Saturday, 13 November 2021 13:24

አሜሪካና አጋሮቿ ለአማፂው "አገር" ይግዙለት

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(5 votes)

  ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት እየተዋጋች ነው
                             
           እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለችው ከአንድ ወይም ሁለት ቡድኖች ጋር ብቻ አይደለም። የትየለሌ ናቸው። በአንድ በኩል አሜሪካና አጋሮቿ፣ ኢትዮጵያን መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተዋታል። የጸጥታው ም/ቤት የጎን ውጋት ሆነውባታል - ለኢትዮጵያ። የተመድ የፀጥታው ም/ቤት ባለፈው ሳምንት ለ12ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተሰብስቧል፡፡ (ሌላ ሥራ የለውም?)  ም/ቤቱ እንደተለመደው ተፋላሚዎች፣ በአስቸኳይ ጠብመንጃቸውን አውርደው፣ ወደ ድርድር እንዲመጡ አሳስቧል፡፡  ውሳኔው እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ በደፈናውና ኢትዮጵያን በመውቀስና በመክሰስ የተላለፈ ነበር - በተለይ ከአሜሪካ፡፡
"ለትግራይ ክልል የምግብ እርዳታ ለመስተጓጎሉ ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግስት ነው።"
"በትግራይ እየተባባሰ ለመጣው የረሃብ አደጋ ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግስት ነው።"
 "የምዕራቡ ዓለም ለሚወተውተው የተኩስ አቁም እውን አለመሆን እንቅፋቱ የኢትዮጵያ መንግስት ነው።"
"በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው፣ በ72 ሰዓት ውስጥ ከአገር ለተባረሩት የተመድ ከፍተኛ ሃላፊዎች ተጠያቂው አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት ነው።"
አሜሪካና ተመድ፣ ከኢትዮጵያ የተባረሩትን የድርጅቱን ሰራተኞች ጉዳይ፣ በራሳቸው አጣርተው እውነቱን ከማረጋገጥ ይልቅ መንግስትን ማስጠንቀቅ ነው የሚቀናቸው፡፡ (አገሩ ግን የማነው?) ምንም ወንጀል ቢሰሩ፣ የኛን ሰራተኞች አትንኩብን ይመስላል። ሰሞኑን ደግሞ የእነ አሜሪካና ሲኤንኤን ውንጀላና ጩኸት ተባብሶ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ለምን ቢሉ?  ባሳለፍነው ሳምንት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ፣ በአዲስ አበባ 16 ያህል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ያስታወቁ ሲሆን፤ 72 የዓለም ምግብ ፕሮግራም የከባድ መኪና ሹፌሮች ደግሞ በአፋር ክልል ሰመራ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል።
የአሜሪካ መንግስትም ተጣድፎ መግለጫ አውጥቷል - “የተመድ ሰራተኞች እስር አሜሪካን ያሳስባታል፤ ማንነትን መሰረት ያደረጉ እስሮች በፍጹም ተቀባይነት የላቸውም” የሚል፡፡
ሰሞኑን ለአሸባሪው ቡድን ድጋፍ ያደርጋሉ በሚል የተጠረጠሩ አያሌ ግለሰቦች፣ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ተከትሎም፣ ማንነት ላይ ያነጣጠረ እስር እየተፈጸመ ነው የሚል ውንጀላም በእነ CNN መሰራጨት ጀምሯል - (ፌክ ኒውስ እንዲሉ!) እነ አሜሪካና  ሚዲያዎቻቸው ያሻቸውን ይበሉ። እኛ ሥራችንን እንስራ። ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚደረገው ኦፕሬሽን፣ ልዩ ጥንቃቄና ትኩረት ይፈልጋል - ንፁሃን  እንዳይንገላቱ። የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም። በተረፈ ግን የህልውና ጦርነት ላይ ነን።  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡
 የአማጺው ሃይል ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ከCNN ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፤ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው የትግራይ ተወላጆችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንዲመቸው ነው ሲል ወንጅሏል። (ግን ለምን?) በእርግጥ በጌታቸው ረዳ  መፍረድ አይቻልም። ለምን ቢሉ? ህወሃት ሥልጣን ላይ ሳለ የአስቸኳይ ጊዜ ለምን እንደሚያውጁ ጠንቅቆ ያውቀዋል። (እንደዛ መስሎት ነው!)
