Monday, 08 November 2021 00:00

ዐቢይ አገሬን አለ፤ ምዕራቡ ዓለም አሻንጉሊቴን

Written by  ማርቆስ ረታ
Rate this item
(0 votes)

ታስታውሱ እንደሆን በእነ ዶ/ር ዐቢይ የሚመራው የለውጥ ኃይል ስልጣን ላይ እንደወጣ አንድ የአሜሪካ ሴናተር ያስተላለፉት መልዕክት፤  “Game over, TPLF” የሚል ነበር። እንደተባለውም ጨዋታው አልቆ ነበር። በአንጻሩ የምዕራቡ ዓለም ድጋፍ ከአዲሱ አመራር ጋር በተለይም ከዶ/ር ዐቢይ ጋር ነበር ለማለት ይቻላል። አልፎ ተርፎ የኖቤል የሰላም ሽልማትም ማግኘታቸው ይታወቃል።
ያም ሁሉ ሆኖ ዛሬ አውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ የሕወሐት ደጋፊ ሆነው  ጠ/ሚር ዐቢይን ለመወንጀል ውሸት ፈብራኪ ዘጋቢዎቻቸውን አሰማርተዋል። በሕወሓት ቀስቃሽነት በተነሳው ጦርነትም ዶ/ር ዐቢይ የሚመሩት የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲያጠቃ “ተዉ” ሲሉ፥ ሲጠቃ "ተደራደሩ" ይላሉ። ግን ለምን? አሰላለፋቸውን ለምን ቀየሩ?
ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል። አንዱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በባይደን መቀየሩ ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ትራምፕ አንድ የአገር መሪ ቅድሚያ ለዜጋው መስጠት እንደሚገባው የሚያምኑና የሚሰብኩም ነበሩ። ስለ አፍሪካ ጸያፍ መናገራቸው፥ በግድባችን ላይም በእብሪት መደንፋታቸው ቢታወቅም «ቅድሚያ ለራስ አገር የሚለውና “አሜሪካ ትቅደም” በሚለው መፈክር የተገለጸው አቋማቸው ፍትሐዊ ነበር ለማለት ይቻላል።
ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያት ግን ሕወሓት ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ይዘውት የነበረው የአገራችንን የፖሊሲ አስተዳደር የመዘወር አቅም ጠ/ሚር ዐቢይ ለአገራቸው ሉዐላዊነትና ለሕዝቧ ጥቅም ለመቆም በመወሰናቸው ምክንያት የተወሰደባቸው መሆኑ ነው።
ሕወሓትን “ጨዋታ ፈረሰ” ባሉበት ጊዜ ዶ/ር ዐቢይን እጃቸው ያስገቡ መስሏቸው ነበር መሰል። ሆኖም ውሎ ሲያድር ሰውየው አገር ወዳድ አርበኛ መሆናቸው ለሁሉም ግልጽ ሆነ። ምዕራባውያኑ አዲስ አሻንጉሊት አገኘን ሲሉ መሸወዳቸው ቆይቶ ገባቸው። ስለሆነም “ጨዋታ ፈረሰ” ብለው የጣሉት አሮጌው አሻንጉሊታቸው ናፈቃቸው። ሕወሓትን ከጣሉበት ለማንሳትና ነፍስ ለመዝራት የማይገባ ድጋፍ ሲሰጡ የምናየው ጠ/ሚር ዐቢይ አሻንጉሊት አልሆንም በማለታቸው ምክንያት ነው። ዛሬ የጦርነት መልክ ይዞ የመጣውና “ተደራደሩ” በሚለው የምዕራባውያኑ ጉትጎታ ታጅቦ የሚታየው ሕወሓትን የመደገፍና ዐቢይን የመንቀፍ ጥረትም የናፍቆታቸው መገለጫ ነው።  
ያገር ልጅ ከዚህ የምትገነዘበው አንድ ታላቅ ቁም ነገር አለ፤ ይኸውም ባለፉት መቶ ዓመታት ኢትዮጵያ አገርኽ ለነጻነቷና ላልተሸራረፈ ሉዐላዊነቷ መረጋገጥ በቁርጠኝነትና በጥበብ የሚሠራላት መሪ ስታገኝ ገና አሁን የመጀመሪያዋ መሆኑ ነው። ዛሬ ጠ/ሚር ዐቢይ ለኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና ሁለንተናዊ ነጻነት መረጋገጥ ቁልፍ የሆነውን የፖሊሲ አስተዳደር ስልጣን ከምዕራባውያን አድራጊ ፈጣሪዎቹ እጅ አውጥተው እጃቸው አግብተዋል። ትልቅ ድል ነው። ካሁን ቀደም እንኳን ሊደረግ ተተሞክሮም አያውቅ[ምናልባት በደርግ ጊዜ፥ ያውም በከፊል ካልሆነ በቀር]።
