Tuesday, 09 November 2021 00:00

ትውስታ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

በሀሳብ መንገድ ላይ
                            
             “ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የበደለ ወይም የገደለ ዕድሜ ልኩን ይሞታል፡፡… ያውም በየቀኑ፡፡ ያሰረም እንደ ታሰረ ይኖራል። ነፃነት፤ የስጋት ምቾትና የማስመሰል ጉዳይ አይደለም፡፡ የመንፈስ መነቃቃትና የአስተሳሰብ ርቀት እንጂ!! aፍትሃዊ ሰዎች የመንፈስ ነፃነት አላቸው።-”
 ሴትየዋ በእርጅና ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈውን  የአባቷን ሀዘን ጨርሳ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ እሷ በአባቷ አሳብ የባሏን፣ ልጆቹ በአያታቸው ሰበብ የአባታቸውን እርም በለቅሶ አውጥተው ተገላገሉ፡፡ የአባታቸው ደብዛ ከጠፋ ስድስት ዓመት ሆነ፡፡ ልጅቹ በአንድ ልብ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ አስባ ነው፡፡ ምናልባት እሷም ሌላ አጋር ያስፈልጋት ይሆናል፡፡… ምናልባት!
በዛው ሰሞን አንድ ሰው ቤታቸው መጣ።
‹‹ጤና ይስጥልኝ››
‹‹አብሮ ይስጥልኝ››
‹‹እገሊት ነሽ››
‹‹አዎ ነኝ››
እንግዳው ስሙን ነግሯት፤ ከአውሮፓ እንደተመለሰ አጫወታት፡፡ ልጆቹ ከት/ቤት መጡ፡፡ ከሳማቸውና ከተዋወቃቸው በኋላ ያመጣውን ሻንጣ ወደ እነሱ እየገፋ ‹‹አባታችሁ የላከላችሁ ነው፤ እሱም በቅርብ ጊዜ ይመጣል፣ ገንዘብም ይኽውና››
አላቸው፡፡ ቤቱ በእልልታ ነደደ፡፡ ቡና ቀረበ፡። እናታቸው ወደ ቀልቧ ስትመለስ፡-
‹‹ከየት አገር ነበር ያሉኝ?›› በማለት ጠየቀች፤ እንግዳውም ነገራት፡፡
‹‹ፈጣሪ ምን ይሳነዋል?... ለመሆኑ ደህና ነው?››
‹‹አሌክስ በጣም፣ በጣም ደህና ነው፣ አውሮፓ ከመጣ ሁለት ዓመት እንደሆነው ነግሮኛል:: አንድ አፓርትመንት ላይ ነው የምንኖረው፡፡ በቀደም ሊፍት ውስጥ ተገናኝተን፣ በማግስቱ ወደ አገር ቤት እንደምሄድ ስነግረው በጣም ደስ አለው። ‹እባክህ እግረ መንገድህን›› ስላለኝ ነው የመጣሁት… ድንገት ቢሆንም፡፡ አሌ ጥሩ ሰው ነው፡፡…”
‹‹ስሙን ቀይሯል እንዴ?››
‹‹ሌላ ነበር ስሙ?… እኔ የማውቀው ‹አሌክስ› መሆኑን ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት ብዙ ሰዎች ስማቸውን ይቀይራሉ፣ ቁጭ ብለን አውርተን አናውቅም፡፡ ››
‹‹ኧረ ይሁን፡፡ ዋናው ደህና መሆን ነው፡፡ ሰውነቱስ እንዴት ነው?››
‹‹ፎቶግራፍ አንስቼዋለሁ፡፡ ወደ ስልክሽ ልላከው›› አለና… ላከላት፡፡
‹‹እንዴ?››
‹‹ምነው?››
‹‹ይኼማ እሱ አይደለም፣ እሱ’ኮ መላጣ ነው:: አፍንጫው ላይ ደግሞ ምልክት የለውም›› አለች ሴትየዋ፤ ግድግዳው ላይ ወደ ተሰቀለው የባለቤቷ ፎቶግራፍ ሄዳ እያመላከተች፡፡… ሰውዬው ተደናገረ።
‹‹ተሳስቼ ይሆን እንዴ?›› በማለት ስሟን፣ የልጆቿን ስም፣ ዕድሜና የመሳሰሉትን በድጋሚ ጠየቃት። አልተሳሳተም። ትንሽ እንደ ማሰብ ብሎ ስልክ መደወል ጀመረ፡፡ አልተሳካለትም፡፡
ስልኩ አይሰራም፡፡ “ለጊዜው አያስፈልገኝም፤ የነሱ  ይበልጥብኛል” ብሎ የሞባይሉን አፓራተስ ለናንተ ልኳል። ሻንጣው ውስጥ አድርጌዋለሁ›› አለ እንግዳው።
የእናትና ልጆች ዓይን ላይ የነበረው ብርሃን ቀስ እያለ ጠወለገ፡፡ ዝምታና አለመረጋጋት ቤቱን አጨናነቀው። መልካሙ ሰው ግን ዘና ባለመንፈስ ሲያጫውታቸው ቆይቶ ለስንብት ተነሳ፡፡…
‹‹ከሰሞኑ ተመልሼ እጠይቃችኋለሁ››
‹‹እናመሰግናለን›› አለች እናት እንባዋን እየተቆጣጠረች፡፡
 ሻንጣውንና ገንዘቡን ለመመለስ ስትዳዳ
‹‹በፍፁም አይደረግም… ስህተት እንኳ ቢሆን እኔ እከፍላለሁ፡፡ እግዜር የላከላችሁ ነው፣ አይዟችሁ›› ብሏቸው፣ ልጆቹን በድጋሚ ስሞ ወጣ። ሸኙት፡፡… ከዚያስ?
