Saturday, 13 November 2021 12:57

ሽርሽር በገነት አጸድ ውስጥ

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

   (የሜሪ ሀስከልና የካህሊል ጅብራን ጥቂት ደብዳቤዎች ለቅምሻ)
                         
            [ከሜሪ የግል ማስታወሻ  የተወሰደ]
    ቦስተን
ሚያዚያ 20፣ 1911 (እ.ኤ.አ)
[ለእግር ጉዞ] ከስዊንበርን (swinburne) ተነሳን፡፡ እየሳቀ...
‹‹እዚህ ያሳለፍኩት ጊዜ ምንኛ ውብ ነበር! እዚህ ስሆን ብቻ ሕይወትን ኑረትን በሙላት አስተናግዳለሁ፡፡ በሌላ ጊዜና ሌላ ቦታማ በድን ነኝ፤ ግዑዝ፡፡›› አለኝ፡፡
‹‹ውስጤ እንዲሰክንና ግለት እንዲሰማኝ ታደርጊኛለሽ፡፡ ለምንም አይደለም ምፈልግሽ... በቃ ስክነትን የተላበሰ፣ ጥርት ያለ  ግለት እንድትፈጥሪብኝ ብቻ...››
እያየሁት አደገ፡፡ በፍጥነት እየጎለመሰ፣ እየተመነደገ ሄደ፡፡ በሥራው፣ በሕይወቱ ብቻ ሳይሆን በሚናገራቸው ሀቲቶች ጭምር ዕድገቱን አስተውያለሁ፡፡ ግላዊ ሕይወቱ ሳይቀር የተሻገረ መልክ ይዞ፣ ከሌሎች ጋር ተጋምዶ፣ ጉልህ እየሆነ ሌሎችን እያስጠለለ በለፀገ፡፡ ከመጠነኛ ስሜታዊነቱ ጋር በተሰናሰለ ጨዋነቱ ጥልቅ የሆነ የሕይወት ሽግግር እያከናወነ ይመስለኛል፡፡
የሕይወቱና የማንነቱ ግዙፋን መለያዎች እየደመቁ፣ ጉልህና ጽኑ እየሆኑ ሄዱ፡፡ ቀጥሎ ተርታ፣ ገር መሆንን ተካነበት፡፡ ፍቅርን በተመለከተ አዘውትሮ ‹በመገለጥ ውስጥ ነው› የምኖረው ይላል፡፡ ይሄንን ሁሉም ሰዎች ይናገሩታል፡፡ ዘወትር እሰማዋለሁ። ሆኖም እሱ ውስጥ ከቃል ባሻገር ከእርሱ የእንግሊዘኛ ቋንቋ የመግለጽ አቅም በላይ በህልውና ተገልጾ አይቼዋለሁ፡፡ ዳስሸዋለሁ።
***
[ቦስተን]
ሚያዚያ 29፣ 1911 (እ.ኤ.አ)
የእሁድ ውሎዬ የማሰማማር ነበር፡፡ እዚህ ያለህን ውድ ሀብቶቻችንን በሙሉ በረበርኩ፡፡ የተወሰኑትን ግድግዳ ላይ ያልዋሉትን በስስት እየሰረቅሁ አየሁ፡፡ የእኔ የተሻገረ ምስል [ከሌሎች ስዕሎች መካከል] ከቤተ መጻሕፍቱ ምድጃ በላይ ተሰቅላ፣ በጨለማው ውስጥ ወጋገኗ ያበራል፡፡ ‹the foumtain pain› በመመገቢያ ክፍሉ ግድግዳ በኩል ተሰቅላ፣ ውኃ ላይ እንደ በቀለች አበባ ትንሳፈፋለች፡፡ ‹spirit of night› በተቃራኒ አቅጣጫ በፒያኖው በኩል ሩቅና ጥልቅ ቦታ ላይ ያለች ትመስላለች። በወርቅ ቅብ ዓይነት አብረቅራቂ ቀለማት የተሳለችው ክብ ስዕል ‹aching heart›  በጓዳ በር በኩል ግድግዳ ላይ ናት፡፡
የሆነ ምሽት እዚህ የፎቁ አናት ላይ ወይናችንን ይዘን በወጋገኑ መካከል የሰራኸው ነገር... የተበለጠጠ ክስመትን የማይቀምስ ፊት፣ ለጋ ወጣትና በእጇ ነበልባልን የጨበጠች የሆነች ተለቅ ያለች ሴት፡፡ የፎቁ በረንዳ በድንገት ወደ ኤደን ገነት አጸድነት የተቀየረ ያህል ነጻ ከባቢና ጥብቅ መሳሳብ... እባክህ ብዙ ነገሮችን ንገረኝ፡፡ አንዳችስ እንኳን ሳይቀር ሁሉንም ነገር!
