Saturday, 13 November 2021 13:01

ሰማይ እንዳንወጣ ራቀበን፣ምድርን እንዳንጠቀልል ሰፋብን

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 (ሰማይ ከይንድይብ ረሐቐና፣ ምድሪ ከይንጥቐልል ገፊሑና)
የትግሪኛ አባባል

  ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ሩቅ አገር የሚኖር አንድ ባለፀጋ ንጉስ ነበር፡፡ 5 ልጆች አሉት፡፡ ዕድሜው ወደ ሞት እየተቃረበ ሲመጣ ዙፋኑን ለማን እንደሚሰጥ ግራ ይጋባል፡፡ በመጨረሻ ግን አምስቱንም ልጆቹን ይጠራና፤
“ውድ ልጆቼ! እነሆ ሰው ነኝና እንደ ንጉስ ብኖርም እንደ ሰው መሞቻዬ ደረሰ፡፡ ከመካከላችሁ ለአንዳችሁ ዙፋነ - መንግስቴን መስጠት የግድ አለብኝ፡፡ ለዚህ የመረጥኩት መንገድ እናንተን ማወዳደርና የተሻለ ውጤት ያመጣ ስልጣነ መንግስቴን እንዲወርስና ሁላችሁንም በእኩል እይን እያየ፣ ሳያዳላ፣ ስርዐቱን ጠብቆ እንዲያስተዳድር፤ ሌሎቻችሁም ወንድማችሁን አንድም እንደ ወንድምነቱ፤ አንድም እንደ መሪያችሁ አድርጋችሁ በቀና-ዐይንና በፍቅር እያገዛችሁት እንድትተዳደሩና አገራችሁን እንድትጠብቁ ማድረግ ነው፡፡;
ልጆቹ በአባታቸው ማርጀትና መድከም ቢያዝኑም ሌላ ምርጫ ስለሌላቸው፤
“የመወዳደሪያ ጥያቄው ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡
ንጉሱም፤
“እያንዳንዳችሁ፣ በየበኩላችሁ እስከዛሬ ደግ ሰርተናል የምትሉትን እጅግ ትልቅ ነገር አምጡና ንገሩኝ፡፡ የተሻለ ደግ ነገር የሰራውን ልጅ መርጬ እኔ ዳኝነት እሰጣለሁ፡፡ አሁን ሂዱና ነገ ከነገ ወዲያ ተመለሱ” ብሎ አሰናበታቸው፡፡
ልጆቹም ወደየክፍላቸው ሄዱ፡፡
በየፊናቸው ሲያስቡበት ቆይተው፣ ከሁለት ሶስት ቀን በኋላ ሁሉም ወደ አባታቸው ተመለሱ፡፡
ንጉሱም፤
“እህስ እጃችሁ ከምን? ምን ምን ደግ ስራ ይዛችሁልኝ መጣችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
የመጀመሪያው የበኩር ልጅ፡-
“ንጉስ ሆይ፣ አንድ ቀን በሰፈራችን ከፍተኛ የቤት ቃጠሎ ደርሶ አይቼ፣ አንዲት ልጃገረድ ቤት ውስጥ ልትቃጠል ስትል፣ ለነብሴ ሳልሳሳ ገብቼ ተሸክሜ አውጥቼ አድኛታለሁ” አለ፡፡
ሁለተኛው ልጅ ቀጠለ፡-
