Print this page
Sunday, 07 November 2021 17:29

“የሙዝ ልጣጭ”፤ ጽጌረዳ ከእነ እሾህዋ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 ውሉ ባልታወቀ አምናና ዘንድሮ፣
ሰምና ወርቅ ገመድ ተቆላልፎ ታስሮ፣
አልፈታ ብሏል የቅኔው ቋጠሮ
ቀጣይ የአገሬ ዕጣ የሕዝቦቿ ኑሮ፡፡
ስሜት የሚፋጅ እሳት ነው። ግጥም የስሜት ግፊት ውጤትና መገለጫ ነው። ደግሞም ምናባዊነት ነው። ታዲያ አንዳንዶቹ ላይ ምናባዊነት ይልቅና ስሜት ያንስና፣ የግጥሙን ሃይል ያጠወልገዋል። እንደ መብረቅ ተወርዋሪ ትንታግና ቀስት የሚያደርገው ስሜት ነው።
ኢ.ኢ ግሪኒንግ ለምቦርን፤ ስሜት የግጥምን ሰንደቅ እንደ ሸንበቆ ያወዛውዘዋል የሚል አተያይ አላቸው፡፡ ምናብ ደግሞ አጣፋጭ፣ አስደማሚ ስሜት ፈጣሪ ነው። ኤስ. ኤች. በርተን፤ ግጥም የሀሳብ ጫፍ ይዞ እየኮመከ እስከ መረብ የሚያደርስበት አቅምና ጥበብ ሲኖረው ይመርጣሉ፡፡ አለበለዚያ ባለ ወላቃ ጥርሶች ሳቅ የሚያደርገው ጉድለት አለበት እላለሁ እኔ!
የኛ ሀገር የቅርብ ዓመታት ከበሮ ድለቃ ደግሞ ሀሳብን ብቻ የግጥም መምረጫ አድርጎ የማሰብ፣ ግልብነት ነው። ሀሳብ ብቻ ግጥም ከሆነ፣… ስሙን መቀየር ግድ ይላል!... ግጥም “ገጠመ” ማለት የተከረከመ - የድድ አጥር (Hedge) ይመስል፣ ውበት ብቻ ሳይሆን ቅርጽ የሚሰራበትም ነው።
እኔም እንደ ገጣሚ ስሜት እያንከባለለ ወደ ራሱ ግብ እንዳይወስደኝ ቆም ልበልና  ወደ ዛሬ መነሻዬ ልመለስ።
 ሰሞኑን አንድ ጎረቤቴ (ሰዓሊ ዮሴፍ ሰይፉ) ያቀበለኝ የግጥም መጽሐፍ ኮርኩራኝ፣ እግረመንገዴንም ገጣሚዎቻችንን ላሳስብ ባልኩት ሀሳብ ላይ አቆይታኝ ነው፡፡ ርዕሷ “የሙዝ ልጣጭ” ይላል፡፡ ገጣሚው ይመር ንጋቱ ነው። 116 ገጾች አሏት፣ ዋጋዋ 120 ብር ነው።
መጽሐፍዋ ውስጥ አልፎ አልፎ የሚገርሙ አተያዮች አሉ። ደሞም የተለመዱና ክሊሼዎች አይጠፉም። በአብዛኛው ግን አዳዲስ ምልከታዎች ደንገጥ ያሰኛሉ። ምናልባት ገጣሚው ወደፊት መፈተሽ አለበት የምለው አሰነኛኘቱን ነው። በስነ-ግጥም ምህዋር ይህ ጉዳይ ወሳኝ ነው። ምጣኔም እንደዚሁ!... የተዝረከረኩ ስንኞች፣ የተሰነካከሉ የጎንዮሽ አሰዳደሮች የሀገራችን የቅርብ ጊዜ ማሳያዎች እየሆኑ ስለመጡ፣ ከሸንጎና አደባባይ ይልቅ ወረቀት ላይ ሲሰፍሩ ጥንቃቄ ያሻቸዋል።
መቼም እኛ ሀገር በተለይ አተያይን በተመለከተ በእውቀቱ ስዩምንና በላይ በቀለን መጥቀስ የማይዘለል እውነት ነው። ቤት አመታትና ሙዚቃ ላይ ታገል ሰይፉና መቅደስ ጀንበሩ ለየት ይላሉ። በፍልስፍናና በተለየ ጥያቄ ፈጣሪነት የሚጠቀሱም አሉ።
ይመር ንጋቱ እንደ ጀማሪ ሀሳቦቹንና ምናቡን ሳይ፣ ኩትኳቶ የሚያስፈልገው የወይን ዛፍ መስሎ ታይቶኛል።… አሰነኛኘቱ ቅሬታ ቢፈጥርብኝም፣ የወደድኳቸው በተኳለ ዐይን የታዩ ግጥሞች አሉት። እነርሱን በልኩ መዳሰስ እፈልጋለሁ።
ገጽ 20 ላይ “ሕይወት በፈረቃ” እንዲህ ይላል፡፡
ምንጊዜም ደንብ ነው
የዚህ ግጥም ስሪት ሕይወት በፈረቃ፣
ይመሻል ይነጋል
አንደኛው ሲያሸልብ ሌላው እንዲነቃ።
ግጥሙ ምሽትና ንጋትን፣ በሞትና በሕይወት መስሎታል… የትኛውም ፈላስፋ፣ የትኛውም አሳቢ፣ ሕይወት ሞት ሳያስደንቁት አያልፉም። ተረኝነት አለ። አንዱ ሲወለድ፣ ሌላው ይሞታል። ሰርግ ሲደገስ ለልቅሶ ድንኳን ይጣላል። አንዱ ሲተኛ አንዱ ይነቃል!
