Saturday, 13 November 2021 14:01

የዳዊት ፍሬው ‹‹የኢትዮጵያዊነት አሻራ››

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ሁለገቡ የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ ባለፈው (ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም) በሃገር ፍቅር ቲያትር  ቤት ‹‹የኢትዮጵያዊነት አሻራ›› የተሰኘ የሰየመውን አዲስ አልበም  አስመርቋል፡፡ በዝግጅቱን ይዘቱ ለየት ያለውና በሙዚቃ መሳርያ የተቀነባበረው አልበሙ፤ አራተኛው የሲዲ ህትመት ነው። ‹‹የኢትዮጵያዊነት አሻራ›› መታሰቢያነቱ ለታላቁ ህዳሴ ግድብና ለ125ኛው የአድዋ ድል በዓል ሲሆን በቅንብሩ ታዋቂው ሙዚቀኛ  ፈለቀ ሀይሉ፣ ሄኖክ መሃሪና ወንድሜነህ ተሳትፈውበታል፡፡
‹‹የኢትዮጵያዊነት አሻራ›› ስያሜ፤
ይዘትና አቀራረብ
ዳዊት ፍሬው ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረገው ልዩ ቃለምልልስ አዲስ አልበሙን ‹‹የኢትዮጵያዊነት አሻራ›› ብሎ የሰየመበትን ምክንያት ሲገልፅ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኮራባቸውን ዋና ዋና የታሪክ አሻራዎችን መታሰቢያ የሚያደርግ ነው፡፡ በመጀመርያ የአድዋ ድል በአያቶቻችን የተሰራ የጀግንነት ውጤትና ምልክት፤ ኢትዮጵያን ከጠላት ነፃ ያወጡበት አሻራ ነው፡፡  በሌላ በኩል፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ  ይህ ትውልድ ለሚቀጥለው ትውልድ ጥሎት የሚሄደው አሻራ ይሆናል።  ከዚህ በመነሳት ‹‹የኢትዮጵያዊነት አሻራ›› የሚለው ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በአልበሙ ውስጥ የቀረቡ ዜማዎችም በቀደምት የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተሰሩና በህዝብ ልብ ውስጥ ያሉ  መሆናቸውም ሌላው አሻራ ነው፡፡›› ብሏል
በአልበሙ ውስጥ 13 ያህል የወርቃማው ዘመን ተወዳጅ ሙዚቃዎች ዳዊት በክላርኔት እየተጫወታቸው በልዩ ቅደም ተከተል ተሰናስለው ቀርበዋል፡፡ ዝነኛው ሙዚቀኛ ፍሬው ሀይሉ ጃንሆይን ያመሰገኑበት የሙዚቃ ግጥም፤ ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ አባይን ለመገደብ የታሰበውን ዕቅድና  የተደረጉ ንግግሮችን አካቶ፣ “አባይ ልብ ግዛ” በሚል ግጥም ተሰርቷል፡፡
