Sunday, 07 November 2021 17:31

በኒውዮርክ ማራቶን የወርቅ ኢዮቤልዩ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • ለቀነኒሳ የመጨረሻው ይሆናል?
    • ለኪፕቾጌ የ‹‹አበበ ቢቂላ አዋርድ›› ይሰጠዋል
    • የሩቲ ትንቅንቅ ከኦሎምፒክ ሜዳልያ አሸናፊዎች ጋር ይሆናል
    • አብይ ስፖንሰሩ TCS በዓመት እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል
    • ከተማዋ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች
    • ባለፉት 15 ዓመታት ለእርዳታ የሚውል ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሰብስቧል


               50ኛው የኒውዮርክ ማራቶን ከ33ሺ በላይ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ ነገ ይካሄዳል፡፡ የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተሳትፎ የውድድሩን የወርቅ ኢዮቤልዩ አካባበር እንደሚያደምቀው የገለፁት አዘጋጆች፤ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ሜዳልያዎችን የተጎናፀፉ ምርጥ አትሌቶች መወዳደራቸውም አጓጉቷቸዋል፡፡
ቀነኒሳ በቀለ በኒውዮርክ ማራቶን ላይ የዓለም ሪከርድን ለማሻሻል የመጨረሻው እድል እንደሆነ  የጠቀሱ ትንታኔዎች ማሸነፍ እንደሚችል ቢጠብቁም የሪከርዱን ጉዳይ ተጠራጥረውታል። ከ3 ዓመት በፊት በበርሊን ማራቶን ሲያሸንፍ  2:01:41 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው  ውጤት በማራቶን ከዓለም ሪከርድ ቀጥሎ የሚጠቀስ ፈጣን ሰዓትና የኢትዮጵያም ሪከርድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቀነኒሳ ብቻ ሳይሆን በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ሜዳልያዎችን የተጎናፀፉ አትሌቶች ተሳትፎም ልዩ ትኩረት አግኝቷል፡፡ በቶኪዮ 2020 ላይ በኦሎምፒክ ማራቶን የብር ሜዳልያ የወሰደውና በግማሽ ማራቶን ከ58 ደቂቃ በታች በመግባት 57:32  በሆነ ጊዜ የዓለም ሪከርድ ያስመዘገበው የኬንያው ኪብዮት ካንዴይ እንዲሁም በኦሎምፒክ  ማራቶን ነሐስ የወሰደው ሆላንዳዊው አብዲ ነገዬ ይገኙበታል፡፡ በሴቶች ምድብ ለድል የተጠበቁት በማራቶን የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነችው ፔሬስ ጄፕቼሪር ከኬንያ እና   የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው  ሞሊ ሴይደል ከአሜሪካ ናቸው፡፡
የኒውዮርክ ማራቶን በ2020 እኤአ ላይ በኮቪድ ሳቢያ ያልተካሄደ ሲሆን ዘንድሮ  የኮቪድ-19  ክትባት የወሰዱ ወይም በቅርብ ጊዜ ምርመራ አድርገው  ኔጌቲቭ መሆናቸውን ያረጋገጡ ብቻ ይሳተፉበታል።  ተሳታፊዎች ከውድድር ውጭ በማንኛውም ጊዜ የፊት መሸፈኛ ማድረግ እንዳለባቸው ተወስኗል። በመሮጫ ጎዳናው መጨናነቅን ለመቀነስም  በአምስት የተለያዩ የጊዜ ሰሌዳዎች ሩጫውን ለማስጀመር መታቀዱን   ለማወቅ ተችሏል፡፡
