላይ ያኖርከኝ፣  ፍልቅልቁ እረኛ እኮ እኔ ነበሩክ፤” እለ ፍርደኛው ጸጸት በተሰማው ስሜት፡፡  
ፍልቅልቁ እረኛና የሞት ፍርደኛው፣ በውስጥህ ያሉ፣ የብርሃንና የጽልማት ተምሳሌት ማንነቶች ናቸው፡፡ ከሁለቱ አንዱ መምረጥ፣ የአንተ ፈንታ ነው። እጅህን ወደ እሳት፣ ወይም ወደ ውሃ መስደድ ትችላለህ፡፡
 ፍልቅልቁ ማንነትህን አትፈጥረውም። ልክ እንደ ከርሰ ምድር ውሃ፣ ከውስጥህ ተቀብሯል፡፡ ከአንተ የሚጠበቀው፣ የተጫነውን መርግ ገሸሽ ማድረግ ነው። ምክር ለሰጪው ቀላል ነው፤ እያልከኝ እንደሆነ ይሰማኛል፤ ግድየለም ይኽንን ድምጽ ለጊዜው ፊት ንሳና ጥቂት ተከተለኝ።
ፍልቅልቁ ጨቅላ ማንነት፣ በውስጥህ አድብቷል እንጂ አልሞተም፡፡ በርግጥ፤ ከዚህ ብርሃን  ጋር ለመወዳጀት፣ ትንሽ ሀሞትን ይጠይቃል፡፡ ለፈሪ እጅ አይሰጥም። ሞትን የሚያሸንፍ ሥነልቦናን እንደ ዝናር መታጠቅ ይኖርብሃል፡፡
አንዳንድ ብልህ ሰዎች፣ የመቃብር ሥፍራን በየጊዜው  የሚጎበኙት ለምን ይመስልሃል? ሞትን ለመለማመድ ነው። ሞትን በናቅከው ቁጥር፣ በላይህ ላይ የተቆለለው የክፋት ክምር፣ የእምቧይ ካብ መሆን ይጀምራል፤ ጨለማው ሰብዕና እጅ ይሰጣል፤ ለቀናኢው፣ለፍልቅልቁ ጨቅላ ፀሐይ ይወጣለታል፡፡
ከዚህ የንቃት ማማ ላይ እንደደረስክ ምልክት የሚሆንህ፣ ተመልሶ የተወዳጀህ የልጅነት ስሜትህ  ነው፡፡ ደርሶ መናኛ ነገር ያስፈነድቅሃል፡፡ ሕይወትን በዜማ ነው፤የምትረዳት፡፡ ከሒሳብ፣ ከስሌት ጋር ጠበኛ ትሆናለህ፡፡ በላይህ ላይ ሴራ ለሚጠነሰሱት የጨለማው ምርኮኞች፤በሀዜን ስሜት ከንፈርህን እየመጠጥክ፤ የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፣ የሚለውን ቀኖና፣ ድንገት አንደበትህ ሲያነበነብ ልታገኘው ትችላለህ፡፡

Read 618 times