***
[ከሜሪ የግል ማስታወሻ የተወሰደ]
ቦስተን
ሚያዚያ 17 1911 (እ.ኤ.አ)
ካህሊል ማክሰኞ ምሽት ለግሪንስ (Greenes) ለማሳየት ያመጣው የንድፍ ደብተሩን ቅዳሜ ዕለት ረስቶት ሄደ፡፡ ይሄን የንድፍ ደብተሩንና ቀይና ብርቱካናማ የአንገት አልባሱን (scarf) ይዤ ከሰዓት በኋላ ወደ ስቱዲዮው ሄድኩ፡፡ ኬ የሚጥመለመል፣ የሚንቀለቀል የሚመስል፣ ቀረብ ሲሉት ምንም ስሜት የማይሰጥ፣ ራቅ ብለው ሲመለከቱት ግን ውበትን በውበት ላይ የተጎናጸፈ የሚመስል ምስል በተመስጦ እያቀለመ ነበር፡፡
እኔም ምልዑነት እየተሰማኝ ግን ምንም ለመናገር ልቤ ዝሎ አጠገቡ ተቀመጥኩ፡፡ ምንም እንቅስቃሴ አላደረኩም፡፡ አንዳንድ አጫጭር መልሶችን ብቻ ሰጥቼዋለሁ፡፡ ግን አጠገቤ በመገኘቱ ብቻ የሕይወት ንዝረት ፍሰት በጉልህ ተሰምቶኛል፡፡
ብርሃንና ሰላም በድንገት ሲያረብብንና ሲከበን ማየቴን ነገርኩት፡፡ በዚያች የቅዳሚት አመሻሽ የሆነ ዓይነት ከፍ ያለ የመቆራኘት፣ የመዋሃድ ስሜት ተላበስን፡፡
ካህሊልም አለ፤ ‹‹እውነትም! ከዚህ በፊት አስቤው የማላቀው አዲስ ዓይነት ውህደት... የሆነ በመካከላችን የተጋረደው፣ በከፊል የከለለን የመጨረሻው ዓይነርግብ የወደቀ ዓይነት፡፡››
‹‹አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም...›› አልኩት፡፡
‹‹አንዳንድ ጊዜ አንተን ከሚቃኝህ ከሚመራህ ስውሩ [ኃይል]፣ ስላንተ ከእርሱ አንደበት የምሰማ ይመስለኛል፡፡››
‹‹እንግዲያውስ ልንገርሽ ያ የሚመራኝ የማይታወቀው ስውሩ ኃይል አንቺ ትመስይኛለሽ፡፡››
ስለ ጋብቻ ሲያስብ ‹‹ታላቅ መሸበር›› ይሰማዋል፡፡ ይህንንም  ያወኩት ራሱ የሆነ ምሽት ነግሮኝ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ሊያገባኝ ይፈልጋል፡፡ ዛሬ ምሽት ለራሴ እንዲህ አልኩ፡፡ ሊያገባኝ የሚፈልገው ጋብቻ ታላቅ፣ ከፍ ያለ ልምምድ ስለሆነና የዘመኑ የተሻሉ ሥራዎችን የከወኑ ጠቢባን ወንዶች ሁሉ ስላገቡ ይሆናል፡፡ ግን ካህሊል ገና ራሱን በሚገባው ልክ በቅጡ መግለጽ እንዳልቻለ፣ እንዳልተገነዘበው ግልጽ ነው፡፡  
ይሄንን ማድረግ ሲችል፣ ‹ሕይወትን በምልዓት ሲቀዳጃት›፣ ያኔ ምናልባት ሊያገባ ይችላል፡፡  
እጅጉን እየወደዱኩት ግን ላገባው እንደማልችል ስረዳ፣ ነጋችን ውስጥ የሚጠብቀን አስቸጋሪ ጊዜ እየተገለጸልኝ ሄደ፡፡
