Tuesday, 16 November 2021 00:00

በህይወት የሌሉ የአመቱ ባለከፍተኛ ገቢ ዝነኞች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ቶም ሃንከስ ለ12 ደቂቃ የጠፈር ጉዞ 28ሚ. ዶላር አልከፍልም ብሎ መቅረቱን ተናገረ

                ከዚህ አለም በሞት ቢለዩም በ2021 የፈረንጆች አመት ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ዝነኞችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው ፎርብስ መጽሔት፣ በህይወት ሳለ ከ43 በላይ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃው የህጻናት መጽሐፍት ደራሲው ሮድል ዳል፣ በ513 ሚሊዮን ዶላር የ1ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ደራሲው ለህትመት ካበቃቸው መጽሐፍት መካከል አብዛኞቹ በፊልም መልክ ተሰርተው በስፋት በመታየት ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ፎርብስ፣ ኔትፍሊክስን ጨምሮ ፊልሞቹ በተለያዩ መንገዶች በስፋት መታየታቸው ከፍተኛ ገቢ እንዳስገኘለትም አመልክቷል፡፡
ከ5 አመታት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለየው ታዋቂው ድምጻዊ ፕሪንስ በ120 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ ላለፉት 8 ተከታታይ አመታት በህይወት ከሌሉ ዝነኞች መካከል ከፍተኛውን ገቢ በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃን ይዞ የዘለቀው የአለማችን የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን፣ ዘንድሮ 75 ሚሊዮን ዶላር ብቻ በማግኘቱ ወደ 3ኛነት ዝቅ ብሏል፡፡
የተከታታይ ፊልሞች ፕሮዲዩሰሩ ቻርለስ ሹልዝ በ40 ሚሊዮን ዶላር፣ የህጻናት መጽሐፍትና ፊልሞች ደራሲው ዶክተር ሲዩስ በ35 ሚሊዮን ዶላር የአራተኛና የአምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውንም ፎርብስ አስታውቋል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ዝነኞች መካከልም የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ እና ኤልቪስ ፕሪስሊ ይገኙበታል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ቶም ሃንከስ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ባለፈው ወር ወደ ጠፈር ባደረጉት ታሪካዊ ጉዞ አብሯቸው እንዲጓዝ ጥያቄ አቅርበውለት እንደነበርና እሱ ግን ክፍያው እጅግ ሲበዛ ውድ ነው በማለትና ግብዣውን ባለመቀበል ከጉዞው መቅረቱን ከሰሞኑ በይፋ መናገሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
12 ደቂቃዎችን በፈጀውና የ28 ሚሊዮን ዶላር ትኬት በተቆረጠበት የጠፈር ጉዞ ላይ እንዲሳተፍ ከጉዞው አዘጋጅ ኩባንያ ብሉ ኦሪጅን ባለቤት የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ጄፍ ቤዞስ ግብዣ ቀርቦለት እንደነበር ያስታወሰው ቶም ሃንከስ፣ ምንም ሃብት ቢኖረኝ ለ12 ደቂቃ በረራ 28 ሚሊዮን ዶላር አልከፍልም፤ በጣም ውድ ነው በማለት ሃሳቡን እንዳልተቀበለው ነው የተናገረው፡፡
የ65 አመቱ የኦስካር ተሸላሚ ቶም ሃንከስ፣ ለ12 ደቂቃ ጠፈር ደርሼ ለመምጣት 28 ሚሊዮን ዶላር ምን አስወጣኝ፤ እዚሁ ሆኜ በምናብ ደርሼ መምጣት እችል የለ እንዴ ብሏል፡፡ እያንዳንዳችን ባለንበት ሆነን ወደ ጠፈር የመጓዝን ስሜት ልንፈጥረውና ወንበራችን ላይ ሆነን ጠፈር ላይ የወጣን ያህል እንዲሰማን ማድረግ እንችላለን ማለቱም ተነግሯል፡፡


Read 7767 times