Sunday, 07 November 2021 19:16

“ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” ምርትን ከገበሬው ለሸማች ማቅረብ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

 ለመከላከያ ሰራዊት ቀለብ የማቅረብ ድጋፍ ፕሮጀክቱን ትላንት ጀምሯል
                            
            በዶ/ር ፍሰሀ እሸቱና በስራ ጓዶቻቸው የተቋቋመውና የጥቁር ህዝቦችን የኢኮኖሚ ልህቀት በመፍጠር ጥቁሮች ይበልጥ እንዲከበሩ የማድረግን ራዕይ የሰነቀው ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ፤ “ቀለብ ከገበሬው” በሚል መርህ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቹ ማቅረብ ጀመረ።
ሀገራችን የገጠማትን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ የሚደረገውን ትግል ለመደገፍ ፐርፐዝ ፕላክ ኢትዮጵያ፣ የድርጅቱን ሰራተኞች፣ መላው ኢትዮጵያውያንና የዲያስፖራውን ማህበረሰብ በማስተባበር ግንባር ለሚፋለመው ሰራዊት በነጻ ቀለብ የማቅረብ ፕሮጀክቱንም ትላንት ከሰአት በኋላ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ዋና  ጽ/ቤቱ ይፋ አድርጓል።
ጠላት ኢትዮጵያን ለመጣል ከሚዋጋበት አንዱ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን በመፍጠርና ህዝቡን በማማረር መሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፤ ይህንን ሴራ ለማክሸፍ በራሱ መኪኖች እንደ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ሙዝ፣ ሀብሀብ፣ ብርቱካን፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብልና ሌሎችንም መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ቀጥታ ከአምራቹ በመግዛት ለሸማቾች ማቅረብ መጀመሩን ባለፈው ሰኞ መካኒሳ በሚገኘው ማዕከሉ አስታውቋል። በእለቱም በርካታ የአካባቢው ህዝብ  ምርቶችን ከዋናው ገበያ 50 በመቶ በሆነ ቅናሽ ሲሸምት ውሏል።
ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ በዚህ አሰራሩ ሸማቹን ብቻ ሳይሆን ዋና አምራች ሆኖ ሳለ ያለ ጥቅም የቆየውን ገበሬ ምርቱን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ በማድረግ፣ ተጠቃሚ የማድረግ አላማን መተግበር መጀመሩን የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሀ እሸቱ ተናግረዋል።
“ቀለብ ከገበሬው” በተሰኘው በዚህ ፕሮጀክት ይፋ  ማድረጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ለፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ የተመረጠው ፀሀፊ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ፣ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የክብር እንግዶች ታድመዋል።
ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ የኑሮ ውድነትን ታሪክ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በመላ ሀገሪቱ ከ1ሺህ በላይ የግብይት ማዕከላትን ለመክፈት በእንቅስቃሴ ላይ ሲሆን በየመስሪያ ቤቱ ምርቶችን የማቅረብ እቅዱን እውን ለማድረግና ይህን ለመተግበርም ከአሰሪዎች ኮንዴደሬሽን ጋር ስምምነት ፈጽሟል። በቀጣይ ቤት ለቤት የፍጆታ እቃዎችን የማቅረብ እቅድ እንዳለውም በዕለቱ ተገልጿል።
ትላንት በዋና ጽ/ቤቱ ይፋ ባደረገው “ቀለብ ለሰራዊታችን” ፕሮጀክት፣ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኞችንና የራሱን ሰራተኞች በማስተባበር፣ በጦር ግንባር ለሚዋደቀው የአገር መከላከያ ሰራዊት ቀለብ ማቅረብ ሊጀምር ሲሆን የድርጅቱ ሰራተኞች ደም እንደሚለግሱም ለማወቅ ተችሏል።

Read 2346 times