Sunday, 07 November 2021 19:19

የፕሉቶክራሲ ሲምፖዚየም

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “-የዲሞክራሲ አራማጅ ያልሆኑት በአሁኑ ሰዓት የካናዳን መንግሥት የሚመሩት የሊበራል ፓርቲ አስተዳደር፣ የሰው መብት አያከብሩም ወይ? ኮንሰርቫቲቮች የመናገር መብትን ያፍናሉ ወይ? ሪፐብሊካንስ?--”

                የፕሉቶክራሲው ሲምፖዚየም የተዘጋጀው በአፍሮፖሊታን ሆቴል አንደኛ ፎቅ አዳራሽ ውስጥ ሲሆን ብዙዎች በአዳራሹ ውስጥ  ታድመው ነበር፡፡
አግማስ ወደ አዳራሹ ሲገባ በነጭ አቡጀዲ ላይ “ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር  ያስፈልጋታል?” የሚለው የደራሲ ሐዲስ አለማየሁ መጽሐፍ ሽፋን ይታያል። የአዳራሹ ወንበሮች በደረጃ ወደ ታች ቁልቁል የተደረደሩ ናቸው። መጨረሻው ወንበር ላይ የተቀመጠ ሳይቀር ተናጋሪውን ከመድረኩ ላይ ሊያየው ይችላል። አልፎ አልፎ አንዳንድ ወንበሮች ባዶ ቢሆኑም፣ አዳራሹ ሙሉ ነው። ሰዓቱ ሲደርስ የፕሮግራሙ አስተዋዋቂ፣
“ሰፋኒት ተድላ እባላለሁ፤ የዛሬውን ውይይት የምመራላችሁ እኔ ነኝ።” ብላ የድምጽ ማጉያ ይዛ መድረኩ ላይ እየተንጎራደደች፤ “ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?” አለችና አድማጮችን ከዳር እስከ ዳር አስተዋለች።
አግማስ የሰፋኒት መድረክ መሪ መሆን በጣም ገርሞታል። እንዴት? መቼ? እና በእንዴት ያለ ሁኔታ የዮሐንስ ቅጥር እንደሆነች ግራ ገባው። እሱ እስከሚያውቀው ድረስ፣ ሰፋኒት እንደ ዮሐንስ ዓይነቱን ሰው በጣም ነው የምትጠላው። ዘንድሮ በጥላቻና በፍቅር መሐከል ያለው ልዩነት፣ ጥቅም በሚባል ቀጭን መስመር የተለየ ሲሆን፣ ገንዘብ በሚባል ትንፋሽ እፍ ሲባል የሚጠፋ ሆኗልና፣ ሰፋኒትም ለዮሐንስ የነበራት ጥላቻ ወደ መውደድ ቢቀየር የዘመኑ ሒደት ነው። ስብሰባው ላይ የተገኙት አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሆኑ ተነግሮታል። ተማሪዎቹ ለጥያቄው መልስ አልሰጡም።
“ዛሬ እዚህ የተሰበሰብነው “ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?; ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት አይደለም። የራይርሰን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ምሩቅና የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቶሮንቶ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ  አምባዬ አትንኩት፣ ፕሎቶክራሲ ለሀገራችን በሚል ሊያወያዩን ነው። ዶ/ር ዮሐንስ አምባዬ ለሀያ ደቂቃ ብቻ ንግግር ያደርጉና ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ የጥያቄና መልስ ይሆናል። አሁን ዶ/ር ዮሐንስ አምባዬ አትንኩትን ወደ መድረኩ እጋበዛለሁ።” ብላ ከመድረኩ ስትወርድ፣ አግማስ አስተዋላት። ውስጧ እንጂ አለባበሷ አልተቀየረም።