በዚያው የCNN ቃለ መጠይቅ ላይ የአማጺው ቡድን ደሴን ሲወር፣ 100 ወጣቶችን ስለ መግደሉ የተጠየቀው ጌታቸው ረዳ፤ ውንጀላውን ሽምጥጥ አድርጎ ክዷል። (የፌደራል መንግስቱ የሚያስወራብን ነው በማለት) ጋዜጠኛዋ ታምነዋለች ብዬ አላስብም። ነገር ግን ማስረጃ ሳትይዝ ስለጠየቀችው፣ ልታፋጥጠው እንኳን አልቻለችም። (ማፋጠጥ ባትፈልግስ?) ለነገሩ በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ ጌታቸው ረዳ፣ አንድም እውነት ስለመናገሩ እርግጠኛ አይደለሁም።
የCNN ጋዜጠኛዋ በዚያው ቀን ከጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ብሌን ስዩም ጋር ቃለ ምልልስ  አድርጋለች- መላ ኢትዮጵያውያን ያደነቁት፡፡ ጋዜጠኛዋ ገመረጃ የምትፈልግ ሳይሆን የኢትዮጵያን መንግስት ወይም ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን መገሰጽ የፈለገች ነበር የሚመስለው፡፡ ደግነቱ ፕሬስ ሴክሬተሪያቷም  የዋዛ አይደለችም። የመጀመሪያውን ጥያቄ ከመመለሷ በፊት፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እነ ሲኤንኤን ቢቢሲ፣ አልጀዚራና ሮይተርስን የመሳሰሉ የምዕራብ ሚዲያዎች፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚያቀርቡት ሃሰተኛና የተዛባ ዘገባ ሳቢያ ማዘናቸውን አስታውቃለች - ጋዜጠኛዋ ብትንጨረጨርም፡፡ እውነት ለመናገር የጠ/ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት "የሳምንቱ ጀግኒት” ነበረች - ለኢትዮጵያውያንና ለእውነት ወዳጆች!
ባለፈው እሁድ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ትዕይንተ ህዝብ የመዲናዋ ነዋሪዎች እነ ቢቢሲን፣ ሲኤንኤንና አልጀዚራን "ፌክ ኒውስ; - ዜና ፈብራኪዎች ሲሉ ተቃውመዋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ገፅታ ለማጠልሸት ተናበው የሚያደርጉትን ዘመቻም አውግዘዋል፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ግን አይደለም። ሰሞኑን በዋሺንግተን ዲሲ ነጩ ቤተ መንግስት ደጃፍ ላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሰልፍ የወጡ ሲሆን፣ እነዚህን የምዕራብ ሚዲያዎች “ፌክ ኒውስ” እያሉ አውግዘዋቸዋል። (ሲያንሳቸው ነው!) በዲሲው ሰልፍ ላይ ትኩረቴን ከሳቡት መፈክሮች መካከል - “Ethiopia is not America’s 51 state” (ኢትዮጵያ የአሜሪካ 51ኛዋ ግዛት አይደለችም) የሚለው ይጠቀሳል። “አገራችንን ተውልን” እንደማለት ነው። (የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ከገባው!) ግን አይመስለኝም። ለምን መሰላችሁ? ምዕራባውያኑ እየመረጡ ነው የሚሰሙት - የሚፈልጉትን ብቻ!!