ይህ ግጥም ባህር ነው። እንደ ዳንቴል ቢተረተር፣ የማይፈታ አንድም ነገር እጅ ላይ አይቀርም! ግን አላማዬ  እርሱ  አይደለም። ብቻውን ገጾች ይፈልጋልና!
ገጽ 59 ላይ “የካድሬው ብሶት” ሊታዩ ከሚገባቸው ግጥሞች አንዱ ነው።
የማይበስል እንጀራ አበስላለሁ ብዬ፣
እንዴት እችላለሁ እኔ ተቃጥዬ!!
አሁን አሁንማ…
ቆስቋሽ አቀጣጣይ እጅግ ስለበዛ፣
ነድጄ ላልቅ ነው..
እንዲህ እንዲህ እንደዋዛ፣
ካድሬ እንጀራ እንጂ ሰው ለማብሰል ያን ያህል ይጨነቃል ብዬ ባላምንም፣ ያቀረበበትን መንገድ ግን ወድጄዋለሁ። ምናልባት ካድሬውን ተሰሚነት ያሳጡት የዘመናችን ቆስቋሾች፣ የካድሬው ድምጽ እንዳይሰማ አድርገውት ይሆናል። በዚህ የተነሳ “ማህበራዊ አንቂ” ነን የሚሉት ፈረንካ ለቃሚዎች፣ እንጀራዬ ብሎ የሚታገለውን ካድሬ በልጠውት ይሆናል! መቼም ጥቂት እውነተኛ ካድሬዎች አይጠፉም ብለን እናስባለን።
ገጣሚው ብዙ ቦታ የብርሃንና ጨለማን ተምሳሌትነት፣ በተለያዩ የብርሃን ምንጮች ያሳያል፤ ሻማን በመሳሰሉት።----ደግሞ ዘመኑን በፍርሃትና በጥርጣሬ፣ በእሾህ የታጠረ እልፍኝ አድርጎ ይስልልናል።… ዘመኑንና የዘመኑን ፍልስፍናና እምነት በፍርሃት ይቃኛል። ለምሳሌ ገጽ 72 ላይ  “ለተንኮሎ” በሚለው ግጥሙ እንዲህ  ያሽሟጥጣል! ወይም  ይተቻል!
በዚህ ዘመን ፣ በዚህ ጊዜ፣
ምን ይገርማል?
ተኩላ ቢሆን የባል ሚዜ።
ይህ ግጥም ስለ ሰርግ ነው  የሚያወራው። ሰርግ ደጋሹ በጉ ነው። ከበጉ አጠገብ ደግሞ ሚዜው ቆሟል። ሚዜው ግን የሙሽራው አጥፊ ነው። ከሰርጉ በኋላ የሰርጉ ድንኳን በልቅሶ ድንካን ሊተካ ነው። ለሰርጉ የተነጠፉት አበቦች፣ በደምና እንባ ሊጨቀዩ ነው።
እና በዚህ ዘመን እንደዚህ ቢሆን ምንም አዲስ ነገር የለም እያለን ነው። የዛሬ ዓመት በመከላከያ ሰራዊታችን የሰሜን ዕዝ ላይ የሆነው እንኳ ለዚህ ማሳያ ነው። ተበልቶ፣ ተጠጥቶ ምናልባትም ከበሮ ተደልቆ ምሽቱን መተራረድ ነበር። ይሁዳ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነበር፣ ራት በልቶ የእግዚአብሔር  በግ የተባለውን አስበልቶታል። ይህ መልክ ነው፤ አሁን በዘመናችን ነግሶ የታየው። ገጣሚው ያለውን አጥብቤ አልስፈርበትና ግጥሙ ብዙ በሮች ያንኳኳል። ሰፊ አድማስ ይነካል። ሩቅ ያየበትም ነው። ይሁንና አንባቢውን መውሰድ ብቻ ሳይሆን አንባቢው በየራሱ መም ይዟቸው ይሮጣል።
ፍሬድማንና አጋራቸው በጻፉት መጽሐፍ እንደሚሉት፤ “Poetry may be viewed in various ways and for various purposes, and consequently may call forth various modes of reading on the part of the reader.”  
