Saturday, 13 November 2021 13:04

ሻምፒዮኑ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ቡድን

Written by  ግሪም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ዩጋንዳ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በተካሄደው የምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ሀገራት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖች ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ዋንጫውን አሸንፏል፡፡ ከአገር ውጭ በተካሄደ የዞን ሻምፒዮና ላይ ሻምፒዮን በመሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ አዲስ ታሪክ ሰርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ቡድኑ በዙር ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ሁሉንም በማሸነፍ 15 ነጥብ አስመዝግቧል። በመጨረሻው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡድን በኡጋንዳ አቻው ቋሚ ተሳላፊ የነበረችውን በረኛ በቀይ ካርድ አጥቶእና በሁለት ጎሎች ሲመራ  የነበረ ቢሆንም ከኋላ ተነስቶ 3-2 በማሸነፉ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎለታል፡፡
የኢትዮጵያ ተጨዋቾች  በውጤቱ እጅግ በመደሰታቸው ማልቀሳቸውን ያወሳው የካፍ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ዋና አሰልጣኛቸው ሐይለገብርኤል  “በጣም ከባድ ጨዋታ ነበር። ቡድኔ ሙሉ ጨዋታውን በጥንካሬ በመቆየቱ ጠንካራ አመሰግነዋለሁ” ማለቱን ዘግቦታል፡፡ የሴካፋ ዋና ዲያሬክተር አዉካ ጌችዮ  በበኩላቸው ሻምፒዮናው ስኬታማ መሆኑን ለካፍ በሰጡት አስተያየት የገለፁ ሲሆን፤ በፊፋ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ ዝግጅት ለሚያደርጉ ቡድኖች ጥሩ ልምድ እንደተገኘበትም ተናግረዋል፡፡ በሻምፒዮናው አዘጋጇ ኡጋንዳ በ12 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ ኡጋንዳዊቷ ፋውዚያ ኒጄምባ በ11 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢ ሆና ስትጨርስ ኢትዮጵያዊቷ ብርቄ አማረ ኮከብ ተጨዋች ሆና ተመርጣለች፡፡

Read 1769 times