 ወደ ሲኤንኤን ቃለ-ምልልስ ልመልሳችሁ። ጋዜጠኛዋም  በተመሳሳይ እየመረጠች ነው  የምትሰማው - የምትፈልገውን ቭቻ፡፡ ፕሬስ ሴክሬተሪዋ ነገሮችን በርጋታ ልታስረዳ ብትሞክርም እንዲገባት አልፈለገችም። ዋና ትኩረቷ፤ የኢትዮጵያን መንግስት- በተለይም ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን መውቀስ… መወንጀል… ማሳጣት ነው የሚመስለው። ጠ/ሚኒስትሩ ሰሞኑን “ኢትዮጵያን የሚያፈርሷትን ቀብረን አገራችንን ቀና እናደርጋታለን” ወይም "ሁሉም አካባቢውን በትጋት ይጠብቅ” ወዘተ ሲሉ የተናገሩትን መዝዛ አውጥታ የጥላቻ ንግግር (hate speech) በሚል ዓይነት መፈረጅ መከራዋን በልታለች።  ማስረጃዋ ደግሞ ፌስቡክ፣ ይህን የጠ/ሚኒስትሩን ጽሁፍ፣ "ግጭት ይቀሰቅሳል” በሚል ከገጻቸው ላይ ማንሳቱ ነው። በጣም የገረመኝ ግን አንድም ጊዜ የአማጺ ቡድን፣ በአማራና አፋር ክልሎች ለወራት የፈጸማቸውን ዕልቂትና ውድመት ተሳስታ እንኳን አለማንሳቷ ነው። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው ጦርነትና ሰብአዊ ቀውስ ሁሉ ተጠያቂው “የሰላም የኖቤል ተሸላሚው” ዐቢይ አህመድ  ነው። ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ ራሷ- - በሲኤንኤን ዕይታ!!
በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት “አሸባሪ” ተብሎ የተፈረጀውና ህዝቦችን ከስሙ በላይ እያሸበረ ያለው የህወሃት አማፂ ቡድንስ? እነ ሲኤንኤን እና አሜሪካ አያውቁትም። ለእነሱ አሸባሪ አይደለም። የጭቁኑን ህዝቦች ነፃ አውጪ ወይም ሽምቅ ተዋጊ ነው። ዋሺንግተን ዲሲ ላይ አሸብሮ አያውቅማ። የሽብር ሜዳው በአማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ ወለጋ ወዘተ ነው። ምናልባት በእነሱ የሳተላይትና ኮሙኒኬሽን መሣሪያ እገዛ አዲስ አበባ ከገባና እንደሚቃዠው የዶ/ር ዐቢይ መንግስትን ለፍርድ ለማቅረብ ካሰበ ራሱ እጁን ይስጥ፡፡ 100 ዓመት የሚያሳስር ወንጀል ነው የፈጸመው፡፡ (እነ አሜሪካ ግን ቡድኑ በኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ፣ኢትዮጵያውያንን ሲጨቁን እንደኖረ አውቀው ዘንግተውታል!)
 ለዚህ ነው ህፃናትን ጠብመንጃ አስታጥቆ፣ ለጦርነት ሲያሰልፍ፣ በጦር ወንጀለኝነት ከመክሰስ ይልቅ  እነ ኒውዮርክ ታይምስ ድርጊቱን አዳንቀው፣ መሳሪያ የታጠቁ የትግራይ ህፃናትን ፎቶ ይዘው የወጡት፡፡ ለነገሩ አማጺው ቡድን፣ የክራይስስ ግሩፑን (የግጭት ቡድን!) ዊሊያም ዴቪሰንን፣ የቢቢሲው አሌክስ ባልድዊንን የመሳሰሉት ጌታቸው ረዳን የሚያስንቁ የህወሃት ተሟጋቾች ናቸው (ያውም እውነትን እየሸመጠጡ!)
