Sunday, 14 November 2021 00:00

“የአምላክን ህያውነት” ያስቀጠለ ፋውንዴሽን

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)


              “በመጀመሪያ ትንሽ ድርጅት እሰራለሁ፣ ይህችን ድርጅት አሰፋና ሰራተኛ እቀጥራለሁ፤ አስከ 1 ሺህ 700 ሄክታር በሚገመት ቦታ ዘመናዊ እርሻ ይኖረኛል፤ ከእርሻ በሚገኘው ገቢ ወላጅ ያጡና የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናትን የሚረዳ ድርጅት እሰራለሁ፡፡ የሀገሬን ድህነት ወደ ተንደላቀቀ ኑሮ እቀይራለሁ፡፡ ዩኒቨርቲ እሰራለሁ፤ የሀገሬን ሰዎች ከማይምነት አወጣለሁ፡፡….”
ይህን ከላይ የሰፈረውን እቅድ በማስታወሻው ላይ ያሰፈረው የ10 ዓመቱ ታዳጊ የአምላክ ፍቅር አለባቸው ነው፡፡ የአምላክ ይህንን ሊተገብር ያሰበውም ልክ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ እንደሆነም በማስታወሻው ላይ ጽፏል፡፡
ወላጆቹ አቶ ፍቅርና ወ/ሮ ፅጌረዳ፣ ይህ ልጅ አድጎ እቅዱን እስኪያሳካና ህልሙን እውን እስኪያደርግ ይጠብቁ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ እንዴት ከጎኑ ሆነው ህልሙን እውን እንዲያደርግ እንደሚያግዙትም ጭምር ይመካከሩ ነበር፡፡ የአምላክ ፍልቅልቅ ደስተኛ፣ ንቁና ሩህሩህ፤ በትምህርቱ ጎበዝ ብዙ ነገሮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ያለውና ብሩህ አዕምሮ የታደለ እንደነበር ከወላጆቹ ባለፈ  የሚያውቁት ሁሉ የሚመሰክሩለት ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን የቀጠለው በአሜሪካ ነበር፡፡ አሜሪካም በዩኒቨርስው ውስጥ ባለው ሁለንተናዊ ተሳትገፎ የሚታወቅ፣ በጓደኞቹ የሚወደድና በሙዚቃ መሳሪያም ተጫዋችነቱ ታወቂ እንደነበረ ወላጆቹ ይናገራሉ፡፡
የአምላክ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ከ3.8 በላይ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ነበር፡፡ ጊዜው 2012 ዓ.ም ሲሆን ወቅቱ ከፍተኛ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም በተለይም በአሜሪካ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለበት ስለነበር አቶ ፍቅርና ወ/ሮ ፅጌረዳ ልጃቸውን ለማስመረቅ ወደ አሜሪካ መሄድ አልተቻላቸውም፤ ይልቁኑም ወደ ሀገሩ ሲመጣ እዚሁ በደማቅ ስነ ስርዓት ምርቃቱን ሊያዘጋጁ ሽርጉድ እያሉ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በአሳዛኝ ሁኔታ  የአምላክ በተመረቀ በሁለት ወሩ በተወለደ በ23 ዓመቱ በድንገት ህይወቱ አለፈ፡፡
የእሱን መርዶ ለወላጆቹ ለመናገር ለዘመድ አዝማድ ለመንገር ጭንቅ ውስጥ ገብተው እንደነበር የ“የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን” ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቀደ….ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የግድ መስማት ስለነበረባቸው መራሩን የልጃቸውን ህልፈት ሰሙ፡፡ ያላሰቡት ከባድ መከራና ሀዘን የወደቀባቸው እነዚህ ወላጆች፤ የልጃቸውን አስከሬን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትም ሌላ ከባድ ፈተና ገጥሟቸው ነበር፡፡ ይሄ አሳዛኝ ታሪክ ከወራት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ልጁን በሞት የተነጠቀውን አንጋፋውን ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱንና የሱን መሪር ሀዘን ያስታውሰኛል፡፡ ቤቴል እሸቱ እጅግ ንቁ በጎ አድራጊ፣ ለሀገሯና ለወገኗ እድገትና መለወጥ ከእድሜዋ በላይ የምትታትር በትምህርቷና  ጉብዝናዋ የት/ቤቷንና ወላጆቿን ስም  በኩራት ከፍ አድርጋ ስታስጠራ  የነበረች ወጣት ናት፡፡  በአሜሪካ የዩቨርስቲ ትምህርቷን አጠናቅቃ ወደ ሀገሯ ልትመጣ በዝግጅት ላይ ሳለች፣ወላጆቿም እሷን ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ በድንገት ህልፈቷ ተሰምቶ ካረፈች ከአንድ ሳምንት በኋላ አስክሬኗ መጥቶ እዚሁ የትውልድ አገሯ መሬት ላይ ዘላለማዊ እረፍቷን አድርጋለች እናም ምንድን ነው ነገሩ እያልኩ ያውም በድንገት እንዴት ህይወታቸው አለፈ? እያልኩ እንዳብሰለስል ሆኛለሁ፡፡ (ብቻ ነፍሳቸውን በሰላም ያሳርፍልን)፡፡