“ንጉስ ሆይ፤ አንድ አዛውንት አይናቸው በቅጡ የማያይ ናቸውና ገደል አፋፋ ላይ ተንጠልጥለው አይቼ፣ ሰው ጉድ! ጉድ! እያለ ሲተራመስ፣ እኔ አፋፉን ወርጄ፣ ከስር ተሸክሜ አወጣኋቸው፡፡ ነብሳቸው ዳነ” አለ፡፡
ሶስተኛው ልጅ ደግሞ የሚከተለውን ተናገረ፡-
“ንጉስ ሆይ፤ እኔ ደግሞ አንድ ነብስ ያላወቀ ህጻን፣ ከቤቱ ደጃፍ ካለ አውራ ጎዳና ላይ እየዳኸ ሲሄድ፣ ታኮ ያልተደረገለት ከባድ መኪና ወደ ኋላ እየተንሸራተተ መጥቶ ሊደፈጥጠው ሲል፣ ከሩቅ እየሮጥኩ ደርሼ፣ ከጎማው ስር አፍሼ አውጥቼ አድኜዋለሁ” አለ፡፡
አራተኛው ወንድምም፡-
“ንጉስ ሆይ፤ እኔም አንዲት አሮጊት መንገድ ላይ ወድቀው፣ የወደቁበት ድንጋይ ጭንቅላታቸውን መቷቸው ደም ሲፈሳቸው ደርሼ ተሸክሜ ወደ አቅራቢያው ጤና ጣቢያ ወስጄ አሳክሜ አድኛቸዋለሁ!”አለ፡፡
የመጨረሻው ወንድም እንዲህ አለ፡-
“ንጉስ ሆይ፤ እኔ ያደረኩት ቀላል ነገር ነው፡፡ አንድ ቀን አንድ ከዚህ ቀደም በድሎኝ ተጣልተን፣ተደባድበን ተኮራርፈን የነበረ ሰው፣ ዋና ሳይችል ውሃ ውስጥ ገብቶ እየሰመጠ ሳለ እኔ ደረስኩ፤ ሰውየውም "እባክህ በድዬሀለሁና ከመሞቴ በፊት ይቅርታ አድርግልኝ?” አለኝ፡፡ እኔም ወዲያው ልብሴን አወላልቄ ውሃ ውስጥ ገብቼ እየቀዘፍኩ፣ በዋና ይዤው ወጣሁ፤ ዳነ!”
ንጉሱም፤
“ልጆቼ ሆይ! ሁላችሁም የፈፀማችሁት ወደር የሌለው መልካም ነገር ነው፤ የመጨረሻ ትንሹ ልጄ ግን ለበደለው ሰው ይቅርታ ማድረጉን፣ ያንንም በተግባር ማሳየቱን የሚያህል ትልቅ ነገር አይገኝም፡፡  እሱ መንግስቴን ይውረስ። እናንተ ደግሞ፣ ምንም ሳትመቀኙ የተለመደውን የደግነት እገዛችሁን ለግሱት፡፡” ብሎ ልጆቹን አሰናበታቸው፡፡
*   *   *
ይቅር-ባይነት የደግነት ሁሉ የበላይ ነው!! ከእኔ ይቅር ማለት ታላቅ ፀጋን መጎናጸፍ ነው፤ ብጎዳም እኔ ልለፈውና የጋራ ህልውናና ደህንነታችን፣ የጋራ ቤታችን በጠነከረ ሁኔታ ይቆይ ማለት፣ አርቆ አስተዋይነት ጭምር ነው፡፡ የመጨረሻ ትንሹ ልጅ ጠላቱን፣ “እንደሰመጠ ይቅር!” ማለት ተስኖት አይደለም፤ ለጠላቱ ሳይቀር ትምህርት ሊሰጥ የሚችል ልባዊ ደግነት ስላለው ነው! ይህን መቀዳጀት ወደ ፍጹም ፍቅር፣ ያለ ሂሳብ ወደ ሚሰጥ ፍቅር፣ መጠጋት ነው፡፡ በአንጻሩ በስሌት የሚሰጥ ደግነትና ፍቅር፣ "ዛሬ ይህን ባደርግለት ነገ ይሄን ይከፍለኛል" የሚባል ዓይነት ፍቅር ወይም ደግነት ዞሮ ዞሮ ወደ ንግድ የሚመደብ ነው! ዲሞክራሲም በተናጽሮ ሲታይ ይህን መሳይ ባህሪ አለው፡፡