ዮሐንስ ነጭ ጋዋን ለብሶ ነው ወደ መድረኩ የመጣው፣ መነፅሩ እንደ ሁሌውም የመልክ መስተዋት አንጸባራቂ ስለሆነ፣ ከውስጥ ወደ ውጭ እንጂ ዐይኑን ከውጭ ማየት አይቻልምና ወደ ማን እያየ እንደሆነ አይታወቅም። ምናልባት በቅርብ ርቀት ሊረዳው ይችል ይሆናል እንጂ፣ እዚህ መነፅር ማድረጉ ጥቅሙ አልታየውም።
ዮሐንስ “ዲሞክራሲ ምንድነው?” በሚለው ጥያቄ ጀመረና እንደገና፤
“ዲሞክራሲ ምንድነው?” ብሎ ጠየቀ። መልስ የሰጠ ግን የለም።
“ዲሞክራሲ ምን እንደሆነ የሚያውቅ አለ? ዲሞክራሲ ምን እንደሆነ የሚያውቅ ካለ…” ሲል አንድ አሥር ያህል እጆች ወጡ። ከፊት ላለችው ዕድል ሰጣት።
“ዲሞክራሲ ሕዝባዊ አስተዳደር ነው።” አለች። ሌላኛው፤ “የሰው ልጅ መብትን ማስከበሪያ ሥርዓት ነው። የሰው ልጅ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት፣ የመስራት መብትን የሚያስከብር ነው…” ብለው መልስ ሰጡ።
ዮሐንስ መላሾቹን አመስግኖ፤
“ባለፈው ሳምንት የትውልድ ቦታዬ፣ ጠዳ በተባለችው አነስተኛ ከተማ ነበርኩ። ጠዳን የማታውቋት ካላችሁ ከጎንደር ሠላሳ ኪ.ሜ ርቀት በአዘዞ በኩል ወደ ባህርዳር የምትወስደው መንገድ ላይ ያለች ትንሽዬ ከተማ ነች። የከተማዋ አስተዳደር ቢሮ ስገባ፣ ጉዳዬን የሚመለከተው ሰው ከሌላ ሰው ጋር እያወራ ነበር። ውይይታቸው ከሞላ ጎደል በዲሞክራሲያዊ መብቱ ተጠቅሞ ክስ መመሥረት እንደሚችል ለሰውየው ይነግረዋል።
“ዲሞክራቶች፣ መብት ዲሞክራሲያዊ ነው ብሎ እንዲያስብ ሕዝቡን አሳምነውታል። አንድ የማጫ ገበሬ ጠላ መጠጣት ዲሞክራሲ ያጎናጸፈው መብቱ ይመስለዋል። አባቴ በደርግ ጊዜ ጠላ ይጠጣ ነበር። አያቱም በዣንሆይ ጊዜ ጠላ ይጠጡ ነበር--።” አዳራሹ በሳቅ አወካ፡፡
“ዲሞክራቶች ገበሬውን፣ እኛ ከሌለን ጠላ መጠጣት የለም ብሎ እንዲያስብ አድርገውታል። እኛ ከሌለን መብት የለም ብለው ስለሚሰብኩ፣ ሕዝብም እየሰገደ “አቤቱ ዲሞክራሲ ሆይ! ያላንተ መናገርና መሰብሰብ አንችልም፣ ያላንተ ዕድገት የለም፤ አንተን ሺህ ዓመት ያኑርልን፣ ፈቃድህ በአሜሪካ እንደሆነች እንዲሁም በኢትዮጵያ ትሁን። አሜን!!” የሚል አምልኮተ ዲሞክራሲ ሰብከውታል።” አለና ዙሪያ ገቡን አስተውሎ፣
“ግን መብት ዲሞክራሲያዊ ነው? ወይንስ ሕገ-መንግስታዊ?” ፀጥ ብሎ አዳራሹን አየና፤ “ምላስ የተፈጠረው ከአዳም ጋር በኤደን ገነት እንጂ በአራተኛው ዘመን በአቴና ዲሞክራቶች አይደለም። ምላስ ተፈጥሮአዊ ከሆነ መናገርም ተፈጥሮአዊ ነው።” የአንድ ሰው ጭብጨባ አቋረጠው። የወርቃለማሁን ጭብጨባ ተከትሎ ሌሎችም አጨበጨቡ። ጭብጨባው ጋብ ሲል፣ “የዲሞክራሲ አራማጅ ያልሆኑት በአሁኑ ሰዓት የካናዳን መንግሥት የሚመሩት የሊበራል ፓርቲ አስተዳደር፣ የሰው መብት አያከብሩም ወይ? ኮንሰርቫቲቮች የመናገር መብትን ያፍናሉ ወይ? ሪፐብሊካንስ?” ብሎ አዳራሹን በጸጥታ ተመለከተና፤”
“መብት ሕገ መንግስታዊ ነው። ታዲያ ዲሞክራሲ ምንድን ነው? በአጭሩ መንግስትን የምንመሰርትበት አንደኛው አሰራር ነው። አሐዳዊ ስርዓት፣ ወይንም የንጉሠ ነገሥት ስርዓት፣ አስተዳደሩን መምረጥ የአንድ ሰው ሥራ ነው። ንጉሡ ልጁን ወይንም የወደደውን ሰው ሀገሪቱን እንዲመራ ይሾመዋል። በዲሞክራሲ ስርዓት መንግሥት የሚመረጠው በህዝቡ ነው። ሕዝብ መሪውን ይመርጣል፣ የተመረጠው ሀገሪቱን ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ ይመራል። አብላጫው ሕዝብ አይስማማም እንጂ ቢስማማ፣ የጥቂቶች መብት ይረገጥ ካለ በአብላጫ ድምጽ የተመረጠው መንግስት፣ የጥቂቶችን መብት መርገጥ ይችላል። ምክንያቱም ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በሕዝቡ ነው የሚመራው። ስለዚህ መብት ሕገ-መንግሥታዊ እንጂ ዲሞክራሲያዊ አይደለም።