በበርሊን ማራቶን ላይ 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃዎች ከ47 ሴኮንዶች በሆነ ጊዜ ሶስተኛ ደረጃ ያገኘው ቀነኒሳ በቀለ በአሜሪካ ምድር የመጨረሻውን ውድድር ማድረጉ ይሆናል።  ማናጀሩ ጆስ ሄርማንስ ከ42 ቀናት በኋላ ሌላ ትልቅ ማራቶን መሮጡን የአትሌቱን ልዩ ብቃት ያሳያል ብለዋል፡፡ በ39 ዓመቱ ሁለት ትልልቅ ማራቶኖችን በ42 ቀናት ልዩነት ለመሮጥ የቻለ ምርጥ አትሌት አለመኖሩንም ጠቁመዋል። የኒውዮርክ ማራቶን አስቸጋሪ እና አቀበት የበዛበት መሆኑን ያወሳው የሌትስራን ዘገባ፤ ቀነነኒሳ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች ያስመዘገበውን ተስተካካይ የሌለው የውጤት ታሪክ የሚያድስለት ዜና በአሸናፊነቱ ሊያገኝ እንደሚችል አብራርቷል፡፡ የዓለም ሪከርድን ማሻሻሉ ግን  አይጠበቅም ብሏል ሌትስ ራን በድረገፁ፡፡ በወንዶች ምድብ ከሚሰለፉት እውቅ አትሌቶች ከሁለት ሰዓት ከ06  ፤ ከ05 ፤ ከ04፤ ከ03 እና ከ02 ደቂቃዎች በመግባት ብቸኛው  ማራቶኒስት ቀነኒሳ ነው፡፡  በአሜሪካ በሚካሄድ ውድድር ላይ ሲሳተፍ ከሰባት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜው ነው፡፡ በኒውዮርክ ማራቶን ላይ ስለመሮጡ በሰጠው አስተያየት ‹‹በሩጫ ዘመኔ ባከናወንኳቸው በርካታ ስኬቶች እኮራለሁ ፤ ሆኖም  በኒውዮርክ ማራቶን  ላይ ለመወዳደር አጋጣሚ አግኝቼ አላውቅም። ዘንድሮ መሮጤ በጣም አስደስቶኛል። ከታላላቅ ስኬቶቼ መካከል ዋናዎቹ በአገር አቋራጭ ሩጫ ያስመዘገብኳቸው ናቸው። የኒውዮርክ  ጎዳና አቀበቶችና ጠመዝማዛ መንገዶች  አትሌቶችን ይፈትናሉ፡፡ በአገር አቋራጭ ከመሮጥ የነበረኝ ጥንካሬ እንደሚያግዘኝ እገምታለሁ ።የኒው ዮርክ ማራቶን ካሸነፉ ታላላቅ አሸናፊዎች ስም ዝርዝር ለመቀላቀል የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።›› ብሏል፡፡
ቀነኒሳ በኒውዮርክ ማራቶን የሚያደርገው ተሳትፎ በአሜሪካ ለሚካሄድ ውድድር የመጨረሻው  እድል ሊሆን ይችላል፡፡   ከሰባት ዓመታት በፊት በአሜሪካ የተወዳደረው በቺካጎ ማራቶን ሲሆን 4ኛ ደረጃ ያገኘበት ነው፡፡ ከዚያ በፊት በአሜሪካ የሮጣቸው  ሌሎች ውድድሮች በኦሬገን ፕሮፌንታይኔ ክላሲክስ በ2013 እኤአ በ10ሺ ሜትር ያሸነፈበት፤ በ2012 እኤአ በ5ሺ ሜትር 4ኛ ደረጃ ያገኘበትና በ2008 እኤአ በ10ሺ ሜትር ያሸነፈበት ይጠቀሳሉ፡፡  በ2006 እኤአ በሚልሮስ በ1 ማይል ሩጫ ሁለተኛ ደረጃ የጨረሰበት እንዲሁም በ2005 እኤአ ላይ በቦስተን ኢንዶር ጌምስ በ3000 ሜትር ሁለተኛ ደረጃ ያገኘበት ሌሎቹ ናቸው፡፡
በወንዶች ምድብ የኢትዮጵያው አትሌት ግርማ በቀለ ገብሬ፤ የኬንያው አልበርት ኮሪርና የኤርትራው ግርማይ ገብረስላሴም ማራቶኑን በአስደናቂ ፉክክር እንደሚያደምቁት ተጠብቀዋል፡፡
