Monday, 15 November 2021 00:00

የዋረን ብፌ አስገራሚ እውነታዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኢንቨስትመንት ዘርፍ በተቀዳጁት የላቀ ስኬት የሚታወቁት አሜሪካዊ ቢሊየነርና ችሮታ አድራጊ ዋረን በፌ፤ እንደማንኛውም ሰው ብዙ ችግሮችና ውጣ ውረዶች ተጋፍጠዋል ሳያሰልሱ ተግተው በፅናት በመስራት ግን የስኬት ማማ ላይ ሊወጡ ችለዋል፡፡
የዓለማችን ቁጥር 1 ባለጸጋ ሊሆኑም በቅተዋል፡፡ በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ለችሮታ አድራጊዎች በመለገስም ስማቸው ይነሳል፡፡
 በፌ ገና በ11 ዓመት ዕድሜው ላይ ነበር የመጀመሪያውን አክስዮን የገዛው፡፡ ኮካ ኮላና አይስክሬም የሰጠ ይድከም ነው፡፡ በእርግጥ የኮካ ኮላ ትልቅ የአክስዮን ድርሻ አለው፡፡ የትዊተር አካውንት ቢኖረውም ተጠቅሞበት አያውቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ105.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያለው ሲሆን ይህም የዓለማችን 10ኛ ባለፀጋ ያደርገዋል፡፡
የቢሊኒየሩን አስር አስገራሚ እውነታዎች እንዲህ አጠናቅረነዋል፡፡ የልጅነት ዘመኑን “አንተ” እያልን እንዘልቅና ወደ ጉልምስና ዕድሜው ላይ “አንቱ” እያልን እንደምንተርክ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን፡፡ እነሆ የቢሊኒየሩ አስገራሚ እውነታዎች፡፡
በፌ የመጀመሪያ አክስዮኑን የገዛው በ11 ዓመት ዕድሜው ነበር
አብዛኞቹ የዕድሜ እኩዮቹ ቤዝ ቦል በሚጫወቱበትና የኮሚክ መፃህፍት በሚያነቡበት ወቅት ነበር፤በፌ አክስዮን  የገዛው፡፡ እ.ኤ.አ በ1942 ዓ.ም በ11 ዓመት ዕድሜው ላይ
የ“Cities Service Preferred (አሁን CITGO በሚል ይታወቃል) አክስዮንን ስድስት ድርሻዎች ገዛ- እያንዳንዳቸውን በ38 ዶላር፡፡
 በ16 ዓመቱ 53 ሺ ዶላር አግኝቷል
በፌ ከልጅነቱ ጀምሮ ዘዴኛ ብቻ ሳይሆን እጅግ ጠንካራ ሰራተኛም ነበር፡፡ አባቱ የኮንግረስ አባል ሆነው ሲመረጡ፣ ቤተሰቡ መኖሪያውን ከኦማሃ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አዛወረ፡፡ በዚያን ጊዜ  ታዳጊው በፌ “ዋሽንግተን ፖስት” ጋዜጣን በየጠዋቱ ለደንበኞች እያደረሰ፣በወር 175 ዶላር ገደማ ያገኝ ነበር፡፡ (በወቅቱ አብዛኞቹ መምህራን ከሚያገኙት ደሞዝ በላይ ማለት ነው፡፡)
በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች ሥራዎችንም ጎን ለጎን ይሰራ ነር፡፡ ለምሳሌ፡- ያገለገሉ የጎልፍ ኳሶችን መሸጥና ሌሎችም፡፡ 16 ዓመት ሲሞላው ታዲያ ከገዛቸው የተለያዩ አክስዮኖችና ኢንቨስትመንቶች 53 ሺ ዶላር አገኘ፡፡
ሃርቫርድ ቢዝነስ ስኩል ለመግባት ፈልጎ ሳይቀበሉት ቀረ
በፌ ከብራኔስካ ዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ ሃርቫርድ ቢዝነስ ስኩል ለመግባት አመልክቶ ነበር፡፡ ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱን በሚወስነው አጭር ቃለ መጠየቅ ወቅት ታዲያ ቁርጡ ተነገረው፡፡ የት/ቤቱ ኃላፊ፤ “እርሳው፣ሃርቫርድ አትገባም” ብለው አሰናበቱት፡፡
ቢሊዬነሩ ከ1958 አንስቶ መኖሪያ ቤታቸውን አለወጡም
ስለ ቢሊኒየር ስናስብ ብዙ ጊዜ ወደ አዕምሮአችን የሚመጣው የተንጣለሉ ቅንጡ ቪላዎችና ወድ አውቶሞቢሎች ናቸው፡፡ ይህ ግን ለዋረን በፌ አይሰራም፡፡ እ.ኤ.አ ከ1958 አንስቶ በ31 ሺ 500 ዶላር በገዙት የኦማሃ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነው የሚኖሩት…ባለ አምስት መኝታ ክፍሎች ያሉት ተራ ቤት ውስጥ!
