Monday, 08 November 2021 00:00

በ1 ወር 845 ሚ. ዶላር ያገኘው የቻይና ፊልም በገቢ ይመራል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ኤልተን ጆን በኮሮና ዝግ የሰራው አልበም 1ኛ ደረጃን መያዙ ተነገረ



             “ባትል አት ሌክ ቻንጂን” የተሰኘው ቻይና ሰራሽ የጦርነት ፊልም በፈረንጆች አመት 2021 በአለማችን ለእይታ ከበቁ ፊልሞች መካከል ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት በ1ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡንና ፊልሙ፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 845 ሚሊዮን ዶላር ማስገባቱን ሉፐር ድረገጽ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1950 የቻይና ጦር ሰራዊት ከአሜሪካ መራሹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጦር ጋር በኮርያ ያደረገውን ጦርነት መነሻ አድርጎ የተሰራውና መስከረም 30 ቀን ለእይታ የበቃው ፊልሙ፣ በ29 ቀናት ውስጥ ብቻ ባገኘው 845 ሚሊዮን ዶላር በቦክስ ኦፊስ 1ኛ ደረጃን መያዙ ነው የተነገረው፡፡
ሶስት ዳይሬክተሮች በጥምረት የሰሩትና በቻይንኛ ቋንቋ የተዘጋጀው ፊልሙ፣ የአገር ፍቅርንና ጀግንነትን ያበረታታል በሚል በቻይና የመንግስት ሰራተኞች ሁሉ እንዲያዩት አስገዳጅ መመሪያ መውጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ፊልሙ የ3 ሰዓት እርዝማኔ እንዳለውም አመልክቷል፡፡
በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው ሌላኛው ቻይና ሰራሽ ኮሜዲ ፊልም #ሃይ ማም; በበኩሉ፤ በ3 ወራት ጊዜ 821 ሚሊዮን ዶላር ቢያስገባም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
በሌላ የመዝናኛው ዘርፍ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሰር ኤልተን ጆን በዘመነ ኮሮና የእንቅስቃሴ ገደብ ወቅት አዘጋጅቶ ለአድማጭ ያቀረበው #ዘ ሎክዳውን ሴሽንስ; የተሰኘ የሙዚቃ አልበሙ በአገረ እንግሊዝ በሙዚቃ ሰንጠረዥ የ1ኛ ደረጃን መያዙን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ74 አመቱ እንግሊዛዊ አቀንቃኝ በአገሪቱ የሙዚቃ አልበም ሽያጭ ታሪክ 1ኛ ደረጃን ሲይዝ ይህ ስምንተኛ ጊዜው እንደሆነ ያስታወሰው ዘገባው፣ ድምጻዊው ከዚህ ቀደም የ1ኛ ደረጃን ከያዘባቸው ተወዳጅ የሙዚቃ አልበሞቹ መካከልም ጉድ ባይ የሎው ብሪክ ሮድ (1973)፣ ካሪቡ (1974)፣ ስሊፒንግ ዊዝ ስፓትስ (1989) እና ጉድ ሞርኒንግ ቱ ዘ ናይት (2012) ይገኙበታል፡፡
ሌላዋ እንግሊዛዊት የሙዚቃ ኮከብ አዴል በቅርቡ የለቀቀቺው ኢዚ ኦን ሚ የተሰኘ ነጠላ ዜማ በበኩሉ፣ ባለፈው ሳምንት በቢልቦርድ ምርጥ 100 ነጠላ ዜማዎች ዝርዝር ውስጥ በ1ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡንና በሳምንቱ በአሜሪካ ብቻ ከ54 ሚሊዮን ጊዜያት በላይ በድረገጽ መደመጡን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በሙዚቃ ስራዎቿ የበርካታ አለማቀፍ ሽልማቶች ባለቤት መሆን የቻለቺው ተወዳጇ ድምጻዊት አዴል፣ ከ6 አመታት በላይ በጉጉት ስትጠበቅ ቆይታ ከሰሞኑ የለቀቀቺው ይህ ዜማ፤ ከ74 ሺህ ጊዜ በላይ ዳውንሎድ የተደረገ ሲሆን፣ በሬዲዮም ከ19 ሺህ ጊዜያት በላይ መደመጡንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2870 times