Monday, 01 November 2021 05:36

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በህይወቴ የሚገርም፣ የሚወራ፣ የሚያምር፣ የሚያስፈነድቅ፣ የተኖረ የፍቅር ታሪኬ ከፍጼ ጋር የነበረኝ ጊዜ ነበር። በጣም ነበር የማፈቅረው። እናቴን እስከ መተው፣ ከእህቴ እስከ መጣላት፣ ከወንድሜ እስከ መደባደብ፣ አባቴ እስኪታዘብ፣ ጎረቤት እስኪፈርድብኝ፣ ትምህርት ቤት ሰነፍ ሆኜ ክፍል እስከ መድገም፣ ጓደኞቼ ተረድተው እስኪያዝኑልኝ… ልቤ ጥፍት እስኪል እወደው ነበር። የምር!
እሱ ግን አይረዳኝም። እሱ የአፍ ፍቅር ይወዳል። ልብ ሳይሆን አንደበት ነው የሚያዳምጠው። “ፍቅሬ፣ ማሬ፣ ባባዬ፣ ቤቢ፣ ፍጼ፣ ሕይወቴ፣ አንጀቴ…” መባል ይፈልጋል። እኔ ደግሞ አልችልም። ልብ ካለው ልቤን አያዳምጥም። እኔ ነገር አቀናብሮ ማውራት አልችልም። ያኔ የምር!
በዚያ ላይ ፍጼን በጣም አፈቅረዋለሁ። በጣም ታላቄ ይመስለኛል። ስለምፈራው ዝም እለዋለሁ። እሱ ሲሳሳትም ሆነ ትክክል ሲሆን አስተያየት ይፈልጋል። እኔ ዝም። ዝም እእእእ… እሱ ንድድ። ንድድድድድ… ለጥፋቱ ወቀሳ ለስራው አድናቆት ይጠብቃል። መጠበቅ ይጎዳል። በጠበቁት ልክ ሲጎድል ህመሙ ይከፋል። ፍጼ ይታመም ነበር። በዚያ ላይ ራሱን እንደ ስሙ ፍጹም አድርጎ ነው የሚያስበው። ትልቁ ስህተቱ። ፍጽምና። ራሱን ፍጹም አድርጎ ማሰቡ ባልከፋ (መቼስ ስሙም ፍጹም አይደል)። ችግሩ ከሌላው ሰው ፍጽምና መጠበቁ ነው።
“ለምን አታወሪም”፤ ለምን ውሎሽን ፍጼ ዛሬ እኮ እንዲህ ሆኖ እንዲህ ተፈጥሮ አትይም… ለምን ስሜን አትጠሪኝም?” ይለኛል። እንዲህ ሲለኝ ይበልጥ መናገር ይደብረኛል። መወቀስ አልፈልግም። ስለዚህ ይብስ ዝም እለዋለሁ።  ይናደዳል። ጭርጭር ላል። ሲናደድ ደስ ይለኛል በጣም የሚወደኝ ይመስኛል።
በፍጼ በጣም ደስ ያለኝ ቀን ትምህርት ቤት ወላጅ የሆነኝ ቀን ነበር። ክፍል ውስጥ “ወክማን” የምትባለውን የሲዲ ማጫወቻ ይዤ ሙዚቃ እየሰማሁ ነው። ልብ ጥፍት የሚያደርጉ የፍቅር ዘፈኖች አቀናብሮ የሰጠኝ ፍጼ ነው። ስለዚህ የቱ ጋ ምን ሊለኝ እንደፈለገ ለማወቅ፣ እያንዳንዱን የሙዚቃ ስንኝ ምዝምዝ አድርጌ እየሰማሁ ለመረዳት በጆሮ ማዳመጫ አድርጌ፣ ሙዚቃው ላይ ተመስጬ እያዳመጥኩ ነው።
በዘፈኑና በመልዕክቱ ተመስጬ ሳላየው ሒሳብ አስተማሪያችንና የክፍል ኃላፊያችን ለካ ወደ ክፍል ገብቷል። ገብቶም ሳይቆይ አልቀረም። እኔ ልብም አላልኩት። ልብስ የታለ? የለም ፍጼጋ ነው። ቀልብ የለም በዘፈኑ ተባብሎ ይዋትታል። ዓይን የለም- በፍጼ ተጋርዷል። ማስተዋል የለም፣ ፍቅር አያስተውልም። አስተማሪያችን ዘሎ መጥቶ ከጆሮዬ ላይ ማመጫውን ሲነቅለው ነው ከትዝታ ሰፈር በፍጥነት ተመልሼ ክፍል ውስጥ የነቃሁት፡፡ ማዳመጫውን ነቅሎ ሲዲ ማጫወቻውን ነጥቆኝ ከመዝጋቱ በፊት የማዳምጠውን ዘፈን ሰማና፣ ክፍል ውስጥ ላሉት ተማሪዎች ነገራቸው።
“ልጆች የምትሰማውን ዘፈን ልንገራችሁ?” እያፌዘ
