Monday, 08 November 2021 00:00

አለማቀፉ የምግብ ዋጋ በ10 አመታት ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የምግብ ዋጋ በአለማቀፍ ደረጃ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ወራት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና በጥቅምት ወር ላይም ባለፉት አስር አመታት ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የተመድ የምግብና የእርሻ ድርጅት ባለፈው ሐሙስ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ የጥቅምት ወር አለማቀፍ የምግብ ዋጋ እ.ኤ.አ ከ2011 ሃምሌ ወር ወዲህ ከፍተኛው ሲሆን፣ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋቸው ከጨመረ የምግብ እህሎች መካከል ጥራጥሬዎችና የአትክልት ዘይቶች ይገኙበታል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥና ድርቅ በአመቱ በአለም ዙሪያ የምግብ ሰብል ምርት እንዲቀንስ ምክንያት መሆናቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፣ የምግብ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ አምራቾች ወደ ሌሎች አገራት የሚልኩትን ምርት መቀነሳቸው፣ የጭነት ትራንስፖርት ዋጋ መናርና የሰው ሃይል እጥረትም የምግብ ሰንሰለቱን ክፉኛ እንደጎዳውም አመልክቷል።
ተቀማጭነቱ በሮም የሆነው የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት የ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን የጥራጥሬ እህሎች አጠቃላይ ምርት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጨምሮ 2.8 ቢሊዮን ቶን ያህል ይደርሳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ምርቱ ግን ከፍላጎቱ ጋር የማይመጣጠን ነው ብሏል፡፡


Read 1068 times