Print this page
Saturday, 13 November 2021 12:40

ህወሃት በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ የ280 ቢ. ብር ሃብት አውድሟል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    የ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማሳ ከጥቅም ውጪ በማድረግ፣ ከ41 ሚ. በላይ ምርት አውድሟል።
                     
          የህውሃት አሸባሪ ቡድን በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ወደ 280 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ሀብት ማውደሙ ተገለጸ። ቡድኑ በክልሉ በወረራቸው የክልል አካባቢዎች፣  የሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሰብል ማሳ ከጥቅም ውጪ በማድረግ፣ ከ41 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማውደሙ ተጠቁሟል።
የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል። በአሸባሪው ቡድን ጉዳት ከደረሰባቸው መሰረተ ልማቶች መካከል ትምህርት፣ ጤና፣ ውሃ፣ መንገድና መስኖ ልማት የሚገኙበት ሲሆን በእነዚህ መሰረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ጥቃት 280 ቢሊየን ብር የሚጠጋ የሃብት ውድመት ደርሷል ብሏል።
ንፁሃን ዜጎችን በጅምላ የጨፈጨፈው ይኸው ቡድን የአርሶ አደሩን ሰብልና የቤት እንስሳት ጭምር ማውደሙንም መረጃው አመላክቷል።
ቡድኑ ለተወሰኑ ጊዜያት ወርሯቸው በነበረው የክልሉ 45 ወረዳዎች በተካሄደ ክልል አቀፍ የዳሰሰ ጥናት እንደተረጋገጠው በ1 ሺ 466 ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን ንብረት አውድሟል። በ6 ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች በፈፀመው ጥቃት 2.3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት አውድሟል። በመንገድና በድልድዮች ላይ በፈጸመው ጥቃትም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ  መውደሙ ተገልጿል።
ጥናቱ በአሁኑ ወቅት  በአሸባሪው ቡድን የተወረሩ የክልሉ ከተሞችን የማያካትት መሆኑን ያመላከተው መረጃው፤ በቀጣይ አዳዲስ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን የጉዳት መጠን ያካተተ ጥናት ሲካሄድ የጉዳቱ ስፋት በእጅጉ የከፋ ይሆናል ተብሏል።
በተያያዘ ዜና፤ አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው የክልሉ አካባቢዎች 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሰብል ማሳ ከጥቅም ውጪ በማድረግ 41 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማውደሙን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል። ቡድኑ በወረራቸው የአማራ ክልል ዞኖች 6.3 ሚሊዮን ህዝብ ለከፋ ችግር እንዲጋለጥ ማድረጉንም ግብርና ቢሮው አስታውቋል።
አሸባሪው ቡድን በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ጉዳት በደረሰባቸው 160 ት/ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች፣ ከትምህርት ገበታ ውጪ ሲሆኑ ከ47 ሺ በላይ መምህራንና ሰራተኞችም ከስራቸው መፈናቀላቸውን- የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ መረጃ ይፋ አድርጓል።

Read 10858 times
Administrator

Latest from Administrator