Sunday, 14 November 2021 00:00

ፈታኙ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በአፍሪካ ዞን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

    ኳታር በ2022 እኤአ ላይ ለምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን የሚካሄዱት የምድብ ማጣርያዎች የፊታችን ማክሰኞ ይጠናቀቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ  በምትገኝበት ምድብ 7 መሪነቱን ይዞ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የሚገባውን ቡድን ለመወሰን ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ወሳኝ ፍልሚያ ያደርጋሉ፡፡
በምድብ 7 ባለፈው ሐሙስ በአምስተኛ ዙር በተካሄዱት ጨዋታዎች ደቡብ አፍሪካ ዚምባቡዌን 1ለ0 ያሸነፈች ሲሆን፤ በደቡብ አፍሪካ ኦርላንዶ ስታድየም ጋናና ኢትዮጵያ 1 እኩል አቻ  ተለያይተዋል፡፡ ከምድብ ማጣርያው የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች በፊት ደቡብ አፍሪካ በ13 ነጥብና በ5 ግብ ክፍያ መሪነቱን ስትይዝ፤ ጋና ደግሞ በ10 ነጥብ እና በ3 ግብ ክፍያ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡  ኢትዮጵያ በ4 ነጥብ እና በ3 የግብ እዳ ሶስተኛ ደረጃ ስትይዝ ዚምባቡዌ በ1 ነጥብ በ5 የግብ እዳ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ናት፡፡ በምድብ 7 የመጨረሻ ምድብ ጨዋታዎች ጋና በኬፕ ኮስት ስታድዬም ደቡብ አፍሪካን ታስተናግዳለች፡፡ ከምድቡ በመሪነት ለማለፍ ጨዋታው በጣም ወሳኝ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ ማሸነፍ እና አቻ መውጣት ወደ መጨረሻው የማጣርያ ምዕራፍ የሚያስገባት ሲሆን ለጋና ግን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ብቸኛው አማራጭ ይሆናል፡፡  ዚምባቡዌ እና ኢትዮጵያ በሃራሬ የሚጫወቱ ሲሆን የመርሃ ግብር ሟሟያ ከመሆኑ ባሻገር ለሁለቱ አገራት የፊፋ እግር ኳስ ደረጃ መሻሻልም አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
ከምድብ ማጣርያው 6ኛ ዙር ጨዋታዎች በፊት ወደ መጨረሻው ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ማለፋቸውን ያረጋገጡ 3 አገራት ማሊ፤ ሞሮኮና ሴኔጋል ናቸው፡፡ አልጄርያ፤ ቡርኪናፋሶ፤ ቱኒዚያ፤ ኢኳቶርያል ጊኒ፤ዛምቢያ፤ ናይጄርያ፤ ኬፕ ቨርዴ፤ ናይጄርያ፤ መካከለኛው አፍሪካ፤ አይቬሪኮስት፤ ካሜሮን፤ ግብፅ፤ ሊቢያ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ቤኒንና ጋቦን ደግሞ የማለፍ እድል እንደያዙ ናቸው፡፡
ከምድብ 1 ኒጀርና ጅቡቲ፤ ከምድብ 2 ሞሪታኒያ፤ ከምድብ 3 ላይቤርያ፤ ከምድብ 4 ማላዊ እና ሞዛምቢክ፤ ከምድብ 5 ኡጋንዳ ኬንያና ሩዋንዳ፤ ከምድብ 6 አንጎላ፤ ከምድብ 7 ኢትዮጵያና ዜምባቡዌ፤ ከምድብ 8 ቶጎ ናሚቢያ ኮንጎ፤ ከምድብ 9 ጊኒ ቢሳዎ ጊኒና ሱዳን እንዲሁም ከምድብ 10 ታንዛኒያ እና ማዳጋስካር የምድብ ማጣርያው ከመጠናቀቁ በፊት ለመጨረሻው ዙር ማጣርያ እንደማያልፉ ያረጋገጡ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ዞን በምድብ ማጣርያው ከሚከናወኑት የመጨረሻ ጨዋታዎች መካከል ዛሬ ላይቤርያ ከናይጄርያ ፤ በነገው እለት ጋና ከደቡብ አፍሪካ፤ ዲሪ ኮንጎ ከቤኒን እንዲሁም የፊታችን ማክሰኞ ናይጄርያ ከኬፕ ቨርዴ እና ካሜሮን ከአይቬሪኮስት የሚገናኙባቸው ፍልሚያዎች ከፍተኛ ትኩረት የሚስቡ ናቸው፡፡  
ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በዓለም ዙርያ ከሚካሄዱት ማጣርያዎች እጅግ ፈታኙ በአፍሪካ ዞን የሚካሄደው እንደሆነ ይገለፃል። ኳታር ለምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ያልቻሉ አገራት ምናልባትም በ2026 እኤአ ላይ በሰሜን አሜሪካ ለሚዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለማቀድ በቂ ግዜ ይኖራቸዋል፡፡አሜሪካ፤ ካናዳ እና ሜክሲኮ የሚያዘጋጁት 23ኛው የዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ኮታ ለአፍሪካ ዞን ከአምስት ወደ ዘጠኝ ብሄራዊ ቡድኖች እንዲያድግ መወሰኑን ተስፋ በማድረግ ሌላ የማጣርያ እድል ለማግኘት አራት ዓመታት ይጠብቃሉ።
በአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣርያዎቹ ሲጠናቀቁ አስሩን ምድቦች በመሪነት ያጠናቀቁት 10 ብሄራዊ ቡድኖች የሚሸጋገሩት እርስ በእርስ ወደየሚገናኙበት የደርሶ መልስ ትንቅንቆች በመጋቢት 2022 የሚካሄዱ ናቸው፡፡ በዚህ ምእራፍ የሚሳካላቸው 5 አገራት በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን በመወከል የሚሳተፉ ሆኗል፡፡ ከአፍሪካ ዞን ዓለም ዋንጫን ወክለው የሚሰለፉት አምስት ብሄራዊ ቡድኖች ከመታወቃቸው በፊት  የአፍሪካ ዋንጫ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡ ካሜሮን የምታስተናግደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ስምንት ሳምንታት የቀሩት ሲሆን ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከካሜሮን፤ ቡርኪናፋሶ እና ኬፕቨርዴ ጋር መደልደሏ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከጋና ጋር ከሜዳው ውጭ በደቡብ አፍሪካው ኦርላንዶ ስታድዬም መጫወቱን ካፍ ቢወስነውም የደቡብ አፍሪካውን አሰልጣኝ ሁጎ ብሮስ አላስደሰታቸውም፡፡ ጋና በተሻለ ሜዳ ጨዋታ በማድረግ የተሻለ እድል ተፈጥሮላታል በሚል ካፍ እና ፊፋን አሰልጣኙ ወቅሰዋል፡፡ ዋልያዎቹ ከዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን በባህርዳር ስታድዬም ሲያደርጉ ዚምባቡዌን 1ለ0 ቢያሸንፉም በደቡብ አፍሪካ 3ለ1 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው ይታወሳል፡፡  ከዓለም ዋንጫው 4ኛ ዙር የምድብ ማጣርያዎች በኋላ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስታድዬሞች ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ብቁ አይደሉም በሚል እገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡  የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ማኔጅመንት የሚመሩት ሃላፊ ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ ካፍ በባህርዳር ስታድዬም ላይ እገዳውን አስቀምጧል፡፡ ስታድዬሙ ሊታገድ የበቃው  ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ በካፍ ከተቀመጡት 11  መስፈርቶች መካከል ሰባቱን ባለማሟላቱ ሲሆን፤ በተለይ ለቪአየፒ፤ ለህክምና እና የሚዲያ ማዕከላት ሌሎችም ወሳኝ የስታድዬም አገልግሎቶች አለመገኘታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ከባህርዳር ስታድዬም በተጨማሪ የጅማና ሐዋሳ ስታድዬሞቹም የአፍሪካ ዋንጫ እና የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ውድድሮችን፤ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ ጨዋታዎችን ማስተናገድ አይችሉም ተብለው ታግደዋል፡፡ የአበበ ቢቂላ ስታድዬም ብቻ የታዳጎዎች እና ወጣቶች ውድድሮች እንዲሁም በሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለሚካሄዱ ጨዋታዎች የኮንፌደሬሽኑን ፈቃድ አግኝቷል፡፡
ደቡብ አፍሪካዊው የካፍ ፕሬዝዳንት ፒትሶ ሞትሶፔ ወደ ሃላፊነቱ መንበር ከመጡ በኋላ የመጀመርያው ከባድ እርምጃቸው በመላው አህጉሪቱ የሚገኙ ስታድዬሞች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እንዲያሟሉ በፈጣን ቀነ ገደብ ማሳሰባቸው ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያው ላይ ተሳታፊ ከሆኑ አገራት መካከል ስምንቱ  የአምስተኛ ዙር ጨዋታቸውን ከሜዳ ውጭ ለማድረግ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ እነሱም ኢትዮጵያ፤ ሴኔጋል፤ ኒጀር፤ ማላዊ፤ ቡርኪናፋሶ፤ መካከለኛው አፍሪካ፤ ላይቤርያ እና ናሚቢያ ናቸው፡፡
የዋልያዎቹ ዋና አምበል የሆነው ጌታነህ ከበደ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በ32 ጎሎች ከፍተኛው ግብ አግቢ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተጫወተባቸው ያለፉት 11 ዓመታት በሴካፋ፤ በአፍሪካና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች፤ በአፍሪካ ዋንጫ ዋና ውድድር  58 ጨዋታዎችን አድርጎ ያስመዘገባቸው ጎሎች 32 ደርሰዋል፡፡  ጌታነህ ግብ ያስቆጠረባቸው ጋና ፤ ደቢብ አፍሪካ፤ አይቬሪኮስት፤ ማዳጋስካር ፤ ማላዊ፤ ኒጀር ፤ ሱዳን፤ ዛምቢያ፤ ሴራሊዮን፤ ብሩንዲ፤ ጂቡቲ፤ ሲሸልስ፤ ሌሶቶ፤ አልጄርያ፤ ኮንጎ፤ ማሊ፤ ቦትስዋናና ሶማሊያ ናቸው፡፡
በትራንስፈር ማርከት ድረገፅ በዝውውር ገበያው እስክ 150ሺ ዩሮ ዋጋ የተተመነው ጌታነህ በክለብ ደረጃ ከኢትዮጵያ ውጭ በደቡብ አፍሪካዎቹ ቢድቬስት ዊትስ እና ዩኒቨርስቲ ኦፍ ፕሪቶርያ ክለቦች ተጫውቷል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በደቡብ ፖሊስ ክለብ መጫወት ጀምሮ ለደደቢት፤ ለመከላከያ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለቦች የተሰለፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊ ለሆነው ለወልቂጤ ከነማ ክለብ እየተጫወተ ነው፡፡

Read 19892 times