Saturday, 13 November 2021 13:19

“ባማ ኢንተርቴይመንት” የፊልም ተማሪዎቹን አስመረቀ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

       የአገር ባለውለታ ላላቸው የኪነ-ጥበብ ሰዎች ሽልማት ሰጥቷል፡፡

            በአርቲስት ገዛኸኝ ጌታቸው (ገዜ) የተቋቋመውና በፊልምና ሌሎች ኪነ-ጥበቦች ዙሪያ የሚሰራው “ባማ ኢንተርቴይመንት” ለአራተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 120 የፊልም ተማሪዎቹን ባፈው እሁድ በኦሊያድ ሲኒማ በድምቀት አስመረቀ፡፡
የአገር ባለውለታ ናቸው ያላቸውን አንጋፋና ወጣት የኪነ-ጥበብ ሰዎችን በመሸለምና እውቅና በመስጠት አመስግኗል፡፡ መቀመጫውን አዳማ (ናዝሬት) ያደረገው ባማ ኢንተርቴይመንት ተሰጥኦና ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች በመመልመል የነፃ ትምህርት (ስልጠና) እድል በመስጠት ለአገር ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራ በመዝለቁ በከሉል ከፍተኛ ሚናን እየተጫወተ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በእለቱ የተመረቁ የፊልም ሰልጣኖች ለማሳየት ያቀረቧቸው አጫጭር ፊልሞችም ሆነ ከዚህ በፊት በዚሁ ድርጅት ሰልጥነው የተመረቁ ባለሙያዎች ለእይታ ያቀረቧቸው   ፊልሞች የአርቲስት ገዛኸን ጌታቸውን ጥረትና ልፋት ውጤት ያሳዩ እንደነበሩ ታዳሚያን ገልጸው፣ወጣቱ ይህንን ሲሰራ ያለ ደጋፊና ያለ እረዳት መሆኑ ቅር እንደሚያሰኛቸው ተናግረዋል፡፡
በዕለቱም የናዝሬት ተወላጁን ደራሲ ሀይሉ ፀጋዬንና አንጋፋዋን አርቲስ ፍቅርተ ደሳለኝ (ማሚ)ን ካባ በማልበስ ያከበረና የሸለመ ሲሆን በከተማዋ አዳማ በጎ በመስራትና ለድሆች በመድረስ የምትታወቀውን ቆንጅት ሁሴንን ጨምሮ ለበርካታ አርቲስቶች የዘፈንና የግጥም ዜማ የሰጠውን ገጣሚ ከድር አሊን፣ዘሪሁን አስማማውንና፣ናታይ ጌታቸውን፣ የፊልም መምሀር ፕሮዲዩሰርና ተዋናይት ማህሌት ሰለሞንንና በርካቶችን ሸልሟል፡፡
አርቲስት ገዛኸኝ ጌታቸው (ገዜ) በግል ጥረቱም ቢሆን የኪነ ጥበብ ፈርጥ የሆኑ ወጣቶችን ለማፍራት ጠንክሮ እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡ በዚህ የምረቃ ስነ-ሥርዓት ላይ ሙዚቃና የተማሪዎች በርካታ ፊልሞችና ድራማዎች ለታዳሚ ቀርበው ነበር፡፡Read 10224 times