Tuesday, 09 November 2021 00:00

“የዘር ማጥፋት አልተፈጸመም፤ ረሃብ ለጦርነት አላማ አልዋለም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በትግራይ ከጥቅምት 2013 እስከ ሰኔ 2013 የተፈጸሙ የሰብአዊ  መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የጋራ ምርመራ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ፤ በወቅቱ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ሃይሎች መጠኑ የተለያየ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን አመልክተዋል።
ተቋማቱ ለሳምንታት ሲያካሂዱ የነበረውን ምርመራ በ156 ገጽ ሪፖርት ያጠናቀሩ ሲሆን በአጠቃላይ የምርaመራ ግኝቱ፤ የሕውኃት ሃይሎች፣ ኢትዮጵያ መከላከያ፣ የአማራ ልዩ ሃይል እና የኤርትራ ወታደሮች ሁሉም በተለያየ የድርሻ መጠን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸው ተረጋግጧል።
የተፈጸሙት የሰብአዊ  መብት ጥሰቶችም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና የህውሃት የፕሮፓጋንዳ መንገዶች እንደሚነገረው፣ የዘር ማጥፋት ሳይሆን አለማቀፍ የስደተኞች መብት ጥሰቶችን ጨምሮ እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ ጥሰቶች መፈጸማቸው ነው የተረጋገጠው።
በዚህ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ከህግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች፣ የንፁሃንን ንብረት መዝረፍ ማውደምና ማጥቃት፣ ህገ-ወጥ የሆነ እስር፣ ማሰቃየትና እገታ፣እንዲሁም ጾታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውም በሪፖርቱ ተረጋግጧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ በህወኃትና በአለማቀፉ ማህበረሰብ የሚወነጀልባቸው የዘር ማጥፋትን ጨምሮ ጾታዊ ጥቃትና ረሃብን ለጦርነት አላማ መጠቀም የመሳሰሉ ክሶች በዚህ ሪፖርት እንዳልተፈጸሙ ተመላክቷል።
የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት በአንጻሩ፣ የኤርትራውያን ስደተኞችን ንብረት ከመዝረፍ ጀምሮ በምርኮ የያዟቸውን የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ብሔርን መሰረት ባደረገ መልኩ ጥቃት መፈፀማቸው በሪፖርቱ ተካትቷል።
የምርመራው አድማስ
ተቋማቱ በዚህ ምርመራቸው ከጥቅምት 24 ቀን 2013 እስከ ሰኔ 21 ቀን 2013 የተፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ያጣሩ ሲሆን ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ለሚኖሩ 269 እማኞች ቃለ-ምልልስ ተደርጓል፤ 64 ያህል ውይይቶች ከክልልና ፌደራል የመንግስት አካላት ጋር ተካሂደዋል።
የተለያዩ የምርመራ ቡድኖች በመቀሌ፣ ውቅሮ፣ ሳምረ፣ አላማጣ፣ ጦራ፣ ማይጨው፣ ዳንሻ፣ ማይካድራና ሁመራ መጠነ ሰፊ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን በአዲአሮ፣ አዲግራት፣  አዲሃገራይ፣ አደዋ፣ ባድመ፣ ደንጎላት፣ ሁመራ ኮረምን ጨምሮ በ16 የተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችም የምርመራው አካል ሆነዋል። ምርመራው በአዲስ አበባ፣ ጎንደርና ባህር ዳርም መካሄዱን ነው የሪፖርት ሰነዱ የሚያመለክተው።
የምርመራው ግኝቶች
ጥቅምት 24 ቀን 2013 የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ በትግራይ በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን፣ በዚህ ጥቃት የወታደራዊ ካምፖችንና የጦር መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር መሞከራቸው በምርመራው ተረጋግጧል።
በበነጋው ጥቅምት 25 ቀን 2013 የፌደራል መንግስት ጥቃቱን ለመቀልበስ የፀረ ማጥቃት እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ በዚህ የጸረ ማጥቃት እንቅስቃሴ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም የኤርትራ  ሰራዊት መሳተፉቸውን ሪፖርቱ ያትታል።
የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ ሰራዊትና የትግራይ ልዩ ሃይል በጦርነቱ ወቅት በንፁሃን ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን፤ በዚህ ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን ህፃናትና ሴቶች እንዲሁም አዛውንቶች መቁሰላቸውን፣ መፈናቀላቸውን፣ የንፁሃን ዜጎች ንብረት መውደሙን፣ የመንግስትና የህዝብ ተቋማትና በተለይም የጤና ተቋማት፣ ት/ቤቶች በተፋላሚ ሃይሎቹ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው የምርመራ ሪፖርቱ አረጋግጧል።
ሁሉም ተፋላሚ ሃይሎች የሲቪል ተቋማት የሆኑ እንደ ት/ቤቶችና የጤና ተቋማትን እንደ ምሽግ መጠቀማቸውን፣ በዚህም በርካታ ውድመት መከሰቱን አመልክቷል- ሪፖርቱ።
የሲቪል ተቋማትን ምሽግ ባደረገው የጦርነቱ ተሳታፊዎች እንቅስቃሴ የተነሳም ከመከላከያ ሰራዊት በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ 29 ንፁሃን በመቀሌ ከተማ መገደላቸውን፤ በሁመራ ከተማ ደግሞ ከኤርትራ መከላከያ ሰራዊትና ከትግራይ ልዩ ሃይል በተተኮሱ --አረሮች 15 ንጹሃን መገደላቸውን ይጠቁማል-ሪፖርቱ።
ህገ-ወጥ የንጹሃን ግድያን በተመለከተም መከላከያ፣ የኤርትራ ሰራዊት፣ ፋኖ እና የአማራ ሚሊሻ፣እንዲሁም የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ሳምሪ የተሰኘው ቡድን በተለያየ መጠን ድርጊቱን መፈጸማቸውን ሪፖርቱ አረጋግጧል።
በዚህ ንፁሃንን ሆን ብሎ ኢላማ ባደረገው ጥቃት፤ በማይካድራ 2መቶ ያህል የአማራ ተወላጆች በሳምሪ ቡድን ሲገደሉ፣ ለዚህ በተሰጠ የበቀል ምላሽ 5 የትግይ ብሔር አባላት በፋኖ መገደላቸው ተመልክቷል። በአክሱም ከተማ ደግሞ ከ100 በላይ ሰዎች በኤርትራ  መከላከያ ሰራዊት መገደላቸውን፣ 70 ያህል ሰዎች ደግሞ በቦራ፣ አምደውሃ፣ ቦራ ጨመላ እና ማይሊሃም በተባሉ ቦታዎች በመከላከያ ሰራዊት በተወሰዱ እርምጃዎች መገደላቸውንም ሪፖርቱ የጠቆመው።
ከግድያዎች ባሻገር በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም በመከላከያ ሃይል የተፈጸሙ የዜጎች ህገ-ወጥ እስር፣ እንግልትና ስቃዮችም እንዳሉ በ156 ገጽ በተጠናቀረው ሪፖርት ተመላክቷል። ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተም ሁሉም የጦርነቱ ተፋላሚ ሃይሎች የድርጊቱ ተሳታፊ እንደነበሩ ነው ሪፖርቱ ያተተው።
በዚህ የጦርነት ወቅት 20 አለማቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞች ህይወት ማለፉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ አድርጓል፤ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል የሚሉ ውንጀላዎች መሰረተ-ቢስ መሆናቸው መረጋገጡን  አመላክቷል።
በወቅቱ የተፈጸሙ ጥቃቶች በሰፊው ሲነገር እንደነበረው የዘር ማጥፋት ባህሪ የሌላቸው መሆኑን ያመላከተው ሪፖርቱ፤ አሁንም ከቀጠለው የሰብአዊ ቀውስ ለመውጣት ሁሉም ተፋላሚዎች ንፁሃንን ኢላማ ካደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ ተቋማቱ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
በዚህ ጥቃት የተሳተፉ ሁሉ ተጣርተው ለህግ መቅረብ እንዳለባቸውም ተቋማቱ በሪፖርታቸው ማጠቃለያ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል። በዚህ የምርመራ ሪፖርት ላይ መንግስታቸው ቅሬታ እንዳለው የገለጹት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ መንግስት ሪፖርቱን ተጎጂዎችን ለመርዳት፣ ተጠያቂነትን ለማስፈንና ጥቃትን ለመከላከል ለሚደረጉ ቀጣይ ጥረቶች እንደ ግብአት ይጠቀምበታል ብለዋል።
“በግጭቱ ወቅት ሰብአዊ ክብራቸው የተነካ ሰዎችን ምስክርነት መስማት እጅጉን ልብ ሰባሪ ነው ያሉት” ጠ/ሚኒስትሩ፤  “በዚያው ልክ መንግስት ሲወነጀልባቸው የነበሩ የዘር ማጥፋት ድርጊት፣ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምና ለንፁሃን የሰብአዊ እርዳታን እንዳይደርስ አድርጓል” የሚለው መሰረተ-ቢስ ውንጀላ እንደነበር መረጋገጡ መልካም እንደሆነ አስታውቀዋል።Read 7705 times