የክፍል ጓደኞቼ እያሾፉና እያሽሟጠጡ በደቦ “አዎ…ኦ!” አሉ።
አስተማሪያችን አየት አድርጎኝ ሳቅ አለና፣ “የፍቅር ዘፈን…የሚካኤል በላይነህን “የነገን ማወቅ ፈለኩኝ… አንቺ ነሽ የሕይወት ምርጫዬ” ይላል። ሃሃሃ…” እያፌዘ። የክፍል ጓደኞቼ ፌዙን በሳቅ አጀቡለት። እኔ ተናደድኩ። ፊቴ ልውጥውጥ አለ።
አስተማሪያችን ጎርደድ እያለ ማውራት ጀመረ “… ማንም ነገን ማወቅ የፈለገ ሰው ዛሬን በርትቶ ይማር። ማንም የሕይወት ምርጫውን መወሰን የሚፈልግ ሰው ዛሬን ጠንክሮ ያጥና። ማንም ነገን ሊቆጣጠር የፈለገ፣ ዛሬ ራሱን ይቆጣጠር። “አንቺ ነሽ የሕይወት ምርጫዬ” ያለሽ ሰው  ነገ አይደግመውም። እርግጠኛ ነኝ ዩንቨርስቲ ካልገባሽ፣ ጥሩ ሕይወት፣ የዘመነ አእምሮ… ከሌለሽ ይሄንኑ ዘፈን ለሌላ  ሴት ይጋብዛል። ልጆች ነገን የምታውቁት ሂሳብ ስታውቁ ነው።”
ወደ እኔ ዞር አለና “… ራሄል ሒሳብ ከአርባው ስንት እንዳለሽ ታውቂያለሽ… እኔ ለሰው አልናገርም… እኔና አንቺ እናውቀዋለን” በክፍል ልጆች ፊት እንዲህ መባል እንዴት እንደሚያሳፍር። አላገጠብኝ። አላገጠብኝ።
“…ይኸውልሽ ራሄል የነገን ማወቅ ከፈለግሽ አጥኚ… የምታዳምጪው ዘፈን የነገን ማወቅ ፈለግኩ አይደል የሚለው። ጎበዝ ተማሪ ሁኚ። የአንቺ ነገ የዛሬ የማትስ፣ የሒስትሪ፣ የኢኮኖሚክስ… ውጤትሽ ላይ ነው የሚወሰነው።” ተማሪዎች ሳቁ። እኔ በጣም አፈርኩ። ተናደድኩ።
“አትሳቁ! አመድ በዱቄት ይስቃል፤ እናንተስ ያው አይደላችሁ። እሷ ዛሬ ተጋልጣ ነው። የክፍል ኃላፊያችሁ መሆኔን አትርሱ። እንግዳ አደረጋችሁኝ እኮ ስትስቁ። ውጤታችሁን አላውቀውም። አንተ ነቢል፤ አሁን አንተ ሰው ላይ የምትስቅ ነህ? አሁን እንደው ረድኤት ይህ ንግግር አንቺን ያስቃል?” ሁሉም አንገታቸውን መድፋት ጀመሩ። “…ኃጢያት የሌለበት ሰው ይውገራት…” ብሎ ኩም አደረገልኝ።
“ለማንኛውም ወላጅ አምጥተሽ ነው ወክማንሽን የምትወስጂው” ብሎ ወደ ቢሮ ወሰደብኝ። በጣም ተጨነቅኩ። ለእናቴ ብነግራት አንቃ ነው የምትገድለኝ። ሲጀመር ሲዲ ማጫወቻው የሰው ነው። የአብሮ አደጌ። የሜሪ።
“ከየት አመጣሽ… ለምን ዘፈን ትሰሚያለሽ… ብለሽ ብለሽ ትምሀርት ቤት ውስጥ… ያውም ክፍል ውስጥ… ውጤትሽ እንደዚያ ተበላሽቶ…” የሚሉትን ቁጣዎች ማስተናገድ በጣም ይከብዳል። ጉልበቱም፣ ኃይሉም፣ ትዕግስቱም… የለኝም።
ስለዚህ ብቸኛው አማራጭ ፍጼን እንደ ወንድም አድርጎ መውሰድ ነበር። ስጠይቀው እሺ አለኝ። እንዴት ደስ እንዳለኝ። ወንድም ሆኖ መምጣቱ ሳይሆን ያንን ኃላፊነት መውሰዱ። ቢታወቅበት የሚፈጥረውን ችግር ለእኔ ሲል ለመቀበል መዘጋጀቱ በጣም ነው ደስ ያለኝ። የተፈጠረውን የተባልኩትን አልነገርኩትም። የነገርኩት ሳዳምጥ እንደተቀማሁ ነበር። ፍቅሩን ተሸክሜ የወጣሁትን ቀራኒዮ ለምን ልንገረው? ሳፈቅር ከዚህ በላይ ልቸነከር ነው።
(ከቃልኪዳን ሃይሉ “ክብር” የተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ)

Read 2083 times