እሱ ግን አለ፤ ‹‹አንቺ እኮ ጉልህ ነሽ፡፡ እና ደግሞ ቅዱስ፡፡ እናስ ቅዱስን ነገር መመኘት ለውጥን መናፈቅ፣ ያንንም ምኞት ወደ መጠቀ ደረጃ የማሻገር መሻት፣ ካለመመኘት ይልቅ መልካም አይደለምን? አንቺ፣ አንቺን ሁኚ፡፡ ልክ እንደማውቅሽ፤ አንቺን ስመኝ ብታገኚኝ እንኳን፣ እባክሽ ችላ በይኝ፡፡››  
                                                                       ሜሪ
***
ኒው ዮርክ
ረቡዕ፣ ግንቦት 10፣ 1911 (እ.ኤ.አ)
በኒው ዮርክ ጎዳናዎች ላይ የምትመለከቺው ሰው በሙሉ አይሁዳዊ ነው፡፡ ቀትር ላይ ሰዎች ለምሳ ሲወጡ በጎዳናው ላይ የምትመለከቺው አይሁድ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ በአስራ አምስተኛው ጎዳና ሁለት ሺህ የሚሆኑ አይሁዳዊያንን አይቻለሁ፡፡ ይህ ነገር አዕምሮን የማናጠብና ለማሰብ የማነሳሳት አቅም አለው። ይህ ነገር እስራኤላዊያን ወደ ባቢሎን ያደረጉትን የምርኮ ጉዞ፣ ወይ በስፔይን የነበራቸውን የሰቆቃ ጊዜያት ያስታውሰኛል። አይሁዳዊያኑን ማየቱ ብቻ አንድን ገጣሚ በግብጽ ስላሳለፉት መከራና በዚህች ምድር (አሜሪካ) ስለሚጠብቃቸው ተስፋ በጥልቅት እንዲያስብ ያስገድደዋል። ምናልባትም ፓሪሳዊያን ወደ ቨርሳይልስ አደባባይ እንደተመሙት፣ እንደዚያው አንድ ቀን፣ በኒው ዮርክ ከተማ የምስራቅ ክንፍ የሰፈሩ አይሁዳዊያንም፣ ወደ አስራ አምስተኛው ጎዳና ይተሙ ይሆናል፡፡
አይሁድ በኒው ዮርክ ከተማ እንደ ንጉሥ ነው፡፡ አስራ አምስተኛው ጎዳና ደግሞ ቤተ መንግስቱ... ታሪክ መልሶ ሠልሶ ራሱን ይደግማል፡፡ ግን ስለ አይሁዳዊው አንድ የማይሻር ሀቅ ይሄውና፡፡ አይሁዳዊ ትንቅንቁን የሚጀምረው ከውልደቱ ቅጽበት ጀምሮ ነው፡፡ ዓለም እንዲያሸንፋት መልሳ ከእጁ ብትወጣ እንኳ እንደገና እንዲያሸንፋት ለማያባራ ግብግብ አሰልፋዋለች፡፡ ሜሪዬ፤ በዚህ አይሁድ በሚሉት የሰው ዘር ልናደንቀው እንጂ ፈጽሞ ልንከውነው የማንችለው፣ የሆነ በትውልዶች ውስጥ የማያቋርጥ እንግዳ ነገር አለ፡፡
አቤት እነዚያ የአንቺ ደብዳቤዎች...! እያንዳንዳቸው ለተራበች ነፍሴ ፌሽታን የሚቸሩ መናዎች ሆነውልኛል፡፡
የሆነ ውብ ነገር ላመጣልሽ እመኛለሁ፤ ውድ ሜሪ፡፡ ከዚህ በፊት ከአንዴም ሁለቴ እንዳደረግሽው፣ አዲስ ስዕል ላይ ዓይኖችሽን እንድታንከራትቺ እፈልጋለሁ፡፡ ታስታውሽ ይሆን? ዓይኖችሽ በመደነቅ ስዕሎቹ ላይ ሲቸነከሩ ልቤ በእጥፍ አድጋ፣ የሕይወት እይታዬ ይበልጥ ጥርት እያለ ሲሄድ ታውቆኛል፡፡ ረስተሺው ይሆን? ይሄው አሁን ደግሞ ‹ዛራስቱራን› ይዤ ወደ አልጋዬ ላመራ ነው፡፡  ከአንቺ ጋር ለማንበብ...
