Tuesday, 09 November 2021 00:00

የክብሩ እና የውርደቱ ሁሉ መነሻ፣…. “ቃል” ነው። ወይስ “ፍቅር” እና “ተግባር”?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


                 ፍቅር ሁሉም ነገር ነው ትላለች - ድምፃዊቷ ሳራ ብራይትማን። በሌላ ዘፈኗ ደግሞ፣ “ፍቅር ሁሉን ይለውጣል” እያለች ታዜማለች። ሃያልነቱን በማድነቅና በማወደስ ብቻ አይደለም። ዘፈኗ፣ የስጋትና የፍርሃት ስሜትንም ያዘለ  ነው፡፡ የፍቅር ሃያልነት፤ ቀልድ አይደለም። በቀላሉ አይገዳደሩትም።
ታዲያ የዘፈኑ ውበትና ጉልበት፣ የዘፈኑን መልዕክት የሚመጥን መሆኑ ላይ ነው። ሙዚቃው፣ዜማውና የተዓምረኛዋ ድምፃዊት አዘፋፈን በህብር፣ ሃያል መንፈስን የሚሞላ የሙዚቃ ጥበብን ፈጥረዋል፡፡
የታዋቂው እንግሊዛዊ ጥበበኛ  የአንድሩ ሎይድ ዌበር ፈጠራ ነው - ዘፈኑ።  ሙዚቀኛው፣በአንድ በኩል፣ በረቂቅ ሙዚቃ፣ የነ ሞዛርት ዓለም ውስጥ አንቱ የተባለ ባለሙያ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በሙዚቃ ስራዎቹ፣ ገበያው፣ እንደ ጉድ የደራለት ስኬታማ ባለጸጋ ሆኗል።  እንግሊዝ ውስጥ ከኤልተን ጆን ቀጥሎ፣ በሦስተኛ ደረጃ ከተቀመጠችው ከሪሃና በፊት የሚጠቀስ፣ እጅግ የተዋጣለት ባለሃብት ነው - ወደ ቢሊዮነርነት የተጠጋ ሙዚቀኛ።
በአንድ በኩል የኦፔራ ደራሲና አዘጋጅ ነው - በኪነጥበብ መዲናዎች ውስጥ የነገሰ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ተራው ተርታው ሰው ለሚደሰትባቸው ለተወዳጅ ፊልሞችም፣ በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን አቀናብሯል - ዝነኛ ዘፈኖችን ሰርቷል።
ጥበብና ሃብት፣ ሙያና ክብር፣ ልሕቀትና ተወዳጅነት እንዲህ ሲሰምሩ፤ ሕይወት ያምራል። ቤቲ ጂ እንዳለችው ነው - ክብር ለአዋቂ፣ ሃብት ለጥበበኛው ብላ አዚማዋለች-በያምሉ ግጥምና የሙዚቃ ቅንብር።
በእርግጥ፣ እውቀትና ክብር፣ ጥበብና ብልፅግና፣ የሙያ ፍቅርና ሃብት፣….ፍቅርና ደስታ የማይገጣጠሙበት ጊዜ አለ፡፡ ነገር ግን፣ ፍቅር ሃያል ነው፡፡ አፍቃሪ፣ በቀላሉ አይሸነፍም፡፡ ብዙ ፈተናዎችን ይቋቋማል፡፡ አልተሸለምኩም ብሎ እውቀትን አይራገምም-አዋቂ፡፡ እውቀትን የሚያፈቅር ሰው፣ በዘመድ በጎረቤቶች ዘንድ አልተከበርኩም ብሎ እውቀቱን አያራክስም። “ጉዱ ካሳ” ብለው ቢዛበቱበትም ከአዳሜ ጋር በከንቱ ከመመሳሰል ይልቅ የእውቀት ፍቅሩን አፅንቶ ለመያዝ ይመርጣል።
የእውቀት ፍቅር እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው።  ከእስር እና ከሞት ጋር ለመጋፈጥ የተገደዱም የደፈሩም አሉ።