"በ1931 እ.ኤ.አ የጸደቀው የንጉስ ኃይለስላሴ ሕገ-መንግሥት፣ የሰው ልጅ መብት ይከበር ይላል። የደርግ ሕገ-መንግሥት ሰብአዊ መብት እንዲከበር ይደነግጋል፣ የኢፌዲሪ መንግስትም እንደዚያው። ሕገ መንግስቱ እንጂ መንግሥታት በእርግጥ መብትን ያከብሩ ነበር? ሕዝቡ መብቱን የማስከበር አቅም እስከሌለው ድረስ…” አለና ንግግሩን ገታ አደረገው።
“የዚህ ሲምፖዚየም ዓላማ የቀደምትን ወይንም አሁን ስልጣን ላይ ያሉትን መንግስታት መውቀስ አይደለም። ምንም ዓይነት መንግሥት ቢመጣ፣ የማይደሰት የኅብረተሰብ ክፍል ስለሚኖር፣ ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ሁሌም ይወቀሳል። ነቢዩ ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ አውጥቷቸው፣ እስከ ተስፋይቱ ምድር ሲጓዙ፣ እግዚአብሔር በመረጠላቸው ሙሴ ነው። ግን ያጉረመርሙ ነበር። ነው ወይስ ሙሴን እግዚአብሔር አልመረጠውም?” አዳራሹ ውስጥ ሳቅ ተሰማ። ዮሐንስ ቀጠለ፤
“ዲሞክራሲ ለሀገራችን ይሠራል ወይ? ለዚህ መልስ ለመስጠት በቅርብ መረጃ ስላለን፣ የአሜሪካንን ዲሞክራሲ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። የአሜሪካ ሕዝብ በትራምፕ አገዛዝ 323 ሚሊዮን ነበር። የ2016 ምርጫ ከተፎካካሪ ሂላሪ ክሊንተን ጋር የተደረገ ሲሆን 138 ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ በምርጫ ተሳትፏል። የተቀሩት 185 ሚሊዮን ሕዝብ በዕድሜ፣ በጤና እና የመምረጥ መብታቸውን የተነጠቁ የሕግ እስረኞች በመሆናቸው፣ የምርጫ ካርድ መውሰድ አይችሉም። 30 ሚሊዮን አሜሪካውያን በሐይማኖት ምክንያት፣ የፖለቲካ ተሳትፎን ባለመፈለግ፣ በምርጫው ባለማመን፣ ስለ ምርጫ በቂ እውቀት ባለመኖርና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች የምርጫ ካርድ አይወስዱምና በምርጫው አይሳተፉም። በዚህ በትራምፕ እና በሂላሪ  ክሊንተን ምርጫ ሂደት 66 ሚሊዮን ገደማ አሜሪካውያን ሂላሪ ክሊንተንን ሲመርጡ፣ 63 ሚሊዮን ገደማ አሜሪካውያን ትራምፕን መርጠዋል። ይህ ማለት ሂላሪ ክሊንተን  በ2 ሚሊዮን አብላጫ ድምጽ አሸንፋ ሳለ ግን ተሸንፋለች። አብላጫ ድምጽ ለሂላሪ ዲሞክራሲ አልሰራም። ትራምፕ በአብላጫ ድምጽ ሳይሆን በምርጫ ጣቢያ ብዛት ነው ያሸነፉት፤ ከ531 የምርጫ ጣቢያዎች ትራምፕ 304ቱን ሲያሸንፉ፤ ሂላሪ ግን 227 የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ በማሸነፏ ተሸንፋለች። ከአሜሪካ 323 ሚሊዮን ሕዝብ 63 ሚሊዮኖቹ ብቻ በመረጡት አስተዳደር ይመራሉ። 260 ሚሊዮን ሕዝብ ባልመረጠው አስተዳደር ስር ወድቋል። እና በአሜሪካ ሕዝባዊ አስተዳደር አለ?