ዲሞክራሲ ያለ ሂሳብ በንጹህ መልኩ ሲተገበር ደግነት አለበት፡፡ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ በሚታሰብ ትከፍለኛለህ ሲባል ግን ዞሮ ዞሮ መግቢያው ንግድ ይሆናል፡፡ ያ ንግድ ደግሞ በትክክለኛ ዋጋው የሚነገድ አይደለም፡፡ “ዋናውን ከመለሰልኝ ይበቃኛል” በሚል ተጀምሮ፣ “ባመጣሁበት ውሰደው” እየተባለ  ስንጥቅ ይተረፍበታል፡፡ ውሎ ሲያድር ደግሞ የተትረፈረፈ ጥቅም ለማግኘት ከእንክርዳድ ደባልቆ መሸጥ ይመጣል፡፡ ቅቤው ሙዝ ይገባበታል፡፡ የማር ጠጅ ይባል የነበረው ሙሉ በሙሉ የስኳር ጠጅ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ (በአራዳ ቋንቋ “የተወጋ ነው” ይባላል) ከዚህም አልፎ “የኔን ሸቀጥ ብቻ ግዛ” ወደ ማለት ይሸጋገራሉ-የተወጋም ቢሆን። “የእኔን ዲሞክራሲ ብቻ ተቀበል” ማለት ይመጣል፡፡ "የተናወጠችው ጀልባ ላይ እኔም አለሁ እኮ፤ ከእናንተው ጋር ነኝ፤ ብንድንም አብረን፣ ብንሰጥምም አብረን ነው" ማለት ይከተላል፡፡ ብቻ እኔንና የእኔን መስመር አትልቀቅ፤ያንን መልክ ለመስጠት እውስጡ ቅድመ ሁኔታ እንደረድራለን። መመሪያ፣ ደምብ፣ ህግ፣ አለማቀፍ የንግድ ህግና የንግድ ውል… እያልን እንቀጥላለን፡፡ “ንጹህ የማር ጠጅ!” የሚል ማስታወቂያ እንለጥፋለን እንደ ማለት ነው!  ከዚያ "ይህን ካልገዛህ ህልውና የለህም" ወደ ማለት እናሳድገዋለን፡፡ እጅ መጠምዘዝ እንጀምራለን፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው እንግዲህ “ስለ ዲሞክራሲ” ሲባል ነው፡፡ “ስለ ሰው ልጆች መብት" ሲባል ነው፡፡ ምናልባት! “ስለ ሶሻል ካፒታል” ሲባል ነው ማለት ያስኬዳል፡፡ ያለንበት ዓለም ይህን ግንዛቤ ከፍ አድርጎ “ግሎባላይዜሽን” ይለውም ይሆናል፡፡ በዚህ ግሎባላይዜሽን ገበያ ዲሞክራሲን በሚያዋጣ ዋጋ እንሸጣለን፡፡ (በአዲስ መልክ የፆም ምግብ ጀምረናል እንደ ማለት ነው) የንግድ ስምምነት እንፈራረማለን፡፡ የብድር ግዴታ ፊርማ እናኖራለን። የዚህ ሁሉ ውስጡ፣ የዚህ ሁሉ ቡጡ፤ የዚያው “የተወጋ ዲሞክራሲ”፣ የዚያው በልካችን የተሰፋ ዲሞክራሲ፣ “በነፃ መስፋፋት” ነው!