ዳዊት የሙዚቃዎቹን አመራረጥ፤ ጭብጥና ቅደም ተከተል በጥልቀት ማሰቡን ለአዲስ አድማስ እንዲህ ይገልፀዋል፡፡ "አባቴ ፍሬው ሃይሉ የ14 ዓመት ልጅ ሆኖ ለንጉሱ በሰራው ዘፈን ይጀምራል፡፡ አባቴ …” ህዝቡን አሳድጎ አገር እያለማ፤ የተፈሪ ዝና በዓለም ተሰማ”…. እያለ በህፃን ልጅ  ድምፅ የሰራው ዜማ ሲሆን፤ ሰምቼው አላውቅም ነበር፤የድሮ ዘፈኖችን በሚያሰባስበው አብዲ ነጋሽ የተባለ ሰው አማካኝነት ነው ያገኘሁት። የአባይ ነገር ሲነሳ የንጉሱ ሚና ቀላል እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ስለዚህም ቀጥሎ የንጉሱ ንግግር ይገባል…”ኢትዮጵያ የሃይል ምንጭ የሆኑ  ወንዞች በየስፍራው አሏት” እያሉ ሲቆጩ የኖሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፣  በአንድ ወቅት ስለ ታላቁ የአባይ ወንዝ እንዲህ ብለው ነበር.. እያለ ተፈሪ ዓለሙ  ይተርከዋል፡፡‹‹ እኛ አባይን እንገድብ ብንል አቅም የለንም፡፡ የውጭ አገራትን ደግሞ አባይን ለመገደብ እርዱን ብንል፤ ግብፅን ላለማስቀየም ፈቃደኛ አይሆኑም። ቀጣዩ ትውልድ ግን በራሱ አቅም ይገነባዋል። …የሚለው ንግግራቸው  ይከተላሉ።
ከዚያም ኢትዮጵያ እኮ የፍቅር የመተሳሰብ የአንድነት አገር የሚል ሃሳብ ይነሳና ‹ፍቅር ከኛ እንዳይለየን› የሚለው ዜማ  ይቀጥላል። ሌሎች ወደ ትላንት የሚወስዱ የተለያዩ ዜማዎች ተከታትለው ይሄዳሉ። አጋማሹ ላይ የሂሩት በቀለ "ኢትዮጵያ ሃገሬ" ዜማ በሽለላ  ሁሉ ታጅቦ የአድዋን መንፈስ ያንፀባርቃል፡፡… ወደ መጨረሻው የሚመጣው የማህሙድ አህመድ  " ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል" የሚለው በመሳርያ ብቻ የተቀነባበረው ዜማ ነው፡፡ የሙዚቃውን ሃሳብ ህዝብ ያውቀዋል አሃ፤ እውነትም ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል ብሎም ያንጎራጉረዋል፡፡ ወዲያውኑ የሚቀርበው ይሄው የኛም አባይ ልብ ገዛ …. ስንቱ ጀግና ትውልድ ዘብ ቋሚ ላገሩ በሚሉ ሃሳቦች የተሞላው የእኔ ግጥም በክላርኔት ታጅቦ እየሄደ፣ ወደ መዝጊያው ላ ቁጭት  ነገር ይመጣል፡፡  ‹አዬ አዬ በሰው አገር ያገር ልጆች ሁሉ፤ የታላቁን ግድብ ዝናውን ቢሰሙ የነገን ብሩህ ቀን በተስፋ እያለሙ ከልብ ከውስጣቸው እንዲህ ሲሉ አዜሙ "መቼ ነው  መቼ ነው… የሚለው ዜማ ይቀጥላል፤ ‹‹ፍቅሬ መቼም አልረሳሽ›› የሚለው ዜማ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአልበሙ ውስጥ የቀረቡት ሙዚቃዎች  እንዲህ በቅደም ተከተል ተሰፍተው የሚሄዱ ዜማዎች ናቸው፡፡  ሳይሰለቹ እስከ መጨረሻው እንድዲሰሙ፡፡›› በማለት ነው የተቀናበሩት፡፡
 አልበሙ ምረቃ- በሃገር
ፍቅር ቲያትር
የኢትዮጵያዊነት አሻራ በሁሉም የምረቃ ስነስርዓት በሙሉ እድሳት ላይ በሚገኘው የሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት ትንሿ አዳራሽ ተከናውኗል፡፡ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፤ የቲያትር ቤቱ ባልደረቦች፤ ታዋቂ ተዋናዮች፤ ደራሲዎች፤ አንጋፋ  ባለሙያዎች የኪነጥበብ … ከፍተኛ ጉጉትና ክብር በተሞላበት ስሜት ተገኝተዋል፡፡  