ገጽ 102 ላይ የሰፈረችው መንቶ ግጥም ለዘመናችንም ለሰሞናችንም የሚሆን ቃና አላት። “አቀጣጣይ” ትላለች።
ቤንዚንና ናፍጣ እያርከፈከፉ፣
የሚጥሩም አሉ እሳቱን ሊያጠፉ።
እሳትና ውሃ ጠላት ስለሆኑ፣ ውሃ እሳትን ያጠፋል። እሳት እሳትነቱን ጨምሮ ያገኘውን ሁሉ እንዲበላ ደግሞ ቤንዚን ያግዘዋል። እና የዘመኑ ተጠቂዎች- “የዕብድ ገላጋይ” የሚባሉ ዓይነት ናቸው። አስታራቂ መስለው ያጣላሉ፣ ነገር አብራጅ መስለው ያጋግላሉ። አመዱን እፍ ብለው፣ የተጋገረ ፍም ከተኛበት ይቀሰቅሳሉ። እንዲህ አይነት ሰዎች እስክንጠግብ ብናይም በዚህ መልክ ሲገለጹ ግን ጎልተው ይወጣሉ።
“የሙዝ ልጣጭ” የዘመናችንን ሞራላዊ ውድቀት፣ መስፈሪያ የለሹን የሰብዕና ዝቅታ የሚተች “ማህበራዊ ሂሶችን” ያጨቀ ነው። መቼቱም በቅርቡ ያለንበትን የሕይወት  ቁመና የሚያሳይ ጥራዝ ነው። በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ርቃን የቆመውን የዝቅጠታችንን ሚዛን እያነበበ የሚነግረን ይመስለኛል፡፡
ገጽ 97 “ከሰወከው” በሚል ርዕስ ይህንኑ ያሳየናል።
ከዝሆኑ ይልቅ፣ ቁንጫ ገዘፈ፤
ኩበቱ ሰመጠ፣ ድንጋይ ተንሳፈፈ፣
በመርፌ ቀዳዳ፣ ግመልም አለፈ፣
ውሃ እንደቤንዚን በክብሪት ነደደ፣
ኮኮቡ ከሰማይ በወንጭፍ ወረደ፣
በሬ ያለግብሩ፣ አምጦ ወለደ፣
የዚህ መንደር ኗሪ፣ ውሸት የለመደ፣
እንደዚህ ይልሃል
ብለህ ሳትጠይቀው “ምን ምን ተካሄደ?”
አራተኛና አምስተኛ ስንኞች ላይ መጠነኛ ለውጥ አድርጌያለሁ፤ ከዋክብት የሚለውን “ኮኮብ”፣ ቤንዚን ይመስል የሚለውን "እንደቤንዚን"፡፡ ገጣሚው የአርትኦት ስራ በእጅጉ ያስፈልገው እንደነበር ከሚያሳዩት ቦታዎች አንዱ ይህ ነው።
ግጥሙ ከላይ እንደጠቀስኩት ዘመናችን በውሸት ያበደ ዓለም፣ በላይክ የሰከረ የዝና ጥማተኛ፣ ትርምስ የሚተች ነው። እኛም ታላሚዎቹ ናፍቆታችን ጥሬ እውነት ሳይሆን በውሸት የተቦካ፣ጣፋጭ ተረትና- በስሜት የጦዘ ትረካ ነውና! ስለዚህ ገጣሚው ከዚህ ባርነት፣ ነፃ  የሚያወጡንን ጥቆማዎች እያሳየ ነው፡፡
ገጣሚ አዲስ ነገር አያሳየንም፤ በአዲስ መንገድ ማየት እንጂ! ሎረንስ ፔሪኔም የሚሉት ይህንን ነው፡፡ የገጣሚው አንዱ ድንቅ ነገር በአዲስ ዓይን ማየት ነው፡፡…ግን ደግሞ ሁሉም አላባውያንና ባህርያት ጅረቶቹን አስተባብረው አንድ ጥሩ ሀይቅ፣ ቀለማማ ሕይወት መፍጠር አለባቸው፡፡ ኳሱን መሀል ሜዳ በቄንጥ ማንከባለል ብቻ ሳይሆን አንጀት የሚያረሰርስ ጎል ማግባት አለባቸው፡፡ ይሁንና ጎል ብቻ ቆጣሪ የጨዋታው ጥበብ ሳይገባው ሊያጨበጭብ ይችላል!...ቢሆንም ገጣሚው ውብ ጎል ያግባ!