  ***
[በዚህ ጊዜ ከ1916 እስከ 1937 ዓ.ም ሥራ ላይ የነበረው ከቦስተን ኒው ዮርክ ቀጥታ የጀልባ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ሜትሮፖሊታን የሚባል የሌሊት የጉዞ መስመር ነበር፡፡ ]
                               አርታኢዋ
   28 ምዕራብ፣ 9ኛው መንገድ ኒው ዮርክ
  ማክሰኞ መስከረም 19፣ 1911
በጀልባው ላይ ረቂቅና እንቅልፍ የለሽ ሌሊት ነበረኝ፡፡ ጀልባው ልዩ ክፍል አልነበረውም፡፡ የመኝታ ክፍሉ የሚያውክ የሰካራም ሽታን ይሰነፍጣል፡፡ እናም ሌሊቱን የጀልባው ወለል ላይ ከክዋክብትና ምላጭ ከመሰለችው ጨረቃ ጋር አሳለፍኩ፡፡ ቀጥሎ አስደናቂው የማለዳ የጸሐይ ብርሃን ንኝት ቦገግ አለ፡፡ ይህን የመሰሉ አዳሮች ትውስታ ለምንጊዜውም ከአዕምሮ አይጠፋም፡፡ ግር በሚል ሁኔታ ከጸጥታ ጋር የተሰናሰለው የባህሩ ንቅናቄና ንቅናቄው የሚፈጥረው ሕብረድምጽ እንዲሁም ዳርቻቸው በማይለካ የባህር ግዛቶች ላይ የሚከናወኑ ስፍር ቁጥር የለሽ ጸጥተኛ ቀዘፋዎች ሁኔታ፣ ሚሊዮናት ሐሳቦችን እንዳውጠነጥን አነሳሱኝ፡፡
ካህሊል
***
ሕዳር 8፣ 1908
 ፓሪስ
ውድ ሜሪ፤ መከፋት በሚሰማኝ ጊዜ ደብዳቤዎችሽን አውጥቼ አነባለሁ። የከበበኝ ጭጋጋማ ነገር እኔነቴን እንድጠራጠር ሲፈትነኝ ከትንሽየዋ ሣጥን ሁለት ደብዳቤዎችሽን አውጥቼ እንደገና አነባቸዋለሁ፡፡ ደብዳቤዎችሽ እውነተኛ እኔነቴን ያስታውሱኛል፡፡ የሕይወትን ትርክምርክ ሁሉ ከፍ ብዬ እንድመለከት ያግዙኛል፡፡ ውድ ሜሪ፤ ሁላችንም ሰብዓዊያን መንፈሳችን የሚያርፍበት የሆነ የስክነት ጥጋት ያስፈልገናል፡፡ የእኔ የነፍስ ማረፊያ የስክነት አጸድ አንቺ ነሽ፡፡
እነሆ አሁን ደግሞ ከቀለማት ጋር ትግል ይዤልሻለሁ፡፡ ግብግቡ እንዴት አስደንጋጭ መሰለሽ፡፡ የግድ አንዳችን ማሸነፍ ይኖርብናል፡፡ ‹‹ስለ ስዕል ምን ትላለህ ካህሊል?›› የሚል ድምጽሽ ውልብ አለብኝ ልበል? ካህሊል በፍላጎት በተቃጠለ ድምጽ ‹‹ኦ አቤቱ፣  ነፍሴን በቀለማት ላጥምቃት፤ እነሆ የምሽቷን ጀንበር ልሰልቅጥ፣ ቀስተደመናዎቹን ልጨልጥ›› ይልሻል፡፡
የስነ-ስዕል አስተማሪያችን፤ "የምትስለውን ነገር አታቆንጀው›› ይሉናል። ነፍሴም በሹክሹክታ፤ ‹‹ነገርየውን ልክ እንደሆነው አቆንጅተህ ሳለው›› ትለኛለች፡፡
እናስ ውድ ሜሪ፤ ምን አድርግ ትይኛለሽ? ነፍሴን ልከተል ወይስ አስተማሪዎቼን? የተከበሩ መምህራኖቻችን ብዙ ነገር ያውቁ ይሆናል፡፡ ሆኖም ነፍስ ምንጊዜም ለእውነታው ቅርብ ነች፡፡
ውድቅት አልፏል፡፡ በልቤ እስከተሸከምኳቸው ተምሰልስሎቶች ወደ አልጋዬ መሄድ ይኖርብኛል፡፡
ሰላም እደሪ ተወዳጇ፡፡ ዛሬም ዘወትርም እግዚአብሔር ይባርክሽ!        


Read 1065 times