በሴቶች ምድብ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅና የነሐስ ሜዳልያዎችን ሜዳልያ ለወሰዱት ለኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቼሪር እና  ለአሜሪካዊቷ ሞሊ ሴይድል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷል፡፡ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል አራቱ ከ2 ሰዓት ከ24 ደቂቃዎች በታች አምስት ደግሞ ከ2 ሰዓት ከ25 ደቂቃዎች በታች የገቡ ናቸው፡፡ በተለይ በኦሎምፒክ መድረክ 2:17:16 በሆነ ጊዜ የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈችው ፔሪስ ጄፕቼሪር ተፎካካሪ እንደማይኖራት ተጠብቋል። የ27 ዓመቷ ኢትጵዮያዊት ሩቲ አጋ በማራቶን ያስመዘገበችው የግሏ ፈጣን ሰዓት 2:18:34 ሲሆን  በ6 ትልልቅ ማራቶኖች ላይ ደረጃ ውስ መግባቷ፤ በ2019 የቶኪዮ ማራቶንን ማሸነፏና በተመሳሳይ የውድድር ዘመን በኒውዮርክ ማራቶን ሶስተኛ ደረጃ ማግኘቷ ተወስቶ ለድሉ ግምት አግኝታለች፡፡ በ2019 የቺካጎ ማራቶን ላይ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው አባቤል የሻነህም ለፉክክሩ የተጠበቀች ሌላዋ የኢትዮጵያ አትሌት ናት።
ባለፉት 49 የኒውዮርክ ማራቶኖች በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው በወንዶች 15 ጊዜ በሴቶች 11 ጊዜ ያሸነፈችው ኬንያ ናት፡፡ አሜሪካ በወንዶች 14 በሴቶች 15 የኒውዮርክ ማራቶን ድሎችን በማስመዝገብ ሁለተኛው ከፍተኛ ውጤት አላት፡፡ ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች 5 ድሎችን ነው ያስመዘገበችው፡፡ በ2001 እኤአ የመጀመርያውን የኢትዮጵያ ድል 2 ሰዓት ኮ0 ደቂቃ ከ43 ሰኮንዶች በሆነ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግቦ ያሸነፈው ተስፋዬ ጅፋር ጅፋር ነበር፡፡ በ2010 እኤአ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም እንዲሁም በ2018 እኤአ ላይ ሌሊሳ ዴሲሳ አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ ደራርቱ ቱሉ በ2009 እኤአ እንዲሁም ፍሬህይወት ዳዶ በ2011 እኤአ አሸንፈዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የኒውዮርክ ማራቶንን የሚያዘጋጀው ኒውዮርክ ሮድ ራነርስ (NYRR) የአበበ ቢቂላ አዋርድን ለኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ በረጅም ርቀት ሩጫ ላይ የጎላ አስተዋፅዖ ያደረጉትን ለማክበር በየዓመቱ የሚያበረክተው ሽልማት ነው፡፡ ኪፕቾጌ በማራቶን በሪዮ እና ቶኪዮ ኦሎምፒኮች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን አከታትሎ በማሸነፍ የአበበን ታሪክ መጋራቱ ይታወሳል።   በ2018 የበርሊን ማራቶን 2፡01፡39 የአለም ሪከርድ መያዙ ምይታወቃል። በማራቶን ያስመዘገበው ስኬት በዓለም አትሌቲከስ ከፍተኛው ክብርና  ዝናን ያጎናፀፈው ሲሆን በልዩ ሽልማቱ የስፖርቱን አጠቃላይ ገፅታ ከፍ ማድረጉ እውቅና ይሰጠዋል። ኪፕቾጌ ከወር በፊት በስሙ ፋውንዴሽን ያቋቋመ ሲሆን በትምህርት እና በአካባቢ ጥበቃ ለትውልድን የሚሰራበትን አቅጣጫ መያዙም በስፖርቱ ዓለም እየተደነቀ ነው፡፡