 ግን እጅ አልሰጡም ፍቅር ሃያል ነው።
ከነገሥታት ከመሳፍንት ትውልድ የመጣችው ውቧ ሰብለወንጌል፣ የዜማ ጥበበኛው የበዛብህ ፍቅር ብልጦባት  መከራ አይታለች። “ኑሮ ከበደኝ ሃብት ዘገየብኝ” ብሎ ከሙያ ፍቅር ጋር አይጣላም ጥበበኛ፡፡ አያስችለውም፡፡ ፍቅር ሃያል ነውና፡፡
 አንዳንዴ ደግሞ፣ የባሰ ነገር አለ፡፡ ከአደገኛ ሱስ ጋር የሚመሳሰሉ፣ በክፉ አመሎችና ስሜቶች የተተበተቡ የባህሪይ ቅኝቶችን አስታውሱ፡፡ እነዚህም ሃያል ናቸው፡፡ “መጥፊያዬ ትሆኛለሽ” ብሎ ዘፍኖ የለ አቤል ተስፋዬ፡፡  
እነዚህን ሁሉ የፍቅር ዓይነቶች የሚጠቀልል ይመስላል-የሳራ ብራይትማን ዘፈን፡፡  “Love Changes Everything” ይላል- ርዕሱ። ቃል በቃል “ፍቅር ሁሉን ነገር ይለውጣል” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ሁሉም ነገር በፍቅር ይቀየራል ብለን ብንረዳውም ያስኬዳል። መልዕክቱ ፣“ፍቅር ያሸንፋል” እና “ፍቅር ሁሉንም ይገዛል” የሚል ነው። ሃያልነቱ ይሾማል ይሽራል በሚል ስሜት መሆኑን አስተውሉ፡፡
ያመጣላችኋል ክብር፣ ያመጣባችኋል ውርደት!
Love, love changes everything
How you live,
and how you die
days are longer
words mean more
pain is deeper than before
love will turn your world around
and that world will last forever
Yes, Love, changes everything,
Love, brings you glorly,
Love, brings you shame,
Nothing in the world will ever be the same
Love will never, never let you be the same
ፍቅር፣ ክብርን ያጎናፅፋል። ፍቅር ውርደትን ያከናንባል ትላለች- ዘፋኟ። እና ምን ይሻላል?። የምትወደውን ለይተህ እወቅ። የምታፈቅሪውን ለይተሽ እወቂ። እንዲህ ለማለት ፈልጋ ነው? መጥፎ ምክር አይደለም። ማወቅና መጠንቀቅ ጥሩ ነው።
በእርግጥ፣ እንደ ማብሪያ ማጥፊያ፣ በመረጠች ጊዜ፣ በፈለገ ጊዜ፣ ብርት ድርግም የሚያደርጉት አይደለም - ፍቅር።  አንቺም፣ “ይሄን ልውደድ! ያንን አልውደድ!” አትዪም። አንተም፣ “ይህችን ላፍቅር! ያችን አላፍቅር” አትልም። “ጥሎብኝ” ብላ የለ ዘፋኟ።
እውነትም፣ ፍቅር፣ እጅግ  ሃያል ነው፤ “ገዢ” ነው፡፡  ግን ደግሞ፣ ፍቅር፣ ጨርሶ ከሰው ቁጥጥር ውጭ የሆነ አንዳች ኃይል፣ የማይጋፉት የማይጠይቁት ባዕድ ገዢ አይደለም።
አዎ፤ ሃያል ነው፤ “ገዢ” ነው። ይህ አይካድም።