*   *   *
ሊቃውንት ‹‹ሕይወት በገጠመኞች የተሞላች ናት (Life is a series of incidences)›› ይላሉ:: ቅጥልጥሎሹ ካንድ ጎን ቦግ ሲል፣ በሌላኛው ዕልም ይላል፡፡… እንደ ሳሙና አረፋ፡፡ ሁሉም ግን ምክንያትና ውጤት (cause and effect) እሳቤ ቅንፍ አይወጡም፡፡
ወዳጄ፡- ሳይወለዱ ሞት፣ ሳይሞቱ መወለድ የለም፡፡  ሞት ውስጥ ‹ሕይወት›፣ ሕይወት ውስጥ ‹ሞት› አለ፡፡ እህል ተፈጭቶ፣ ተጠብሶ፣ ተወቅቶ፣ ተቀቅሎ ወይም ተጋግሮ ይበላል፡፡ ስጋና ደምም ይሆናል፡፡ ሰውነት ያፋፋል፣ ጉልበት ይሰጣል፡፡ ስጋ በተራው ሲሞት፣ ሲበሰብስ አፈር ይሆናል:: እህል ይበቅልበታል፡። ከበሰበሰ ፍሬ ዋርካ፣ ከሞተ ህዋስ ሰው ይፈጠራል፣ ይበቅላል። በሕይወት ሸክርክሮሽ (Vicious Circle) ውስጥ ሁሉም ነገር ተቃራኒ እኩያ አለው፡፡ ‹‹ When some thing is lost, some thing is gained›› እንደሚሉት፡፡… ተፈጥሮ ፍትሃዊ ናት፡፡
ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የበደለ ወይም የገደለ ዕድሜ ልኩን ይሞታል፡፡… ያውም በየቀኑ፡፡ ያሰረም እንደ ታሰረ ይኖራል። ነፃነት፤ የስጋት ምቾትና የማስመሰል ጉዳይ አይደለም:: የመንፈስ መነቃቃትና የአስተሳሰብ ርቀት እንጂ!! ፍትሃዊ ሰዎች የመንፈስ ነፃነት አላቸው። ላመኑበት ጉዳይ በገዳምም ሆነ በእስር ቤት ቢቆዩ ስጋቸው እንጂ መንፈሳቸው ወይም ውስጣቸው አይታሰርም፡፡ ኢ-ፍትሃውያን ደግሞ በገነትም ሆነ በሰባት ኮከብ ሆቴል ቢኖሩ፣ ምቾቱ የስጋ እንጂ የውስጥ አይሆንም፡፡
ወዳጄ፡- በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወይም በኑሮ አስገዳጅነት በመታለል ለተፈፀመ ጥፋት ‹ይቅር ብለናል› ሲባል፤ ፈጥኖ ከማመስገንም በላይ በዕድሉ በመጠቀም ለመካስ መሞከር ተገቢነት ብቻ ሳይሆን ጥቅም አለው፡፡ .. ሰላምና ነፃነት!!...
‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ወይም “እኔ ያልኩት ካልሆነ ፀሐይ አትወጣም” ብሎ ወደ ክፉ ጥፋት ማሽቆልቆል ዳግም ዕብሪት ነው፡፡ ዕብሪት ‹የመጨረሻው ፉከራ› ምልክት ነው። … ‹‹The last hurrah!›› … እንደሚሉት፡፡…ሁለት ወዶ አይዘለቅም፡፡ ታላቁ ፓትሪክ ሄነሪ፤ ‹‹ወይ ነፃነቴን ወይ ሞቴን? አንዱን ስጡኝ›› ነበር ያለው። አላምታታም፡፡ ሰላም፤ የገና ስጦታ አይደለም፡፡
*   *   *
ወደ ታሪካችን እንመለስ፡- አንድ ቀን የሴትየዋ በር ተንኳኳ፡፡
‹‹ማነው?››
‹‹እኔ… አሌክስ›› አለ ኮልታፋ ድምፅ። በመጀመሪያ ግራ ገባት፡፡ በሁዋላ ግን እንግዳው ወደ ሞባይሏ በላከው ፎቶ ላይ የሚታየው ሰው እንደሆነ አስታወሰች፡፡
‹‹እኔ አላውቅኾትም››
‹‹ኧረ እባክዎ ያውቁኛል›› የባሏን ስም ጠርቶ፣ የሱ ወንድም እንደሆነ ነገራት፡፡ ባለቤቷ መንታ ወንድም ነበረው። አግኝታው ግን አታውቅም፡፡
‹‹ውይ ጉዴ ፈላ አንተ ነህ እንዴ?››
ጎንበስ ብሎ መነፅሩን እያስተካከለ፡- ‹‹አንመሳሰልም?››
‹‹አፍንጫህ ትንሽ ሰበር ይላል እንጂ ትመሳሰላላችሁ፡፡ እሱ ደግሞ መላጣ ነው።›› … በመሃል የቤተሰቡ ውሻ እየሮጠ ገባ፡፡
ሰውየው ላይ እየተንጠላጠለ በደስታ መጮህ ጀመረ:: ቦታ ጠበበው። አሌክስ ሳያስበው የውሻውን ስም ጠራ። ሊያሻሸው ጎንበስ ሲል፣ አርቴፊሻል ፀጉሩ ወደ ፊት ተከነበለ፡፡ መነፅሩ ወደቀ፡፡ ቀና ሲል ሚስቱ ነቃች፡፡
‹‹አንተ!›› ጠራችው፤ በድሮ ስሙ፡፡
“… አሁንም በሰው መቀለድ አልተውክም?››… ዕልልታዋን አስነካችውም። ተቃቀፉ፡፡ ዓለም ሆነ፡፡ ሊያደናግራት ወደ ውስጥ ያጠፈውን ምላሱን ዘርግቶ መሳቅ ጀመረ፡።
‹‹ይኸ ምንድን ነው?... እኛን ለማታለል ነው?›› ወደ ፀጉሩ እያሳየች፡፡ ‹‹አፍንጫህን ምን ሆነህ ነው?›› ነገራት፡። ሁሉንም፡፡ ልጆቿን ለመጥራት ወደ ጎረቤት ሄደች፡፡
ኤሌክስ የቀድሞ ስሙ ጆኒ ነበር። ጆኒ በማያውቀው ጉዳይ ‹‹አሸባሪ› ተብሎ፣ ሁለት ዓመት ጨለማ ቤት ታሰረ። አሰቃዩት፡፡ እንዳይሞትባቸው ወደ ሆስፒታል ወሰዱት፡፡ ጠባቂው ወደ ሃኪሙ ቢሮ ሲያስገባው፣ ሃኪሙ እጁን እየታጠበ ነበር፡፡ ጆኒ ድንገት ወሰነ፡፡ ራሱን ለማጥፋት ከአምስተኛ ፎቅ ላይ ዘለለ። ያረፈው ግን የመኝታ ስፖንጅ ጭኖ የሚጓጓዝ አይሱዙ መኪና ላይ ነበር። አናቱና አፍንጫው በግጭት ከመጎዳቱ በቀር ሕይወቱ ተርፏል፡፡ ከሰመመኑ ሲመለስ ተሰደደ፡፡ ስሙን ቀይሮ ኬንያ ስደተኞች ካምፕ ሁለት ዓመት ኖረ። ዕድል ሲያገኝ ወደ አውሮፓ መጣ፡፡… ዛሬ የአውሮፓውያኑ የገና ዋዜማ ነው፡፡
ሠላም!!Read 7032 times