ከተመሰረተ 62 ዓመታትን ያስቆጠረው ኒውዮርክ ሮድ ራነርስ በዓለም አትሌቲክስ ላይ የጎላ እንቅስቃሴ በመፍጠር  ከበሬታን አትርፏል፡፡  ከማራቶኑ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ከ695ሺ በላይ ስፖርት አፍቃሪዎችን የሚያስተባብር ተቋም ነው፡፡ የኒውዮርክ ማራቶን ከበርካታ ግብረሰናይ ተቋማት እና በጎ አድራጊዎች ጋር በመስራት ለእርዳታ የሚውል ገንዘብ በማሰባሰብም ተሳክቶለታል፡፡ በ2018 እኤአ ላይ በተካሄደው ማራቶን የስፖርት ተቋሙ ለእርዳታ የሚውል ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማሰባሰብ በቅቷል፡፡ ከማራቶን ውድድሩ  በተፈጠረው አጋርነት  ከ2006 እኤአ ጀምሮ ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለእርዳታ የሚውል ገንዘብ ሊያስባስብም መቻሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኒውዮርክ ማራቶን በቱሪዝም እና በተለያዩ መንገዶች ለከተማዋ በዓመት የሚያስገባው ገቢ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡
የኒውዮርክ ማራቶን አብይ ስፖንሰር የህንዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ Tata Consultancy Services (TCS) ሲሆን እስከ ከ2022 እስከ 2029 የታላቁ የማራቶን ውድድር  አብይ ስፖንሰር ሲሆን በዓመት ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል፡፡  በህንድ የአክሲዮን ገበያ እስከ 159 ቢሊዮን ዶላር የሚተመነው የቴክኖሎጂ ኩባንያው ከኒውዮርክ ማራቶን ባሻገር የቺካጎ እና የቦስተን ማራቶኖችን እንዲሁም በአውሮፓ እና በአውስትራሊያ የሚካሄዱ ውድድሮችን ስፖንሰር ያደርጋል፡፡ ከ2027 እኤአ ጀምሮ ደግሞ የለንደን ማራቶን አብይ ስፖንሰር እንደሚሆን ታውቋል፡፡
ከኮቪድ በፊት የኒውዮርክ ማራቶን ከ1.5 ሚሊዮን ተመልካቾች በየጎዳናው የሚታደሙት ሲሆን የዓለማችን ግዙፉ ማራቶን ሲሆን በ2019 እኤአ ላይ ሲካሄድ ርቀቱን 53,640 ተሳታፊዎች መጨረሳቸው በክብረወሰን ተመዝግቧል፡፡የቦታውን ሪከርድ በወንዶች በ2011 እኤአ ላይ ኬንያዊው ጄፍሪ ሙታይ በ2፡05፡06 እንዲሁም በሴቶች በ2003 እኤአ ላይ ኬንያዊቷ ማረጋሬት ኦኮዮ ይዘውታል፡፡ በኒውዮርክ ማራቶን ለሽልማት የቀረበው ገንዘብ 534ሺ ዶላር  ነው፡፡  በዋናው ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉት 100ሺ ዶላር፤ ለሁለተኛ 60ሺ ዶላር፤ ለሶስተኛ 40ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ ለአራተኛ 25ሺ፤ ለአምስተኛ 15 ሺ ፤ ለስድስተኛ 10ሺ ለሰባተኛ 7500 ለስምንተኛ 5ሺ፤ ለዘጠነኛ 2500 እንዲሁም ለአስርኛ ደረጃ 2ሺ ዶላር ተዘጋጅቷል፡፡



Read 9753 times