አዎ፣ እንደ ልብስ፣ ጥዋት ማታ የሚደርቡት የሚያወልቁት፣ እንደ አየሩ ፀባይ እያማረጡ የሚቀይሩት የሚለብሱት ነገር አይደለም - ፍቅር።
ትናንት ተቦክቶ ለዛሬ የሚደርስ ምግብ አይደለም ፍቅር፡፡ እዚሁ የሚጋግሩትና፣ እዚያው በቅመም አጣፍጠው የሚያበስሉት፣ ወዲያው ለምሳ የሚያቀርቡት፣ የሚያጣጥሙትና የሚያቃምሱት፣ ለነገ ደግሞ ሌላ አይነት ምግብ በሌላ ጣዕም የሚተኩት ነገር አይደለም - ፍቅር ማለት።
ይሄ ሲባል ግን፣ ፍቅር፣ እንደ ንቅሳት ነው ለማለት አይደለም - መርጠው የሚለብሱት፣  ከለበሱት በኋላ ግን አውልቀው የማይጥሉት  የእድሜ ልክ ውበትና ጌጥ ወይም የዘላለም እዳና ጠባሳ አይደለም - ፍቅር።
በአጠቃላይ፣ ፍቅር፣ በአንድ አፍታ፣ በአንድ ውሳኔና በአንድ ጀምበር የሚመጣ  የሚጠፋ ነገር አይደለም።
ፍቅር፣ የግል ማንነት አንድ ገፅታ ነው፤የማንነት መንፈስ ነው። የማንነት ገፅታ እንደመሆኑም፣ ከእያንዳንዱ ሰው ውስጥ፣ በጊዜ ሂደት የሚበቅል የማንነት ዋርካ ወይም ትክል አለት ነው - የተቃና አልያም የጠመመ።
በአንድ ጀንበር ሳይሆን፣ በጊዜ ሂደት፣ የግል ተፈጥሮን የሚቀርፅ ኃያል የነፍስ ውቅር ነው- ፍቅር፡፡
የማይከዳና የማያመልጡት የመንፈስ ቅኝት ነው ፍቅር።
 በድንገት አይጠናወትም፡፡ በአንድ ጀንበር አይፈጠርም- በረዥም ጊዜ እንጂ።
በአንድ ጀምበር አይጠፋም፤ ድንገት አያመልጡትም።
ነገር ግን፣ በጊዜ ሂደት፣ አይቱን መለወጥ፣ ቅኝቱን መቀየር ይቻላል።
ፍቅር፣ እንደ ሰው ባሕርይ ነው። በጊዜ ሂደት፣ ስር እየሰደደ ይፀናል ወይም ይገነግናል። በጊዜ ሂደትም፣ እየከሰመ በሌላ ይለወጣል - እየተሻሻለ ወይም እየተበላሸ።
ፍቅርም እንደዚያው ነው - እንደ ባሕርይ፣ ወይም እንደ ባሕል። ኃያልነቱም የዚያኑ ያህል ነው - ለክፉም ለደጉም፣ ለእልልታም ለዋይታም፣ ለፅድቅም ለኩነኔም፣ ለኩራትና ለክብር፣ አልያም ለሃፍረትና ለውርደት።
ያበለፅጋልም ያደኸያልም። ያጎናፅፋልም፣ ያራቁታልም። አቀበቱን የሚያሸንፍ ብርቱ አቅም ይሆንልናል፤ ቁልቁል የሚያወርድ ልምሻም ይሆንብናል። በአጭሩ፣ ፍቅር፣ የግል ማንነት ገፅታ ስለሆነ፣ ሰው የመሆን ወይም ያለመሆን ጉዳይ ነው፡፡
አኗኗርህም አኗኗርሽም በብርሃናማ ፍቅር ይደምቃል፣ ባልተገጣጠመ ፍቅር ይደበዝዛል፡፡ ጥላሸት በለበሰ ውስጣዊ መንፈስ ሳቢያም ኑሮ ይጨልማ- ከጥላቻ ስሜት ባልተለየ የጨለማ ፍቅር ሳቢያ፡፡  ምናለፋችሁ! የፍቅር በረከትና እጦት፣  የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ ነው።
