Print this page
Saturday, 13 November 2021 12:44

“በዚህ ወቅት የሽግግር መንግስትም ሆነ በውጭ ተፈጥሮ የሚመጣ አሻንጉሊት መንግስት ተቀባይነት የለውም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

          የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፣ በየትኛውም ሁኔታ ከውጭ ተሠርቶ የሚመጣን “አሻንጉሊት መንግስት” እንደማይቀበል ያስታወቀ ሲሆን በቅርቡ አሸባሪው ህወኃትን ጨምሮ ጥቂት አካላት በአሜሪካን ሃገር መስርተዋል የተባለውን የሽግግር መንግስትም እንደሚቀበለው አስታውቋል፡፡
በሠላማዊ መንገድ ለመታገል የሚንቀሳቀሰው ሁሉም ፓርቲዎች አባል የሆኑበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤቱ፤ በውጭ ሃይሎች ተቀናብሮ የሚፈጠርን የሽግግር መንግስት አስመልክቶ ባወጣው በዚህ መግለጫው፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ መርጦ የሚያቆመው እንጂ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር ተፈጥሮ የሚመጣለትን አሻንጉሊት መንግስት በታሪክ  ተቀብሎ አያውቅም ዛሬም አይቀበልም”ብሏል፡፡
“ሃገራችን ኢትዮጵያ  በታሪክ ምዕራፍ ውስጥ  የመጀመሪያውን ረድፍ ከሚይዙት ሃገራት የምትመደብ ብቻ ሳትሆን ለብዙዎች የድል ቀንዲል፣የጥቁር ህዝቦች አይበገሬነት መነሻና መገለጫ የነፃነት አውራ ናት” ያለው መግለጫው፤ ሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከአምባገነናዊ አገዛዝ ተላቅቆ ወደ ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓት ለመሸጋገር በርካታ ሙከራዎች እያደረገች ነው ብሏል፡፡
በከፍተኛ የህዝብ ትግልና መስዋእትነት የተገኘውንና በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የዘለቀውን የለውጥ ሂደት፣ የከፋ ፈተና ውስጥ የከተተው የዛሬ ዓመት ገደማ በህወኃት የተፈፀመው የክህደት ተግባር መሆኑን በመግለጫው ያወሳው የጋራ ም/ቤቱ ለጦርነቱና ጦርነቱ ላስከተላቸው ምስቅልቅሎች ዋነኛ ተጠያቂ ህወኃት ነው ብሏል፡፡
በዚህ ጦርነት አንዳንድ የውጭ ሃገር መንግስት ተቋማትና ግለሰቦች አገሪቱ ያለቀላት አስመስለው የሚፈበርኩት የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ሃገራችንን ችግር ውስጥ ለመክተት የሚካሄድባትን የሰይጣናዊ ጉዞ ርቀት የሚያሳይ ነው ብሏል-የጋራ ም/ቤቱ መግለጫ ፡፡
የጋራ ም/ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳይ አቋም የወሰደባቸውን ጉዳዮችም በመግለጫው ያስቀመጠ ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን ከተጋረጠባት አደጋ ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዚህ ፈታኝ ወቅት ሁሉም ዜጋ በተለይ የቀድሞ ሠራዊት አባላትና የውትድርና ስልጠና ያላቸው ሁሉ ነቅተውና ተደራጅቶ አገራቸው የምትጠይቀውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያን ከውጭም ሆነ ከውስጥም ችግር ፈጣሪዎች እንዲጠብቁ፤ በዚህ ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋም ላይ መንግስት ትኩረት እንዲያደርግ ዜጎችም እንዲረባረቡ የጋራ ም/ቤቱ ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት አጠያያቂ አለመሆኑን ያወሳው የም/ቤቱ መግለጫ፤ በትግበራ ወቅት የንፁሃን ዜጎችን በተለይ የትግራይ ተወላጆች  እንግልት እንዳይደርስባቸው አፈፃፀሙ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግስት በቀጣይ በሚኖረው የአገራዊ መግባባት መድረክ ገለልተኛ ሆኖ ሂደቱ የሚጀመርበትንና የሚፈጥርበትን ሁኔታ በማመቻቸት ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች የ21ኛው ክ/ዘመንን  በሚመጥን ደረጃ የሃሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል የጋራ ም/ቤቱ፡፡

Read 11202 times