የፖሊሲ አስተድደር ነጻነት ከሌለ ሉዐላዊነት የለም፥ ላገር ችግር መፍትሔ የሚሆን አገር በቀል ዕቅድ ነድፎ መተግበር አይቻልም። አዛዡ ሌላ ነዋ። ኢህአዴግ ሃያ ሰባት ዓመታት በስልጣን ላይ ሲቆይ በምዕራባውያን አገሮችና የገንዘብ ተቋሞች ከሚሰጡት ትዕዛዞች አንድ ሁሉቱን ብቻ አልቀበል ከማለት (ባንክና ቴሌን አልሸጥም ከማለት) ውጭ በገዛ አገሩ ፖሊሲ አስተዳደር ላይ መብት ያልነበረው በመሆኑ ዕድሜ ልኩን ጥሩ ፖሊሲ እንዳለውና ችግሩ ያፈጻጸም መሆኑን ለማሳመን ሲጣጣር መኖሩ ይታወቃል። ሆኖም የፖሊሲው እውነተኛ ባለቤቶች ምዕራባውያኑ በመሆናቸው የአገራችንን እውነተኛ ችግር የሚፈታ ፖሊሲ ነድፎና በጀት መድቦ ሳይተገብር እንዲሁ በስልጣን ላይ ኖሮ ለማለፍ ተገዷል።
በአንጻሩ ዶ/ር ዐቢይ መንግሥታቸውን ከባዕዳን ትዕዛዝ፥ ራሳቸውንም ከአሻንጉሊትነት ነጻ በማድረግ ኢትዮጵያን ከስውር ባርነትና የእጃዙር የቅኝ አገዛዝ ለማላቀቅ ቆርጠው በመነሳት በፈጸሙት ታላቅ ገድል ምክንያት የባዕዳኑ ፈላጭ ቆራጭነት አብቅቷል።
በእነ ዶ/ር ዐቢይ በሚመራው የለውጥ ኃይል አስቀድሞ ከስልጣን የተሻረው ህወሓት ቢሆንም፣ የምዕራባውያኑም አድራጊ ፈጣሪነት አብሮ ተሽሯል። ስለሆነም እነሆ ዛሬ ሕዋሃትና ምዕራባውያኑ አንድ ዓላማ አንግበው፥ አንድ ዓይነት ስልት በመጠቀም ያጡትን ለማስመለስ እየታገሉ ነው። ዓላማው ስልጣን ሲሆን ስልቱ ደግሞ የትግራይና አጎራባች ክልሎችን ሕዝብ በርስ በርስ ጦርነት በመማገድና ዶ/ር ዐቢይን ባልዋሉበት በመክሰስ፥ ለኢትዮጵያውያን ጥቅም ቁርጠኛ አቋም የያዘውን የመሪ አርበኛ” የገዛ ወገኖቹን በብሔር ለይቶ የሚያጠቃ አረመኔ” አስመስሎ በማቅረብ፣ ስሙንና ክብሩን ማጉደፍና በዚያውም የሚቻለውን ያክል የድርድር ዓቅም ለማግኘት ነው።
ስለሆነም ዛሬ በዶ/ር ዐቢይ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ሁሉ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነጻነት ላይ የተሰነዘረ መሆኑን በጥንቃቄ ማስተዋል ያስፈልጋል።
በውሸት ወሬ ሕዝቡን ከእውነተኛ መሪው ጋር ለማጋጨት፥ ጥርጣሬ ለመዝራት፥ ስጋት ለማጫር የማይሽርቡት ተንኮል፥ የማይቀምሩት ተረክ፥ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደማይኖር እስከዛሬ ከታየ ከተሰማው ለመገንዘብ ይቻላል። ይሁንና እኛ ለመሞኘት ካልፈቀድን በቀር ጥረታቸው ሁሉ ከንቱ እንደሚቀር ጥርጥር የለውም። «አንድ እንሁን፤ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ” ሲባልም ዓላማና ግቡ ያው ነው፤ አለመሞኘት፤ ለጠላት አለመመቸት፤ ለመሠሪ ሰበካ ጆሮ አለመስጠት። ኢትዮጵያ ሰው ማግኘቷን በማስተዋል ተመስገን ማለት። ለአገር ነጻነት ቆርጦ የተነሳው የመሪ አርበኛና ላነገበው ኢትዮጵያዊ ዓላማ “እንሆኝ» ማለት። ደቀቅ ስናደርገው ደግሞ በተለይ ምዕራባውያን ኤምባሲዎችና ሚዲያዎቻቸው በሚያሰራጩት ወሬና፥ “የኢትዮጵያ የደኅንነት ሁኔታ አስጊ ሆኗል” ከሚል አሸባሪ መንደርደር በመነሳት ለዜጎቻቸው በሚያወጡት ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ አለመሸበር። የኢትዮጵያ አምላክ የጀመረውን የኢትዮጵያ ትንሣኤ ጉዞ ዳር ሳያደርሰው እንደማይቀር ያለ ጥርጥር ማመን. . . ደግሞም ከአዲሱ የቴዲ አፍሮ ዜማ ጋር አብሮ “ቀን አለ ገና፤ ቀና በል አሁን” ማለት፤ ”የኢትዮጵያዊነት አሁን ነው  ተራው “. . . ማለት!

Read 3099 times