ታዲያ፤ ኑሮዬን ያፈካል ብለህና ብለሽ አስልተህና አሰላስለሽ የምትቀበሉት አይደለም ፍቅር፡፡ አዎ፣ኑሮን ሊያፈካ ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ የኑሮ ገዢ ነው፡፡ ውሎና አዳር ሁሉ ላይ መሪ የመሆን ጉልበቱ ሃያል ነው። ትኩረትና ሃሳብን፣ ተግባርና ምኞትን ሁሉ የመቆጣጠርና የመንዳት፣የመገፋፋትና የመዘወር ጉልበቱ ሃያል ነው፡፡
“የሕይወት ትርጉምን የምሰጣችሁና የምነሳችሁ  ነኝ” እኔ የማለት ሃይል አለው ፍቅር። ዓለም ሁሉ የሚሽከረከረው የሚሾረው በፍቅር ነው ትላለች-ሳራ በድንቅ ድምጽዋና ዜማዋ፡፡ ደግሞስ፣ ዓለም ያለ ፍቅር ቢሾር ባይሾር ምን ትርጉም አለው? የጊዜ ትርጉም፣ ከፍቅር በረከትና እጦት ጋር የተዛመደ ነው።
አለበለዚያማ፣ ዓለም ብትዞር ብትሽከረከር፣ ቢነጋ ቢመሽ፣ ለውጥ የለውም።  የፍቅር ቀጠሮ ቶሎ አይደርስም፤ ይጎተታል፡፡ የፍቅር ማዕድ ላይ ሲሆኑ ደግሞ፣ ሰዓቱ ይከንፋል፡፡
Love, love changes everything,
How you live,
and how you die
የእውቀትም ሆነ የሙያ ፍቅር፣ የሕይወትና የግል ማንነት ፍቅር፣ የብቃትም ሆነ የጾታ ፍቅር፣ የአበባ ውበትንም ሆነ የውሃ ፣ የምግብ ጣዕምም ሆነ ሌላ፣… የማንኛውም ነገር ትርጉም፣ በመውደድና በፍቅር መንፈሳችን አማካኝነት የተቃኘ ነው ማለት ይቻላል።
በሌላ አነጋገር፤ የተቃናና የጠመመ ፍቅር ማለት፣ ብሩህ የማንነት መንፈስና ጨለማ የማንነት መንፈስ ማለት፣ የሕይወትን ጣዕም ያጣፍጣል ወይም  ጣዕሙን ያጠፋብናል። እናም፤ የመለምለምና የመደላደል፣ አልያም የመመንመንና የመጠውለግ፣ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው - የፍቅር በረከትና እጦት!።
በአንድ በኩል፣ የተጣመመውን፣ የተዛባውንና የተበላሸውን የግል መንፈስ አለመግታት፣  አለማስተካከል፣ አሳዛኝ ድክመት ነው። ይህም አንሶ ይባስኑ ማበላሸት፣ ይባስኑ ከፍቅር ብዥታ ወደ ፍቅር ፅልመት  መጓዝ ደግሞ ውድቀትን የሚያፋጥን ስንፍና ወይም አስፀያፊ ክፋት ይሆናል።
በሌላ በኩልም፣ የተቃናውን መልካም ጅምር፣ ፀድቆ ያቆጠቆጠውን  የፍቅር ቡቃያ አለመንከባከብ፣ አለማሳደግ፣ ይህም አንሶ ይብስኑ በእንጭጩ መቅጨት፣አሳዛኝ ስህተትና የዋህነት ነው፡፡ የፍቅር ወገግታን ማድመቅ እንጂ ማደብዘዝ፣ የብርሃንን ዋጋ አለማወቅና አለማክበር ነው፡፡
 ከጊዜ በፊት የተገነባው የመልካም ስራ ምሳሌና አርአያን፣ ውርስና ቅርስን አክብሮ፣ ለላቀ ስኬት ተግቶ እንደመገንባት፣ ነባሩን ቅርስ በቸልታ መዘንጋት፣ ይብስኑም መሸርሸር፣ ከዚያም አልፎ በዘመቻ መናድ፣…. አሳፋሪ አላዋቂነት፣ አልያም ወራዳ ክፋት ይሆናል።
ታዲያ፤ነባሩ ጠባሳ እንዳይሰፋና እንዳይዛመት መከላከል፣ ለዘለቄታውም መፈወስ፣ የተጣመመውንና የተበላሸውን ማስተካከል፣ የሚቻለው እንዴት ነው?