ስነስርዓቱ የተጀመረው  ‹‹ኢትዮጵያ ሃገሬ መመኪያ ጋሻዬ›› የተሰኘውን  ዜማ ዳዊት በክላርኔቱ እየተጫወተ ወደ አደራሹ ሲገባ ሲሆን ታዳሚውም ከመቀመጫው ተነስቶ ሞቅ ባለ ጭብጨባ ወደ መድረኩ ላይ እስኪወጣ አጅቦታል፡፡ የአልበሙን ምረቃ በመድረክ ላይ የመራው ታዋቂው ተዋናይ ግሩም ዘነበ  ነበር፡፡ የእለቱን መርሃ ግብሮች ካስተዋወቀ በኋላ በሁሉም የዳዊት በዳዊት ፍሬው ሁሉም አልበሞችን ምርቃት መድረክ ላይ መገኘቱን አስታውሷል፡፡ ታዳሚው በጭብጨባው በልዩ ሁኔታ አልበሙን እንዲመርቀው ያደረገ ሲሆን ዳዊትን ለታዳሚው ሲገልፀው‹‹ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኢንጅነር፤ ኢንቨስተር ወይንም ኮንትራክተር አይደለም፤ ዳዊት ሁለገብ ሙዚቀኛና የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው፡፡ በአዲሱ አልበሙ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል›› በማለት አመስግኖታል፡፡ በቅርብ ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በመዘዋወር ስላከናወኗቸው ተግባራትም አንስቷል፡፡ እነ ሙሉዓለም ታደሰ፤ አለማየሁ ታደሰ፤ ጋሽ አበራ ሞላ፤ በእውቀቱ ስዩም እና ሌሎችም በተሰባሰቡበት ቡድን ዳዊት ፍሬውም አንዱ ነበር፡፡  ከሰመራ እስከ ጅግጅጋ ከአክሱም እስከ ወለጋ ዩኒቨርስቲዎች  ተዘዋውረው ስለ ኢትዮጵያ ፍቅር፤ ሰላምና አንድነት ሰርተዋል፡፡ በዚህ ወቅት ዳዊት ፍሬው ጉልህ ሚና መጫወቱን ግሩም ሲገልፅ፤ የኢትዮጵያ ወዳጅና በተለያዩ መልኮች አገሩን በመደገፍ የሚሰራ ባለሙያ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ዳዊት ይህን አስታውሶ ለአዲስ አድማስ ሲናገርም ‹‹የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ፍቅር እንዲኖራቸው ነበር የሰራነው፤ አንዴ ክላርኔት ሌላ ግዜ ሳክስፎን ደግሞ ክራር እያነሳሁ ስጫወት ተመልክቶኛል፡፡ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆነ ሁለገብ የሙዚቃ ባለሙያ ብሎ ያደነቀው፡ ከዚያ ልምዳችን ይሆናል፡፡›› ብሏል፡፡
በምረቃው ስነስርዓት ላይ ዳዊት ፍሬው በሃገር ፍቅር ትንሿ አዳራሽ መድረክ ላይ ከወጣ በኋላ ‹‹አባይ ልብ ገዛ›› የተሰኘውን ግጥም የተወሰኑ ስንኞች ያቀረበ ሲሆን ከነበረው ባንድ ጋር ክላርኔቱን በልዩ ስሜት ተጫውቷታል፡፡  
በእድሳት ላይ የሚገኘው የሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት ሙሉ በሙሉ ስራው ሳይጠናቀቅ ለአልበሙ ምርቃት ትንሿን አዳራሽ መፍቀዱን በመጥቀስ ዳዊትና ግሩም  በጋራ አመስግነዋል፡፡ የአድዋ ውጤት በሆነውና በአፍሪካ የመጀመርያው ፈርቀዳጅ ቲያትር ቤት አልበሙ ሊመረቅ መብቃቱ የእለቱን ታዳሚዎች ማኩራቱንም መታዘብ ተችሏል፡፡ ለዳዊት ፍሬው ይህ ምን ትርጉም ይሰጠዋል? ዳዊት ለአዲስ አድማስ በሰጠው ልዩ ቃለምልልስ ምላሹን ሲሰጥ፤