የዚያው “የመልካም አስተዳደር” መስፈን መንሰራፋት ነው፡፡ የዚያው “የፍትህና እኩልነት” ዜማ “የተሻሻለ ቅንብር” በእገሌ ሙዚቃ ቤት እየተባለ መለፍለፍ ነው፡፡ ከጥንታዊት ግሪክ ዲሞክራሲ እስከ ዛሬው “ዲሞክራሲ” የሄድንበት መንገድ “የንግድ ህግን” የተከተለ ነው፡፡ ለትርፍ የተቀነበበ በመሆኑ መቼም ቢሆን ሙስና አያጣውም! እርግጥ ሙስናው፤ ዝማሬ-ቃናው ቅኔ ዘረፋና አቋቋሙ ይለያያል፡፡ እንደየ አገሩ የውጪ ምንዛሬ መጠኑም ይለየያል፡፡ እንጂ ውስጠ -ነገሩ አንድ ነው፡፡ የናይጄሪያው ይከፋል፣የኬኒያው ትንሽ መለስ ያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያው ጠየም ይላል፡፡ የሱዳኑም በጣም አልለየለትም ወዘተ.. እንበል እንጂ ሙስና ሙስና ነው!! ሁሉም በዲሞክራሲ ስም፣ ሁሉም በሰፊው ህዝብ ስም፣ ሁሉም በፍትሐዊነት ስም፣ ሁሉም በነፃና አድልዎ- አልባ ምርጫ ስም፣ ሁሉም በሰላም ስም… የሚፈጸም ምዝበራ ነው፡፡ ግለሰብ ሰሪው፣ ፓርቲ ሰሪው፣ መንግስት ሰሪው  አያጨቃጭቅም፡፡ የሙስና  ቦቃ የለውም፡፡ ስለ ዲሞክራሲ ስናወራም፤ የአሜሪካ ተፅዕኖ፣ የእንግሊዝ ተፅዕኖ፣ የፈረንሳይ ተፅዕኖ፣ የጀርመን ተፅዕኖ ያመጣው ወዘተ… ማለትም አያዋጣም፡፡…ዞሮ ዞሮ “ለአምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል” ይላልና መፅሐፉ!
ሀገራችን ከላይ ካለንው የዲሞክራሲ ሂደት ውጪ አይደለችም፡፡ በእርግጥ የራሷ ንቅሳት የራሷ ክትባት የራሷ ዕትብት አላት፡፡ ውስጧ ስንገባ ጓዳ ጎድጓዳዋ ብዙ እንደ መሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮዋ ዘርፈ ብዙ ጣጣ ፈንጣጣ ያለው ነው፡፡ ኢኮኖሚዋና ኢኮኖሚስቷ፣ ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ - የሚባል ዓይነት ነው። ማህበራዊ ኑሮዋና ነዋሪዋ- “የባሰ አታምጣ” የሚል ነው፡፡ ፖለቲካዋና ፖለቲከኛዋ “ሰማይ እንዳንወጣ ራቀብን፤ ምድርን እንዳንጠቀልል ሰፋብን” የሚል፤ ራስ ሳይኖረው ትራስ ፍለጋ የሚዞር ነው!
ስለሆነም፤ ከፊሉ የሞተ ፈረስ ይጋልባል፤ ከፊሉ የሌለ ፈረስ አለኝ ይላል፤ከፊሉ ያገኘውን ፈረስ ከመጋለብ ይልቅ አፉን ይዞ ይጎትታል፡፡ ደግሞ ከፊሉም መውደቁን ረስቶ ብቻውን እየሮጠ፤ አለው እየጋለብኩ ነው፤ ይላል፡፡ ከፊሉ ደግሞ ከፈረሱ ይልቅ ራሱ ያልተገራ ሆኖ ይደነባበራል፡፡ አንዳንዴም ጋላቢው ፈረሱ፤ ተጋላቢው ባለፈረሱ ይሆናል፡፡ ብዙ ዘመን ጋልቤያለሁ የሚለው ደግሞ ራሱም ማርጀቱን፣ ፈረሱም መገጣጠቡንና ማነከሱን፣ ማለክለኩንና አረፋ መድፈቁን ሳያስተውል መጭ ይለዋል….ከዚህ ሁሉ ይሰውረን! የተሻለ ቀን እንመኝ!


Read 11797 times