ጅምር ቡቃያን ተንከባክቦ ማሳደግ፣ ነባር ቅርሶችን አክብሮ በአርአያነታቸው መነቃቃትና አዳዲስ ስኬቶችን መገንባት የሚቻለው እንዴት ነው?
ነባሩን ጠባሳ ማባባስ፣ የተበላሸውን ማስፋፋት፣ ጅምር ቡቃያዎችን መቅጨት፣ ነባር ቅርሶችን ማፍረስስ እንዴት ነው?
ቀላል አይደለም ጉዳዩ። ባሕልና ባሕርይ፣ ልማድና ፀባይ፣ የግል ማንነትና ፍቅር…. ድምር ውጤት ናቸው።
አንደኛ ነገር፣፣የረዥም ጊዜ ድምር ናቸው። የሚታነፁትም የሚፈርሱትም፣ በአንድ ጀምበር ሳይሆን፣ በጊዜ ሂደት ነው።
የብዙ ነገሮች ድምር ናቸው። የሚታነፁትም የሚፈርሱትም፣ በአንድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ ነገሮች የእርስ በርስ ጥምረት ወይም በብዙ ነገሮች የእርስ በርስ ስብራት ነው - የአንዱ ብልሽት የሌላውን በሽታ እያባባሰ።
ሰው ሊቆጣጠራቸው ከሚችላቸው ጉዳዮች ሁሉ የሚመነጩና የሚጠራቀሙ፣ የእልፍ ሰበቦችና መዘዞች፣ የእልፍ መንስኤዎችና ውጤቶች ድምር ናቸው።  ባሕልና ባሕርይ፣ ፍቅርና ጥላቻ የሚታነፁትም የሚፈርሱትም፣ በሰዎች የዘወትር ሃሳብና ንግግር፣ አላማና እቅድ፣ ተግባርና ኑሮ አማካኝነት ነው። በብዙ ነገሮችና በረዥም ጊዜ
በሌላ አነጋገር፣ መልካም የግል ማንነት መገንቢያና ማፍረሻ፣ መልካም የአገር ባህል ማሳደጊያና ማሰናከያ፣ መፈወሻና ማርከሻ፣ መጠገኛና ወጌሻ፣ መሰርሰሪያና መስበሪያ፣…. የእለት ተእለት ሃሳቦቻችንና ንግግሮቻችን ናቸው። የእለት ተእለት ተግባራችንና ኑሯችን ናቸው ውለው አድረው ድንቅ ብቃት የሚሆኑልን፤ወይም ክፉ አመል የሚሆኑብን።
እለት ተእለት የምንከተለው አላማና ውጥን ነው  - በጊዜ ሂደት ባሕሪይና ባሕል፤ ፍቅርና ስልጣኔ የሚሆነው ወይም ጥላቻና ውድቀት፡፡
 እናም፤ ልብ በሉ፡፡ የዛሬ ነገራችን ሁሉ  ተደራርቦ ተሳስሮ፣ ውሎ አድሮ፣ያማረ ወይም የመረረ ባሕል ይሆናል፡፡ የፈካ ወይም የጨለመ ሕይወት የሚፈጠረው ከእለት ተእለት ሃሳብና ንግግር፣ ተግባርና እርምጃ፣ ምኞትና ውጥን ነው፡፡
አሁን ብል በሉ።
የምትመኙትን ተጠቀንቀቁ። ውጥናችሁን አስተውሉ።
የምትናገሩትን እወቁ። የምታስቡትን አጢኑ።
የምታደርጉትን ምረጡ። የምትሰሩትን ለዩ። እርምጃችሁን አስተውሉ።




Read 1180 times