Saturday, 13 November 2021 12:34

የህወኃት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ከ2 ሺ 950 በላይ ት/ቤቶችን አውድሟል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ንብረት በክልሉ በጦርነት ወድሟል
  • ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል
                  
              የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በወረሯቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች  ከ2950 (ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ ሃምሳ) በላይ ት/ቤቶች በላይ ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን፣ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ያስታወቁ ሲሆን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ በበኩሉ በአጠቃላይ በወረራው ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት መውደሙን አመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኒስኮ) 41ኛ ጠቅላላ  ጉባኤ ላይ የትምህርት ሚኒስተሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ባቀረቡት ንግግር፤ በኢትዮጵያ በተለይም ከጦርነት ጋር ተያይዞ ስላጋጠመው ጉዳቶች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
በዚህም ሕወኃት ካለፈው  ሰኔ መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፈፀማቸው ወረራዎች፣ ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ  እስከ ኮሌጅ ድረስ ያሉ የትምህርት ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን አመልክተዋል፡፡
ታጣቂ ሃይሎች የሁሉንም ት/ቤቶች የመማሪያና ማስተማሪያ ግብአቶች መዝረፋቸውን፣ ግማሹን ማቃጠላቸውን ሆን ብለው ውድመት መፈፀማቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ  አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ት/ቤቶች ላይ ያነጣጠረ አውዳሚ ጥቃት፣ በአማራ ክልል ዋግምህራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ሰሜን ወሎና ወረሪው ሃይል በያዛቸው የክልሉ አካባቢዎች ከ2950 በላይ ት/ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን፤ በዚህም ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ መገደዳቸውን አመልክተዋል፡፡
እነዚህን ት/ቤቶች   ከጦርነቱ በኋላ መልሶ ለማቋቋምና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ለሚደረገው ጥረት አለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ከህወኃት ወረራ እና በአማራ ክልል ካደረሰው ጉዳት ጋር በተያያዘ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው መረጃ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ሃብት ማውደሙን አመልክቷል፡፡
በዚህ ጥቃት በ45 የአማራ ክልል ወረዳዎች ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ችግር የተጋለጡ ሲሆን ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያአቸው ተፈናቅለዋል፡፡
በክልሉ ከወደሙት ት/ቤቶች ባሻገር 1 ሺህ 466 ሆስፒታሎች፣ጤና ጣቢያዎችና ኬላዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ከ2ነጥብ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም፣በመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በመስኖ ልማት ላይ በደረሱ ጉዳቶች ደግሞ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ወድሟል ሲል የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ የህወኃት ወራሪ ሃይል በግብርና፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በገንዘብ፣ በውሃ በስራ እድል ፈጠራ በአዲስ ኢንቨስትመ፣ንት በንግድና በሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ ማድረሱን የቢሮ መረጃ አመልክቷል፡፡


Read 10928 times