‹‹የአልበሙ መታሰቢያነት ከተደረጉ የታሪክ አሻራዎች አንዱ የአድዋ ድል ነው፡፡  ከአድዋ ድል በኋላ የተከፈተው የሃገር ፍቅር ቲያትር ለአፍሪካም የመጀመርያው ፈርቀዳጅ ነው፡፡ አሁን በሙሉ እድሳት ላይ ይገኛል። በትንሹ አዳራሽ አልበሙ ሲመረቅ ደስ የሚል ስሜት መፍጠሩን ተመልክተኸዋል። ከቲያትር ቤቱ አስተዳደር ጋር ባለኝ ቀና ግንኙነትና ታሪኬንም የሚያውቁ በመሆናቸው እድሉን ሰጥተውኛል፡፡" ብሏል። የምረቃው ስነስርዓት ልዩ ክብርና ሞገስ የተጎናፀፈው በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ታዳሚ ሆነው በመገኘታቸው ብቻ ሳይሆን በመድረኩም ላይ አጫጭር ትርኢቶችን በማቅረባቸው ነው፡፡ ጋዜጠኛ ተዋናይና ገጣሚ ተፈሪ ዓለሙ፣ ለፍሬው ሃይሉ መታሰቢያ ያደረገውን የግጥም ስራውን አንብቧል፡፡
ተዋናይ ሳምሶን ከበደ (ቤቢ) ከገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ  “ባለቅኔው ምህላ” መድብል  የመረጠውን ‹‹የቀረንን እንጫወት›› ካሰማ በኋላ ፤  ተዋናይ አለማየሁ ታደሰ ደግሞ የባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬገ/መድህንን ‹‹ዋ ያቺ አድዋ›› በመድረኩ ላይ እንደአንበሳ እየተንጎማለለ አንብቧል። በሁለቱ ተዋናዮች በቀረቡት የግጥም ንባቦች ዳዊት ፍሬው ክላርኔቱን በልዩ ሁኔታ እየተጫወተ በማጀብ ታዳሚውን ያስደመመ የሙያ ፍቅር አሳይቷል፡፡ ተዋናይና ኮሜዲያን ፍቃዱ ከበደ ደግሞ "እዘፍናለሁ" በሚል ርእስ የወርቃማውና የአሁን ዘመን ሙዚቃዎችን በስላቅ እያነፃፀረ አዝናኝ ወጉን ለታዳሚው አስደምሟል።  ዳዊት  ለአልበሙ ምረቃ በመድረክ ላይ የቀረቡትን የተለያዩ ትርኢቶች በክላርኔቱ ከማጀብ ባሻገር የሃገር ፍቅር የሙዚቃ ሰዎችና ወዳጆቹ ሙዚቀኞች ከተሰባሰቡበት ባንድ ጋር በመሆን ሰርቷል፡፡ የዘነበች ደስታ ‹‹ሎሚ ብወረውር›› እና የሂሩት በቀለን ‹‹ኢትዮጵያ ሃገሬ›› በሚያስደንቅ ብቃት ሲጫወቱ ታዳሚው ሞቅ ባለ ስሜትና ጭብጨባ አድንቋቸዋል፡፡
‹‹በአልበሙ ምርቃት ላይ በዛሬ ዘመን በሀሉም ዘርፍ ጫፍ ላይ የደረሱ ሁሉ መጥተው በመድረክ ስራዎችን ማቅረባቸው ለእኔ ካላቸው ክብርና ፍቅር የመነጨ ነው። በመድረክ ላይ አብረው የተጫወቱት ሙዚቀኞችም እኔን ለማክበር ነው ተሰባስበው የመጡት፡፡ ሰው መቀመጡን ሳያውቀው የአልበም ምርቃቱን በድምቀት በማካሄዳቸው ከልብ አመሰግናለሁ›› በማለት ዳዊት ፍሬው አቅርቧል፡፡
በኢትዮጵያ ኪነጥበብ
የአባቱ ልጅ ለመባል ሲበቃ…