ለማንኛውም የህወሃትን አማፂ ቡድን ምስኪን ወይም ሰላማዊ አድርገው ለሚያስቡ አሊያም እንደምንም አንድ የስልጣን ዕድል ለሚመኙለት ምዕራባውያን፣ ሰሞኑን የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ በህወሃት ቡድኖች የተፈጸሙ ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት በቅጡ ይመልከቱት። የሚወዱትንና ከውድቀት ሊታደጉት የሚሟሟቱለትን ቡድን ጠንቅቀው ቢያውቁት በኋላ ከመጸጸት ይድናሉ። (ከእነ ክፋቱ ነው የምንወደው ካሉም መብታቸው ነው!) ሌላ 30 ዓመት በመንግስትነት የሚገዛው ወይም የሚያሽከርክረው “አገር” ገዝተው ወይም “ተከራይተው” በስጦታ ሊያበረክቱለት ይችላሉ። በ21ኛው ክ/ዘመን ህዝብ ገዝቶ ወይም ተከራይቶ በስጦታ ማበርከት ግን አይቻልም።
ብዙዎች ዘግይቷል  ብለው የተቹት የአምነስቲ ኢንተርናሽል ሪፖርት፣ እጅግ አሰቃቂ፣ ዘግናኝና አረመኔያዊ ድርጊቶችን ነው የያዘ ነው። በሪፖርቱ መሰረት፤ ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ የህወሃት ሃይሎች በአማራ ክልል የነፋስ መውጫ ከተማን በወረሩበት ወቅት አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋና አካላዊ ጥቃቶችን በነዋሪዎች ላይ ፈጽመዋል። አምነስቲ ያነጋገራቸው 16 ሴቶች፤ በህወሃት ሃይሎች የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
የመደፈር ጥቃት ከተፈጸመባቸው 16 ሴቶች መካከል 14ቱ ጥቃቱ በቡድን እንደተፈጸመባቸው አምነስቲ  አረጋግጧል- በቃለ ምልልስ። (ከዚህ በላይ ሽብር ከየት ይምጣ!)
አንድ የክልሉ አስተዳደር ባለስልጣን ለአምነስቲ እንደገለጹት፣ አማጺያኑ በነፋስ መውጫ ከተማ የቆዩት ከነሐሴ 6 እስከ ነሐሴ 15 ለ9 ቀናት ሲሆን  በእነዚህ ጊዜያትም ከ70 በላይ ሴቶች በአማጺያኑ የመደፈር ጥቃት እንደተፈጸመባው ሪፖርት አድርገዋል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሃፊ አግነስ ካላማርድ፤ “የህወሃት ታጋዮች የፈጸሟቸው አፀያፊ ተግባራት፣ ከጦር ወንጀሎችና በሰብአዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ ናቸው። ድርጊቶቹ ከሞራል ወይም ከሰብአዊነት ያፈነገጡ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
አማጺያኑ ከመድፈር ጥቃት በተጨማሪ በሴቶቹ ላይ ሰብአዊነትን የሚያጣጥል፣ የብሄር ማንነታቸው ላይ ያነጣጠሩ ስድቦችና አዋራጅ ንግግሮች መሰንዘራቸውንም ሪፖርቱ ይጠቁማል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ደግሞ “የመድፈር ጥቃቱን የሚፈጽሙት በትግራይ ሴቶች ላይ የተፈጸመውን ተመሳሳይ ጥቃት ለመበቀል” መሆኑን ይናገሩ ነበር ብለዋል።
በህወሐት ሃይሎች የመደፈር ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ለአምነስቲ አንደተናገሩት፤ ንብረታቸውን አውድመውባቸዋል።
ጌጣጌጦችን፣ ገንዘብና ሞባይል ስልኮችንም  ወስደውባቸዋል። ይሄ እንግዲህ የተፈጸመው በማይታወቅ የሽፍታ ቡድን አይደለም። ዘመኔን ሁሉ ለነጻነትና ዲሞክራሲ ታግያለሁ በሚል፣ ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን ሳይወዳትም ቢሆን በገዛት  ቡድን ነው።  እስካሁን የተባበሩት መንግስታት፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ  እርምጃ ለመውሰድ 12 ጊዜ ተሰብስቧል። በዚህስ ጉዳይ ይሰበሰብ ይሆን? ወይስ  ጉዳዩ ለስብሰባ አይመጥንም? የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያ ወደ ኤርትራ አጓጉዟል የሚል የፈጠራ ዘገባ ያስራጨው ሲኤንኤንስ (ፌክ ኒውስ) ለዚህ አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት  ምን ያህል ትኩረት ይሰጥ ይሆን? ወይስ እንዳላየ እንዳልሰማ ያልፈዋል? አብረን የምንታዘበው ይሆናል። በነገራችን ላይ “ምዕራባውያን እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” የሚለው የዳያስፖራ  ሰልፈኞች  መፈክር ተመችቶኛል። (ቢያነሱም ባያነሱም!)
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
 (Hate speech አይደለም!)


Read 1326 times