በፌ በ2013 በቀን 37 ሚሊዮን ዶላር ያስገቡ ነበር
እ.ኤ.አ በ2013 መጨረሻ ላይ የሃብታቸው መጠን የተጣራ 59 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በዚያው ዓመት በቀን በአማካይ 37 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኙ ነበር፡፡
94 በመቶ ገደማ ሃብታቸውን ያገኙት 60 ዓመት ከሞላቸው በኋላ ነው
ስኬት በማናቸውም ዕድሜ ላይ ይመጣል፡፡ በፌ ከ60 ዓመታቸው በፊት በእጅጉ ስኬታማ ነበሩ …በ52 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ የሀብታቸው መጠን 372 ሚሊዮን ዶላር ይገመት ነበር …99 በመቶ ሃብታቸውን ያገኙት 50 ዓመት ከሞላቸው በኋላ ነው፡፡ በ89 ዓመታቸው ላይ የሀብታቸው መጠን 81.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
በትዊተራቸው ላይ ፅፈው አያውቁም
ዋረን በፌ ከ1.25 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር ገጽ (e warren Buffett) ቢኖራቸውም፣ ስምንት ጽሁፎች ብቻ ናቸው የተለጠፉት፡፡ አንዱም ታዲያ በእሳቸው የተጻፈ አይደለም፡፡
“የትዊተር መልዕክት ስለመፍጠር ያጫወተችኝ አንድ ወዳጄ ነበረች፡፡ እርሷ ናት እነዚያን ጽሁፎች የለጠፈችው። እኔ ግን ትዊተር ላይ ምንም ነገር ጽፌ አላውቅም።” ሲሉ ለCNBC አጋርተዋል። ቢሊኒየሩ፣ የማንም ትዊተር ተከታይ አይደሉም፡፡ ኢሜይል ልከውም አያውቁም፡፡
የቀናቸውን 80  በመቶ የሚያሳልፉት በማንበብ ነው
ከመኝታቸው ከነቁበት ቅጽበት አንስቶ ጋዜጣ ላይ እንዳቀረቀሩ ነው፡፡ እንዲያውም የቀኑን 80 በመቶ ያህል የሚያሳልፉት በንባብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በፌ ለስኬታቸው ቁልፍ ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ፣ወደ መጻህፍት ክምር እየጠቆሙ፤”በየቀኑ እንደዚህ 500 ገጾችን አንብብ፡፡ ዕውቀት የሚሰራው እንዲያ ነው። እንደሚባዛ ወለድ ይበራከታል፡፡” ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
በፌ 20 ሙሉ ልብስ ቢኖራቸውም፤ ለአንዱም እንኳ አልከፈሉበትም
ዋረን በፌ 20 የሚጠጉ ሙሉ ልብሶች አሏቸው፤በአንድ ዲዛይነር የተሰሩ ….በማዳም ሊ፡፡
በአንድ ወቅት በፌ ወደ ቻይና በተጓዙበት ወቅት፣ ሆቴላቸው እንደደረሱ ፣”ሁለት ወንዶች ወደ ክፍሉ ዘለው ይገባሉ….ወዲያው ዙሪያዬን እየተሽከረከሩ በሜትር መለካት ጀመሩ፤ ከዚያም የሙሉ ልብስ ናሙናዎች የያዘ መጽሀፍ አሳዩኝና አንዱን ምረጥ አሉኝ፤ ማዳም  ሊ አንድ ሙሉ ልብስ ልታበረክትል ትሻለች” እንዳሏቸው ለCNBC ተናግረዋል፡፡
ዲዛይነሯን ሳያገኟት፣አንድ ሙሉ ልብስ መርጠው ወሰዱ፤ ሌላም ደገሙ፡፡ በመጨረሻም ከምስጢረኛዋ ዲዛይነር ጋር መገናኘታቸውን ተከትሎ፣ ሙያዊ ግንኑነት ያዳበሩ ሲሆን፣እሷም ለበፌ ሙሉ ልብሶች መላኳን ቀጠለች፡፡ 20ዎቹም የበፌ ሙሉ ልብሶች የዲዛይነሯ ስጦታዎች ናቸው፡፡
ዳግም በሊ ዋረን በፌ ዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ ትካፈል የነበረ ሲሆን እንደ ቢል ጌት ላሉ ሌሎች ስኬታማ የቢዝነስ  ሥራ አስፈጻሚዎችም ሙሉ ልብስ ሰርታ ማልበስ ጀመረች፡፡
የበርክሻየር ሃታዌይ አክስዮናቸውን 85 በመቶ ለችሮታ አድራጊ ድርጅቶች ለመለገስ ቃል ገብተዋል
በፌ ስኬታማ ኢንቨስተርና የተዋጣለቻው የቢዝነስ አስፈፃሚ ከመሆንም ባሻገር የታወቁ በጎ አድራጊም ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም 85  ፐርሰንት የበርክሻየር ሃታዌይ አክስዮናቸውን ለአምስት ፋውንዴሽኖች ቀስ በቀስ ለመለገስ ማቀዳቸውን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ቃላቸውንም አክብረው አድርገውታል፡፡ በጁላይ 2019 ዓ.ም ከ3.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የበርክሻየር ሃታዌይ  አክስዮን፣ለአምስት ፋውንዴሽኖች የለገሱ ሲሆን ከእነዚያም ውስጥ አንዱ ቢል ጌትስና ባለቤታቸው የመሰረቱት “ቢል ኤንድ ጌትስ ፋውንዴሸን” ነው፡፡ ዋረን በፌ ከ2006 አንስቶ 34.5 ቢሊዮን ዶላር ለችሮታ አድራጊ ድርጅቶች ለግሰዋል። ቢሊዮነሩ ገንዘብ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ገንዘብ መለገስም ያውቁበታል፡፡

Read 481 times