Saturday, 13 November 2021 12:50

የአሸባሪው ቡድን አዲስ አበባን የሽብር ቀጠና የማድረግ ሴራ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(12 votes)

  ሽብርተኞች የተለያዩ የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብሶች በመልበስ ለመንቀሳቀስ እንዳቀዱ ስለተደረሰበት ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት  እንዲጠብቅ መመሪያ ተላልፏል

    • በከተማዋ ለ3 ቀናት ብቻ በተካሄደ የቤት ለቤት ፍተሻ ተተኳሽ የቡድን መሳሪያዎች፣ በርካታ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ በተሽከርካሪ ተጭነው ወደ  ከተማዋ የገቡ መትረየሶች፣ የጦር ሜዳ መነጽሮች፣ መገናኛ ሬዲዮኖች፣ ወታደራዊ ማዕረጎችና የውጭ አገር ገንዘቦች ተገኝተዋል
   • የሽብር ተልዕኮ ተሰጥቷአቸው በቤተእምነቶችና በፀበል ቦታዎች የሃይማኖት አባትና ፀበልተኛ በመምሰል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎች
     በቁጥጥር ስር ውለዋል
   • ሀሰተኛ ሰነዶችና የማዘጋጃ መሳሪያዎች እንዲሁም በግለሰብ እጅ ሊገኙ የማይገባቸው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሰነዶችም ተገኝተዋል
   • መኖሪያና ንግድ ቤቶችን፣ መጋዘንና ተሸከርካሪዎችን ያከራዩ የከተማዋ ነዋሪዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለፖሊስ ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዟል
   • ከ27 ሺ በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ተደራጅተው የከተማዋን ጸጥታ እየጠብቁ ነው

            ከአሸባሪው የህውሃት ቡድን የተሰጣቸውን አዲስ አበባ ከተማን የሽብር ቀጠና የማድረግ ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ተጠርጣዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና፤ ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት 3 ቀናት ብቻ ባደረገው የቤት ለቤት ፍተሻ፣ በርካታ ተተኳሽ የቡድን መሳሪያዎች፣ በተሸከርካሪ በድብቅ ተጭነው ወደ ከተማዋ የገቡ በርካታ ክላሽና ጠመንጃዎች፣ መትረየሶችና፣ ቦንቦች፣ የብሬን ጥይቶች፣ ኤስኬኤስ ጠመንጃዎች፣ የጦር ሜዳ መነጽሮች፣ የፀጥታ አካላት መገልገያ ቁሳቁሶች፣ የመገናኛ ሬዲዮኖች፣ ወታደራዊ ኮምፓስ፣ ወታደራዊ ማእረጎችና አልባሳት፣ ሀሰተኛ ሰነዶች ከነማዘጋጃ መሳሪያዎቻቸው፣ በግለሰቦች እጅ ሊገኙ የማይገባቸው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሰነዶችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መሰረት በማድረግ ለከተማዋ ፀጥታና ለህዝቡ ደህንነት ስጋት ናቸው ባላቸው ግለሰቦች መኖሪያና ንግድ ቤቶች ለ3 ቀናት ብቻ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ የተገኙት ወታደራዊ ቁሳቁሶችና የጦር መሳሪያዎች፣ የከተማዋን ፀጥታ ለማደፍረስና የሽብር ተግባር ለመፈጸም ታስቦ የተዘጋጁ እንደነበሩም አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርገው እንደተናገሩት፤ ሽብርተኛው ቡድን በአገር ህልውናና ሉአለዊነት ላይ አደጋ ለማድረስ በማቀድ፤ ለእኩይ ዓላማው መሳካት በተለያዩ  የአገራችን አካባቢዎች አባላቶቹን ስደተኛ አስመስሎ አስርጎ በማስገባት፣ በንፁሃን  ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ፣ ዝርፊያና ሌሎችም ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላባቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ከግምት ውስጥ በማስገባት የፀጥታ ኃይሉ የፀጥታ ደህንነት የጋራ ግብር ኃይል አቋቋሞ እየሰራ ይገኛል። በዚሁ መሰረትም ግብረሃይሉ ከህብረተሰቡ የሚደርሰውን መረጃ በመቀበልና በመተንተን፣ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የሽብር ቡድኑ ደጋፊ በሆኑና በተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖሪያና ንግድ ቤቶች ላይ ፍተሻ በማድረግ የጦር መሳሪያዎችንና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን፣ የከተማቸ የአሜሪካ ዶላር፣ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች፣ የዝሆን ጉርስ፣ ሀሰተኛ መታወቂያና ልዩ ልዩ ሰነዶች፣ ፓስፖርቶች መያዛቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የሽብር ቡድኑ አባላት የፀጥታ አካላቱ ክትትልና ቁጥጥር ሲጠናከርባቸው በተለያዩ ስፍራዎች የጣሏቸው ፈንጂዎችና ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች በህዝብ ጥቆማ መያዛቸውንም ገልፀዋል።
የሽብር ቡድኑ ለተልዕው መሳካት የመለመላቸውና ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያመላከቱት ኮሚሽነሩ፤ በቤተ እምነቶችና በፀበል ቦታዎች የሃይማኖት አባላትና ፀበልተኛ በመምሰል፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች በመምሰል እንዲሁም ሃሰተኛ መታወቂያ በመያዝና ሰላማዊ ዜጋ በመምሰል የገቡና ተልዕኮ ወስደው የተሰማሩ ግለሰቦችም በአሰሳ መያዛቸውንና ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የተቋቋመ የደህንነትና የፀጥታ ግብረሃይል እንደገለጸው፤ የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ለመግታት መንግስት እየወሰደ ያለውን ህጋዊ እርምጃ በመደገፍ፣ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በከተማዋ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ተከራይተው በጋራ የሚንቀሳቀሱ፣ ሰዋራ ስፍራ በመምረጥ የሚገናኙ የሽብር ቡድኑ አባላትና ደጋፊዎች መኖራቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ መኖሪያና ንግድ ቤቶች፣ መጋዘኖችና ተሽከርካሪዎችን ያከራዩ ሰዎች የተከራዮችን ማንነት በጥንቃቄ በማጣራት መረጃውን በአስቸኳይ  ለፖሊስ እንዲያሳውቁ አዝዟል።
ከዚህ በተጨማሪም የሽብር ቡድኑ ህብረተሰቡን ለማደናገር በከተማዋ ውስጥ የተለያዩ የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ለመንቀሳቀስ ማቀዱን ስለተደረሰበት ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን በሚመለከትበት ወቅት በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታና ደህንነት ተቋም እንዲያሳውቅ ተጠይቋል።
ይህንን የሽብር ቡድኑን የሽብር እንቅስቃሴ ለመቆጣጣር ከ27 ሺ በላይ የከተማዋ ወጣቶች ተደራጅተው ከተማዋን እየጠበቁ እንደሚገኙ ተገልጿል።
“እኔ የከተማዬ የሰላም ዘብ ነኝ” በሚል መሪ መልዕክት፣ 27ሺ 540 የሚሆኑ ወጣቶች ከመሃል ከተማ እስከ መውጫና መግቢያ በሮች ድረስ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት ጥበቃ እያደረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለከተማዋ ነዋሪዎች ባስተላለፈው መልዕክትም፤ የሽብር ቡድኑ በከተማዋ ውስጥ የጻጥታ ስጋት ለመፍጠር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲከታተለውና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከትም ለፀጥታ አካላት ጥቆማና መረጃ በመስጠት እንዲተባበርና የከተማዋን ፀጥታ በጋራ እንዲጠብቅ አሳስቧል።

Read 12103 times