Sunday, 07 November 2021 18:50

“ዓይናችሁን ህዝባችሁና ሀገራችሁ ላይ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡— ምስኪኑ ሀበሻ እንዴት ነህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ደህና አይደለሁም አንድዬ! ደህና አይደለሁም!
አንድዬ፡— ረጋ በል፣ ግዴለህም ረጋ በል።
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! እንዴት አድርጌ ነው ረጋ የምለው! ያለንበትን ሁኔታ እያየኸው፣ እያወቅኸው እንዴት አድርጌ ነው ረጋ የምለው!
አንድዬ፡— እኮ፣ ረጋ ካላልክ የምትለውን እንዴት ነው የምሰማህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን አድርገንህ ነው ይህን ያህል መከራ የምታበዛብን! በየትኛው ሀጢአታችን ነው ይህ ሁሉ መአት! ለአንተ ከመጸለይ በስተቀር፣ አንተን ከመማጸን በስተቀር፣ አንተን ከመለመን በስተቀር ምን አድርገንህ ነው?
አንድዬ፡— ቆይ እንጂ፣ እኮ እሺ ተረጋጋና ትወቅሰኛለህ፡፡
(ዝምታ)
ምስኪን ሀበሻ፡— ምነው አንድዬ ሰለቸንህ እንዴ!
አንድዬ፡— መች አልኩኝ! መች ሰለቻችሁኝ አልኩህ! ለነገሩ ዛሬ በጣም ተቆጥተህ ስለመጣህ ምንም ብትለኝ አይከፋኝም!
ምስኪን ሀበሻ፡— ታዲያ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስብን፣ ይህ ሁሉ ክህደት ሲፈጸምብን፣ ዝም ብለህ የምታየን ምን እስከምንሆን ነው! አልበዛም ወይ አንድዬ፣ አልበዛም ወይ!
አንድዬ፡— እኔን እኮ ግራ አጋባኸኝ! ግራ አጋባችሁኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንዴት ነው ግራ የምናጋባህ! ይኸው በተቻለው መንገድ ሁሉ “በቃችሁ በለን! የእስከዛሬው ይበቃናል፣ ምህረቱን ላክልን!” እያለ ስንት ሚሊዮን ህዝብ እየተለማመንህ አስችሎህ ነው ዝም ያልከው፤ የራሳቸው ጉዳይ ብለህ ነው እንጂ እንደ ወትሮውማ ቢሆን ቢያንስ አይዟችሁ እያልክ ታናጽናን፣ ተስፋ ትሆነን ነበር!
አንድዬ፡— ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እኔን መውቀሱን ለጊዜው እናቆየው፡፡ ግዴለህም ከፈለግህ ሙሉ ቀን እንወቃቀሳለን፡፡ ስለ አሁኑ ብናወራ አይሻልም?
ምስኪን ሀበሻ፡— እ...እሺ አንድዬ፣ እሺ፡፡
አንድዬ፡— መጀመሪያ ነገር ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ቁጣ ለማንም አይበጅም። የተቆጣ ሰው በብልሀት ሳይሆን በስሜት ነው የሚመራው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እየተሠራብን ያለው እኮ ከማስቆጣትም በላይ ነው፡፡
አንድዬ፡— ይገባኛል፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ይገባኛል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እስቲ ከስንትና ስንት ዘመን መከራና ስቃይ በኋላ ትንሽ እፎይ ልንል ነው ስንል፣ እሰየው ተረጋግተን ሀገራችንና ህዝቧን ከድህነት ለማውጣት እድሉን ልናገኝ ነው ስንል፣ ገና ቀበቷችንን በቅጡ ሳንታጠቅ ከማዶ ያሰፈሰፈውም፣ በየምናምኑ ያደፈጠውም፣ እንደ ምስጥ አፈር ውስጥ ራሱን ቀብሮ የኖረውም እየተጠራራ እኛ ላይ ሲረባረብ ያልተቆጣን በምን እንቆጣ፡፡
አንድዬ፡— ይገባኛል አልኩ እኮ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አሁንስ በጣም ተዳፈርከኝ አትበለኝና ይህ ሁሉ መከራችን እየገባህ ዝም ብለህ የምታየን ለምንድነው!
አንድዬ፡— ምስኪኑ ሀበሻ፣ ቅድም ስነግርህ ነገሬ ብለህ አልሰማኸኝም መሰለኝ።
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ፣ እንደዛሬ ነቅቼ ሰምቼህም አላውቅም፡፡
አንድዬ፡— ጥሩ፣ እንግዲያው ምን መሰለህ...
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምነው ጀመርክና ዝም አልከኝ?
አንድዬ፡— ዝም አላልኩህም፣ እንዴት ልንገርህ እያልኩ ነው፡፡ ስማኝ፣ እኔ አሁን ትልቁ ችግር የሆነብኝ ምን መሰለህ?! እናንተን መለየቱ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አልገባኝም አንድዬ!
አንድዬ፡— እየው ሁላችሁም ላይ ላዩን ሳያችሁ ትመሳሰሉብኛላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እዚህ ላይ እቃወማለሁ፡፡
አንድዬ፡— ተቃወመኝ...
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ በሌላ እንዳትወስድብኝ፡፡ አንተን ሳይሆን ያልከውን ነው የምቃወመው፡፡
አንድዬ፡— አየህ አይደል፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ አየህ አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑን አንድዬ?