"ይህንን ምሳሌ ወደ ሀገራችን ብንመልሰው፣ ሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ ትችላለች ወይ? አብላጫው ሕዝብ በመረጠው ሕዝብ የመመራት ዕድሉ ምን ያህል ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ እንደ አሜሪካ ሕዝብ ወደ ሕገ-መንግሥቱ የተሰባሰበ አይደለም። ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከሕገ-መንግሥቷ በፊት ስለነበረች ሕዝቡ ቀድሞም ኢትዮጵያ ነው። ስለዚህ የዛሬይቷ ኢትዮጵያ አንድ ፍላጎት ባላቸው ህዝቦች የተመሰረተች አይደለችም።
"አሁን ያለው ፌደራላዊ አስተዳደር፣ በቋንቋ የተዋቀረ ነውና፣ ምርጫ በአብላጫ ድምፅ ቢደረግ፣ ብዙ ቁጥር ተናጋሪ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊመሩን ግድ ነው። እና ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ይሠራል? ከንግግሬ እንደምትረዱት የዲሞክራሲ ደጋፊ አይደለሁም።” አለና ጠረጴዛው ላይ ከተከመሩት መጽሐፍት አንዱን ብድግ  አድርጎ፤
“በዚህ ሲምፖዚየም መጨረሻ በሚታደላችሁ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ዲሞክራሲና ስለተቀባው ውሸቱ የፃፍኩትን ወስዳችሁ ማንበብ ትችላላችሁ። ዲሞክራቲክ ነን የሚሉትን ሀገሮች ልምድ ያካተተ ነው። ዲሞክራተስን በመርዝ ከገደለው የአቴና ዲሞክራሲ ጀምሮ ዛሬ ሃገራችንን ሊገሏት ከተነሱት 71 የዲሞክራሲ ፖለቲካ ድርጅቶች ድረስ ያሉትን የዲሞክራሲ ሂደት ይገመግማል።”
አግማስ አዳራሹ ውስጥ ያሉትን በጥንቃቄ ማየት ጀመረ። ማስታወሻ የሚይዙት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ንግግሩ እንደመሰጣቸው አያጠራጥርም፡፡ የዛሬው ዮሐንስ፣ የቀድሞው ጓደኛው፣ አንደበተ ርቱዕ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አስተዳደር ፕሎቶክራሲ ነው በሚለው ሐሳብ ግን ማንም የተስማማለት አይመስልም። ሀብታሞች፣ ድሃን ይምሩ የሚለውን ሐሳብ ማንም አይቀበልም። ግን አድማጮቹ በአንድ ነገር ተስማምተዋል። በዓለማችን ላይ የሚታየው እውነታ፣ ሀብታሞች ድሆችን እየመሩ መሆኑ ነው።
ዮሐንስ በንግግሩ መጨረሻ፤ “ዙሪያችሁን ተመልከቱ፤ ሀገራችን ወደዬት እያመራች ነው? ይህንን አሰላስሉት፤ አሁን ለንግግር የተሰጠኝ ሃያ ደቂቃ አልቋል። የሚቀጥለው የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ነው” አለና ጠረጴዛው ላይ የነበረውን ውሃ አነሳ።
(ከልዑል ዳዊት “አግማስ” የተሰኘ ታሪክ ቀመስ ልቦለድ የተቀነጨበ፤ 2014 ዓ.ም)


Read 1857 times