ዳዊት ፍሬው  በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ የቤተሰባቸውን  ፈለግ በመከተል ወደ ሙያው ከገቡ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከአንጋፋ ሙዚቀኛ ልጆች መካከል እንደሱ የተሳካለት እንደሌለ ይነገራል በክላርኔት ተጫዋችነት የኢትዮጵያ ሙዚቃን በማስተዋወቅ የተመሰገነ ባለሙያ ሆኗል፡፡ ዳዊት የአባቱን የሙዚቃ ገድል ለአዲስ አድማስ ሲገልፅ፤ ለሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት ያበረከተውን አስተዋፅኦ አስቀድሞ በማንሳት ነው፡፡  
‹‹ፍሬው ለሃገር ፍቅር ቲያትር ከልጅነቱ እስከ እለተ ሞቱ ያልዋለው ውለታ የለም።  ይህንንም በአልበሙ ምረቃ ላይ በመግቢያው በተፈሪ አለሙ የቀረበው ግጥም ይገልፀዋል፡፡›› ብሎ የተወሰኑ ስንኞችን እንዲህ ጠቅሷል፡-
በምንም ሁኔታ ሰው ከተቸገረ ለፍሬው
ንገሩት የሚባል ነበረ
ፍሬው በምን ታማ ፍሬው ምን ተባለ
ራሱን ጎዳ እንጂ ሌላ ሰው ገደለ…
ዝነኛው የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች፣ ድምፃዊ፣ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ተዋናይ እና የግጥምና ዜማ ደራሲ ፍሬው ኃይሉ በ1950ዎቹ ከፍተኛ እውቅና ካተረፉ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች  አንዱ   ነበር። በትግራይ ክ/ሀገር ተንቤን አውራጃ  የተወለደው ሲሆን፤  በድቁና ሲያገለግል ከቆየ በኋላ  ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት በለጋ እድሜው ተቀጥሮ በድምፃዊነት ከሰራ በኋላ በአኮርዲዮን አጨዋወት ቅልጥፍናው ለመደነቅ በቅቷል፡፡
በቲያትር ቤቱ ወርቃማ ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ እንደቻለም ይነገርለታል። ፍሬው ሀይሉ በሕይወት ዘመኑ ከአንድ መቶ በላይ ዜማዎችን ተጫውቷል። ከተጫወታቸው ዜማዎች በተለይ «ዐይን የተፈጠረው»፣ «እሽሩሩ»፣ «ሱቅ በደረቴ» እና «ኑኑዬ ጨቅላዋ» የተሰኙት ዜማዎች ተወዳጅነታቸው ላቅ ያለ ነው። አምስት የሚሆኑ የባህል ዜማዎችን በሸክላ አስቀርፆ ለሕዝብ አድርሷል።
ዳዊት ፍሬው የልጅነት ሕይወቱን ያሳለፈው አኮርዲዮን ባለበት ቤት ነው፡፡ የዝነኛው አባቱን ፍሬው ሃይሉን ሙዚቃዎች  በቤት ውስጥ እየሰማ በመድረክና በቴሌቪዥን እያየ ነው ያደገው። ከልጅነቱ ጀምሮም ከፍተኛ የሆነ የሙዚቃ ፍላጎት ስለነበረው ከፍተኛ ትምህርቱን ሲጨርስ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቶ በዋናነት በክላሪኔት ተመርቋል፡፡ ፒያኖና የማሲንቆ መሳርያዎችንም አጥንቷል።ክራር በመጫወትም የተካነ ነው፡፡  ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርን ተቀላቅሎ በአልቶ ሳክሶፎን ተጫዋችነት ለአስር ዓመታት ያህል ሰርቷል።  ክላርኔት ለዳዊት ፍሬው እንደ ሀገር፣ ሰው፣ እናት፣ እኅት ፤ ወዳጅ የምትቆጠር ናት፡፡


Read 1159 times