አንድዬ፡— አንድም እያስጠቃችሁ ያለው ይህ ባህሪያችሁ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— የትኛው ባህሪያችን፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— ይሄ...ምን ነበር ራሳችሁ የምትሉት... አዎ፣ ከዻዻሱ በላይ ቅዱስ ለመሆን መሞከር፡፡ ግራ አጋባሁህ እንዴ ምሰኪኑ ሀበሻ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አትታዘበኝና አዎ...
አንድዬ፡— አየህ ደገምከው! ልልህ የፈለግሁትን ደገምከው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አን..አንድዬ...
አንድዬ፡— ላስረዳህ... መናገር ያለባችሁን፣ የምታምኑትን፣ በልባችሁ ውስጥ ያለውን ፊት ለፊት እንደመናገር ራሳችሁን ቅዱስ ለማሰመሰል ነው መሰለኝ ዙሪያውን ትሽከራከራላችሁ፡፡ “እቃወማለሁ” አልክ፣ “ተቃወመኝ፣” ስልህ አንተን አይደለም ምናምን እያልክ ዙሪያ ጥምጥም ትዞራለህ። በቃ ኮስተር ብለህ እቃወምሀለሁ ብትል ምን ትሆናለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንዳላስቀይምሀ ፈርቼ ነው፣ አንድዬ!
አንድዬ፡— አየህ አይደል ምስኪኑ ሀበሻ! እኔን ላለማስቀየም ፈርተህ ማለት የፈለግኸውን ነገር ሳትናገር አልኮስኩሰህ ልታልፈው ነው ማለት ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ...
አንድዬ፡— ቆይ አስጨርሰኝማ...ደገምኩና “ግራ አጋባሁህ ወይ፣” ስልህ “አዎ ግራ አጋባኸኝ፣ መለየት አቃተኝ፣”  ብትለኝ ምን ትሆናለህ? አንተ ግን “አትታዘበኝና...” ምናምን አልክ፡፡ እዚህ ውስጥ ትዝብት ምን አመጣው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እ...እሱን ነገር በዚህ መልኩ አስቤበት አላውቅም፡፡
አንድዬ፡— አንተ ብቻ ሳትሆን አብዛኞቻችሁ ጠንከር ብላችሁ ማለት የሚገባችሁን እንደማለት በማያስፈልግበት ቦታ እየተለሳለሳችሁ ነው እንደ ድክመት እየተቆጠረባችሁ ያለው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እውነት ነው፣ አንድዬ። እውነት ነው፡፡  
አንድዬ፡— አሁን ወደተነሳንበት እንመለስና ሁላችሁም ትመሰሳሉብኛላችሁ ስልህ እቃወማለሁ አልክ፡፡ እሺ፣ ለምንድነው የምትቃወመው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ትመሳሰሉብኛላችሁ ላልከው ነው፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— እኮ ንገረኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ክህደት እየተፈጸመብን ያለነው እኛ! ባጎረስን እየተነከስን ያለነው እኛ! ከሌሎቹ ጋር እንዴት ነው አንድ የምንመስልህ?
አንድዬ፡— ሌሎቹ የትኞቹ ናቸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ክህደት ፈጻሚዎቹ ናቸዋ፡፡ አብረን በልተን፣ ጠጥተን ለሆዳቸው ሲሉ ወንድም እህቶቻቸው ላይ ሸፍጥ የሚፈጽሙትን ነዋ!
አንድዬ፡— እኮ እሱን አይደለም እኔስ የምልህ! ማናችሁ በየትኛው ወገን እንደሆናችሁ እንዴት ልለያችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— በድርጊታችን ነዋ፣ አንድዬ፣ በድርጊታችን ነዋ!
አንድዬ፡— ጎሽ አሁን መጣህልኝ፡፡ ዋነኛው ችግሬ እኮ ይኸው ነው፡፡ ሁላችሁም እኔ ቤት ጋቢያችሁን አጣፍታችሁ፣ ነጠላችሁን ጣል አድርጋችሁ ስትመላለሱ ነው የማየው፡፡ ጠዋት ማታ የጸሎት መጽሀፋችሁን አንስታችሁ ስትጸልዩ ነው የማየው፡፡ በእኔ ስም ስትምሉና ስትገዘቱ ነው የምሰማው! ጉድ የሚመጣው በኋላ፡፡ እኔ የስንታችሁን ሆድ ልወቅ! ንገረኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እሱስ ልክ ነህ፡፡
አንድዬ፡— ብቻ ነገር አናብዛና፣ አሁን ያላችሁበት አስቸጋሪ ሁኔታ ይገባኛል፡፡ አንድ ልታውቁት የሚገባ ነገር አለ...ይህ ሁሉ የመጣው ምድር ላይ ባሉ እንጂ የእኔ እጅ የለበትም፡፡ እኔ ከዓለም ህዝብ ለይቼ እዚህ ምስኪን ህዝብ ላይ መአት የማወርድበት ምክንያት የለኝም፡፡ የሀጢያችን ብዛት ነው የምትሉትን ነገር ተዉኝ!  
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደሱ ስትል ልቤን አረጋጋህልኝ፡፡
አንድዬ፡— ዋናው ነገር ወደ ውስጣችሁ ተመልከቱ፡፡ እኔም ዓይኔን ከእናንተ ላይ አላነሳም፡፡ እናንተም ዓይናችሁን ከምስኪኑ ህዝብና ከሀገራችሁ ላይ አታንሱ! በል ደህና ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን  አንድዬ፣  አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1592 times