የሆነ ሆኖ የአምላክ አስክሬን ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ወላጆቹና ወዳጅ ዘመዶቹ የአምላክን ህያው የሚያደርግ፣ ይህንን መሪር ሀዘንና መከራ ወደ መልካም አጋጣሚ የሚቀይር አንድ ሀሳብ በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ ይፋ አደረጉ፡፡ ለቀብር ለመጣው ዘመድ ወዳጅ “የአምላክን ህልም እውን የሚያደርግ ነፍሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራ የሚከናወንበት “የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን” የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት መመስረታቸውን ይፋ አደረጉ፡፡ እናም “ለእዝን ይዛችሁ የምትመጡትን ነገር ተውና ወደ ፍራንክ ቀይራችሁ ለዚሁ ጉዳይ ወደ ተከፈተው የባንክ ሂሳብ አስገቡ የሚል መልዕክትም ተላለፈ፡፡ እነሆ “የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን” በቀብሩ እለት እሱን ህያው ሊያደርግ ተመሰረተ፡፡
ፋውንዴሽኑ በአንድ ዓመት ውስጥ አራት ዋና ዋና አዕማዶችን መነሻ አድርጎም በርካታ የበጎ ስራውን ሲያከናውን መቆየቱን ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 26 ቀን 2014 ዓ.ም በኢሰመኮ አዳራሽ ይፋ አደረገ፡
ፋውንዴሽኑ ትኩረት ያደረገባቸው አራት ዋና ዋና ጉዳዮች፡- አንደኛ በልዩ ልዩ ምክንያት ቤተሰብ እንዳይፈርስና ልጆች ጎዳና እንዳይወጡ የወላጆችን አቅም በትምህርት፣በስልጠና በምክር በመደገፍ የቤተሰብ ግንባታ ልዩ ትኩረት አድርጎ መስራት ሲሆን፣ሁለተኛው በዝቅተኛ የገቢ መጠን ምክንያት ልጆች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ቤተሰብን መደገፍና ራስን ማስቻል፣በሌላ በኩል በብዙዎች ዘንድ ቀልብን የገዛውና አዲስ የሆነው “አራስ ቤት” የተሰኘው ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ሶስተኛው ፕሮጀክት በጎዳና ላይ ያረገዙና የደረሱ እናቶችን ህይወት ወዳልተጠበቀ አስገራሚ አቅጣጫ የሚቀይርና እስከዛሬ የትኛውም በጎ አድራጎት ድርጅት ያልሞክረው  ነው፡፡ የደረሱ ነፍሰ ጡሮችን በማመሳብሰብና ማረፊያ በማዘጋጀት ሁሉ ነገር ተሟልቶ የአራስ ወጉ ደርሷቸው እፎይ ብለው የሚታረሱበትና ለ6 ወራት ልጆቻቸውን ያለምንም ተጨማሪ ምግብ ጡት የሚያጠቡት (exclusive burst feeding) የሚባለውን መንግስት ሁሌም እንዲሳካ የሚለፍፍበትን ፕሮጀክት እውን የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
እናት ልብሷ፣መኝታዋ፣ምግቧ፣የአራስ ልጅ አልባሳት ተሟልቶላት እፎይ ብላ በአራስ ወግ ትታረሳለች፡፡ ከ6 ወራት በኋላ የአራስ ቤቷን ቆይታ ስትጨርስ የህይወት ክህሎት ሥልጠና፣የቤት ኪራይና የንግድ መነሻ ገንዘብ ተሰጥቷት ንግድ እንድትጀምር  ይደረግና ከጎዳና ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፍቺ ትፈጽማለች፡፡ እድሜ ለየአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን! በዚህ ሁኔታ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከ50 በላይ የጎዳና እናቶች እና ከ40 በላይ ልጆቻቸው ተጠቃሚ እንደሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
ሌላኛው አራተኛው ዋና ፕሮጀክት፤ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ከሱሰኝነት ተላቀው፣ስነ ልቦናዊ ማህበራዊና አካላዊ ተግዳሮቶችን ተቋቁመው እንዲያልፍ እንዲሁም ለሀገር ጠቃሚና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማገዝ ሲሆን ከዚያም ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ ማህበረሰቡ  እንዲቀላቀሉ የማድረግ  ስራ ይሰራል፡፡ ይህም “አምለካ ጎዳና” የተሰኘው አራተኛው ፕሮጀክታቸው ነው፡፡
ፋውንዴሽኑ በታማኝ፣ በእኩልነት፣ በቅንነትና በሞራል ልዕልና እርዳታውን ለሚገባቸው ዜጎች አገልግሎት ለመስጠት ቃል የገባ ሲሆን እነዚህን የአምላክን ህልሞች እውን ለማድረግ ከንፋስ ስለክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ጋር የ3 ዓመት የስራ ውል ስምምነት መፈፀሙንም የፋውንዴሽኑ ሀላፊዎች ተናግረዋል፡፡ በቅዳሜ እለቱ አጠቃላይ የአንድ ዓመት እንቅስቃሴ ሪፖርትና ገቢ ማሰባሰብ ጥሪ መርሃ ግበር ላይ የየአምላክ ቤተሰቦች ፣ወዳጅ ዘመዶች፣በጎ ፈቃደኛ አገልጋዮች በጎ ፈቃደኛ ለጋሾችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል የፋውንዴሽኑ መስራችና የስራ ሀላፊዎች እስከዛሬ ድጋፍ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ምስጋናና እውቅና የሰጡ ሲሆን በቀጣይ ፋውንዴሽኑ ለሚያከውናቸው ተግባራት በገንዘብም በእውቀትም፣በጉልበትም ሆነ በሀሳብ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ በማስተላለፍ መርሃ ግብሩ ተቋጭቷል፡፡

Read 1849 times