ገፅ 78 ላይ “እንቆቅልሽ” የምትለውን ግጥም ገጣሚው በቅርብ ጊዜ መታገጊያ አስቀምጧታል፡፡…. እኔ ግን እንደ አንባቢ አጥር አስዘልዬ፣ አድማስ አስፍቼ ባያት እመርጣለሁ፡፡
ውሉ ባልታወቀ አምናና ዘንድሮ፣
ሰምና ወርቅ ገመድ ተቆላልፎ ታስሮ፣
አልፈታ ብሏል የቅኔው ቋጠሮ
ቀጣይ የአገሬ ዕጣ የሕዝቦቿ ኑሮ፡፡
ይህ ግጥም ያለንበትን “የለውጥ” ጊዜ ውስብስብ ችግር ብቻ አጥብቦ ያየ ይመስለኛል፡፡ ገደል አፋፍ ቆሞ፣ “ነጋ” የሚለው ጭው ያለና መስመር የለሽ ጉዞ ሆዱን ባር ባር ያሰኘው ያህል ይተነፍሳል። ነገሩ ሁሉ ቅኔ ፈች የሚያስፈልገው እንቆቅልሽ ነው እያለን ነው፡፡…..
ይሁን እንጂ ነገሩ በጥልቀት ሲጤን የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የጦርነትና የምጥ ሁሉ ልቀት (climax) ላይ የደረስንበትን ጊዜ ይመስላል፡፡ አለዚያ ታሪክን ወደ ኋላ ካየን በዘመናይቱ ኢትዮጵያ እንኳ፣ በቴዎድሮስ ሞት ቀን፣ በዮሐንስ ግራና ቀኝ ፍልሚያ ጊዜ፣ በንጉስ ኃይለስላሴ የማይጨው ጦርነት፣ በዘመነ ደርግ ሀገር በጠላት ተወርራ ብዙ ከተሞች በሶማሊያ ወረራ በወደቁበት፣ በወያኔ ዘመን ህዝብ በዘር ተከፋፍሎ እየተባላ አንድነቱ ተከርክሮ አጽቆቹ ሊበጠሱ በደረሱበት ሰዓት፤ ብዙ ተስፋቸው የሚሸሹ ገጠመኞች አሉን፡፡ ስለዚህ የብዙ ጊዜ ኑሮአችን አድርገን ብናሳልፈው የሚል እምነት አለኝ፤ ቢሆንም እንዲህ ማሰቡም፣ እንዲህ ማቅረቡም ጥሩ ነው፡፡
መሻሻል ያለባቸውን ነገሮች ቆም ብሎ ማጤንና ራስን ማብቃት ለነገው ስራ ጠቃሚ ነው፡፡ መጽሐፉ ውስጥ ሊካተቱ  የማይገባቸው ደካማና ተመሳሳይ ጭብጥ ያላቸው ግጥሞችን ማስቀረት ያስፈልግ ነበር፡፡ ለምሳሌ ገጽ 58 ላይ “ብሶት አደባባይ” የሚለው ዓይነት ግጥም በየትኛውም መመዘኛ ለአደባባይ መቅረብ አልነበረበትም፡፡
ሌሎች መነሻዬ ላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች በንባብ ሊቃኑ ይችላሉ፡፡ አንጓዊ መዋቅሮች፣ ቤት መምቻ ፈዛዛ አናባቢዎችን መቀነስ፣ ከፊል አናባቢዎች በቤት መምቻ ላይ በብዛት ያለመጠቀምና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለማንኛውም በተጣበበ ጊዜ ዳሰሳ እንድሠራበት ያስገደደኝ የገጣሚው ጠንካራ ጎን ነውና፣ ፅጌረዳየን ከእነ እሾህዋ ወድጃታለሁ፡፡


Read 1135 times